ኢስላምን ለመረዳት

መሠረታዊ እና አንገብጋቢ ርዕሶችን ያካተተ

إرشاد الأنام إلى أصول ومهمات دين الإسلام        

 የሳዑዲ  ሙፍቲ መቅድም

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩሕሩሕ በጣም አዛኝ በሆነው

ምስጋና ሁሉ ለአላህ ነው፡፡ የአላህ ሰላት እና ሰላም በመልዕክተኛው ሙሐመድ ﷺ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ ይሁን፡፡

ከዚህም በማስከተል፦

በእርግጥም “إرشاد الأنام إلى أصول ومهمات دين الإسلام“ | ”ኢርሻዱ‐ል‐አናም ኢላ ኡሱሊ ወሙሂማቲ ዲኒ‐ል‐ኢስላም” (በሚል ርዕስ) ዶክተር ዑመር ዐብዱረሕማን አል ዑመር ያዘጋጁትን መጽሐፍ አንብቤዋለሁ (ገምግሜዋለሁ)፡፡

የመጽሐፉ ገጽ መጠን (ይዘት) ምንም አነስተኛ ቢሆንም በውስጡ አሳሳቢ የሆኑ የተውሒድ እና የአህለ ሱንና ወል ጀማዓን ዐቂዳ ፣ የውዱእ ፣ የሶላት ፣ የዘካና የሐጅ ህግጋትን በአጭሩ አካቶ ይዟል፡፡

በእርግጥም መጽሐፉ በያዘው ርዕስ ላይ ጠቃሚ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ለንባብ ገር እንዲሆን እና አንባቢው በቀላሉ እንዲረዳው በጥያቄና መልስ ይዘት የተዘጋጀ ነው፡፡

ዐረብኛ ተናጋሪ ያልሆኑ ወገኖች ይጠቀሙበት ዘንድ  መጽሐፉ በሌላ ቋንቋ ቢተረጎም መልካም ነው፡፡

የአላህ ሰላትና ሰላም በመልዕክተኛው ሙሐመድ ﷺ ላይ ይስፈን፡፡

ወሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱላሂ ወበረካትሁ!

የሳዑዲ ዐረቢያ ታላቁ ሙፍቲ

በሳዑዲ ዐረቢያ የታላላቅ ዑለማዎች የቦርድ ሰብሳቢ፣ የምርምርና ፈትዋ ፕሬዝዳንት

ዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብዲላህ ቢን ሙሐመድ አሊ ሸይኽ


 የታላቁ ሸይኽ ሷሊሕ አል ፈውዛን መቅድም

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩሕሩሕ በጣም አዛኝ በሆነው

ምስጋና ሁሉ ለአላህ ነው፡፡

በመቀጠል፦

በሸይኽ ዑመር ዐብዱረሕማን አል ዑመር የተዘጋጀውን “ኢርሻዱል አናም ኢላ ኡሱሊ ወሙሂማቲ ዲኒል ኢስላም” የተሰኘውን አጭር ጽሁፍ  አንብቤዋለሁ (ገምግሜዋለሁ)፡፡ አጭር ከመሆኑም ጋር በጣም ጥሩና ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

አላህ መልካም ምንዳውን ይቸራቸው፡፡ መጽሐፉንም ጠቃሚ ያድርገው፡፡

የአላህ ሰላትና ሰላም በነብያችን ሙሐመድ ﷺ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረባዎቻቸው ላይ ይሁን፡፡

ሷሊሕ ቢን ፈውዛን አል ፈውዛን   

በሳዑዲ ዐረቢያ የታላላቅ ዑለማዎች ምክር ቤት አባል

ቀን: 10/2/1437 ሂ


 የአዘጋጁ መቅድም

ምስጋና ለዚያ ለተውሒድና ሱንና ለመራን አላህ ይሁን::

የአላህ ሰላትና ሰላም የምራቻ እና የእዝነት ነቢይ በሆኑት መልዕክተኛችን ሙሐመድ ﷺ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረባዎቻቸው ላይ ይሁን::

ከዚህም በማስከተል፦

ዐቂዳ (እምነት) ትክክለኛ እምነት እንዲሆን ፣ ዒባዳ (አምልኮም) በሸሪዓ የተደነገገ ፣  የአላህ ፊት ተፈልጎበት ጥርት የተደረገና  የመልዕክተኛውን ﷺ ድንጋጌ የገጠመ አምልኮ ይሆን ዘንድ፤ ተውሒድ እና የዲን መሠረቶችን መማር የአንገብጋቢ ነገሮች ሁሉ አንገብጋቢ ፣ ከግዴታዎች ሁሉ ግዴታ  ነው::

ለዚህም ስል ከቁርኣን ፣ ከሱንና እንዲሁም የዑማው ሊቃውንትና የዳዕዋ መሪዎች ካዘጋጇቸው ጠቃሚና አንገብጋቢ መልዕክቶች ብርሃን የተቃኘች ይህችን አጠር ያለች መልዕክት አዘጋጅቻለሁ::  

إرشاد الأنام إلى أصول ومهمات دين الإسلام ” | “ኢርሻዱል አናም ኢላ ኡሱሊ ወሙሂማቲ ዲኒል ኢስላም” | ”ሰዎችን  ወደ መሰረታዊና አንገብጋቢ ኢስላማዊ ትምህርት ማመላከት” ብዬ ሰይምያታለሁ::   

ለግንዛቤ እንድትቀልና ለትክክለኝነትም የቀረበች እንድትሆን በርዕስ የተከፋፈለችና የጥያቄና መልስ ይዘት ያላት አድርጊያታለሁ::

የእርሱ ፊት ብቻ ተፈልጎባት ጥርት ተደርጋ የተሰራች ፣ ለውዴታው የምትገጥምና ባሮቹን የምትጠቅም እንዲያደርጋት አላህን ብቻ እጠይቀዋለሁ:: የአላህ ሰላትና ሰላም በነብያችን ሙሐመድ ﷺ በቤተሰቦቻቸና በባልደረቦቻቸው ሁሉ ላይ ይሁን::

 ዑመር ዐብዱረሕማን አል ዑመር

በሳዑዲ ዐረቢያ የከፍተኛ የፍትሕ ጥናት ተቋም ፉኩልቲ አባል

 የተርጓሚው መቅድም

ምስጋና ለዚያ ”ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ፡፡ ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ፡፡ ለእናንተም ኢስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ፡፡“ ላለው አምላካችን አላህ ይሁን ፤ የአላህ ሰላትና ሰላም “አላህ መልካም  የሻለትን ሰው የሃይማኖትን (ግንዛቤ) መረዳት ይሰጠዋል፡፡” ባሉት ተወዳጁ ነብያችን ሙሐመድ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረባዎቻቸው ላይ ይሁን::

           አላህ በዚህ ምድር ላይ ከዋለልን ተቆጥረው የማይዘለቁ ጸጋዎች መካከል ታላቁ ጸጋ ከኩፍርና ሺርክ ድቅድቅ ጨለማ ጠብቆ የኢስላም እና የኢማንን ብርሃን ማጎናጸፉ ነው፤ ይህንን ታላቅ ስጦታ ከቸረን ዘንድ ደግሞ ወደዚህች ዓለም የመጣንበትን ዋነኛ ዓላማ አላህን በብቸኝነት የማምለክ ተልዕኮ በአግባቡ ልንረዳ ፤ የሕይወት ጎዳናችንን በዕውቀት የታጀበ በትክክለኛ ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ልናደርግ ይገባል::    

በመሆኑም ኢስላምን በትንሹም ቢሆን ለመረዳት ትጠቅም ዘንድ ይህችን በታላላቅ የዘመናችን ዓሊሞች የተገመገመችና ትተረጎም ዘንድ አደራ የተባለላትን “ኢርሻዱል አናም ኢላ ኡሱሊ ወሙሂማቲ ዲኒል ኢስላም” በሚል ርዕስ በሸይኽ ዑመር ዐብዱረሕማን አል ዑመር የተዘጋጀች አጭር መጽሐፍ፤ የአማርኛ ትርጉሟ ”ሰዎችን  ወደ መሰረታዊና አንገብጋቢ ኢስላማዊ ትምህርት ማመላከት ” የሚል ሲሆን ለመጽሐፍ ርዕስነት ስለማይመች “ኢስላምን ለመረዳት” የሚል ስያሜ ሰጥቼ ወደ አማርኛ መልሼ እንካችሁ ብያለሁ፡፡

በትርጉም ሥራዬ ላይ በአብዛኛው የተጠቀምኩት የቃል በቃል ትርጉምን ሲሆን ፤ አንዳንዴም ነፃ የትርጉም ስልትን ተጠቅሜያለሁ፡፡ አስፈላጊ የሆኑ ቃላትን በቅንፍ ውስጥና በህዳግ አብራርቻለሁ፡፡

ምስጋና  

ሁሉን በወሰንክለት ጊዜ እውን የምታደርግ፤  ይህን ሥራ አስጀምረህ ስላስጨረስከኝ ለልዕቅናህ በሚገባ መልኩ ምስጋናዬ ይድረስህ ፤ የለመኑህን ልትሰማ ነውና ለምኑኝ ያልከው ይህችን በለገስክልኝ ጥቂት ዕውቀት የሠራኋትን ትንሽ ሥራ በመልካም እንድትቀበለኝ እና የመልካም ሥራ ሚዛን ማክበጃ እንድታደርግልኝ እማፀንሃለሁ፡፡

መጽሐፉን በመገምገም ከጎኔ ሆናችሁ ለተባበራችሁኝ ወንድሞቼ ኡስታዝ ኸድር ዐብደላህ ፣ አሕመዲን ኸድር ፣ ዐብዱረሕማን ከማል እና ሙሐመድ መሕሙዱ ፤ በጽሁፍ ለቀማው ላይ አንዋር ግደይ ፤ የሽፋን ገጽ በማዘጋጀቱ ላይ ሰዒድ ሙሐመድ ፤  አላህ ከለፋችሁልኝ በበለጠ ይመንዳችሁ ፤ ባለቤቴ ኡሙ ሐማድ ደጋፊዬ ሆነሻልና አላህ ምንዳሽን ያብዛልሽ ፤ በሥራዬ ላይ አሻራቹን ያሳረፋችሁ በስም የጠቀስኳችሁም ሆነ ያልጠቀስኳችሁም ውድ ወንድምና እህቶች ሁሉ አላህ በፊርደውሱ ያበስራችሁ፡፡ 

ሙሉነት ለአላህ ብቻ ነው፤ የአንዳችን ጉድለት በሌላኛችን ዕውቀትና ብስለት የሚደፈን ነው፤ በትርጉም ሥራዬ ላይ ክፍተትን የተመለከተ ማንኛውም ሙስሊም እንዲያርመኝና አስተያየቱን  እንዲቸረኝ በአላህ ስም እጠይቃለሁ፡፡                                                                                                                                          

የአላህ ሰላትና ሰላም በነብያችን ሙሐመድ ﷺ በቤተሰቦቻቸና በባልደረቦቻቸው ሁሉ ላይ ይሁን::

ሐይደር ኸድር ዐብደላህ (አቡ ሐማድ)

ሙሐረም 13/ 1441 - መስከረም 1/ 2012

Face Book : Haider Khedir                                                       Telegram : https://telegram.me/HaiderKhedir                                       e-mail : [email protected]

 ሦስቱ መሠረቶች

ጥያቄ 1  እያንዳንዱ ወንድም ሆነ ሴት ሙስሊም ሊያውቋቸው ግዴታ የሆኑ ሦስት መሠረቶች ምን ምን ናቸው?

መልስ 1 እያንዳንዱ ወንድም ሆነ ሴት ሙስሊም ሊያውቃቸው ግዴታ የሆኑት ሦስት መሠረቶች የሚከተሉት ናቸው ፡- አንድ የአላህ አገልጋይ ባሪያ

1 ጌታውን ማወቅ

2 ሃይማኖቱን ማወቅ 

3 መልዕክተኛውን ሙሐመድ ﷺ ማወቅ ነው፡፡

ጥያቄ 2 ጌታህ ማን ነው? ማስረጃውስ?

መልስ 2 ጌታዬ አላህ ነው፡፡ ያ እኔንም ሆነ መላ ፍጥረተ ዓለሙን በአጠቃላይ በችሮታው (በሲሳዩ) የሚንከባከብ ነው፡፡ እርሱም በብቸኝነት የማመልከው ነው፤ ከእርሱ ውጪ ሌላ የማመልከው የለኝም፡፡ ማስረጃው የአላህ ንግግር ነው ፡-

﴿ٱلۡحَمۡدُ لِلَّهِ رَبِّ ٱلۡعَٰلَمِينَ٢﴾ [الفاتحة: 2]

“ምስጋና (ሁሉ) ለአላህ የተገባ ነው፤ የዓለማት ጌታ ለሆነው፡፡” (ፋቲሓ 2)

ጥያቄ 3 ጌታህን በምን (እንዴት) አወቅኸው? ማስረጃው?

መልስ 3 ጌታዬን ያወቅኹት በተዓምራቱ (ምልክቶቹ) እና በፍጥረታቱ ነው፡፡

ከተዓምሮቹም (ከምልክቶቹ) መካከል ሌሊትና ቀን ፣ ፀሐይ እና ጨረቃ ይገኙበታል፡፡

﴿وَمِنۡ ءَايَٰتِهِ ٱلَّيۡلُ وَٱلنَّهَارُ وَٱلشَّمۡسُ وَٱلۡقَمَرُۚ ٣٧﴾ [فصلت: 37]

“ሌሊትና ቀንም ፀሐይና ጨረቃም ከምልክቶቹ ናቸው፡፡” (ፉሲለት 37)

ከፍጥረታቱ መካከል ደግሞ ሰባት ሰማያት እና ሰባት ምድሮች በውስጣቸው እና በመካከላቸው ያሉት ይገኙበታል፡፡

﴿ٱللَّهُ ٱلَّذِي خَلَقَ ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضَ ٣٢﴾ [إبراهيم: 32]

“አላህ ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ነው፡፡” (ኢብራሂም 32)

ጥያቄ 4 ሃይማኖትህ ምንድን ነው? ማስረጃውስ?

መልስ 4 ሃይማኖቴ እስልምና ነው፡፡ እርሱም ፡-

ለአላህ ትዕዛዝ ሁለመናን ሰጥቶ እርሱን በብቸኝነት ማምለክ ፣ ለትዕዛዙ ፍፁም ታዛዥ መሆን (መጎተት) ፣ ከሺርክና ከባለቤቶቹ (ሺርክን ከሚፈፅሙ ሰዎች) ሙሉ በሙሉ መጥራት ነው፡፡  ማስረጃው የተከበረው የአላህ ቃል ነው፡-

﴿وَمَن يَبۡتَغِ غَيۡرَ ٱلۡإِسۡلَٰمِ دِينٗا فَلَن يُقۡبَلَ مِنۡهُ وَهُوَ فِي ٱلۡأٓخِرَةِ مِنَ ٱلۡخَٰسِرِينَ٨٥﴾   

  [آل عمران: 85]

 ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለውም፡፡ እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው፡፡       

 (አሊ ዒምራን፡85)


ጥያቄ 5 የዲን ደረጃዎች ስንት ናቸው?

መልስ 5 የዲን ደረጃዎች ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

1ኛ አል ኢስላም  

2ኛ አል ኢማን 

3ኛ አል ኢሕሳን ናቸው፡፡  

ጥያቄ 6 ነብይህ ማን ነው?

መልስ 6 ለኔ (ለዚህ ዑማ ከአላህ) የተላኩት (የመጨረሻ)  ነብይ፡-

ሙሐመድ ብን ዐብደላህ ብን ዐብድል ሙጠሊብ ብን ሃሺም ናቸው ፤ ሃሺም ከቁረይሽ ጎሳ ሲሆኑ ቁረይሽ ደግሞ ከዐረብ ጎሳዎች መካከል አንዱ ነው ፤ ዐረብ ደግሞ የአላህ ወዳጅ የሆኑት የነብዩ ኢብራሂም ልጅ የኢስማኢል ዝርያ ነው፡፡  የአላህ ላቅ ያለና በላጭ የሆነው ሰላት እና ሰላም በነብያችን እና በእነርሱም ላይ ይሁን፡፡ ማስረጃው የተከበረው የአላህ ቃል ነው፡-

﴿مَّا كَانَ مُحَمَّدٌ أَبَآ أَحَدٖ مِّن رِّجَالِكُمۡ وَلَٰكِن رَّسُولَ ٱللَّهِ وَخَاتَمَ ٱلنَّبِيِّ‍ۧنَۗ ٤٠﴾ [الأحزاب:1

1 40]

“ሙሐመድ ከወንዶቻችሁ የአንድም ሰው አባት አይደለም፡፡ ግን የአላህ መልክተኛና የነቢዮች መደምደሚያ ነው፡፡”

(አል አሕዛብ፡40)

]]]

 የኢስላም ማዕዘናት እና የሸሀደተይን ትርጉም

ጥያቄ 7 የእስልምና ማዕዘናት ስንት ናቸው?

መልስ 7 የእስልምና ማዕዘናት (አርካን) አምስት ናቸው፡፡ እነርሱም ፡-

1 ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ ሌላ አምላክ አለመኖሩንና ሙሐመድም ﷺ የእርሱ ባሪያና መልዕክተኛ መሆናቸውን መመስከር

2 ሶላትን ደንብ እና ስርዓቱን ጠብቆ መስገድ

3 ዘካ መስጠት

4 የረመዳንን ወር መፆም

5 የጉዞውን ጣጣ ለቻለ ሰው የአላህን ቤት መጎብኘት (ሐጅ ማድረግ) ፡፡

ጥያቄ 8 ላኢላሀ ኢለላህ ማለት ምን ማለት ነው? ማስረጃውስ?

መልስ 8 ላኢላሀ ኢለላህ ማለት ፡- ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ ሌላ አምላክ የለም ማለት ነው፡፡

ማስረጃውም የተከበረው የአላህ ንግግር ነው፡-

﴿ذَٰلِكَ بِأَنَّ ٱللَّهَ هُوَ ٱلۡحَقُّ وَأَنَّ مَا يَدۡعُونَ مِن دُونِهِۦ هُوَ ٱلۡبَٰطِلُ وَأَنَّ ٱللَّهَ هُوَ ٱلۡعَلِيُّ ٱلۡكَبِيرُ٦٢﴾ [الحج: 62]

 “ይህ አላህ እርሱ እውነት በመሆኑ ከእርሱም ሌላ የሚግገዙት ነገር እርሱ ፍጹም ውሸት በመሆኑ አላህም እርሱ የሁሉ በላይ ታላቅ በመሆኑ ነው፡፡”    

(አል ሐጅ፡62)

ጥያቄ 9 የላኢላሀ ኢለላህ መሠረቶች ስንት ናቸው? ማስረጃውስ?

መልስ 9 የላኢላሀ ኢለላህ አርካን (መሠረቶች) ሁለት ናቸው፡፡ እነርሱም ፡-

አንደኛ፡- ነፊይ (ከአላህ ውጪ የሚመለኩ አማልክትን ማራቅ ወይም ውድቅ ማድረግ) ነው፡፡ እርሱም ((ላ ኢላህ)) ከሚለው ቃል የሚወሰደው መልዕክት ነው፡፡

ሁለተኛ፡- ኢሥባት (አምልኮን ለአላህ ብቻ ማፅደቅ) ነው፡፡ ይህም ((ኢለላህ)) ከሚለው ቃል የሚወሰደው መልዕክት ነው፡፡

ማስረጃው ተከታዩ የአላህ ንግግር ነው፡-

﴿ فَمَن يَكۡفُرۡ بِٱلطَّٰغُوتِ وَيُؤۡمِنۢ بِٱللَّهِ فَقَدِ ٱسۡتَمۡسَكَ بِٱلۡعُرۡوَةِ ٱلۡوُثۡقَىٰ لَا ٱنفِصَامَ لَهَاۗ ٢٥٦﴾ [البقرة: 256]

 “በጣዖትም የሚክድና በአላህ የሚያምን ሰው ለርሷ መበጠስ (መመንመን) የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ፡፡“ (አልበቀራህ ፡ 256)

( فَمَن يَكۡفُرۡ بِٱلطَّٰغُوتِ) (በጣዖታት የሚክድ) የሚለው የአንቀፁ ክፍል ለ “ነፊይ” ማስረጃ ሲሆን

( وَيُؤۡمِنۢ بِٱللَّهِ )(በአላህ የሚያምን) የሚለው ደግሞ ለ “ኢሥባት” ማስረጃ    ይሆናል፡፡

ጥያቄ 10 የላኢላሀ ኢለላህ ሸርጦች (ቅድመ መስፈርቶች) ስንት ናቸው?

መልስ 10 የላኢላሀ ኢለላህ መስፈርቶች ስምንት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

1ኛ ዕውቀት ያለ ማወቅ ተቃራኒ የሆነ   

2ኛ እርግጠኝነት የጥርጣሬ ተቃራኒ የሆነ

3ኛ ኢኽላስ የሺርክ ተቃራኒ የሆነ  

4ኛ እውነተኝነት ውሸትን የሚያስወግድ የሆነ

5ኛ ውዴታ የጥላቻ ተቃራኒ የሆነ           

6ኛ መታዘዝ (መጎተት) የመተው ተቃራኒ የሆነ

7ኛ መቀበል ያለመቀበል (መመለስ) ተቃራኒ የሆነ 

8ኛ ከአላህ ውጪ የሚመለኩ አማልክትን በጠቅላላ መካድ ናቸው፡፡

እነዚህ ስምንት መስፈርቶች በተከታዩ ግጥም ይጠቃለላሉ:-

علمٌ يقينٌ وإخلاص وصدقك مع    ...       محبةٍ وانقيادٍ والقبول لها     

وزيدنا ثامنها الكفران منك بما ...        سوى الإله من الأشياء قد أُلِهَا    

  ዕውቀት ፣እርግጠኝነት፣ ኢኽላስና እውነተኝነት                            

ውዴታ፣ መታዘዝና እርሷንም መቀበል

ስምንተኛው ደግሞ          . . .     ከአላህ ውጪ በሚመለኩ አማልክት መካድ ነው            

ጥያቄ 11 ላኢላሀ ኢለላህ የምታስገድዳቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

መልስ 11 ላኢላሀ ኢለላህ የምታስፈርዳቸው ወይም ግዴታ የምታደርጋቸው ነገሮች ሁለት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

1 በአላህ ማመን ፡- የእርሱን ብቸኛ ተመላኪነት ማረጋገጥና አምልኮን ለእርሱ ብቻ ጥርት ማድረግ፡፡ (ይህ ኢሥባት (የምታስገድደው) የምታስፈርደው ነው፡፡)

2 ከአላህ ውጪ በሚመለኩ አካላት ባጠቃላይ መካድ ፡- ከሺርክና ባለቤቶቹ ፍጹም መጥራት ፣ ዲንን (እስልምናን) ከሚያበላሹ ነገሮች ሙሉ በሙሉ መራቅ፡፡ (ይህ ደግሞ ነፊይ (የምታስገድደው) የምታስፈርደው ነው፡፡)

ጥያቄ 12 ሙሐመደን ረሱሉላህ የሚለው የምስክርነት ቃል ምን ማለት ነው?

መልስ 12 ሙሐመደን ረሱሉላህ የሚለው የምስክርነት ቃል ፡- 

በግልፅም ይሁን በውስጥ (በምላስም ይሁን በልብ) ሙሐመድ ﷺ የአላህ አገልጋይና መልዕክተኛ መሆናቸውን፤ ለሰው ልጆች በሙሉ የተላኩ የነብያትና የሩሱሎች መደምደሚያ መሆናቸውን የእምነት ምስክርነት ቃል መስጠት ነው፡፡

ጥያቄ 13 ሙሐመደን ረሱሉላህ የምታስፈርዳቸው (የምታስገድዳቸው) ነገሮች ምን ምን ናቸው?

መልስ 13 ሙሐመደን ረሱሉላህ የሚለው የምስክርነት ቃል የሚያስፈርደው ወይም ግዴታ የሚያደርጋቸው የሚከተሉትን ነው ፡-

1 መልዕክተኛው ﷺ ያዘዙትን መታዘዝ

2 መልዕክተኛው ﷺ የተናገሩትን እውነት ብሎ መቀበል

3 መልዕክተኛው ﷺ ከከለከሉትና ካስጠነቀቁት ነገር መራቅ

4 አላህን መልዕክተኛው ﷺ ባስተማሩት መልኩ እንጂ አለማምለክ ነው፡፡

]]]

 የእምነት ማዕዘናት እና ፍሬዎቻቸው

ጥያቄ 14 የእምነት ማዕዘናት ስንት ናቸው?

መልስ 14 አርካኑል ኢማን ወይም የእምነት ማዕዘናት ስድስት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

1 በአላህ ማመን                   2 በመላኢኮች ማመን                                 3 በመጽሐፍት ማመን        

4 በመልዕክተኞች ማመን        5 በመጨረሻው ቀን ማመን

6 በአላህ ውሳኔ (ቀደር) መልካምም ይሁን መጥፎ ከአላህ መሆኑን ማመን፡፡

ጥያቄ 15 በአላህ ማመን ሲባል ምን ማለት ነው?

መልስ 15 በአላህ ማመን ማለት፡- ቁርጠኛ በሆነ ሁኔታ አላህ በመኖሩ እውነት ብሎ መቀበል፣ በጌትነቱ፣ በአምላክነቱና በስምና ባህሪያቱ ብቸኛ መሆኑን ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡

ጥያቄ 16 በአላህ ማመን ያለው ጥቅም ምንድን ነው?

መልስ 16 በአላህ ማመን ያሉት ጥቅሞች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ከእነርሱም ውስጥ፡

አንደኛ፡- የአላህን ብቸኛ አምላክነት ለማረጋገጥ እንዲሁም አምልኮን ለአላህ ብቻ እንድናደርግ ይረዳናል፡፡

ሁለተኛ፡- ያማሩ ስሞቹና ምሉዕ የሆኑ ባህሪያቱ በሚያስፈርዱት መልኩ ለአላህ ሙሉ የሆነ ውዴታ እንዲኖረን፣ እንድናልቀውና እንድንፈራው ይረዳናል፡፡

ሶስተኛ፡- አላህ ያዘዘውን በመታዘዝና የከለከለውን በመከልከል አምልኮቱ የሚያስገድደውን ሁሉ ለማረጋገጥ ያግዘናል።

ጥያቄ 17 በመላኢኮች ማመን ሲባል ምን ማለት ነው?

መልስ 17 በመላኢኮች ማመን ማለት መኖራቸውን በሙሉ እርግጠኝነት ማመን ፣ (ከብርሃን የፈጠራቸው የሆኑ) የተከበሩ የአላህ ባሪያዎች መሆናቸውን ፣ አላህ ያዘዛቸውን የማያምፁ መሆናቸውን እና የታዘዙትንም የሚፈፅሙት በሙሉ ታዛዥነት መሆኑን ማመን ነው፡፡ አላህ ስማቸውን የገለፀልንን እንደ ጂብሪል፣ ሚካኢል፣ ኢስራፊል እንዲሁም ስማቸውን ባልገለፀውም ማመን[1] ነው ፡፡

ጥያቄ 18 በመላኢኮች ማመን ጥቅሙ ምንድን ነው?

መልስ 18 በመላኢኮች ማመን ብዙ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን ከእነርሱም መካከል፡-

አንደኛ፡- የአላህን ታላቅነት ፣ ኃይለ ብርቱነት ፣ ባለስልጣንነቱን እንረዳለን፡፡ ምክንያቱም የፍጥረታቱ ታላቅነት የፈጣሪውን የበለጠ ታላቅና የላቀ መሆን ያመላክታልና፡፡

ሁለተኛ፡- አላህን እንድንወደውና እንድናመሰግነው ያደርገናል ምክንያቱም የአደም ልጆችን (ከአደጋ) እንዲጠብቁ መላኢኮችን ለእነርሱ ወክሏልና፡፡

ሶስተኛ፡- መልካም ተግባራትን እንድንፈጽም ያነሳሳናል በተቃራኒው ከመጥፎ እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል፤ ምክንያቱም አላህ ከመላኢኮች መካከል የሰው ልጅ የሚሠራውን እያንዳንዱን ሥራ መልካምም ይሁን መጥፎ እንዲመዘግቡ የወካለቸው መላኢኮች   አሉና፡፡

ጥያቄ 19 በመጽሐፍቱ ማመን ሲባል ምን ማለት ነው?

መልስ 19 አላህ ለመልዕክተኞቹ ባወረዳቸው መጽሐፍት በእርግጠኝነት እውነት ብሎ ማመንና መቀበል ፣ የአላህ ንግግር እና እውነተኛ መመሪያ መሆናቸውን ማመን እንዲሁም አላህ ስማቸው የነገረንን እንደ ቁርኣን፣ ተውራት፣ ኢንጂል እና ዘቡር እንዲሁም ስማቸው ባልተነገረንም ማመን ማለት ነው፡፡

ጥያቄ 20 በመጽሐፍት ማመን ጥቅሙ ምንድን ነው?

መልስ 20 በመጽሐፍት ማመን ብዙ ጥቅሞችን የያዘ ሲሆን ከእነርሱም መካከል፡-

አንደኛ ፡- አላህ ለባሮቹ እጅግ አዛኝ እንደሆነ ያስረዳናል፤ ምክንያቱም ለሁሉም ህዝቦች ወደ ቀጥተኛው መንገድ የተመሩ ይሆኑ ዘንድ መጽሐፍትን ለሁሉም አውርዷል፡፡

ሁለተኛ፡- የአላህ ድንጋጌዎችን የላቀ ጥበብ እንረዳለን፤ ምክንያቱም ለሁሉም ህዝቦች ከእነርሱ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ ህግጋትን ደንግጓልና፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-

﴿ لِكُلّٖ جَعَلۡنَا مِنكُمۡ شِرۡعَةٗ وَمِنۡهَاجٗاۚ ٤٨﴾ [المائدة: 48]

 “ከእናንተ ለሁሉም ሕግንና መንገድን አደረግን፡፡” (አል ማኢዳ፡ 48)

ሶስተኛ፡- የአምልኮ ዓይነቶችን በዝርዝር በመጽሐፍቱ ላይ በማብራራቱ የአላህን ፀጋ ለማመስገን ይረዳናል፡፡

አራተኛ፡- በወረዱት መጽሐፍት ላይና መልዕክተኞች ባብራሩት መልኩ አላህን ትክክለኛና እርግጠኛ በሆነ ማስረጃ ላይ ሆነን እንድናመልከው ይረዳል፡፡

ጥያቄ 21 በመልዕክተኞች ማመን ሲባል ምን ማለት ነው?

መልስ 21 በመልዕክተኞች ማመን ማለት መልዕክተኞች በጠቅላላ ከአላህ የተላኩ መሆናቸውን ከልብ እውነት ብሎ ማመን ፤ የተናገሩትን እውነት ብሎ መቀበል ፣ አላህ ስማቸውን በገለፀው ማመን ለምሳሌ እንደ ኑሕ ፣ ኢብራሂም ፣ ሙሳ ፣ ዒሳ እና ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእነርሱ ላይ ይሁንና እንዲሁም ስማቸውም ባልተጠቀሰውም ማመን ነው፡፡

ጥያቄ 22 በመልዕክተኞች ማመን ጥቅሙ ምንድን ነው?

መልስ 22 በመልዕክተኞች ማመን ብዙ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን ከእነርሱም ውስጥ፡-

አንደኛ ፡- አላህ ለባሮቹ ያለውን እዝነትና አሳቢነት እናውቃለን፡፡ ምክንያቱም ወደ ቀጥተኛው መንገድና ትክክለኛው ሃይማኖት እንዲመሩ መልዕክተኞችን ልኮላቸዋል፡፡

ሁለተኛ ፡- በመጽሐፉ ላይ በደነገገው፣ መልዕክተኞች ባስተማሩትና በተገበሩት መልኩ አላህን በመረጃ ላይ ሆነን እንድናመልክ ይረዳናል፡፡

ሶስተኛ ፡- መልዕክተኞችን እንድንወድ ፣ እንድናልቃቸውና ለእነርሱ ተገቢ በሆነ መልኩ እንድናወድሳቸው (እንድናስታውሳቸው) ያስችለናል፡፡

አራተኛ፡- አላህን ለዚህ ታላቅ የሆነ ፀጋው እንድናመሰግነው ይረዳናል፡፡

ጥያቄ 23 በመጨረሻው ቀን ማመን ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 23 በመጨረሻው ቀን ማመን ማለት የሰው ልጆች ለምርመራና ለምንዳ የሚቀሰቀሱበት በሆነው የመጨረሻው ቀን በቁርጠኝነትና በእርግጠኝነት ማመንና እውነት ብሎ መቀበል ማለት ነው፡፡

ጥያቄ 24 በመጨረሻው ቀን ማመን ጥቅሙ ምንድን ነው?

መልስ 24 በመጨረሻው ቀን ማመን ብዙ ጥቅሞች አሉት ከእነርሱም ውስጥ፡-

አንደኛ ፡- መልካም ሥራ ለመሥራት እንድንነሳሳ ፣ ጉጉት እንዲኖረንና የመጨረሻው ቀን መልካም ምንዳን ከአላህ እንድንከጅል ያደርጋል፡፡

ሁለተኛ፡- የመጨረሻውን ቀን ቅጣት ፈርተን መጥፎ እና ክልክል ተግባራት ከመፈፀም እንድንቆጠብና እንድንፈራ፤ ከእርሱም እንድንርቅ ያደርጋል፡፡

ሶስተኛ ፡- አንድ ሙዕሚን ጠፊ ከሆነችው የዱንያ ፀጋ ሲያመልጠው ዘውታሪ የሆነውን የአኼራ ፀጋ በመከጀል መንፈሱ የታደሰና ደስተኛ እነዲሆን ያደርገዋል፡፡

ጥያቄ 25 በቀደር ማመን ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 25 በቀደር ማመን ማለት አላህ ነገራት ከመከሰታቸው በፊት የሚያውቃቸው መሆኑን ፣ ክስተቱንም በለውሐል መሕፉዝ በተጠበቀው ሰሌዳ እንደፃፈው፣ በእርሱ ፍቃድና መሻት ብቻ የሚፈጸሙና የሚከሰቱ መሆኑን እና ሁሉን የሚፈጥረው እርሱ መሆኑን በቁርጠኝነት ማመንና እውነት ብሎ መቀበል ነው፡፡

ጥያቄ 26 በቀደር ማመን ጥቅሙ ምንድን ነው?

መልስ 26 በቀደር ማመን ብዙ ጥቅሞች አሉት ከእነርሱም ውስጥ፡-

አንደኛ፡- በአላህ ላይ እውነተኛ መመካት እንዲኖረን ፣ ሰበቦችን ስናደርስ በአላህ ላይ እንድንደገፍ ይረዳል፡፡ ምክንያቱም ሰበብን ያስገኘው እርሱ በመሆኑና ሁሉም ነገር የሚሆነው በእርሱ ውሳኔ ስለሆነ ነው፡፡

ሁለተኛ ፡- በአላህ ውሳኔ ምክንያት ሰውየው ላይ በሚከሰቱ ነገሮች ላይ እርጋታና ውዴታ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ የሚወደው አካል ሲለየው ወይም መጥፎ ነገሮች ሲከሰቱ ከቁጣ ይርቃል፡፡

ሶስተኛ፡- በሚገጥሙን ችግሮች ላይ ፅናት እንዲኖረን እንዲሁም የሕይወትን አስቸጋሪ ክፍሎች ደንዳና በሆነ ልብና እውነተኛ በሆነ በአላህ መተማመን እንድናልፍ      ይረዳናል፡፡

አራተኛ፡- አንድ ሰው የሚፈልገው ሲሳካለት በራሱ ከመደመምና ከመጎረር እንዲርቅና እንዲቆጠብ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም የሚፈልገው ነገር የተሳካለትና ለስኬት የበቃው በአላህ ውሳኔ ችሮታና መገጠም በመሆኑ ነው፡፡

]]]

 ኢሕሳን እና ፍሬዎቹ

ጥያቄ 27 ኢሕሳን ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 27 ኢሕሳን ማለት አላህን ልክ እንደምታየው ሆነህ ማምለክ ነው፤ አንተ ባታየው እንኳ እርሱ ያይሀልና፡፡

ጥያቄ 28 የኢሕሳን ደረጃዎች ስንት ናቸው?

መልስ 28 ኢሕሳን ሁለት ደረጃዎች አሉት

አንደኛው ደረጃ ፡- የልባዊ ምልከታ ደረጃ ሲሆን ይህም አንድ ባሪያ አላህን በሚያመልከው ጊዜ ልክ ጌታውን እንደሚያየው አድርጎ ማምለክ ነው፡፡ ይህ ከፍ ያለውና የላቀው ደረጃ ነው፡፡

ሁለተኛው ደረጃ ፡- አላህን የመጠባበቅ (ማሰብ) ደረጃ ሲሆን ይህም አንድ ሰው የትም ቦታ ቢሆን ወይም በየትኛውም ተግባር ላይ ቢሆን አላህ እንደሚያየውና እንደሚቆጣጠረው ማወቅ ነው፡፡

ጥያቄ 29 ኢሕሳን ምን ምን ፍሬዎች (ጥቅሞች) አሉት?

መልስ 29 ኢሕሳን እጅግ በጣም ብዙ ፍሬዎች ያሉት ሲሆን ከእነርሱም ውስጥ፡-

1 አላህ በግልፅም ይሁን በድብቅ የምንሠራውን የሚያውቅ በመሆኑ እርሱን እንድንፈራ ይረዳናል፡፡                                                                                                  2 አምልኮን ለአላህ ብቻ ጥርት እንድናደርግ ፣ ለእርሱም በመተናነስ አሳምረንና አሟልተን እንድንሠራ ይረዳናል፡፡                                                                                      3 አላህ ለሙሕሲኖች የተለየ የሆነ አብሮነት አለው፡፡                                                        4 ጀነትን ለመጎናፀፍና አላህን ለማየት ይረዳል፡፡

]]]

 ተውሒድ እና ፍሬዎቹ

ጥያቄ 30 ተውሒድ ማለት ምን ማለት ነው? ክፍሎች ስንት ናቸው?

መልስ 30 ተውሒድ ማለት አላህን እርሱ ብቻ በሚለይባቸው ነገሮች ብቸኛ አድርጎ መነጠል ማለት ነው፡፡ የተውሒድ ክፍሎች ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

1 ተውሒድ አር‐ሩቡብያህ         (የጌትነት ተውሒድ)  

2 ተውሒድ አል‐ኡሉሂያህ        (የአምላክነት ተውሒድ)

3 ተውሒድ አል‐አስማኢ ወስ‐ሲፋት (የስምና ባሕሪያት ተውሒድ) ናቸው፡፡ 

ጥያቄ 31 ተውሒድ አር‐ሩቡብያህ ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 31 ተውሒድ አር‐ሩቡብያህ ማለት፡- አላህን በሥራዎቹ ብቸኛ ባለቤት አድርጎ መነጠል ማለት ነው፡፡ በመፍጠር ፣ ሲሳይ በመስጠት ፣ በመግደል እና በመሳሰሉት ሥራዎች ጥራት የተገባውን አላህን ብቸኛ ማድረግ ማለት ነው፡፡

ጥያቄ 32 ወደ ኢስላም ለመግባት ተውሒዱ አር‐ሩቡብያህ ብቻ በቂ ነውን? 

መልስ 32 ተውሒዱ አር‐ሩቡብያህ ብቻውን ወደ እስልምና ለመግባት በቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በነብዩ ﷺ ዘመን የነበሩት የመካ ሙሽሪኮች (አጋሪዎች) በተውሒድ አር‐ሩቡብያህ የሚያረጋግጡ ቢሆንም ምንም የጠቀማቸው ነገር አልነበረም፡፡       

 ለዚህም ማስረጃው የአላህ ንግግር ነው፡-

﴿وَلَئِن سَأَلۡتَهُم مَّنۡ خَلَقَهُمۡ لَيَقُولُنَّ ٱللَّهُۖ فَأَنَّىٰ يُؤۡفَكُونَ٨٧﴾ [الزخرف: 87]

ማን እንደፈጠራቸውም ብትጠይቃቸው «በእርግጥ አላህ ነው» ይላሉ፡፡ ታዲያ (ከእምነት) ወዴት ይዞራሉ፡፡    ( ዙኽሩፍ፡87)

ጥያቄ 33 ተውሒዱል‐ኡሉሂያ ምን ማለት ነው?

መልስ 33 ተውሒዱል‐ኡሉሂያ ማለት፡-  

ሰዎች በሚሠሩት የአምልኮ ተግባር አላህን ብቻ መነጠል ማለት ነው፡፡

በሌላ አገላለፅ አላህን በአምልኮ ተግባራት ብቸኛ አድርጎ መነጠል ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት በሌላ አነጋገር የላኢላሀ ኢለላህ ትርጓሜ ነው፡፡

ጥያቄ 34 ተውሒዱል‐ኡሉሂያን አንገብጋቢ ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው?

መልስ 34 ተውሒዱል‐ኡሉሂያ አንገብጋቢ የሆነበት ምክንያት፡-

1 ተውሒዱል‐ኡሉህያ የሰው ልጆች የተፈጠሩበት ዋነኛ አላማ በመሆኑ

2 የአንቢያ እና ሩሱሎች ዋነኛ የዳዕዋ አላማና ጥሪ በመሆኑ

3 አላህ በባሮቹ ላይ ያለው ትልቁ ሐቅ (መብት) በመሆኑ

4 ሥራ ተቀባይነት እንዲያገኝ ዋነኛ መሰረት በመሆኑ ነው፡፡

ጥያቄ 35 ተውሒዱል‐አስማኢ ወስ‐ሲፋት ምን ማለት ነው?

መልስ 35 ተውሒድ አል‐አስማኢ ወስ‐ሲፋት ማለት፡-

አላህን በስምና ባህሪያቱ ብቸኛ አድርጎ መነጠል ማለት ነው፡፡ በቁርኣንና በመልዕክተኛው ትክክለኛ ሐዲሥ የመጡትን ስምና ባህሪያት እነርሱ ያፀደቁትን ማፅደቅ ፣ ውድቅ ያደረጉትን ውድቅ ማድረግ ትርጉሙን ሳይቆለምሙ (ያለ ተሕሪፍ) ፣ ትርጉም አልባ ሳያደርጉ (ያለ ተዕጢል) ፣ አኳኋኑን (ሁኔታው እንዲህ ነው እንዲያ ነው) ብለው ሳይገልፁ (ያለ ተክዪፍ) ፣ ከፍጡራን ጋር ሳያመሳስሉ (ያለ ተምሢል) ማመን ማለት ነው፡፡

ጥያቄ 36 አህለ ሱና ወል ጀማዓህ የአላህ ስምና ባህሪያትን በተመለከተ ያላቸው አቋም ምንድን ነው?

መልስ 36 አህለ ሱና ወል ጀማዓህ የአላህን ስምና ባህሪያት በተመለከተ ያላቸው አቋም አላህ ለራሱ ያፀደቃቸውን ስምና ባህሪያት ከፍጡራን ጋር ሳያመሳስሉ ማፅደቅ፤ ከራሱ ያራቃቸውንና ውድቅ ያደረጋቸውን ትርጉም አልባ ሳያደርጉ (ያለ ተዕጢል) ውድቅ ማድረግ ነው፡፡

ማስረጃውም ተከታዩ የአላህ ቃል ነው፦

﴿ لَيۡسَ كَمِثۡلِهِۦ شَيۡءٞۖ وَهُوَ ٱلسَّمِيعُ ٱلۡبَصِيرُ١١﴾ [الشورى: 11]

“የሚመስለው ምንም ነገር የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ተመልካችም  ነው፡፡”              (አሽ ሹራ ፡11)

(لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ ) “የሚመስለው ምንም ነገር  የለም” የሚለው ለተሽቢህ እና ተምሢል  (ከፍጡራን ጋር ለሚያመሳስሉ አካላት) ምላሽ ይሰጣል፡፡

( وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ ) “እርሱም ሰሚው ተመልካቹም ነው” የሚለው ደግሞ ተዕጢል (ትርጉም አልባ ለሚያደርጉ አካላት) ምላሽ ይሰጣል፡፡

ጥያቄ 37 ተውሒድ አል‐አስማኢ ወስ‐ሲፋት አንገብጋቢ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው?

መልስ 37 ተውሒድ አል‐አስማኢ ወስ‐ሲፋት አንገብጋቢ እንዲሆን ያደረገው፡-

1 በአላህ ላይ ያለን እምነት እንዲጨምር ስለሚያደርግ

2 የአላህን ስምና ባህሪያት ማወቅ ስለ አላህ ያለን ዕውቀት እንዲጨምር ስለሚረዳ

3 የልብ ሥራዎች የሚጠነክሩት አላህን በመውደድ፣ በመፍራትና እርሱን በመከጀል ስለሆነ

4 በአላህ ስምና ባህሪያት ዙሪያ ጀሀሚያ፣ ሙዕተዚላ እና አሽዓሪያ ከተዘፈቁበት አላህን ከፍጡራን ጋር ማመሳሰልና ባህሪያቱን ከማራቆት ጥፋት መጥጠበቂያ ስለሚሆነን፡፡

ጥያቄ 38 የተውሒድ ትሩፋቶች ምንድን ናቸው?

መልስ 38 የተውሒድ ትሩፋቶች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው ከእነርሱም ውስጥ፡-

1 ደምና ንብረት የተጠበቅ እንዲሆን ያደርጋል

2 ከዱኒያም ከአኼራ ጭንቀት ይገላግላል

3 በጠላት ላይ ድልን ለመቀዳጀትና  በምድር ላይ መረጋጋትን ያስገኛል

4 በዱኒያም ሆነ በአኼራ ሰላም ለመሆን ሙሉ ዋስትና ነው

5 በዱኒያ መልካም ሕይወትን መታደልና በአኼራም ታላቅ ምንዳን ለመጎናፀፍ ይረዳል

6 ወንጀል እና ጥፋትን ያስምራል

7 ከእሳት ነፃ ለመውጣት ጋሻ ነው

8 ጀነት ለመግባት ይረዳል፡፡

]]]

 ከእስልምና የሚያስወጡ ነገሮች (ሪ‐ድ‐ዳህ)

ጥያቄ 39 ሪድዳህ ማለት ምን ማለት ነው? ማስረጃውስ?

መልስ 39 ሪድዳህ ማለት ፡- ከእስልምና (ሙስሊም ከሆኑ በኃላ) መካድ ነው፡፡

ማስረጃውም የአላህ ንግግር ነው፡-

﴿ وَمَن يَرۡتَدِدۡ مِنكُمۡ عَن دِينِهِۦ فَيَمُتۡ وَهُوَ كَافِرٞ فَأُوْلَٰٓئِكَ حَبِطَتۡ أَعۡمَٰلُهُمۡ فِي ٱلدُّنۡيَا وَٱلۡأٓخِرَةِۖ وَأُوْلَٰٓئِكَ أَصۡحَٰبُ ٱلنَّارِۖ هُمۡ فِيهَا خَٰلِدُونَ٢١٧﴾ [البقرة: 217]

 “ከእናንተ ውስጥም ከሃይማኖቱ የሚመለስና እርሱም ከሐዲ ሆኖ የሚሞት ሰው እነዚያ (በጎ) ሥራቸው በቅርቢቱም በመጨረሻይቱም አገር ተበላሸች፡፡ እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡ እነርሱ በርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡” (አል በቀራህ፡217)

ጥያቄ 40 የሪ‐ድ‐ዳህ አይነቶች ስንት ናቸው?

መልስ 40 የሪ‐ድ‐ዳህ ዓይነቶች አምስት ናቸው፡፡

1 የንግግር (ቀውል)           2 የተግባር/ የድርጊት  (ፊዕል)

3 የእምነት (ኢዕቲቃድ)       4 የጥርጣሬ  (ሸክ)                 

5 የመተው (ተርክ) ናቸው፡፡

ጥያቄ 41 በንግግር የሚከሰት ሪ‐ድ‐ዳህ የምንለው ምሳሌው ምንድን ነው?

መልስ 41 በንግግር የሚከሰት ክህደት በብዙ መልኩ ሊገለጽ ይችላል፡፡       

ከእነርሱም ውስጥ፡-

1 አላህን ወይም መልዕክተኛውን መሳደብ

2 በቁርኣን ወይም በሶሒሕ ሐዲሥ ወይም በግልጽ በሚታዩ የኢስላም መገለጫዎች ማሾፍና ማላገጥ

3 (አላህ እንጂ ሌላ በማያውቀው) የሩቅ ሚስጥርን አውቃለሁ ብሎ መሞገት

4 ነብይነትን (ነብይ ነኝ ብሎ) መሞገት

5 አላህ እንጂ ሌላ አካል በማይችለው ነገር ላይ ከአላህ ውጪ ያሉትን መለመን ፡፡

ጥያቄ 42 በተግባር (ድርጊት) ምክንያት ለሚከሰት ክህደት ምሳሌው ምንድን ነው?

መልስ 42 የተግባር ክህደት በተለያየ ምክንያት ሊከሰት ይችላል፡፡ ከእነርሱም ውስጥ፡-

1 ከአላህ ውጪ እንደ ጣዖት ወይም ቀብር ላሉ አካላት ሱጁድ ማድረግ 

2 ለጂኖች ከእነርሱ ከጅሎ ወይም እነርሱን ፈርቶ ማረድ ወይም ወደ ሙታኖች ለመቃረብ ብሎ ማረድ

3 መጥፎና ቆሻሻ ቦታ ላይ ሆን ብሎ  ቁርኣንን (ሙስሐፍን) መጣል                                                                                     4 ሲሕር መሥራት፤ መማር እና ማስተማር፡፡

ጥያቄ 43 በእምነት ምክንያት የሚከሰት ክህደት ምሳሌው ምንድን ነው?

መልስ 43 የእምነት ክህደት በበርካታ ነገሮች ሊገኝ ይችላል:: ከእነዚህም ውስጥ፦

1 ለአላህ ተጋሪ አለው ብሎ ማመን

2 ከሞት በኃላ መቀስቀስ የለም ብሎ ማመን ወይም ጀነትና ጀሀነም የሚባል ነገር የለም ብሎ ማመን

3 አላህ ሐራም ያደረገውን ሐላል ማለት ለምሳሌ ዝሙት፣ ኸምር መጠጣትና አላህ ካወረደው ህግ ውጪ መፍረድ ይቻላል ብሎ ማመን

4 የዲን መሠረቶችንና ግዴታዎችን ማስተባበል ለምሳሌ ሶላት ፣ ዘካ ፣ የረመዳን ፆም ወይም ሐጅን ማስተባበል፡፡

ጥያቄ 44 በጥርጣሬ ምክንያት የሚከሰት ክህደት ምሳሌው ምንድን ነው?

መልስ 44 በጥርጣሬ የሚመጣ ክህደት በበርካታ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል:: ከእነዚህም ውስጥ፦

1 ሞቶ መቀስቀስ ወይም ጀነትና ጀሀነም በመኖራቸው ላይ መጠራጠር

2 የእስልምና ሃይማኖትን ትክክለኛነት መጠራጠር ወይም ለዚህ ዘመን ተስማሚ መሆኑን መጠራጠር

3 በነብዩ ﷺ  መላክ ወይም እውነተኛነት ላይ መጠራጠር

4 በተከበረው ቁርኣን ወይም የአላህ ቃል መሆኑን መጠራጠር፡፡

ጥያቄ 45 በመተው ምክንያት የሚከሰት ክህደት ምንድን ነው?

መልስ 45  በመተው ምክንያት የሚከሰት ክህደት (ለምሳሌ) ሶላትን እያወቁ በመተው ይከሰታል ምክንያቱም መልዕክተኛው ﷺ እንዲህ ብለዋል፡-

" إن بين الرجل وبين الشرك والكفر ترك الصلاة. "

“በሰውየውና በሺርክ ወይም ኩፍር መካከል ያለው ሰላትን መተው  ነው፡፡”                       (ሙስሊም 82 ዘግበውታል፡፡)

] ] ]

 ሺርክ

ጥያቄ 46 ሺርክ ማለት ምን ማለት ነው? ዓይነቶቹስ ስንት ናቸው?

መልስ 46 በአላህ ላይ ማጋራት (ሺርክ) ማለት በአምልኮ ከአላህ ጋር ሌላን አካል ተጋሪ አድርጎ መያዝ ነው፡፡ሁለት ክፍሎች አሉት እነርሱም፡-

1 ሺርኩል አክበር (ታላቁ ሺርክ)           

2 ሺርኩል አስገር (ትንሹ ሺርክ)

ጥያቄ 47 ሺርኩል አክበር ምንድን ነው?

መልስ 47 ሺርኩል አክበር (ታላቁ ሺርክ) ማለት ከአምልኮ ዓይነቶች መካከል አንዱንም ቢሆን ከአላህ ውጪ ላለ አካል አካፍሎ መስጠት ነው፡፡

ጥያቄ 48 የሺርኩል አክበር ምሳሌ ምንድን ነው?

መልስ 48 ለሺርኩል አክበር የተለያየ ምሳሌዎች አሉት። ከእነዚያም ውስጥ፡-

ከአላህ ውጪ ያለን አካል መለመን፣ ከአላህ ውጪ ላሉ አካላት እንደ ቀብር፣ ጂንና ሸይጣን ለመሳሰሉት እርድን በማቅረብ እና ስለትን በመሳል ወደ እነርሱ መቃረብ ፣ አላህ እንጂ ሌላ አካል በማይችለው ነገር ላይ ጉዳይን እንዲፈጽሙለት ከአላህ ውጪ ያሉ አካላትን መከጀል እና ጭንቅን እንዲያስወግዱለት መፈለግ ይገኙበታል፡፡  

ጥያቄ 49 የሺርኩል አክበር ተፅዕኖና መጥፎ ጉዳት ምንድን ነው?

መልስ 49 ሺርኩል አክበር እጅግ በጣም ከባድ ወንጀል ሲሆን የሚያደርሰውም ጉዳት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

ከእነርሱም ውስጥ፡-

1 ሺርኩል አክበር ከእስልምና ያስወጣል፡፡

2 ሥራን በጠቅላላ ያበላሻል፡፡

3 አላህ ትልቁን ሺርክ እየሰራ የሞተን አይምርም፡፡

4 ጀነት ከመግባት ይከለክላል፣ ግለሰቡ በአላህ ላይ እያጋራ (ተውበት ሳያደርግ) ከሞተ በእሳት ዘውታሪ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

ጥያቄ 50 ሺርኩል አክበር ላይ ለመውደቅ ምክንያቱ ምንድን ነው?

መልስ 50 ሺርኩል አክበር ላይ ለመውደቅ የሚዳርጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ ከእነርሱም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ፡-

1 በሷሊሕ (መልካም) የአላህ ባሪያዎች ላይ ድንበር ማለፍ፡፡ 

2 ተውሒድን በተገቢው መልኩ አለመረዳት እና የላኢላሀ ኢለላህን ትርጉም   አለማወቅ፡፡

3 ስሜትን መከተል፡፡                 4 ጭፍን ተከታይነት፡፡

ጥያቄ 51 ሺርኩል አስገር ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 51 ሺርኩል አስገር ወይም ትንሹ ሺርክ ማለት ፡- ወደ ትልቁ ሺርክ እንዳያዳርሱ ብሎ ሸሪዓ ሙሉ በሙሉ የከለከላቸው ነገሮች ሲሆኑ በቁርኣንና ሐዲሥ ሺርክ  በሚለው (ገለጻ) ስያሜ የመጡ ናቸው፡፡

ጥያቄ 52 የትንሹ ሺርክ አይነቶች ስንት ናቸው?

መልስ 52 የትንሹ ሺርክ አይነቶች ሁለት ናቸው፦ 

የመጀመሪያው ፡-

ሽርኩን ዟሂር ወይም ግልፅ ሺርክ ሲሆን እርሱም ሁለት ዓይነት ነው፦ 

1 የንግግር ሺርክ ፡- ከአላህ ውጪ ባለ አካል መማል ወይም አላህና አንተ ካሻችሁ የመሰለን ንግግር መናገር፡፡

2 የተግባር ሺርክ ፡- ለምሳሌ አደጋንና ጉዳትን ለመከላከል ብሎ ቀለበትን ማጥለቅ ወይም ክር ማሰር፣ ዓይነ ናስ (የሰው ዓይን) ፈርቶ እርዝን ማንጠልጠልና  የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡

ሁለተኛው ዓይነት ፡-

ሽርኩን ኸፊይ ወይም ድብቁ ሺርክ ሲሆን እርሱም አምልኮን በሚፈፅሙ ጊዜ ይዬልኝና ይስሙልኝን መፈለግ ነው፡፡

ጥያቄ 53 በትልቁና በትንሹ ሺርክ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

መልስ 53 በታላቁ እና በትንሹ ሺርክ መካከል ያሉት ልዩነቶች የሚከተሉት ናቸው፡-

1 ታላቁ ሺርክ ከእስልምና ያስወጣል፤ ትንሹ ሺርክ ከእስልምና አያስወጣም ነገር ግን ተውሒድን ያጓድላል፡፡

2 ታላቁ ሺርክ የተውሒድን ዋና መሠረት የሚጻረር ሲሆን ፤ ትንሹ ሺርክ ተውሒድን  ሙሉ ለሙሉ በሚፈለገው መልኩ ከሟሟላት የሚከለክል ነው፡፡

3 ታላቁ ሺርክ ሥራን በጠቅላላ ያበላሻል፤ ትንሹ ሺርክ ሥራን በጠቅላላ አያበላሽም የሚያበላሸው ትንሹ ሺርክ የተቀላቀለበትን (ይዩልኝ ይስሙልኝ ፈልጎ የሠራውን) ሥራ ብቻ ነው፡፡

4 ታላቁ ሺርክ ሰውየው (ተውበት ሳያደርግ ከሞተ) በእሳት በዘውታሪነት እንዲቀጣ ያደርጋል፤ ትንሹ ሺርክ ግን ሰውየው እሳት ከገባ (የወንጀሉን ያህል ተቀጥቶ ከእሳት ይወጣል) በዘውታሪነት እንዲቀጣ አያደርግም፡፡

] ] ]

 ኒፋቅ (ንፍቅና)

ጥያቄ 54 ኒፋቅ ምን ማለት ነው? ዓይነቶቹስ ስንት ናቸው?

መልስ 54 ኒፋቅ ማለት መልካምን ግልፅ ማድረግና መጥፎን በውስጥ መደበቅ ነው፡፡ 

የኒፋቅ ዓይነቶች ሁለት ናቸው እነርሱም፡-

1 የእምነት ንፍቅና (ኒፋቅ አልኢዕቲቃዲይ) ሲሆን (ኒፋቁ-ል-አክበር) ትልቁ ኒፋቅ ተብሎ ይጠራል፡፡

2 የተግባር ንፍቅና (ኒፋቅ አል አመሊይ) ሲሆን (ኒፋቁ-ል-አስገር) ትንሹ ኒፋቅ ተብሎ ይጠራል፡፡

ጥያቄ 55 የእምነት ኒፋቅ የሚባለው ምንድን ነው?

መልስ 55 ኒፋቅ አል ኢዕቲቃዲይ (የእምነት ንፍቅና) የሚባለው ፡- እስልምናን ግልፅ አድርጎ ኩፍርን በውስጥ ደብቆ መያዝ ነው፡፡ (ላይ ላዩን ሙስሊም እየመሰለ በውስጡ ክህደትን ደብቆ መያዝ ነው)፡፡

ጥያቄ 56 የእምነት ንፍቅና ዓይነቶች ስንት ናቸው?

መልስ 56 የእምነት ንፍቅና ዓይነቶች ስድስት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

1 መልዕክተኛውን ﷺ ማስተባበል

2 መልዕክተኛው ﷺ ይዘውት ከመጡት ከፊሉን ማስተባበል

3 መልዕክተኛውን ﷺ መጥላት

4 መልዕክተኛው ﷺ ይዘውት ከመጡት ከፊሉን መጥላት

5 የመልዕክተኛው ﷺ ዲን ዝቅ ሲል (ሽንፈት ሲደርስበት) መደሰት

6 የእስልምና ሃይማኖት ድልን ሲጎናፀፍ (መከፋት) መጥላት፡፡

ጥያቄ 57 የተግባር ንፍቅና (ኒፋቅ አል‐አመሊይ) የሚባለው ምንድን ነው?

መልስ 57 የተግባር ንፍቅና ማለት፦ በልብ ውስጥ ኢማን ከመኖሩም ጋር ሙናፊቆች የሚገለጹበት (የሚሠሩት) የሆነን አንዳች ሥራ መሥራት ነው፡፡

ለምሳሌ ውሸት ፣ መክዳት ፣ ከሰላተል ጀማዓ (የሕብረት ሶላት) መሳነፍ፡፡  

ጥያቄ 58 በኒፋቅ ኢዕቲቃዲይ እና በኒፋቅ አመልይ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

መልስ 58 በኒፋቅ ኢዕቲቃዲይ እና በኒፋቅ አመልይ መካከል ያለው ልዩነት የሚከተለው ነው፡-

1 የእምነት ንፍቅና ከእስልምና የሚያስወጣ ሲሆን፤ የተግባር ንፍቅና ግን ከእስልምና አያስወጣም፡፡

2 የእምነት ንፍቅና ውስጣዊው እና ውጪያዊው (የምላስ እና የልብ) እምነት ሙሉ  በሙሉ  መጣረስ ፣ መቃረንና አለመስማማት ሲሆን ፤ የተግባር ንፍቅና ግን የምላስ እና የልብ እምነት ሙሉ  በሙሉ  መጣረስ፣ መቃረንና አለመስማማት አይደለም::

3 እምነታዊው ኒፋቅ ሙዕሚን ላይ አይከሰትም:: ተግባራዊው ኒፋቅ ግን ሊከሰት  ይችላል::

] ] ]

 በሸሪዓ የተደነገጉ አምልኮዎች እና የተከለከሉ የቢድዓ ተግባራት

ጥያቄ 59 አላህ የፈጠረን ለምንድን ነው? ማስረጃውስ?

መልስ 59 አላህ የፈጠረን እርሱን በብቸኝነት እንድናመልክና በእርሱ ላይ ማንንም ምንንም እንዳናጋራ ነው፡፡ ማስረጃው የአላህ ንግግር ነው፡-

﴿وَمَا خَلَقۡتُ ٱلۡجِنَّ وَٱلۡإِنسَ إِلَّا لِيَعۡبُدُونِ٥٦﴾ [الذاريات: 56]

 “ጂኒንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡”  (አዝ ዛሪያት ፡56)

ጥያቄ 60 ዒባዳ (አምልኮ) ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 60 ዒባዳ (አምልኮ) ማለት አላህ ለሚወዳቸውና ለሚቀበላቸው ንግግርም ሆነ ተግባር ግልፅም ይሁን ውስጣዊ ለሆኑ ነገሮች ሁሉ የተሰጠ ጥቅል ስያሜ ነው፡፡

ጥያቄ 61 አምልኮ ተቀባይነት እንዲያገኝ (ሸርጡ) ቅድመ መስፈርቱ ምንድን ነው?

መልስ 61 አምልኮ አላህ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኘው ሁለት መስፈርቶች ሲሟሉ ብቻ ነው፡፡ እነርሱም፡-

1ኛ ኢኽላስ አምልኮን ለአላህ ብቻ ጥርት አድርጎ ሲተገበር፡፡

2ኛ ሙታበዓ መልዕክተኛው ባዘዙት መልኩ የእርሳቸውን ፈለግ ተከትሎ ሲፈፀም    ነው፡፡

ጥያቄ 62 ኢኽላስ ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 62 ኢኽላስ ማለት አምልኮን ከሺርክ ቆሻሻ፣ ከይዩልኝና ይስሙልኝ ጥርት አድርጎ ለአላህ ብቻ ብሎ መፈፀም ነው፡፡

ጥያቄ 63 ኢኽላስን ለአላህ ብቻ ማድረግ ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 63 ኢኽላስ ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው ተከታዩ የአላህ ንግግር ነው፡-

﴿وَمَآ أُمِرُوٓاْ إِلَّا لِيَعۡبُدُواْ ٱللَّهَ مُخۡلِصِينَ لَهُ ٱلدِّينَ حُنَفَآءَ ٥﴾ [البينة: 5]

“አላህን ሃይማኖትን ለእርሱ ብቻ አጥሪዎች፣ ቀጥተኞች ሆነው ሊግገዙት፣ እንጅ አልታዘዙም፡፡” (አል በይናህ ፡5)

ጥያቄ 64 ሙታበዓ ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 64 ሙታበዓ ማለት ፡- አላህን በምናመልክበት ጊዜ በመልዕክተኛው (አስተምህሮ መሠረት) መመራት፣ የምንሠራው አምልኮ የእርሳቸውን ሱንና የገጠመና ከቢድዓ የጠራ መሆኑ ነው፡፡

ጥያቄ 65 መልዕክተኛውን መከተል ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 65 መልዕክተኛውን መከተል ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው የአላህ ንግግር ነው፡-

﴿قُلۡ إِن كُنتُمۡ تُحِبُّونَ ٱللَّهَ فَٱتَّبِعُونِي يُحۡبِبۡكُمُ ٱللَّهُ وَيَغۡفِرۡ لَكُمۡ ذُنُوبَكُمۡۚ وَٱللَّهُ غَفُورٞ رَّحِيمٞ٣١﴾ [آل عمران: 31]

“በላቸው፡- “አላህን የምትወዱ እንደሆናችሁ ተከተሉኝ፤ አላህ ይወዳችኋልና፡፡ ኀጢኣቶቻችሁንም ለናንተ ይምራልና፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡”                         (አሊ ዒምራን፡ 31)

ጥያቄ 66 በዲን ውስጥ የሚሠራ ቢድዓ ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 66 በዲን ውስጥ የሚሠራ ቢድዓ ማለት ፡- ነብዩ ﷺ ወይም አራቱ ቅን ኸሊፋዎች (ምትኮች) ባልሠሩት መልኩ አላህን ማምለክ ማለት ነው፡፡  

እንዲህም ተብሏል፡- ያለ ቁርኣንና ሐዲሥ መረጃ በዲን ውስጥ የሚጨመር የፈጠራ ተግባር ሁሉ ቢድዓ ነው፡፡

ጥያቄ 67 በዲን ውስጥ ቢድዓን መፍጠር ሸሪዓዊ ብይኑ ምንድን ነው? ማስረጃውስ?

መልስ 67 በዲን ላይ የሚሠራን ቢድዓ (ፈጠራ) መተግበር በአጠቃላይ ሐራም (ክልክል) የሆነና የጥመት ተግባር ነው፡፡ ማስረጃውም የአላህ መልዕክተኛ ﷺ ንግግር ነው፡-

وقال صلى الله عليه وسلم : «من أحدث في أمرنا هذا ما ليس منه فهو رد»

“በዚህ በጉዳያችን (ዲናችን)ላይ ከእርሱ ያልሆነን አዲስ ነገር ያመጣ ሥራው ተመላሽ ነው (ተቀባይነት የለውም) ፡፡” (ቡኻሪ (2697) ሙስሊም (1718))

በሌላ ሐዲሣቸው ደግሞ «وكل بدعة ضلالة»

“ሁሉም የቢድዓ ተግባር ጥመት ነው፡፡” (ሙስሊም (867))

ጥያቄ 68 በዲን ውስጥ የሚሠሩ የቢድዓ ዓይነቶች ስንት ናቸው?

መልስ 68 በዲን ውስጥ የሚሠሩ የቢድዓ ዓይነቶች ሁለት ዓይነት ሲሆኑ

እነርሱም፡-

አንደኛው፡- የንግግርና የተግባር ቢድዓ ሲሆን የጀሀምያ ፣ ሙዕተዚላህ ፣ ኸዋሪጆች ፣ ራፊዳዎችና የተቀሩትም ከቀጥተኛው መንገድ የሳቱ ቡድኖች ንግግርና እምነት ነው፡፡

ሁለተኛው፡- የአምልኮ ቢድዓ ይህም ማለት አላህን እርሱ ባልደነገገው መልኩ ማምለክ ነው፡፡ ይህም ሦስት ክፍሎች አሉት፡-

አንደኛ ፡- በሸሪዓ መሠረት ባለው የአምልኮ ተግባር ላይ የሚጨመር የሚለጠፍ ነው፡፡ ለምሳሌ በቀብር ዙሪያ መጠወፍ ወይም (የነብያትና ሷሊሆችን) መውሊዶችን ማክበርና የመሳሰሉትን ይገኙበታል፡፡

ሁለተኛ ፡- በሸሪዓ በተደነገገ የአምልኮ ተግባር አፈፃፀም ስርዓት ላይ የሚከሰት ነው፡፡ ለምሳሌ በጀመዓ ዚክር ማድረግ፡፡

ሶስተኛ ፡- ሸሪዓ በጊዜ ያልገደባቸውን የአምልኮ ተግባራትን በጊዜ ገድቦ መፈፀም፡፡ ለምሳሌ የሻዕባን ወርን ግማሽ (አስራ አምስተኛውን ቀን) ቀኑን በጾም ለሊቱን በሶላት ማሳለፍ፡፡

ጥያቄ 69 በዲን ውስጥ ከሚሠሩ የቢድዓ ተግባራት መካከል ምሳሌ ጥቀስ?

መልስ 69 በዲን ውስጥ የሚተገበሩ መሠረት የሌላቸው የቢድዓ ተግባራት ብዙ ናቸው፡፡ ከእነርሱ መካከል ዋና ዋናዎቹ እና በጣም የታወቁት የሚከተሉት ናቸው፡-

1 የመልዕክተኛውን መውሊድ በዓል፡፡

2 የኢስራዕ እና የሚዕራጅን ለሊት ማክበር፡፡

3 በቀብር ላይ መገንባትና መስጂድ አድርጎ መያዝ፡፡

ጥያቄ 70 ቢድዓ ውስጥ ለመውደቅ ምክንያቱ ምንድን ነው?

መልስ 70 ቢድዓ ውስጥ ለመውደቅ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ ከእነርሱም መካከል፡-

1 የዲን ህግጋትን አለማወቅ                        

2 ስሜትን መከተል

3 ጭፍን ተከታይነት                                 

4 ከከሀዲያን ጋር መመሳሰል፡፡

]]] 

 ውዱእ እና ትጥበት

ጥያቄ 71 ውዱእ ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 71 ውዱእ ማለት የታወቁ (የተለዩ) የሆኑ የአካል ክፍሎችን ማጠብ ወይም ማበስ ነው፡፡

ጥያቄ 72 የውዱእ ሸርጦች ስንት ናቸው?

መልስ 72 የውዱእ ሸርጦች (ቅድመ መስፈርቶች) አሥር ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

1 ኢስላም (ሙስሊም መሆን)          2 ዐቅል (አዕምሮ ጤነኛ መሆን)

3 አት‐ተምዪዝ (የመለያ እድሜ ላይ መድረስ የእድሜ መብሰል)

4 ኒያ (በልብ ማሰብ)   

5 ውዱእ አድርጎ እስኪጨርስ ውዱእ አቋርጣለሁ ብሎ አለማሰብ

6 ውዱእ የሚያስገድዱ ነገሮች ሙሉ በሙሉ መወገድ (ለምሳሌ ውኃ ሽንት፣ አይነ ምድር ወዘተ)

7 ለውኃ ሽንት ወይም ለአይነ ምድር ከውዱእ በፊት ኢስቲንጃእ ማድረግ (በውኃ መፀዳዳት) ወይም ኢስቲጅማር ማድረግ (በወረቀት ፣በድንጋይ ወይም በሶፍትና መሰል ነገሮች መፀዳዳት)

8 ውኃው ንፁህ የሚያፀዳና የተፈቀደ መሆን

9 ውኃ ወደ አካል እንዳይደርስ የሚያደርጉ (እንደ ሻማ ፣ ሊጥና ጥፍር ቀለም የመሳሰሉ) ነገሮችን ማስወገድ                                                                                  

10 ውዱእ የሚያጠፉ ነገሮች (ለምሳሌ የውኃ ሽንት ያለመቋረጥ ያለበት ወይም ሰለሰል) በዘውታሪነት የሚከሰትበት ለሆነ ሰው የሶላት ወቅት መግባት ናቸው፡፡

ጥያቄ 73 የውዱእ ግዴታዎች ስንት ናቸው?

መልስ 73 የውዱእ ግዴታዎች (ፉሩዱል-ውዱእ) ስድስት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

1 ፊትን መታጠብ ከእርሱ ጋርም መጉመጥመጥና መሰርነቅ (ውኃ በአፍንጫ አስገብቶ ማስወጣት) አብሮ ይካተታል

2 እጆችን ክርንን ጨምሮ ማጠብ         

3 ሙሉ ራስን ጆሮን ጨምሮ ማበስ

4 እግሮችን ቁርጭምጭሚትን ጨምሮ ማጠብ

5 ቅደም ተከተሉን መጠበቅ ይህም ማለት በወዱ አካሎች መካከል ማለት ነው፤ አላህ በተከበረ ቃሉ እንዳለው በመጀመሪያ ፊትን ማጠብ ለጥቆ እጆችን ለጥቆ ራስን (ጭንቅላትን) ማበስ ለጥቆ እግሮችን ማጠብ ነው፡፡  

6 ማከታተል ይህም ማለት አንዱን የውዱእ አካል አጥቦ በቻሉት አቅም ሳይዘገዩ ወደ ሌላው አካል ማለፍ ፡፡

ጥያቄ 74 ውዱእ የሚያበላሹ ነገሮች ስንት ናቸው?

መልስ 74 ውዱእ የሚያበላሹ ነገሮች (ነዋቂዱል-ውዱእ) አራት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

1 ከውኃ ሽንት እና አይነ ምድር መውጫ ቦታዎች በኩል የሚወጡ ነገሮች፡፡ ውኃ ሽንት፣ መዝይ፣ ሰገራ፣ ከፊንጢጣ የሚወጣ አየር እና የመሳሰሉት

2 በእብደት ወይም ራስን በመሳት ወይም ጭልጥ ባለ እንቅልፍ ምክንያት የአዕምሮ መሸፈን ቀለል ያለ እንቅልፍ (ሰመመን) ግን አያጠፋም

3 የግመል ስጋ መብላት

4 ያለ ምንም ግርዶሽ በባዶ እጅ ብልትን መንካት ፡፡

ጥያቄ 75 ለሶላት ውዱእ ማድረግ ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 75 ለሶላት ውዱእ ማድረግ ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው የአላህ ንግግር ነው፡፡

﴿يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓاْ إِذَا قُمۡتُمۡ إِلَى ٱلصَّلَوٰةِ فَٱغۡسِلُواْ وُجُوهَكُمۡ وَأَيۡدِيَكُمۡ إِلَى ٱلۡمَرَافِقِ وَٱمۡسَحُواْ بِرُءُوسِكُمۡ وَأَرۡجُلَكُمۡ إِلَى ٱلۡكَعۡبَيۡنِۚ ٦﴾ [المائدة: 6]

"እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ወደ ሶላት በቆማችሁ (ለመቆም ባሰባችሁ) ጊዜ ፊቶቻችሁን፣ እጆቻችሁንም እስከ ክርኖች እጠቡ፡፡ ራሶቻችሁንም (በውኃ) አብሱ፡፡ እግሮቻችሁንም እስከ ቁርጭምጭሚቶቻችሁ (እጠቡ)፡፡" (አል ማኢዳ፡6)

ጥያቄ 76 “አል ጉስል” ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 76 “አል ጉስል” (ትጥበት) ማለት፡- (አምልኮ ታስቦበት) ሙሉ አካልን ሸሪዓ በደነገገው መልኩ በውኃ ማዳረስ ማለት ነው፡፡

ጥያቄ 77 ትጥበትን ግዴታ የሚያደርጉ ነገሮች ምን ምን ናቸው?

መልስ 77 ትጥበትን ግዴታ የሚያደርጉ ነገሮች ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም ፡-

1 የፍትወት ጠብታ መፍሰስ፤ በኃይልና በስሜት የሚወጣ  

2 አል‐ጂማዕ የግብረ ስጋ ግንኙነት የዘር ፈሳሽ ባይወጣም እንኳን

3 የወር አበባ ወይም የወሊድ ደም ሙሉ በሙሉ ሲያበቃ ፡፡

ጥያቄ 78 ትጥበትን ግዴታ የሚያደርግ ነገር ሲከሰት መታጠቡ ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 78 ትጥበት ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው የአላህ ንግግር ነው፡-

﴿ وَإِن كُنتُمۡ جُنُبٗا فَٱطَّهَّرُواْۚ ٦﴾ [المائدة: 6]

" ጀናባ ከሆናችሁ ታጠቡ” (አል ማኢዳ ፡6)

ጥያቄ 79 የውዱእ እና የገላ ትጥበት ጥቅም ምንድን ነው?

መልስ 79 የውዱእ እና የገላ ትጥበት ጥቅሞች ብዙ ናቸው ዋና ዋናዎቹ ፡-

1 እስልምና ታላቅ ሃይማኖት በመሆኑ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ንፅህናን ወደ መጠበቅ ይጠራል፡፡

2 ውዱእ ማድረግ የውዱእ አካሎችን ባጠብን ቁጥር ወንጀልና ጥፋታችን እንዲማርልን ያደርጋል፡፡

3 የአካልን ጤንነት ለመጠበቅ ፤ ሰላማዊነትና ንቁነት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡

4 ሶላት በምንሰግድበት ጊዜ ከአላህ ጋር በጥሩ ሁኔታ ለመገናኘት (ለመመሳጠር) በጥሩ ሁኔታም ለመቅረብ ይረዳል፡፡

] ] ]

 ሶላት

ጥያቄ 80 ሶላት ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 80 ሶላት ማለት ፡- በአካል የሚሠራ (ለየት ያለና የታወቀ በውስጡ) ንግግሮችን እና ተግባራትን የያዘ በተክቢራ የሚጀመርና በማሰላመት የሚጠናቀቅ አምልኮ ነው፡፡

ጥያቄ 81 በእያንዳንዱ ወንድም ሆነ ሴት ሙስሊም ላይ ግዴታ የሆኑ ሶላቶች ብዛት ስንት ነው?

መልስ 81 ግዴታ የሆኑ ሶላቶች በቀንና በለሊት ውስጥ የሚተገበሩ አምስት ሶላቶች ናቸው፡፡

1 ፈጅር ወይም ሱብሒ (ሁለት ረከዓ)

2 ዙሁር (አራት ረከዓ)

3 ዐሱር (አራት ረከዓ)

4 መግሪብ (ሦስት ረከዓ)

5 ዒሻእ (አራት ረከዓ) ናቸው፡፡

ጥያቄ 82 አምስት ወቅት ሶላቶች ግዴታ ለመሆናቸው ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 82 አምስት ወቅት ሶላቶች ግዴታ ለመሆናቸው ማስረጃው የአላህ ንግግር      ነው፡፡

﴿حَٰفِظُواْ عَلَى ٱلصَّلَوَٰتِ وَٱلصَّلَوٰةِ ٱلۡوُسۡطَىٰ وَقُومُواْ لِلَّهِ قَٰنِتِينَ٢٣٨﴾ [البقرة: 238]

 (በ አምስት ወቅት) ሶላቶች  እና በመካከለኛዋ ሶላት ላይ ትጉ ለአላህም ታዛዦች ሆናችሁ  ቁሙ፡፡” (አል በቀራህ ፡238)

ጥያቄ 83 ሶላት መተው ሸሪዓዊ ብያኔው ምንድን ነው? ማስረጃውስ?

መልስ 83 ሶላት መተው ሸሪዓዊ ብያኔው ከእስልምና የሚያስወጣ የክህደት ተግባር   ነው፡፡ ማስረጃው የአላህ መልዕክተኛ ﷺ ንግግር ነው፡-

إن بين الرجل وبين الشرك والكفر ترك الصلاة

“በአንድ ሰውና በሺርክ (ማጋራት) ወይም ኩፍር (ክህደት) መካከል መለያው ሶላትን መተው ነው፡፡”   (ሙስሊም 82)

ጥያቄ 84 የሶላት (ሸርጦች) ቅድመ መስፈርቶች ስንት ናቸው?

መልስ 84 የሶላት ሸርጦች (ቅድመ መስፈርቶች) ዘጠኝ ናቸው እነርሱም፡-

1 ሙስሊም መሆን  

2 አዕምሮ ጤነኛ መሆን

3 ለአካለ መጠን መድረስ

4 ሐደሥን[2] ማስወገድ

5 ነጃሳን ማስወገድ (ከአካል፣ ከልብስና ከመስገጃ ስፍራ)

6 ሐፍረተ ገላን መሸፈን

7 የሶላት ወቅት መግባት

8 ወደ ቂብላ (ካዕባ አቅጣጫ) መዞር   

9 ኒያ (በልብ ማሰብ) ናቸው፡፡

ጥያቄ 85 የሶላት አርካን (ማዕዘናት) ስንት ናቸው?

መልስ 85 የሶላት ማዕዘናት አስራ አራት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

1 ለቻለ ሰው ቀጥ ብሎ መቆም

2 የመክፈቻ ተክቢራ ማድረግ (ተክቢረቱ’ል ኢሕራም)

3 ፋቲሓን ማንበብ

4 ሩኩዕ ማድረግ

5 ከሩኩዕ ቀና ማለትና ቀጥ ብሎ መቆም

6 በሰባት የሱጁድ አካላት[3] ሱጁድ ማድረግ

7 ከሱጁድ መነሳት

8 በሁለቱ ሱጁዶች መካከል መቀመጥ

9 በእያንዳንዱ መሰረት (ሩክን) ላይ ረጋ ማለት

10 ቅደም ተከተሉን መጠበቅ (ተርቲብ)

11 የመጨረሻ ተሸሁድ ማንበብ

12 የመጨረሻ ተሸሁድ ለማንበብ መቀመጥ

13 በነብዩ ﷺ ላይ ሰላዋት ማውረድ

14 ሁለት ማሰላመት (በቀኝና በግራ በኩል መዞር) ናቸው፡፡

ጥያቄ 86 ሱረቱል ፋቲሓ የምትባለው ምዕራፍ የቷ ናት?

መልስ 86 ሱረቱል ፋቲሓ ፡- ከቁርኣን ውስጥ እጅግ ታላቅ ምዕራፍ ናት፡፡ ያለ እርሷ ሶላት ትክክል አይሆንም (ተቀባይነት የለውም) ፡፡

እርሷም ተከታዩ የአላህ ንግግር ናት፡-

﴿ ٱلۡحَمۡدُ لِلَّهِ رَبِّ ٱلۡعَٰلَمِينَ٢ ٱلرَّحۡمَٰنِ ٱلرَّحِيمِ٣ مَٰلِكِ يَوۡمِ ٱلدِّينِ٤ إِيَّاكَ نَعۡبُدُ وَإِيَّاكَ نَسۡتَعِينُ٥ ٱهۡدِنَا ٱلصِّرَٰطَ ٱلۡمُسۡتَقِيمَ٦ صِرَٰطَ ٱلَّذِينَ أَنۡعَمۡتَ عَلَيۡهِمۡ غَيۡرِ ٱلۡمَغۡضُوبِ عَلَيۡهِمۡ وَلَا ٱلضَّآلِّينَ٧﴾ [الفاتحة: 1-7]

“ምስጋና (ሁሉ) ለአላህ የተገባ ነው፤ የዓለማት ጌታ ለሆነው ¨ እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ ¨ የፍርዱ ቀን ባለቤት ለሆነው፡፡ ¨ አንተን ብቻ እንግገዛለን፤ አንተንም ብቻ እርዳታን እንለምናለን፡፡ ¨ ቀጥተኛውን መንገድ ምራን፡፡ ¨  የእነዚያን በነርሱ ላይ በጎ የዋልክላቸውን በነሱ ላይ ያልተቆጣህባቸውንና ያልተሳሳቱትንም ሰዎች መንገድ ምራን፤ በሉ፡፡”  (አል ፋቲሐህ 1-7)

ጥያቄ 87 የሶላት ዋጂባት (ግዴታዎች) ስንት ናቸው?

መልስ 87 የሶላት ግዴታዎች ስምንት ናቸው፡- 

1 ከመክፈቻው ተክቢራ (ተክቢረቱ’ል ኢሕራም) ውጪ ያሉ ሁሉም ተክቢራዎች

2 ሩኩዕ ላይ ሱብሐነ ረብቢየል-ዐዚም (ኃያል ለሆነው ጌታዬ ጥራት ተገባው) ማለት

3 አሰጋጅ ወይም ብቻውን የሚሰግድ ሰው ሰሚዐልላሁ ሊመን ሐሚደህ (አላህ የአመስጋኙን ምስጋና ሰማ) ማለት

4 ረብበና ወለከል ሐምዱ (ጌታችን ሆይ ምስጋና ላንተ ነው) ሁሉም ሰጋጆች (አሰጋጅ፣ ተከትሎ የሚሰግድ እንዲሁም ብቻውን የሚሰግድ) ማለት አለባቸው 

5 ሱጁድ ላይ ሱብሐነ ረብቢየል-አዕላ (ከሁሉ የበላይ ጌታዬ ጥራት ተገባው) ማለት

6 በሱጁዶች መካከል ሲቀመጥ ረብቢግፊርሊ (ጌታዬ ሆይ ማረኝ) ማለት

7 የመጀመሪያውን ተሸሁድ ማንበብ  

8 ለመጀመሪያው ተሸሁድ መቀመጥ ናቸው፡፡

ጥያቄ 88 የመጀመሪያ ተሸሁድ የሚባለው ምንድን ነው?

መልስ 88 ተሸሁደ’ል አወል (የመጀመሪያ ተሸሁድ) ላይ ሰጋጁ የሚከተለውን ይላል ፡-

“አትተሒያቱ ሊላሂ ወስሶላዋቱ ወጥጠይዪባቱ ፣ አስሰላሙ ዐለይከ አይዩሀን-ነቢይዩ ወረሕመቱልላሂ ወበረካትሁ ፤ አስሰላሙ ዐለይና ወዓላ ዒባዲላሂ አስሷሊሒነ ፣ አሽሀዱ አንላኢላሀ ኢልለልላህ ወአሽሀዱ አንነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ፡፡”

ትርጉም ፡-

“ክብርና ልዕልና እንዲሁም ሶላቶችና መልካም ነገሮች ሁሉ ለአላህ ናቸው፡፡ አንቱ ነቢዩ ሆይ! የአላህ ሰላም፣ እዝነቱና በረከቶች በእርሶ ላይ ይስፈን ፤ ሰላም በእኛና በአላህ ደጋግ ባሮችም ላይ ይስፈን ፤ ከአላህ ሌላ በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለ እመሰክራለሁ ፤ ሙሐመድም የአላህ አገልጋይና መልዕክተኛ መሆናቸውን    እመሰክራለሁ፡፡”

ጥያቄ 89 የመጀመሪያው ተሸሁድ የሚደረገው መቼ ነው?

መልስ 89 የመጀመሪያው ተሸሁድ የሚደረገው ሰጋጁ የሁለተኛ ረከዓ ሱጁድን ጨርሶ ቀና ብሎ ሲቀመጥ ነው፡፡ ለዙሁር፣ ለዐሱር ለመግሪብና ለዒሻ ሶላቶች፡፡

ጥያቄ 90 ተሸሁድ አል-አኺር የመጨረሻ ተሸሁድ የሚባለው እንዴት ነው?

መልስ 90 በመጨረሻው ተሸሁድ ሰጋጁ እንዲህ ይላል፡-

“አትተሒያቱ ሊላሂ ወስሶላዋቱ ወጥጠይዪባቱ ፣ አስሰላሙ ዐለይከ አይዩሀን-ነቢይዩ ወረሕመቱልላሂ ወበረካትሁ ፤ አስሰላሙ ዐለይና ወዓላ ዒባዲላሂ አስሷሊሒነ ፣ አሽሀዱ አንላኢላሀ ኢልለልላህ ወአሽሀዱ አንነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ፡፡ አልላሁምመ ሰልሊ ዐላ ሙሐመዲን ወዐላ ኣሊ ሙሐመዲን ከማ ሶልለይተ ዐላ ኢብራሂመ ወዐላ ኣሊ ኢብራሂመ ኢንነከ ሐሚዱን መጂድ፡፡ አልላሁምመ ባሪክ ዓላ ሙሐመዲን ወዐላ አሊ ሙሐመዲን ከማ ባረክተ ዐላ ኢብራሂመ ወዓላ አሊ ኢብራሂመ ኢንነከ ሐሚዱን መጂድ፡፡”

ትርጉም ፡-

“ክብርና ልዕልና እንዲሁም ሶላቶችና መልካም ነገሮች ሁሉ ለአላህ ናቸው፡፡ አንቱ ነቢዩ ሆይ! የአላህ ሰላም፣ እዝነቱና በረከቶች በእርሶ ላይ ይስፈን ፤ ሰላም በእኛና በአላህ ደጋግ ባሮችም ላይ ይስፈን ፤ ከአላህ ሌላ በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለ እመሰክራለሁ ፤ ሙሐመድም የአላህ አገልጋይና መልዕክተኛ መሆናቸውን እመሰክራለሁ፤ አላህ ሆይ! ውዳሴህን ለኢብራሂምና ለቤተሰቦቻቸው እንዳወረድክላቸው ሁሉ ለሙሐመድና ለቤተሰቦቻቸው አውርድላቸው፤ አንተ ምስጉንና ኋያል (የላቅክ) ነህና፡፡አላህ ሆይ! ለኢብራሂምና ለቤተሰቦቻቸው ረድዔትን እንዳወረድክላቸው ሁሉ ለሙሐመድና ለቤተሰቦቻቸውም ረድዔትን አውርድላቸው፡፡ አንተ ምስጉንና ኋያል (የላቅክ)         ነህና፡፡”

ጥያቄ 91 የመጨረሻው ተሸሁድ የሚደረገው መቼ ነው?

መልስ 91 የመጨረሻው ተሸሁድ የሚደረገው ሰጋጁ በመጨረሻው ረከዓ ከሁለተኛው ሱጁድ ቀና ከተባለለ በኃላ ነው፡፡

ጥያቄ 92 የሶላት ሱናዎች ስንት ናቸው?

መልስ 92 የሶላት ሱናዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከእነርሱም ውስጥ፡-

1 ዱዓኡል ኢስቲፍታሕ የመክፈቻ ዱዓ ማድረግ

2 በሚቆምበት ጊዜ ቀኝ እጁን በግራ እጁ ላይ አድርጎ በደረት ላይ ማድረግ

3 በተክቢረቱል ኢሕራም ጊዜ፣ ሩኩዕ ሲወርድ፣ ከሩኩዕ ቀና ሲል እና የመጀመሪያውን ተሸሁድ አጠናቆ ለሶስተኛ ረከዓ ሲቆም እጆቹን ከትከሻ ወይም ከጆሮዎች አቅጣጫ ከፍ ማድረግ፡፡

4 በሩኩዕና በሱጁድ ጊዜ የሚባሉ ዚክሮችን ከአንድ በላይ መጨመር

5 ከሁለት ሱጁዶች መካከል የሚባለውን ዚክር ረቢግፊርሊ ከአንድ በላይ መጨመር

6 ለሩኩዕ ሲጎነበስ ራስን ከወገብ ትይዩ ማድረግ

7 በሱጁድ ወቅት የእጅ ጡንቻዎችን ከብብት እና ከጎን እንዲሁም ሆድን ከጭኖች ማራራቅ

8 በሱጁድ ወቅት ክንዶችን ከምድር ከፍ ማድረግ

9 በመጀመሪያው ተሸሁድ ፣ በሱጁዶች መካከልና በባለ ሁለት ረከዓ ሶላቶች የመጨረሻው ተሸሁድ ጊዜ መቀመጫን በግራ እግር ላይ ማሳረፍና ቀኝ እግርን ቀጥ አድርጎ ማቆም፡፡ ይህ አቀማመጥ ኢፍቲራሽ ተብሎ ይጠራል፡፡  

10 በባለ ሦስትና አራት ረከዓ ሶላቶች የመጨረሻው ተሸሁድ ላይ በተወሩክ መቀመጥ፡፡ ተወሩክ ማለት በመቀመጫ መሬት ላይ ተቀምጦ የግራ እግርን ከቀኝ እግር ቅልጥም ሥር ማውጣትና የቀኝ እግር ጣቶችን ደግሞ መሬት ላይ ቀጥ አድርጎ ማቆም ነው፡፡

11 በመጨረሻው ተሸሁድ ወቅት ዱዓ ማድረግ

12 በሱብሒ፣ በጁምዓ፣ በሁለቱ ዒዶች፣ በሶላተል ኢስቲስቃእ (ዝናብ ሲጠፋ በሚሰገድ ሶላት) እንዲሁም በመግሪብና ዒሻ የመጀመሪያ ሁለት ረከዓዎች ላይ ድምፅን ከፍ አድርጎ መቅራት

13 በዙሁር፣ በዐሱር፣ በመግሪብ ሶስተኛው ረከዓና በዒሻ የመጨረሻዎቹ ሁለት ረከዓዎች ላይ ድምፅን ዝቅ ማድረግ

14 ከፋቲሓ ውጪ ያሉ የቁርኣን አያዎችን ማንበብ ናቸው፡፡

ጥያቄ 93 በሶላት መሠረቶች፣ ግዴታዎችና ሱንናዎች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

መልስ 93 በሶስቱ መካከል ያለው ልዩነት የሚከተለው ነው፡-

የሶላት አርካን (መሠረቶች) ፡- አውቆም ይሁን ረስቶ ከተተወ ሶላት ይበላሻል፡፡

የሶላት ዋጂብ (ግዴታዎች) ፡- ሆን ተብሎ ከተተወ ሶላት ያበላሻል በመርሳት ከተተወ ግን ሱጁዱ ሰህው (የመርሳት ሱጁድ) እንዲሰግድ ይገደዳል፡፡

የሶላትን ሱናዎች ፡- መሥራቱ ተወዳጅ ሲሆን ሰጋጁ ቢተወው ምንም ችግር የለውም፡፡

ጥያቄ 94 ሶላትን የሚያበላሹ ነገሮች ስንት ናቸው?

መልስ 94 ሙብጢላቱ አስ’ሶላት (ሶላትን የሚያበላሹ) ነገሮች ስምንት ናቸው፡-

1 ሆን ብሎ እያስታወሰና እያወቀ መናገር፡፡ የረሳ ወይም ጃሂል (ክልክል መሆኑን ሳያውቅ) ከሆነ በዚህ ምክንያት ሶላቱ አይበላሽም

2 ድምፅ ያለው ሳቅ            

3 መብላት ወይም መጠጣት                                                                  

4 አውራ (ሶላት ውስጥ መሸፈን ያለበትን የሰውነት አካል) መገለፅ                                                 

5 የቂብላ አቅጣጫን ለቆ መዞር                                                                                            

6 ከሶላት እንቅስቃሴ ውጪ የሆነ ብዙ እንቅስቃሴ ማድረግ                                                         

7 የጦሀራ መበላሸት                                                                                                               

8 ከሰላት አርካን ማዕዘናት መካከል አንዱን ማዕዘን መተው ለምሳሌ ጡምአኒና (እርጋታን) መተው ወይም በሰባት የሱጁድ አካላት ሱጁድ አለማድረግ ናቸው፡፡

እዚህ ጋር በሶላት ውስጥ ማድረግ የማይቻሉ ክልክል ተግባራትን ማንሳት ያስፈልጋል ለምሳሌ ዓይንን ወደ ሰማይ (ወደላይ) ማንጋጥ ፣ ማእሙም (ተከታይ) ኢማምን (መሪ/አሰጋጅን) መቅደም ፣ ሰጋጆችን የሚረብሹ መጥፎ ጠረን ያለው ነገር መጠቀም ፣ ምላስን ሳያንቀሳቅሱ በልብ ብቻ ቁርኣንን ማንበብ ይገኙበታል፡፡  

ጥያቄ 95 የሶላት ጥቅም ምንድን ነው?

መልስ 95 የሶላት ጥቅም በጣም ብዙ ሲሆን፡፡ ከእነርሱም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ፡-

1 ሶላት የቀልብን እርጋታ ይቸራል ፣ ልብን ያሰፋል ፣ ከአላህ ጋር በቅርበት የሚገናኙበት (የሚመሳጠሩበት) አጋጣሚ ነው፡፡

2 ሶላት ወንጀልንና ጥፋትን ታስምራለች፡፡

3 ሶላት ሙስሊምን ከመጥፎ አደጋ ትጠብቃለች፡፡ በአላህ ጥበቃ ከለላ ውስጥ እንዲሆን ታደርጋለች፡፡

4 ሶላት ሙስሊምን ከአስፀያፊና መጥፎ ተግባሮች ትከለክላለች፡፡

5 ሶላት ከአላህ እርዳታ ለማግኘትና ጉዳይን ለማስፈፀም በእርሷ ይታገዙባታል፡፡

] ] ]

 ዘካ

ጥያቄ 96 ዘካ ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 96 ዘካ ማለት ፡- የተወሰነ መጠን የደረሰን ገንዘብ ፣ (በተወሰኑ መስፈርቶች) ለተወሰኑ ተገቢ ቡድኖች ፣ በተወሰነ ጊዜ የሚሰጥ ንብረት ማለት ነው፡፡

ጥያቄ 97 ዘካ ግዴታ ለመሆኑ መረጃው ምንድን ነው?

መልስ 97 ዘካ ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው ተከታዩ የአላህ ንግግር ነው፡-

﴿وَأَقِيمُواْ ٱلصَّلَوٰةَ وَءَاتُواْ ٱلزَّكَوٰةَ ٤٣﴾ [البقرة: 43]

 “ሶላትንም አቋቁሙ ዘካንም  ስጡ፡፡” (አል በቀራህ፡43)

ጥያቄ 98 ዘካ ግዴታ የሚሆንባቸው የንብረት ዓይነቶች ስንት ናቸው?

መልስ 98 ዘካ ግዴታ የሚሆንባቸው የንብረት ዓይነቶች አምስት ናቸው፡-

1 የቤት እንስሳት እነርሱም ግመል ፣ የጋማ ከብት ፣ በግና ፍየል ናቸው፡፡

2 ከምድር የሚበቅሉ አዝርዕት እና ሰብሎች ፡፡

3 ወርቅ እና ብር (silver/ ሲልቨር) እንዲሁም የእነርሱን ቦታ ተክቶ የሚሠራ ማንኛውም የገንዘብ ኖት፡፡

4 ለሽያጭ (ንግድ) የቀረቡ እቃዎች ፡፡

5 ከመሬት ሥር የሚወጡ ማዕድናት ወይም የድሮ ሰዎች ከቀበሩት ቅርስ የሚገኙ ንብረቶች፡፡

ጥያቄ 99 ዘካ ግዴታ እንዲሆን ሸርጡ (ቅድመ መስፈርቱ) ምንድን ነው?

መልስ 99 ዘካ ግዴታ እንዲሆን የሚያደርጉ ሸርጦች አራት ናቸው፡-

1 ሙስሊም መሆን

2 ከባርነት ነፃ መሆን

3 የ «ኒሷብ» (ዘካህ ግዴታ የሚሆንበት አነስተኛው መጠን) ባለቤት መሆን

4 ንብረቱ በባለቤቱ ይዞታ ሥር ሆኖ በጨረቃ አቆጣጠር አንድ ዓመት መቆየት[4]፡፡

ጥያቄ 100 ዘካ የሚገባቸው አካላት እነማን ናቸው?

መልስ 100 ዘካ የሚገባቸው አካላት ስምንት[5] ዓይነት ናቸው፡፡ አላህም በተከበረው ቃሉ ማንነታቸውን ገድቦ ገልፆልናል፡፡

﴿۞إِنَّمَا ٱلصَّدَقَٰتُ لِلۡفُقَرَآءِ وَٱلۡمَسَٰكِينِ وَٱلۡعَٰمِلِينَ عَلَيۡهَا وَٱلۡمُؤَلَّفَةِ قُلُوبُهُمۡ وَفِي ٱلرِّقَابِ وَٱلۡغَٰرِمِينَ وَفِي سَبِيلِ ٱللَّهِ وَٱبۡنِ ٱلسَّبِيلِۖ فَرِيضَةٗ مِّنَ ٱللَّهِۗ وَٱللَّهُ عَلِيمٌ حَكِيمٞ٦٠﴾ [التوبة: 60]

(ግዴታ) ምጽዋቶች ለድሆች፣ ለምስኪኖች፣  በርሷም ላይ ሠሪዎች ለሆኑ፣ ልቦቻቸውም (ኢስላምን) ለሚለማመዱ፣ ጫንቃዎችንም (በባርነት ተገዢዎችን) ነጻ በማውጣት፣ በባለ ዕዳዎችም፣ በአላህ መንገድም በሚሠሩ፣ (ካገሩ ለወጣ) መንገደኛ ብቻ ነው፡፡ ከአላህ ዘንድ (የተገደበች) ግዴታ ናት፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡”                      (አት ተውባ፡60)

ጥያቄ 101 የዘካ መደንገግ ጥበቡ (ጥቅም/አስፈላጊነቱ) ምንድን ነው?

መልስ 101 የዘካ መደንገግ ጥቅምና አስፈላጊነቱ በጣም ብዙ ሲሆኑ ከእነርሱም  ውስጥ፡-

1 እርስ በርስ መኗኗርን፣ መረዳዳት ፣ በሀብታምና ድሃ ሙስሊሞች መካከል መዋደድና መፋቀርን ይፈጥራል፡፡

2 ነፍስን ያነፃል ፣ ያጠራል ፣ ከስስትና ከስቁንቁንነት ባህሪ ለመራቅ ይረዳል፡፡

3 በረካን ያመጣል ፣ እድሜን ይጨምራል ፣ ከአላህ የሆነ መተኪያም ያስገኛል፡፡

]]]

 ፆም

ጥያቄ 102 ፆም ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 102 ፆም ማለት ከመብል ፣ ከመጠጥና ከሌሎች ፆምን ከሚያፈርሱ ነገሮች አስቦበት ከእውነተኛው ጎህ መቅደድ ጀምሮ ፀሀይ እስከምትጠልቅበት ሰዓት ድረስ መቆጠብና መታቀብ ነው፡፡

ጥያቄ 103 የረመዳን ወር ፆም ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 103 የረመዳን ወር መፆም ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው ተከታዩ                                የአላህ ቃል ነው፡-

﴿يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ كُتِبَ عَلَيۡكُمُ ٱلصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى ٱلَّذِينَ مِن قَبۡلِكُمۡ لَعَلَّكُمۡ تَتَّقُونَ١٨٣﴾ [البقرة: 183]

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ፆም በነዚያ ከእናንተ በፊት በነበሩት ህዝቦች ላይ እንደተፃፈ (እንደተደነገገ) በእናንተ ላይም ተፃፈ ትጠነቀቁ ዘንድ፡፡” (አል በቀራህ ፡183)

ጥያቄ 104 የፆም ሸርጦች (ቅድመ መስፈርቶች) ስንት ናቸው?

መልስ 104 የፆም ቅድመ መስፈርቶች ስድስት ናቸው ፡-

1 ሙስሊም መሆን

2 ለአቅመ አደም ወይም ሀዋ መድረስ

3 አቅል (አዕምሮ) ጤናማ መሆን

4 ከህመም ነጻ መሆን

5 አገር ቤት ተቀማጭ መሆን (ጉዞ ላይ አለመሆን)

6 ለሴት ከወር አበባና ከወሊድ ደም መጽዳት ናቸው፡፡

ጥያቄ 105 በረመዷን ለማፍጠር የሚያስችሉ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው?

መልስ 105 በረመዷን ለማፍጠር የሚያስችሉ ምከንያቶች አራት ናቸው፡-

1 ህመም ወይም እርጅና፤ ከህመሙ ወይም እርጅናው ጋር መፆም የሚከብዳቸው ከሆነ

2 መንገደኛ መሆን

3 እርግዝና ወይም ጡት ማጥባት

4 የወር አበባ ወይም የወሊድ ደም ናቸው፡፡

ጥያቄ 106 ፆምን የሚያበላሹ ነገሮች ስንት ናቸው?

መልስ 106 ሙፍሲዳቱ አስ’ሰውም (ፆምን የሚያበላሹ) ነገሮች ሰባት ናቸው፡-

1 ግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀም

2 የዘር ፈሳሽ (ፍትወትን ማፍሰስ)

3 መብላት ወይም መጠጣት

4 ምግብን ሊተኩ የሚችሉ (ኃይል ሰጪ) መርፌዎችን መወጋት

5 ዋግምት (መታገም)                      

6 ሆን ብሎ ማስመለስ፤ በሆድ ውስጥ ያለን ምግብ ወይም መጠጥ ማስወጣት

7 የወር አበባ ወይም የወሊድ ደም መፍሰስ ናቸው፡፡

ጥያቄ 107 ፆምን የሚያፈርሱ ነገሮች ፆምን የሚያፈርሱት መቼ ነው?

መልስ 107 ፆምን የሚያበላሹ ነገሮች ላይ ሦስት መስፈርቶች ካልተሟሉ ፆምን አያበላሹም

1 ጾመኛው የሸሪዓዊ ፍርዱን ወይም ጊዜውን የሚያውቅ ከሆነ፡፡

2 ጾመኛ መሆኑን እያስታወሰ ከሆነ (ረስቶ ከሆነ ችግር የለውም) ፡፡

3 በምርጫው የሚያደርገው ከሆነ (ተገዶ ከሆነ አያፈርስም) ፡፡

ጥያቄ 108 የፆም መደንገግ ጥበቦች ምን ምን ናቸው?

መልስ 108 የፆም መደንገግ (ጥበቦች) ጥቅሞች በጣም ብዙ ናቸው ከእነርሱም       ውስጥ፡-

1 ነፍስን እንደ ትዕግስትና ቻይነት ባሉ መልካምና የላቁ ባህሪያት ያንፃል፡፡

2 አላህ ምግብና መጠጥን በመቸሩ ለባሮቹ የዋለውን ታላቅ ፀጋ ለማስታወስ ይረዳል፡፡

3 የድሆችን ችግር ለመረዳትና ለእነርሱም መልካም እንድንውል ያደርጋል፡፡

4 የሰውነትን ጤንነትና ሰላም ለመጠበቅ ይረዳል፡፡

] ] ]

 ሐጅ

ጥያቄ 109 ሐጅ ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 109 ሐጅ[6] ማለት፡- የተወሰኑ ተግባራትን ለመፈፀም፣ የተወሰነ በሆነ ጊዜ መካ ለመሄድ ማሰብ ማለት ነው፡፡

ጥያቄ 110 ሐጅ ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 110 ሐጅ ማድረግ ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው ተከታዩ የአላህ ቃል ነው፡-

﴿ وَلِلَّهِ عَلَى ٱلنَّاسِ حِجُّ ٱلۡبَيۡتِ مَنِ ٱسۡتَطَاعَ إِلَيۡهِ سَبِيلٗاۚ ٩٧﴾ [آل عمران: 97]

 “ለአላህም በሰዎች ላይ ወደርሱ መሄድን በቻለ ሁሉ ላይ ቤቱን መጎብኘት ግዴታ አለባቸው፡፡” (አሊ ዒምራን፡97)

ጥያቄ 111 የሐጅ ሹሩጥ (ቅድመ መስፈርቶች) ስንት ናቸው?

መልስ 111 የሐጅ ሹሩጥ (ቅድመ መስፈርቶች) አምስት ናቸው፡-

1 ኢስላም (ሙስሊም መሆን)

2 ዐቅል (የአዕምሮ ጤናማ) መሆን

3 ለአቅመ አደም ወይም ሐዋ መድረስ

4 ከባርነት ነፃ መሆን

5 ችሎታ አቅም መኖር ናቸው፡፡

ጥያቄ 112 የሐጅ አፈፃፀም ዓይነቶች ስንት ናቸው?

መልስ 112 የሐጅ አፈፃፀም ዓይነቶች ሦስት ናቸው

1 አት-ተመቱዕ ይህም በሐጅ ወራት (ማለትም ከሸዋል ወር መጀመሪያ አንስቶ እስከ ዙልሂጃ ወር አስረኛ ቀን ጎህ መቅደድ) ድረስ ባሉት ጊዜያት ለዑምራ ኒያ (ኢሕራም) በማድረግ ዑምራን ጨርሶ (ወደ መደበኛ አኗኗር ከተመለሰ በኋላ በዚያው ዓመት) ዙልሂጃ ስምንተኛው ቀን (የወመ-አትተርዊያ) ለሐጅ ኒያ (ኢሕራም) ማድረግ ነው፡፡      

2 አል-ቂራን ማለት በሐጅ ወራት ዑምራንና ሐጅን በማጣመር በአንድ ላይ በመነየት (ኢሕራም) ማድረግ ነው፡፡   

3 አል-ኢፍራድ ለሐጅ ብቻ ኒያ (ኢሕራም) ማድረግ ነው፡፡

በላጩ የሐጅ አፈፃፀም ተመቱዕ ከዚያም ቂራን ከዚያም ኢፍራድ ነው፤ ቃሪንና ሙፍሪድ የሐጅ አፈፃፀማቸው ተመሳሳይ ሲሆን የሚለያዩት ቃሪን ሀዲዩ[7]ን ከራሱ ጋር አብሮ ይዞ መጓዙ ግዴታ ሲሆንበት ሙፍሪድ ግን ግዴታ አይሆንበትም፡፡

ጥያቄ 113 የሐጅ አርካን (ማዕዘናት) ስንት ናቸው?

መልስ 113 የሐጅ አርካን (ማዕዘናት) አራት ናቸው፡-

1 ኢሕራም[8] ማድረግ    

2 ዓረፋ ሜዳ (ክልል) ላይ መቆም

3 ጠዋፍ[9] አል ኢፋዳህ ማድረግ

4 በ “ሰፋ” እና “መርዋ” ኮረብታዎች ሰዕይ[10] ማድረግ ናቸው፡፡

ጥያቄ 114 የሐጅ ዋጂባት (ግዴታዎች) ስንት ናቸው?

መልስ 114 የሐጅ ግዴታዎች ሰባት ናቸው፡-

1 ኢሕራምን ከሚቃት[11] ማድረግ

2 በቀኑ ክፍለ ጊዜ ወደ ዐረፋ ክልል ላይ ለደረሰ ፀሐይ እስክትጠልቅ እዛው መቆየት

3 የእርዱ ቀን አጥቢያ ለሊቱን በሙዝደሊፋ ማደር

4 የአያመ ተሽሪቅ[12] ለሊቶችን ሚና ላይ ማደር

5 የሚወረወሩ ጠጠሮችን ቅደም ተከተል ጠብቆ መወርወር

6 ፀጉርን መላጨት ወይም ማሳጠር (ሴቶች ከሙሉ ፀጉራቸው ጫፍ ላይ የአንድ ጣት አንጓ ርዝመት ያህል ያሳጥራሉ)

7 ጠዋፈል ወዳዕ (የመሰናበቻ ጠዋፍ) ማድረግ፡፡ የወር አበባ ወይም የወሊድ ደም ከገጠማት ሴት ውጪ ላሉ ሑጃጅ፡፡

ጥያቄ 115 የሐጅ ሱናዎች ምን ምን ናቸው?

መልስ 115 የሐጅ ሱናዎች ብዙ ናቸው ከእነርሱም ውስጥ፡-

1 ከኢሕራም በፊት ገላን መታጠብና ሽቶ መቀባት (ሽቶ መቀባት ለወንድ ብቻ ነው)

2 ሙፍሪድ ወይም ቃሪን ለሆነ ሰው መካ እንደገባ (ጠዋፈል ቁዱም) የመግቢያ ጠዋፍ ማድረግ

3 ጠዋፈል ቁዱም በሚያደርጉበት ጊዜ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ዙሮች በዝግታ ሩጫ (ሶም ሶማ) መዞር

4 በጠዋፈል ቁዱም ጊዜ ቀኝ እጅን ከፎጣ ማውጣትና ፎጣውን ከብብት ስር አሳልፎ ግራ ትከሻ ላይ መጣል (አል ኢድጢባዕ)

5 ከጠዋፍ በኃላ ሁለት ረከዓ መስገድ

6 የዓረፋ አጥቢያ ለሊት በሚና ማደር

7 ከኢሕራም ጀምሮ ጀምረቱል-ዐቀባ[13] ላይ ጠጠር እስከሚወረወርበት ቀን ድረስ ተልቢያ[14] ማድረግ፡፡

8 የዙሁር እና የዐሱር ሶላትን (ጀምዕ) አጣምሮ ጀምዕ ተቅዲም አስቀድሞ በዙሁር ሶላት ወቅት መስገድ፡፡ መግሪብና ዒሻን ደግሞ አጣምሮ ሙዝደሊፋ ላይ በደረሰበት ወቅት የዒሻ ሶላት ጊዜ እስካልወጣ ድረስ መስገድ፡፡ 

ጥያቄ 116 በሐጅ አርካን፣ ዋጂባት እና ሱናዎች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

መልስ 116 አርካን ማለት ያለ እርሱ ሐጅ ትክክል የማይሆንበት ማለት ነው፡፡

ዋጂብ ማለት እርሱን ያልፈፀመ እንስሳ ማረድ ግዴታ የሚሆንበት ነው፡፡

ሱና ማለት ቢፈጸም ተወዳጅ የሆነ ሲሆን በአንጻሩ ባይፈጸም ደግሞ ምንም ችግር የሌለው ተግባር ነው፡፡

ጥያቄ 117 ለሐጅ ወይም ለዑምራ ኢሕራም ባደረገ ሰው ላይ የተከለከሉ ነገሮች (መህዙራት) ምን ምን ናቸው?

መልስ 117 መህዙራት አል ኢሕራም ማለት ለሐጅ ወይም ለዑምራ ኢሕራም ባደረገ ሰው ላይ የተከለከሉ ተግባራት ናቸው፡፡ እነርሱም ሦስት ዓይነት ናቸው፡፡

የመጀመሪያው ፡- ይህ ክፍል በወንድም ሆነ በሴት ሙሕሪም ላይ የተከለከሉ ተግባራት ናቸው፡፡ እነርሱም ሰባት ናቸው፡-

1 የራስን ፀጉር በመላጨትም ይሁን በሌላ መንገድ ማስወገድ[15]

2 ጥፍርን መቁረጥ

3 አካልን ወይም ልብስን ሽቶ መቀባት (ለወንድ ከኢሕራም በፊት ግን ይቻላል)

4 ጋብቻን ለራሱ ወይም ለሌላ መፈፀም

5 ከግብረ ስጋ ግንኙነት ውጪ በስሜት መነካካት (መሳሳምና መተሻሸት)

6 የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀም

7 የዱር አራዊትን ማደን (ወይም ሌላ ሰው እንዲያድን ማዘዝ) ናቸው፡፡

ሁለተኛው ፡- ይህ ክፍል ደግሞ ክልክልነታቸው ለወንዶች ብቻ ሲሆኑ ሁለት ክልከላዎች ናቸው እነርሱም፡-

1 ራስን መሸፈን[16]

2 በአካል ቅርፅ የተሰሩ ልብሶችን መልበስ[17]፡፡

ሶስተኛ ፡- ይህ ክፍል ደግሞ ክልክልነቱ ለሴቶች ብቻ የሆነ ነው፡፡

1 ኒቃብ[18] መልበስ     

 2 የእጅ ጓንት ማጥለቅ፡፡

ጥያቄ 118 የሐጅ መደንገግ ጥቅም ምንድን ነው?

መልስ 118 የሐጅ መደንገግ እጅግ ብዙ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን ከእነርሱም ውስጥ፡-

1 ዓለም ላይ ካሉ ሀገራት በጠቅላላ የተገኙ ሙስሊሞች በአንድ ስፍራ ተሰባስበው ውዴታና ፍቅርን ይፈጥራሉ እርስ በእርስ ይተዋወቃሉ፡፡

2 በሙስሊሞች መካከል ያለው አንድነት በግልፅ ይታያል፡፡ በሀብታምና በድሀ፣ በዓረብና በአጀም፣ በነጭና በጥቁር መካከል ምንም አይነት ልዩነት ሳይኖር በአንድ ጊዜ አንድ ዓይነት ልብስ ለብሰው በአንድ ቦታ ይሰባሰባሉ በዚህም አንድ ህዝብ መሆናቸው ይንፀባረቃል፡፡

3 አኼራን ያስታውሳል ፤ ባሮች የቂያማ ዕለት አላህ ፊት የሚቆሙበትንም ሁኔታ እንዲሁ ያስታውሳል፡፡

] ] ]

 የአህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ ጥቅል እምነቶች

ጥያቄ 119 እስልምና ውስጥ ካሉ ጀማዓዎች ነፃ የምትወጣው የቷ ናት?

መልስ 119 ከእሳት ነጻ የምትወጣው ጀማዓ አህለ ሱንና ወል ጀማዓህ[19] ናት፡፡

ጥያቄ 120 አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ የሚባሉት እነማን ናቸው?

መልስ 120 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ የሚባሉት የመልዕክተኛውን ሱንና አጥብቀው የያዙና በእርሱም በውስጥም በግልጽም፣ በንግግርም፣ በተግባርም፣ በእምነትም የሚሠሩበት በዚያ ላይም የተሰባሰቡ ናቸው፡፡

በሌላ አገላለፅ ፡-

  የቀጥተኛው መንገድ ባለቤቶች፣ ትክክለኛውን እስልምና አጥብቀው የያዙ፣ መልዕክተኛው ሙሐመድ ﷺ የመጡበትንና አስ’ሰለፉ አስ’ሷሊሕ (መልካም ቀደምቶች) የተጓዙበትን አጥብቀው የያዙ ናቸው፡፡ ለዚህም ተብሎ የሰለፉነ ሷሊሕን ጎዳና በመከተላቸው ወደ እነርሱ (ተጠግተው) ሰለፊይ (የሰለፎችን መንገድ ተከታይ) ተብለውም ይጠራሉ፡፡

ጥያቄ 121 አህለ ሱንናህ ወልጀማዓህ ተብለው የተሰየሙበት ምክንያት ምንድን ነው?

መልስ 121 አህለ ሱንናህ ተብለው የተሰየሙበት ምክንያት ሱናን አጥብቀው የያዙ በመሆናቸው ነው፡፡ ወል ጀማዓህ (የህብረት ባለቤቶች) የተባሉት ደግሞ በሱንና ላይ የተሰባሰቡ በመሆናቸው ነው፡፡

ጥያቄ 122 ሰለፊይ ተብለው የተሰየሙበት ምክንያት ምንድን ነው?

መልስ 122 ሰለፊይ ተብለው የተሰየሙበት ምክንያት በነዚያ መልካም በሆኑ ቀደምቶች (አስ’ሰለፉ አስ’ሳሊሕ) ሰሓቦች አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና እና እነርሱን በመልካም በተከተሏቸው መንገድ የሚጓዙ በመሆናቸው ነው፡፡

ጥያቄ 123 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ ነፃ የምትወጣው ቡድን ለመሆኗ ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 123 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ አልፊርቀቱ አንናጂያ (ነፃ የምትወጣው ጀማዓ) ለመሆኗ ማስረጃው የመልዕክተኛው ﷺ ንግግር ነው፡-

“አይሁድ ወደ ሰባ አንድ ቦታ ተከፋፈለች ፣ ነሳራ ደግሞ ወደ ሰባ ሁለት ቦታ ተከፋፈለች ፣   ይህችኛዋ ህዝብ ደግሞ ወደ ሰባ ሦስት ቦታ ትከፋፈላለች ፣ ሁሉም (ሰባ ሁለቱም) የእሳት ናቸው አንዷ ስትቀር ፡፡ ሶሐባዎችም  ፡-አንቱ የአላህ መልእክተኛ ﷺ ሆይ እነርሱ እነማን ናቸው አሉ :: እርሳቸውም ዛሬ እኔና ባልደረቦቼ ባለንበት ላይ የሆኑ ናቸው፡፡” አሉ፡፡  በሌላ ዘጋባ ደግሞ “ጀማዓህ [20] (ህብረት) ናቸው” ብለዋል፡፡

ጥያቄ 124 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ የአላህን የበላይነት “ዑሉው” እና ከዐርሽ በላይ መሆኑ “ኢስቲዋእ” ላይ ያላቸው እምነት ምንድን ነው? 

መልስ 124 የአላህን የበላይነት ዑሉው እና ከዐርሽ በላይ ከፍ ማለት ኢስቲዋእ በተመለከተ የአህሉ ሱንና ወልጀማዓህ እምነት ሶሓባዎች የተስማሙበት እና የአላህ መልዕክተኞች በአጠቃላይ የተስማሙበት ነው፡፡ ይህም አላህ ከሰማይ በላይ መሆኑን ፣ ከፍጥረታቱ በአጠቃላይ የበላይ ሆኖ ለልቅናውና ለታላቅነቱ በሚገባ መልኩ ከዐርሽ በላይ ከፍ ማለቱን ነው፡፡ ፍጥረታቱ ከአላህ ባህሪያት ጋር በየትኛውም መልኩ ፍፁም አይመሳሰሉም፡፡

ጥያቄ 125 የአላህን (ከፍጡራን ሁሉ) የበላይነት ባህሪ “ዑሉው” የሚያፀድቀው የቁርኣን መረጃ ምንድን ነው?

መልስ 125 የአላህን የበላይ መሆን ዑሉው የሚያፀድቀው የቁርኣን መረጃ ተከታዩ የላቀው አላህ ንግግር ነው፡-

﴿ءَأَمِنتُم مَّن فِي ٱلسَّمَآءِ أَن يَخۡسِفَ بِكُمُ ٱلۡأَرۡضَ فَإِذَا هِيَ تَمُورُ١٦﴾ [الملك: 16]

“ከሰማይ በላይ ያለው በእናንተ ምድርን ቢደረባባችሁ ወዲያውም እርሷ የምታረገርግ ብትሆን ትተማመናላችሁን?” (አል ሙልክ: 16)   

﴿سَبِّحِ ٱسۡمَ رَبِّكَ ٱلۡأَعۡلَى١﴾ [الأعلى: 1]

 “ከሁሉ በላይ የሆነውን ጌታህን ስም አሞግሥ(አጥራ)፡፡” (አል አዕላ፡ 1) እና እነዚህን የመሳሰሉ አንቀጾች ይገኙበታል፡፡  

ጥያቄ 126 የአላህን የበላይነት የሚያፀድቀው የሐዲሥ መረጃ ምንድን ነው?

መልስ 126 የአላህን የበላይ መሆን የሚያፀድቀው የሐዲሥ መረጃ ሐዲሡል ጃሪያ “የባሪያዋ ሐዲሥ” በመባል በሚታወቀው ሐዲሥ ላይ መልዕክተኛው ﷺ በጠየቋት ጊዜ ባሪያዋ የመለሰችው መልስ ነው፡፡ 

መልዕክተኛው ﷺ እንዲህ አሏት፡- አላህ የት ነው?               فقال: أين الله؟

እርሷም፡-  በሰማይ (ከሰማይ በላይ) አለች                                            

ከዛም እርሳቸውም፡-  እኔ ማን ነኝ? አሏት                       ثم قال: من أنا ؟            እርሷም፡- እርሶ የአላህ መልዕክተኛ ﷺ ነዎት አለቻቸው          فقالت: أنت رسول الله

قال: اعتقها فإنها مؤمنة.

እርሳቸውም፡- “ልቀቃት (ነፃ አውጣት) እርሷ አማኝ ነች፡፡” አሉ፡፡                       (ሙስሊም (537) ዘግበውታል፡፡)

ጥያቄ 127 የአላህ ከዐርሽ በላይ የመሆንን “ኢስቲዋእ” ባህሪ ለማፅደቅ ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 127 አላህ ከዐርሽ በላይ ለመሆኑ ማስረጃው የአላህ ቃል ነው፡-

﴿ٱلرَّحۡمَٰنُ عَلَى ٱلۡعَرۡشِ ٱسۡتَوَىٰ٥﴾ [طه: 5]

“አርረሕማን ከዐርሽ በላይ ከፍ አለ፡፡” (ጣሃ፡5)

በቁርኣን ውስጥ ከዚህ አንቀፅ ሌላ በስድስት የተለያዩ ቦታዎች ላይ አላህ እንዲህ ብሏል፡- ﴿ ثُمَّ ٱسۡتَوَىٰ عَلَى ٱلۡعَرۡشِۖ ٥٤﴾ [الأعراف: 54] “ከዚያም ከአርሹ በላይ ከፍ አለ፡፡” ሱረቱ (አል አዕራፍ ፡54) ፣ ሱረቱ (ዩኑስ ፡3) ፣ ሱረቱ (አር ረዕድ ፡2) ፣ ሱረቱ (አል ፉርቃን ፡59) ፣ ሱረቱ (አስ ሰጀዳህ ፡43) እና ሱረቱ (አል ሐዲድ ፡4) ናቸው፡፡

ጥያቄ 128 ኢስቲዋእ ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ 128 ኢስቲዋእ ማለት ፡- ከበላይ መሆን ፣ ከፍ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት አላህ ከዐርሽ በላይ ከፍ አለ ፣ ከበላይ ሆነ ማለት ነው፡፡

በመሆኑም ኢስቲዋእ የሚለው ቃል የዐረብኛ ቋንቋ ትርጉሙ የታወቀ ሲሆን የአላህ ከዐርሽ በላይ የሆነበት አኳኋን ግን አይታወቅም፡፡

ኢማሙ ማሊክ እንዳሉት ፡- “ኢስቲዋእ የታወቀ ነው፡፡ አኳኃኑ አይታወቅም ፣ በእርሱ ማመን (ዋጂብ) ግዴታ ነው ፣ ስለ እርሱ (አኳኃኑ) መጠየቅ ቢድዓ ነው፡፡”

ማለትም ስለ (ከይፊያው) አኳኃኑ መጠየቅ (ቢድዓ ነው) ማለት ነው፡፡ ይህ የእርሳቸው ንግግር ለሁሉም የአላህ ባህሪያት የሚሆን (ምላሽ ለመስጠት የሚረዳ) ቃዒዳ (መርሆ) ነው፡፡ የአላህ ባህሪያት ትርጉማቸው የታወቀ ነው አኳኃኑ ግን አይታወቅም፡፡

ጥያቄ 129 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ ቁርኣንን በተመለከተ ያላቸው አቋም ምንድን ነው?

መልስ 129 የአህሉ ሱንና አቋም (መዝሀብ) ቁርኣን የአላህ ቃል ነው የሚል ነው ሑሩፉ (ቃላቶቹም)፣ ማዕናው (ትርጉሙም)፡፡ ከአላህ የተወረደ ነው ፍጡር አይደለም ፣ ከእርሱ ከአላህ የተጀመረ ወደ እርሱም የሚመለስ ነው፣ (በእውነታው) በቀጥታው አላህ የተናገረው ነው ዘይቤያዊ (ቅኔያዊ) አገላለፅ አይደለም፤ ወደ ጂብሪል ያስተላለፈው ከዚያም በመልዕክተኛው ሙሐመድ ﷺ ቀልብ ላይ የተወረደ ነው፡፡ 

ጥያቄ 130 ቁርኣን የአላህ ቃል ለመሆኑ ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 130 ቁርኣን የአላህ ቃል ለመሆኑ ማስረጃው የአላህ ንግግር ነው፡-

﴿وَإِنۡ أَحَدٞ مِّنَ ٱلۡمُشۡرِكِينَ ٱسۡتَجَارَكَ فَأَجِرۡهُ حَتَّىٰ يَسۡمَعَ كَلَٰمَ ٱللَّهِ ٦﴾ [التوبة: 6]

“ከአጋሪዎች አንዱ ጥገኝነትን ቢጠይቅህ አስጠጋው ፤ የአላህን ንግግር ይሰማ ዘንድ፡፡”      (አት ተውባ፡6)

በዚህ አያ (አንቀጽ) ላይ የአላህን ቃል (ንግግር) በሚለው የተፈለገው ቁርኣንን ነው፡፡

ጥያቄ 131 ቁርኣን ከአላህ የወረደ እንጂ ፍጡር ላለመሆኑ ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 131 ከአላህ የተወረደ ለመሆኑ ማስረጃው የአላህ ንግግር ነው፡-

﴿تَبَارَكَ ٱلَّذِي نَزَّلَ ٱلۡفُرۡقَانَ عَلَىٰ عَبۡدِهِۦ لِيَكُونَ لِلۡعَٰلَمِينَ نَذِيرًا١﴾ [الفرقان: 1]

“ያ ፉርቃንን በባሪያው ላይ ለዓለማት አስፈራሪ ይሆን ዘንድ ያወረደው (አምላክ) ክብርና ጥራት ተገባው፡፡” (አል ፉርቃን፡1)

ፍጡር ላለመሆኑ (ይልቁኑ የአላህ ቃል ለመሆኑ) ማስረጃው ደግሞ ተከታዩ የአላህ ቃል ነው፡-

﴿ أَلَا لَهُ ٱلۡخَلۡقُ وَٱلۡأَمۡرُۗ ٥٤﴾ [الأعراف: 54]

“ንቁ! መፍጠርና ማዘዝ የእርሱ ብቻ ነው፡፡” (አል አዕራፍ፡54) 

(በዚህ የቁርአን አንቀፅ በግልፅ) አላህ ትዕዛዝን ፍጡር (የፍጥረታቱ አካል) ያልሆነ አድርጎታል፡፡ ቁርኣን ደግሞ ከትዕዛዝ ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡                                አላህ እንዲህ ብሏልና ፡-

﴿وَكَذَٰلِكَ أَوۡحَيۡنَآ إِلَيۡكَ رُوحٗا مِّنۡ أَمۡرِنَاۚ ٥٢﴾ [الشورى: 52]

“እንደዚሁም ወደ አንተ ከትእዛዛችን ሲሆን መንፈስን (ቁርኣንን) አወረድን፡፡”                 (አሽ ሹራ፡52) 

የአላህ ንግግር ደግሞ ከእርሱ ባህሪዎች መካከል አንዱ ባህሪ ነው፡፡ የእርሱ ባህሪያት ደግሞ ፍጡር አይደሉም፡፡

ጥያቄ 132 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ አላህን ስለ ማየት ያላቸው አቋም ምንድን ነው?

መልስ 132 አህሉ ሱንናወል ጀማዓህ አላህን ማየት በተመለከተ ያላቸው አቋም ፡-

ሙእሚኖች የቂያማ (የምፅአት) ዕለት እና በጀነት ውስጥ ጌታቸውን ይመለከቱታል፣ በዓይናቸው ያዩታል የሚል ነው፡፡

ጥያቄ 133 ሙእሚኖች ጌታቸውን በአኼራ እንደሚያዩት ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 133 ሙእሚኖች ጌታቸውን እንደሚመለከቱት ማስረጃው የአላህ ቃል ነው፡-

﴿وُجُوهٞ يَوۡمَئِذٖ نَّاضِرَةٌ٢٢ إِلَىٰ رَبِّهَا نَاظِرَةٞ٢٣﴾ [القيامة: 22-23]

“ፊቶች በዚያ እለት ያበራሉ ፤ ወደ ጌታቸውም ይመለከታሉ”     (አል ቂያማ፡22-23)

በሌላም አንቀጽ አላህ እንዲህ ይላል፡-

﴿لِّلَّذِينَ أَحۡسَنُواْ ٱلۡحُسۡنَىٰ وَزِيَادَةٞۖ ٢٦﴾ [يونس: 26]

 “ለነዚያ መልካም ለሠሩ መልካም  እና  ጭማሪ አላቸው”       (ዩኑስ ፡26)

በሰሒሕ ሐዲሥ ላይ እንደመጣው “ٱلۡحُسۡنَىٰ” የተባለው ጀነት ሲሆን “زِيَادَةٞۖ” ጭማሪ የተባለው ደግሞ ወደ ተከበረው የአላህ ፊት መመልከት ነው፡፡ (ሙስሊም 181 ይመልከቱ)                       

ጥያቄ 134 ኢማንን በተመለከተ አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ ያላቸው አቋም ምንድን ነው?

መልስ 134 አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ ዘንድ ኢማን ማለት በምላስ የሚነገር፣ በልብ የሚቋጠር፣ በአካል የሚተገበር፣ አላህን በመታዘዝ የሚጨምር አላህን በማመፅ (ሸይጧንን በመታዘዝ) የሚቀንስ ማለት ነው፡፡

ጥያቄ 135 ንግግርና ተግባር ከኢማን ክፍል ለመሆናቸው ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 135 ማስረጃው የመልዕክተኛው ﷺ ንግግር ነው፡-

" الإيمان بضع وسبعون شعبة فأفضلها قول : لا إله إلا الله وأدناها إماطة الأذى عن الطريق والحياء شعبة من الإيمان "

“ኢማን ከሰባ አንድ እስከ ሰባ ዘጠኝ የሚሆን ቅርንጫፍ አሉት፡፡ በላጩ (የበላዩ) ላኢላሀ ኢለላህ የሚለው ንግግር ሲሆን፤ ዝቅተኛው ደግሞ ሰዎችን የሚያስቸግርን ነገር ከመንገድ ማስወገድ ነው፡፡ ሐያእ አንዱ የኢማን ቅርንጫፍ ነው፡፡”[21]

(ከሐዲሡ እንደምንረዳው) ነብዩ ﷺ ንግግርንና ተግባርን ከኢማን ክፍል[22]    አድርገዋቸዋል፡፡

ጥያቄ 136 ኢማን እንደሚጨምርና እንደሚቀንስ ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 136 ኢማን እንደሚጨምር ማስረጃው ተከታዩ የአላህ ንግግር ነው፡-

﴿ وَيَزۡدَادَ ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓاْ إِيمَٰنٗا ٣١﴾ [المدثر: 31]

“እነዚያም ያመኑት እምነትን እንዲጨምሩ፡፡” (አል ሙደሢር ፡31)

ኢማን እንደሚጨምር የሚያሳየው መረጃ ራሱ ሊቀንስ እንደሚችል ማስረጃ       ይሆናል፡፡

ጥያቄ 137 አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ አንድነትን በተመለከተ ያላቸው አቋም ምንድን ነው ማስረጃውስ?

መልስ 137 አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ ከሙስሊሞች ጀመዓ እና ከመሪያቸው ጋር አብሮ መሆን ግዴታ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ከእነርሱም  ከመለየት (ከመነጠል) መራቅ እንዳለብንም ያምናሉ፡፡ አላህ እንዲህ ብሎ አዟልና ፡-

﴿وَٱعۡتَصِمُواْ بِحَبۡلِ ٱللَّهِ جَمِيعٗا وَلَا تَفَرَّقُواْۚ ١٠٣﴾ [آل عمران: 103]

“በአላህ የእምነት ገመድ ተሳሰሩ አትለያዩም፡፡” (አሊ ዒምራን፡103)

ጥያቄ 138 አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ መሪዎችን ስለመታዘዝ ያላቸው እምነት ምንድን ነው ማስረጃውስ?

መልስ 138 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ ሙስሊም መሪዎች በመልካም እስካዘዙ ድረስ እነርሱን መታዘዝ ግዴታ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ምንም እንኳን መሪው ጨቋኝ መጥፎ ቢሆንም፡፡ ማስረጃውም የአላህ መልዕክተኛ ﷺ (ግልፅ) ንግግር ነው፡-

"على المرء المسلم السمع والطاعة فيما أحب وكره إلا أن يؤمر بمعصية فإن أُمر بمعصية فلا سمع ولا طاعة."

“በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ መስማትና መታዘዝ ግዴታ ነው ፤ በወደደውም በጠላውም በወንጀል ላይ እስካልታዘዘ ድረስ ፤ በወንጀል ላይ ከታዘዘ መስማትና መታዘዝ የለም፡፡”

(ቡኻሪ (7144) ፣ ሙስሊም (1839))

ጥያቄ 139 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ ከባባድ ወንጀልን ስለፈፀመ ሰው ያላቸው እምነት ምንድን ነው? ማስረጃውስ?

መልስ 139 አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ ዘንድ ከባባድ ወንጀሎችን የፈፀመ ሰው ያለው ብያኔ ሰውየው ከሀዲ አይሆንም፤ በአኼራም እንዲሁ በጀሀነም እሳት ዘውታሪ አይሆንም፤ ፍርዱ /ጉዳዩ/ አላህ ዘንድ ነው፡፡ ከፈለገ በሚግገባው ልክ ይቀጣዋል ፣ ከፈለገ ደግሞ ይቅር ብሎ ይምረዋል፡፡ አላህ እንዲህ ብላል፡-

﴿إِنَّ ٱللَّهَ لَا يَغۡفِرُ أَن يُشۡرَكَ بِهِۦ وَيَغۡفِرُ مَا دُونَ ذَٰلِكَ لِمَن يَشَآءُۚ ٤٨﴾ [النساء: 48]

“አላህ በእርሱ ላይ ማጋራትን አይምርም ፤ ከእርሱ ውጪ ያለን ለፈለገው ይምራል፡፡”     (አን ኒሳእ ፡48)

ጥያቄ 140 ሙስሊምን ማክፈር (ከሀዲ ማለት) ብያኔው ምንድን ነው? ማስረጃውስ?

መልስ 140 ሙስሊምን ማክፈር (በከሀዲነት መፈረጅ) ሐራም (ክልክል) የሆነ ተግባር ነው፡፡ ማስረጃውም የመልዕክተኛው ﷺ ንግግር ነው፡-

"مـن رمـى مؤمنـا بكفر فهو كقتله"

“ሙስሊምን በክህደት የሰደበ (ያነወረ) እርሱን እንደመግደል ነው፡፡” (ቡኻሪ (6105))

ጥያቄ 141 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ ሶሐባዎችን በተመለከተ ያላቸው እምነት ምንድን ነው?

መልስ 141 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ ሶሐባዎችን በተመለከተ ያላቸው እምነት ፡-

ቀልባቸው ለመልዕክተኛው  ባልደረቦች ሰላማዊ ነው፤ ከምቀኝነት፣ ከጥላቻ፣ በጠላትነት ከመፈረጅ፣ ምላሳቸው እነርሱን ከማነወር እና ከመሳደብ የፀዳ ሰላማዊ ነው፡፡ ይወዷቸዋል፣ የአላህን ውዴታ ይለምኑላቸዋል፣ በመልካምም ይከተሏቸዋል፡፡ አላህም በገለፀው መልኩ ለእነርሱም ዱዓ ያደርጉላቸዋል ፡-

﴿ رَبَّنَا ٱغۡفِرۡ لَنَا وَلِإِخۡوَٰنِنَا ٱلَّذِينَ سَبَقُونَا بِٱلۡإِيمَٰنِ ١٠﴾ [الحشر: 10]

“ጌታችን ሆይ! ለእኛም ለእነዚያም በእምነት ለቀደሙን ወንድሞቻችን ምሕረት አድርግ፡፡ ” (አል ሐሽር ፡10) 

ጥያቄ 142 አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ የመልዕክተኛውን   ቤተሰቦች አስመልክቶ ያላቸው እምነት ምንድን ነው?

መልስ 142 አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ የመልዕክተኛውን   የቅርብ ቤተሰቦች (አሊ-በይት) በተመለከተ ለሁለት ምክንያቶች ሲሉ እነርሱን ይወዳሉ ፡-

አንደኛ ፡- ለኢማናቸው ሲሉ (ሙእሚን በመሆናቸው)

ሁለተኛ ፡- የመልዕክተኛው   የቅርብ ወገን በመሆናቸው ነው፡፡

ነገር ግን በእነርሱ ላይ ድንበር አያልፉም፤ እነርሱን ከአላህ ውጪ በማምለክ ወይም ደግሞ በግለሰብ ደረጃ ከስህተት የፀዱ ናቸው ብለው አያምኑም፡፡ (በጥቅል ስንመለከት ግን ሶሐባዎች በጠቅላላ ጥብቆችና ታማኞች ናቸው፡፡)

ጥያቄ 143 አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ አል ወላእ ወል በራእን በተመለከተ ያላቸው እምነት ምንድን ነው?

መልስ 143 አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ ወላእ እና በራእን በተመለከተ ያላቸው እምነት፡-

ወላእ እና በራእ ኢማን ከምታስገድዳቸው እና ላኢላሀ ኢለላህ ከምታስፈርዳቸው ነገሮች መሆናቸውን ነው፡፡

ወላእ ማለት ትርጉሙ አላህን ፣ መልዕክተኛውን  እና ሙእሚኖችን መውደድ ማለት ነው፡፡

በራእ ማለት ደግሞ ከክህደት እና ከከሀዲያን መራቅ ነው፤ እነርሱን በእምነታዊ ጉዳያቸውና በጥፋት ላይ ከመርዳት መቆጠብ፤ እነርሱ ብቻ በሚለዩበት ነገር ላይ ከእነርሱ ጋር ከመመሳሰል መራቅ ማለት ነው፡፡ 

ነገር ግን ከከሀዲያን መራቅ ሲባል እነርሱን መበደል፣ በእነርሱ ላይ ድንበር ማለፍ ከእነርሱ ጋር መኗኗርን መከልከል ማለት አይደለም፤ ይህንን ፈጽሞ      አያስይዝም፡፡ ይልቁኑ በሰላም መኗኗርን መልካም ማድረግንና በጎ መዋልን እስልምና ደንግጓል፡፡

ጥያቄ 144 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ ነብዩላህ ዒሳን በተመለከተ ያላቸው እምነት ምንድን ነው?

መልስ 144 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ ዒሳን በተመለከተ ያላቸው እምነት ዒሳ የአላህ አገልጋይ እና መልዕክተኛ፣ የማይመለኩ ሰው እና የአላህ ባሪያ እንደሆኑ፣ የማይስተባበሉ መልዕክተኛ፣ ከአደም ዘር የሆኑ የሰው ልጅ መሆናቸውን እና ያለ አባት ከእናት ብቻ የተፈጠሩ መሆናቸውን ያምናሉ፡፡

ጥያቄ 145 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ ከእስልምና ውጪ ያሉ ሃይማኖቶች እንደ የሁዳና ነሳራ ያሉት ላይ ያላቸው አቋም ምንድን ነው? ማስረጃውስ?

መልስ 145 አህሉ ሱንና ወል ጀማዓህ ኢስላም ከዚህ ቀደም የነበሩ እምነቶችን የሻረ መሆኑን ያምናሉ፡፡ አላህ ዘንድ ከነብዩ ሙሐመድ ﷺ መላክ በኃላ ከእስልምና ሃይማኖት ውጪ ያለ ሃይማኖት ተቀባይነት የለውም፡፡

ጥያቄ 146 እስልምና ትክክለኛ ሃይማኖት ለመሆኑና ከእርሱ ውጪ ያሉ ሃይማኖቶች ውድቅ ለመሆናቸው የቁርኣን ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 146 እስልምና ትክክለኛ ሃይማኖት ለመሆኑና ከእርሱ ውጪ ያሉ ውድቅ ለመሆናቸው የቁርኣን ማስረጃው ተከታዩ የአላህ ንግግር ነው፡-

﴿وَمَن يَبۡتَغِ غَيۡرَ ٱلۡإِسۡلَٰمِ دِينٗا فَلَن يُقۡبَلَ مِنۡهُ وَهُوَ فِي ٱلۡأٓخِرَةِ مِنَ ٱلۡخَٰسِرِينَ٨٥﴾ [آل عمران: 85]

“ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለውም፡፡ እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው፡፡ ”        (አሊ ዒምራን፡ 85)

ጥያቄ 147 በመልዕክተኛው ሙሐመድ ﷺ እና ይዘውት በመጡት እስልምና ሃይማኖት ማመን ግዴታ ለመሆኑ የሐዲሥ ማስረጃው ምንድን ነው?

መልስ 147 በመልዕክተኛው ሙሐመድ ﷺ እና በተላኩበት የእስልምና ሃይማኖት ማመን ግዴታ ለመሆኑ ማስረጃው ተከታዩ የአላህ መልዕክተኛ ﷺ ንግግር ነው፡-

"والذي نفس محمد بيده لا يسمع بي من هذه الأمة يهودي ولا نصراني ثم يموت ولم يؤمن بالذي أرسلت به إلا كان من أصحاب النار. "

“የሙሐመድ ነፍሱ በእጁ በሆነችው አምላክ (አላህ) እምላለሁ ከዚህ ዑማ የሆነ የሁዲም ይሁን ነሳራ የኔን መላክ ሰምቶ ከዚያም እኔ በተላኩበት ሳያምን ከሞተ የእሳት ጓድ ይሆናል፡፡” (ሙስሊም 153)

ጥያቄ 148 አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ የቁርኣንና የሐዲሥ መረጃዎችን በተመለከተ ያላቸው  አቋም ምንድን ነው? ማስረጃውስ?

መልስ 148 አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ የቁርኣን እና የሐዲሥን ማስረጃዎች በተመለከተ ያላቸው አቋም ለቁርኣንና ለሰሒሕ ሐዲሥ መረጃዎች እጅ ይሰጣሉ ፤ በእርሱም ይመራሉ (ይከተላሉ) ፣ ለግል አስተሳሰብና አመለካከት ብለው እነርሱን ከመቃረን ይርቃሉ፡፡

﴿فَلَا وَرَبِّكَ لَا يُؤۡمِنُونَ حَتَّىٰ يُحَكِّمُوكَ فِيمَا شَجَرَ بَيۡنَهُمۡ ثُمَّ لَا يَجِدُواْ فِيٓ أَنفُسِهِمۡ حَرَجٗا مِّمَّا قَضَيۡتَ وَيُسَلِّمُواْ تَسۡلِيمٗا٦٥﴾ [النساء: 65]

“በጌታህም እምላለሁ በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍጹም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም፤ (ምእመን አይሆኑም)፡፡”  (አን ኒሳእ ፡65)

ጥያቄ 149 አህሉ ሱንና ወልጀማዓህ በአላህ መንገድ ስለመታገል “ጂሃድ” ያላቸው አቋም ምንድን ነው?

መልስ 149 አህሉ ሱንና መልጀማዓህ በአላህ መንገድ ላይ መታገል “ጂሃድ” የኢስላም የላይኛው ጉልላት ማማ መሆኑን እና የአላህ ቃል የበላይ እንድትሆን የተደነገገ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ለእርሱ መሟላት ያለባቸው ሸርጦች (ቅድመ መስፈርቶች) አሉ፡፡ ከዋና ዋናዎቹና አንገብጋቢዎቹ መካከል አቅም (ችሎታ) እና በቂ ጥንካሬ መኖር እንዲሁም በሙስሊም መሪ ባንዲራ ስር (በእርሱ መሪነት) መሆን ይገኙበታል፡፡

ጥያቄ 150 አህሉ ሱንና መልጀማዓህ ጽንፈኛ ቡድኖች በሚፈጽሙትና “ጂሃድ” ብለው በሚሰይሙት ተግባር ላይ ያላቸው አቋም ምንድን ነው?   

መልስ 150 አህሉ ሱንና ጽንፈኛ ቡድኖች በሚፈፅሙትና “ጂሃድ” ብለው ከሚሰይሙት ተግባር ራሳቸውን ያርቃሉ ያጠራሉም፡፡ ምክንያቱም እነርሱ የኸዋሪጆች[23]ን ጎዳና ስለሚከተሉ ነው፡፡ ተግባራቸውም መጥፎና እስልምናን የሚያጠለሽ ፣ ሰላምን የሚያናጋ የንጹሀንን እና የሰላማዊያንን ሕይወት የሚቀጥፍ ደም የሚያፈስ ፣ ጉዳትና ብልሹነትን በሙስሊም ሀገራት ላይ የሚያመጣና የሚያስፋፋ በመሆኑ ነው፡፡

መልካምን መገጠም ከአላህ ነው! የአላህ ሰላትና ሰላም በመልዕክተኛው ሙሐመድ ﷺ ላይ ይሁን!

] ] ]

إرشاد الأنام إلى أصول ومهمات دين الإسلام        

سؤال وجواب

قدم له وأوصى بترجمته

سماحت الشيخ عبد العزيز بن عبد الله آل الشيخ

المفتي العام للمملكة ورئيس هيئة كبار العلماء

وقرأ وقدم له

معالي الشيخ العلامة صالح بن فوزان الفوزان

عضو هيئة كبار العلماء

إعداد

د. عمر بن عبد الرحمن بن محمد العمر

عضو هيئة التدريس بالمعهد العالي للقضاء

ترجمة

حيدر خضر عبد الله

باللغة الأمهرية (الإثيوبية)



[1] የሥራ ዓይነታቸውም በተገለጸልን ለምሳሌ ጂብሪል ወሕይን በማስተላለፍ፤ ሥራቸው ባልተገለጸልንም ማመንንም ያካትታል:: (ተርጓሚው)

[2] ሐደሦች በሁለት የሚከፈሉ ሲሆን ትልቁና ትንሹ ይባላሉ፤ ትልቁ ሐደሥ የገላ ትጥበትን ግዴታ የሚያደርግ ሲሆን ትንሹ ደግሞ ዉዱእ ብቻ ግዴታ የሚያደርግ ነው፡፡

[3] ሰባት የሱጁድ አካላት የሚባሉት ግንባር ፣ ሁለት የእጅ መዳፎች ፣ ሁለት ጉልበት እና የሁለት እግር ጫፎች ናቸው፡፡

[4] ይህ አራተኛ መስፈርት ተፈፃሚ የሚሆነው በከብቶች ፣ በብርና ወርቅ (በገንዘብ ኖቶች) እና በንግድ ዕቃዎች ላይ ነው፡፡

ከምድር የሚበቅሉ አዝርእት እና ሰብሎች ላይ ከሆነ ዘካ ግዴታ የሚሆነው በአዝመራ ወቅት ነው፡፡ ማዕድናት እና ተቀብረው የተገኙ ንብረቶች (ሪካዝ) ላይ ደግሞ ዘካ ግዴታ የሚሆነው በተገኙበት ወቅት ነው፡፡

የቤት እንስሳት ውጤትና የንግድ ትርፍ ዓመታቸው የሚዞረው ከካፒታሉ ጋር አብሮ ነው፡፡ (መጀመሪያ ኒሳብ ከሞላው ንብረት ጋር አብሮ ነው፡፡)

[5] 1. ድሆች፣ 2. ምስኪኖች፣ 3. የዘካህ ሰብሳቢዎችና አከፋፋዮች፣ 4. ልቦናቸው (ኢስላምን) የሚላመድ፣ 5. በባርነት ሥር ያሉ ሙስሊም ወገኖች፣ 6. ባለዕዳዎች፣ 7. በ አላህ መንገድ ላይ ታጋይ የሆኑ፣ 8. ወደ አገሩ የሚመለስበት ወጪ ያጣ መንገደኛ ናቸው፡፡

[6] ሐጅ ማለት በሌላ አገላለፅ የታወቀ ቦታ ላይ ፣ በታወቁ ወቅቶች ነብዩ ﷺ ባስተማሩት መልኩ ውስን የሆኑ አምልኳዊ ተግባራትን መፈፀም ማለት ነው፡፡ (ተርጓሚው)

[7] ሀድይ፦ ማለት ወደ አላህ ለመቃረብ ከበግ ፣ ፍየል ፣ ግመል ወይም ከብት መካከል በሐረም ክልል የሚሰዋ እንስሳ ነው።  (ተርጓሚው)

[8] ኢሕራም፦ ማለት ሐጅ ወይም ዑምራ ስነ-ስርአት ውስጥ መግባትን መነየት ነው። (ተርጓሚው)

[9] ጠዋፍ፦ ማለት በብቸኝነት ወደ አላህ መቃረብን በማሰብ አላህን በማውሳት ወይም እርሱን በመማፀን አልያም ቁርአንን በማንበብ ከሐጀረል አስወድ ጀምሮ ካዕባን በስተግራ አደርጎ በርሱ ዙርያ ሰባት ጊዜ መዞር ነው። (ተርጓሚው)

[10] ሰዕይ፦ ማለት በሰፋና መርዋ ኮረብታዎች መካከል ወደ አላህ ለመቃረብ እርሱን እያወሱ፣ እየተማፀኑና እያመሰገኑ የሚከናወን የሰባት ጊዜ ምልልስ ነው። (ተርጓሚው) 

[11]  ሚቃት  ማለት ፦ በሸሪዓ ለሐጅ መጀመሪያ ተድርጎ የተመደበ ኢሕራም ማድረጊያ ቦታ ነው። እነርሱም አምስት ሲሆኑ አንደኛ:- ዙል ሑለይፋህ የመዲናና በመዲና በኩል የሚመጡ ሑጃጅ (ሐጅ አድራጊዎች) ኢሕራም የሚያደርጉበት ክልል (ሚቃት) ነው፤ በአሁኑ ወቅት አብያር ዓሊ በመባል ይታወቃል፤ ከመካ 450 ኪ.ሜ ይርቃል፤ ለመዲና በጣም ቅርብ ሲሆን ከመካ ግን ሩቁ ሚቃት ነው።

ሁለተኛ:-  አል ጁሕፋ  የሻም (፣ የግብፅ ፣የሞሮኮ) እና በእነርሱ በኩል አቋርጠው የሚመጡ ሑጃጅ ኢሕራም የሚያደርጉበት ክልል ነው፤ (ይህ ክልል ለራቢግ ከተማ ስለሚጠጋ) በአሁኑ ወቅት ሑጃጆች ከራቢግ ነው ኢሕራም የሚያደርጉት፤ ከመካ 186 ኪ.ሜ ይርቃል።

ሦስተኛ:-  ቀርነል መናዚል የነጅድና በእነርሱ በኩል አቋርጠው የሚመጡ ሑጃጅ ኢሕራም የሚያደርጉበት ክልል ነው፤ በአሁኑ ወቅት አስሰይለል-ከቢር በመባል ይታወቃል፤ ከመካ 78 ኪ.ሜ ይርቃል። 

አራተኛ:-  የለምለም የየመንና በእነርሱ በኩል አቋርጠው የሚመጡ ሑጃጅ  ኢሕራም የሚያደርጉበት ክልል ነው፤ ሰዎች በአሁኑ ወቅት አስሰዕድያ የሚባለው ቦታ ላይ ነው ኢሕራም የሚያደርጉት፤ ከመካ በስተ-ሰሜን 120 ኪ.ሜ ይርቃል።

አምስተኛ:- ዛቱ ዒርቅ ኢራቆችና በእነርሱ በኩል የሚያልፉ ሑጃጅ ኢሕራም የሚያደርጉበት ክልል ነው፤ ከመካ በስተ-ምስራቅ 100 ኪ.ሜ ይርቃል። 

[12] የዙልሒጃ 11ኛ 12ኛ እና 13ኛ ቀናት ናቸው:: (ተርጓሚው)

[13] ጀምረቱል-ዐቀባ፦ ማለት በዒዱ ዕለት ሑጃጆች ጠጠር የሚወረውሩበት ብቸኛው ጠጠር መወርወሪያ ሲሆን እርሱም ከሶስቱ ጀመራት መካከል ለመካ የበለጠ ቅርብ የሆነው እና ጀምረቱል ኩብራ በመባል የሚታወቀው ነው። (ተርጓሚው)

[14] ተልቢያ፦ የሚለው የቃሉ ጥሬ ትርጉም አቤት ወይም እሺ ማለትን የሚያመለክት ሲሆን በእዚህ አገባብ የተፈለገው ለአላህ ትእዛዛት እና ጥሪዎች ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀትን የሚያመለክተው « ለብበይክ አልላሁምመ ለብበይክ ለብበይከ ላ ሸሪከ ለከ ለብበይክ፣ ኢንነልሐምደ ወንኒዕመተ ለከ ወልሙልክ ላ ሸሪከ ለክ» የሚለው ቃል ነው። ትርጉሙም «አቤት አላህ ሆይ! አሁንም አቤት፤ አቤት አላህ ሆይ! አሁንም አቤት ለአንተ አጋር የለህም። ምስጋና፣ ፀጋና ንግስናም ለአንተ ነው። አጋር የለህም።» ተልቢያን በማለት ላይ ወንዶች ድምፃቸውን ከፍ ሲያደርጉ ሴቶች ግን ድምፃቸውን ከፍ አያደርጉም፡፡ (ተርጓሚው)

[15] ከየትኛውም የአካል ክፍል ቢሆን ፀጉርን መላጨት ወይም መቁረጥ ወይም በሌላ መንገድ ማስወገድ አይቻልም፡፡(ተርጓሚው)

[16] ከራስ ጋር ቀጥተኛ ንክኪ ባላቸው ነገሮች መሸፈን እንጂ በጥላ መጠቀም ወይም ጥላ ቦታ ስር መሆን ግን አይከለከልም፡፡

[17] ለምሳሌ ሱሪ ፣ ኮት ፣ የውስጥ ሱሪና የመሳሰሉት ክልክል ናቸው፡፡ ክፍት ሽርጥ ያላገኘ ግን ሱሪ መልበስ ተፈቅዶለታል፡፡

[18] ኒቃብ ማለት: - ሴት ልጅ የፊቷን ክፍል ለመሸፈን የምትጠቀምበት ነው። ባዕድ (መሕረሞቿ ያልሆኑ) ወንዶች ባሉበት ቦታ ፊቷን በሻሽዋ (ኺማር) እና በመሳሰሉት ነገሮች መሸፈን ልክ በኢሕራም ላይ ከመሆኗ በፊት ግዴታ እንደነበር ሁሉ ግዴታ ይሆንባታል፡፡ (ተርጓሚው)

[19] አህለ ሱንና ወል ጀማዓህ በዐረብኛው أهل السنة والجمعة ይህ ስያሜ የሚወክለው የቁርኣንና የትክክለኛ ሐዲሥን አስተምህሮ በቅን አበው ሶሓባ ታቢዒይና የታቢዒይ ታቢዒይ በተረዱት መንገድ ተገንዝበው ለሚተገብሩ ፣ መጤ የዲን ርዕዮቶችን ከመከተል እና ኢስላምን ራሳቸው በተመቻቸው መልኩ ከመረዳትና ከመተግበር የራቁ ሙስሊሞችን ነው፡፡ (ተርጓሚው)  

[20] /ቲርሚዚይ (2641) ፣ አቡ ዳውድ (4596) ፣ ኢብኑ ማጃህ (3992) ኢማሙ አልባኒ ሶሒሕ ኢብኑ ማጃህ ላይ ሶሒሕ ብለውታል (21364)/

[21] /ቡኻሪ (9) እና ሙስሊም (35) ቃሉ የሙስሊም ነው፡፡/

[22] “በላጩ (የበላዩ) ላኢላሀ ኢለላህ የሚለው ንግግር” ለንግግር ማስረጃ ሲሆን “ሰዎችን የሚያስቸግርን ነገር ከመንገድ ማስወገድ ነው፡፡”  የሚለው ደግሞ ለተግባር ማስረጃ ነው፡፡ (ተርጓሚው)

[23] ኸዋሪጆች ማለት ከነብዩ መላክ በኋላ ባለው የመጀመሪያው የኢስላም ዘመን አካባቢ ከተፈለፈሉ አንጃዎች መካከል ሲሆኑ ከጥንስሳቸው ጀምሮ ጠርዘኝነት በተሞላበት ጽንፈኛ አካሄዳቸው ፣ ሙስሊሞችን በማክፈርና ደማቸውን በማፍሰስ የሚታወቁ ናቸው፤ በዚህ ዘመን ደግሞ የእነርሱ አስተሳሰብ የተጠናወታቸውና ተጽዕኖ ያደረባቸው በጂሃድ ስም ህፃን፣ ሴት፣ አዛውንት፣ ንፁሃን ፣ ሰላማውያንን እና የእምነት ተቋማትን ጭምር ሳይለዩ በማፈንዳት፣ በአጥፍቶ መጥፋትና በመሳሰሉት ከኢስላም አስተምሮ ባፈነገጠ አካሄድ ላይ የሚገኙ የኢስላምን ገጽታ እጅጉን እያጠለሹ ያሉ ናቸው፡፡