(1) 1. አሊፍ፤ ላም፤ ራ፤ (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ይህ ቁርኣን ሰዎችን በጌታቸው ፈቃድ ከጨለማዎች ወደ ብርሃን አሸናፊ፤ ምስጉን ወደ ሆነው ጌታ መንገድ ታወጣ ዘንድ ወደ አንተ ያወረድነው መጽሐፍ ነው::
(2) 2. ወደ እዚያ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የእርሱ ብቻ ወደ ሆነው ጌታ ወደ አላህ መንገድ (ታወጣ ዘንድ ):: ለከሓዲያን ሁሉ ከብርቱ ቅጣት ወዮላቸው::
(3) 3. እነዚያ የቅርቢቱን ህይወት ከመጨረሻይቱ ህይወት ይበልጥ የሚወዱና ከአላህ መንገድ ሰዎችን የሚያግዱ፤ መጥመሟንም (ደካማ ጎኗን) የሚፈልጓት ናቸው:: እነዚያ በሩቅ ስህተት ውስጥ ናቸው::
(4) 4. ከመልዕክተኞች ማንኛውንም ለእነርሱ ያብራራላቸው ዘንድ በወገኖቹ ቋንቋ እንጂ በሌላ አልላክንም:: አላህ የሚፈልገውንም ያጠምማል:: የሚፈልገውንም ያቀናል:: እርሱ ሁሉን አሸናፊውና ጥበበኛው ነውና::
(5) 5. ሙሳን ወገኖችህን ከጨለማዎች ወደ ብርሃን አውጣ:: የአላህንም ቀናት አስገንዝባቸው በማለት በተዓምራታችን አጠናክረን በእርግጥ ላክነው:: በዚህ ውስጥ በብዙ ታጋሽና በብዙ አመስጋኝ ለሆኑት ሁሉ በእርግጥ ብዙ ተዓምራት አሉበት::
(6) 6. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሙሳም ለህዝቦቹ «ከፈርዖን ቤተሰቦች መጥፎን ቅጣት የሚያቀምሷችሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁን የሚያርዱና ሴቶቻችሁንም የሚተው ሲሆን በአዳናችሁ ጊዜ በእናንተ ላይ የዋለላችሁን የአላህን ጸጋ አስታውሱ:: በዚሃችሁ ከጌታችሁ የሆነ ታላቅ ፈተና አለበት።» ባለ ጊዜ የሆነውን አስታውስ::
(7) 7. ጌታችሁም፦ «ብታመሰግኑ በእርግጥ እጨምርላችኋለሁ:: ብትክዱም እቀጣችኋለሁ:: ቅጣቴ በእርግጥ ብርቱ ነው።» በማለት ባስታወቀ ጊዜ (የሆነዉን አስታውሱ)::
(8) 8. ሙሳ፡- «እናንተም በምድር ያለዉም ሁሉ በመላ ብትክዱ አላህ ተብቃቂና ምስጉን ነው።» አለ።
(9) 9. (ሙስሊሞች ሆይ!) የእነዚያ ከእናንተ በፊት የነበሩት የኑህ ህዝቦች፤ የዓድ፣ የሠሙድም የእነዚያም ከእነርሱ በኋላ የነበሩት ከአላህ በስተቀር ሌላ የማያውቃቸው ህዝቦች ወሬ (ታሪክ) አልመጣላችሁምን? መልዕክተኞቻቸው በማስረጃዎች መጡላቸውና እጆቻቸውን በቁጭት ሊነክሱ ወደ አፎቻቸው መለሱ: «በተላካችሁበት ነገር ካድን እኛም ወደ እርሱ ከምትጠሩን ነገር አወላዋይ በሆነ ጥርጣሬ ውስጥ ነን።» አሉ።
(10) 10. መልዕክተኞቻቸው «ከኃጢአቶቻችሁ እንዲሚራችሁ ወደ ተወሰነ ጊዜም ያለ ቅጣት እንዲያቆያችሁ የሚጠራችሁ ሲሆን ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ በሆነው አላህ በመኖሩ ጥርጣሬ አለን?» አሏቸው:: ህዝቦቹም፡ «እናንተ ብጤያችን ሰው እንጂ (ሌላ ፍጡር) አይደላችሁም:: አባቶቻችን ይገዙት ከነበሩት ልትከለክሉን ትሻላችሁን? ግልጽን አስረጅ ካመጣችሁት ሌላ እስቲ አምጡልን።» አሉ::
(11) 11. መልዕክተኞቻቸውም ለእነርሱ አሉ: «እኛ ብጤያችሁ ሰዎች እንጂ ሌላ አይደለንም:: ግን አላህ ከባሮቹ መካከል በሚሻው ሰው ላይ ይለግሳል:: እኛም በአላህ ፈቃድ እንጂ ማስረጃን ልናመጣላችሁ አይገባንም:: በአላህ ላይ ብቻ ምእመናን ይጠጉ (ይመኩ)።
(12) 12. «መንገዳችንን በእርግጥ የመራን ሲሆን በአላህ ላይ የማንመካበት ምን አለን? በማሰቃየታችሁም ላይ እንታገሳለን:: በአላህ ላይ ብቻ ተመኪዎች ሁሉ ይመኩ።» (አሉ)
(13) 13. እነዚያ በአላህ የካዱት ለመልእክተኞቻቸው: «ከምድራችን በእርግጥ እናወጣችኋለን ወይም ወደ ሃይማኖታችን ትመለሳላችሁ።» አሉ:: ወደ እነርሱም ጌታቸው እንዲህ ሲል ላከ: «(ከሓዲያን) በዳዮችን እናጠፋለን።
(14) 14. «ከእነርሱ በኋላም በምድሪቱ በእርግጥ እናስቀምጣችኋለን:: ይህ በፊቴ መቆሙን ለሚፈራና ዛቻዬን ለሚፈራ ነው።»
(15) 15. እርዳታንም ከአላህ ፈለጉ፤ ተረዱም። ጨካኝ ሞገደኛ የሆነም ሁሉ አፈረ።
(16) 16. ከስተፊቱ ገሀነም አለበት:: እዥ ከሆነም ውሃ ይጋታል::
(17) 17. ይጎነጨዋል፤ ሊውጠዉም አይቀርብም:: ሞትም ከየስፍራው ሁሉ ይመጣበታል:: እርሱም የሚሞት አይደለም:: ከበስተፊቱም ከባድ ቅጣት አለ::
(18) 18. የእነዚያ በጌታቸው የካዱት ሰዎች መልካም ሥራዎቻቸው ምሳሌ በነፋሻ ቀን ነፋስ እንደ በረታችበት አመድ ነው:: በሠሩት ሥራ በምንም ላይ ሊጠቀሙ አይችሉም። ይህ እርሱ ሩቅ ጥፋት ነው::
(19) 19. (የሰው ልጅ ሆይ!) አላህ ሰማያትንና ምድርን በእውነት የፈጠረ መሆኑን አታይምን? ቢሻ ያጠፋችኋል:: አዲስ ፍጡርንም ያመጣል::
(20) 20. ይህም እናንተን አጥፍቶ አዲስ ፍጥረትን ማምጣት በአላህ ላይ አስቸጋሪ ጉዳይ አይደለም::
(21) 21. የተሰበሰቡ ሆነው ለአላህ ይገለጻሉ። ሐሳበ ደካማዎቹም ተከታዮች ለእነዚያ ለኮሩት «እኛ ለእናንተ ተከታዮች ነበርን እናንተ ከአላህ ቅጣት ከእኛ ላይ አንዳችን ነገር ተከላካዮች ናችሁን?» ይሏቸዋል። አስከታዮቹም። «አላህ ባቀናን ኖሮ በመራናችሁ ነበር።» ይሏቸዋል:: «ብንበሳጭ ወይም ብንታገሥም በእኛ ላይ ሁሉም እኩል ነው:: ለእኛ ምንም መጠጊያ የለንም።» ይላሉ።
(22) 22. ነገሩም በተፈጸመ ጊዜ ሰይጣን ይላቸዋል: «አላህ እውነተኛውን ቃል ኪዳን ገባላችሁ እኔም ቃል ኪዳንም ገባሁላችሁ:: አፈረስኩባችሁም:: ለእኔም በእናንተ ላይ ምንም ሥልጣን አልነበረኝም:: ግና ጠራኋችሁና ታዘዛችሁኝ:: ስለዚህ አትውቀሱኝ ነፍሶቻችሁንም ውቀሱ:: እኔ የምረዳችሁ አይደለሁም እናንተም የምትረዱኝ አይደላችሁም። እኔ ከአሁን በፊት ለአላህ ተጋሪ በአደረጋችሁት ነገር ሁሉ ካድኩ በዳዮቹ ሁሉ አሳማሚ ቅጣት አለባቸው።»
(23) 23. እነዚያ በትክክል ያመኑና መልካም ሥራዎችን የሠሩ ሁሉ ከስሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲሆኑ በጌታቸው ፈቃድ እንዲገቡ ይደረጋሉ:: በውስጣቸው መከባበሪያቸው ሰላምታቸው «ሰላም ለእናንተ ይሁን መባባል» ነው።
(24) 24. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ መልካምን ቃል ሥሯ በምድር ውስጥ የተደላደለች ቅርንጫፏም ወደ ሰማይ የረዘመች እንደሆነች መልካም ዛፍ አድርጎ ምሳሌን እንዴት እንደገለጸ አላየህምን?
(25) 25. ፍሬዋን (ምግቧን) በጌታዋ ፈቃድ በየጊዜው ትሰጣለች:: አላህም ለሰዎች ይገሰጹ ዘንድ ምሳሌዎችን ይገልጻል::
(26) 26. የመጥፎ ቃል ምሳሌ ከምድር በላይ የተገረሰሰች ለእርሷ ምንም መደላደል የሌላት እንደ ሆነች መጥፎ ዛፍ ነው::
(27) 27. አላህ እነዚያን በትክክል ያመኑትን በቅርቢቱም ህይወት ሆነ በመጨረሻይቱም በመቃብር በተረጋገጠው ቃል (በሸሀዳ) ላይ ያደርጋቸዋል (ያጸናቸዋል):: ከሓዲያንንም አላህ ያሳስታቸዋል፤ አላህም የሚሻውን ይሰራልና::
(28) 28. ወደ እነዚያ የአላህን ጸጋ በክህደት ወደ ለወጡትና ህዝቦቻቸውን በጥፋት ሀገር ወዳሰፈሩት (ወደ ቁረይሾች) አላየህምን? (አልተመለከትክምን?)
(29) 29. ሀገሪቱም የሚገቡባት ስትሆን ገሀነም ናት:: መርጊያነቷ ምንኛ ትከፋ!
(30) 30. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለአላህ ከመንገዱ ያሳስቱ ዘንድ ባላንጣዎችን አደረጉለት:: (ሙሐመድ ሆይ!) «ጥቂትን ተጠቀሙ መመለሻችሁም ወደ እሳት ነው።» በላቸው።
(31) 31. መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ! ለእነዚያ ላመኑት ባሮቼ ሽያጭና ወዳጅነት የሌለበት ቀን ከመምጣቱ በፊት ሶላትን በደንቡ እንዲሰግዱ፤ ከሰጠናቸውም ሲሳይ በሚስጢርም ሆነ በግልጽ እንዲለግሱም ንገራቸው።
(32) 32. አላህ ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ከሰማይ ዳመናም ውሃን ያወረደ፤ በእርሱም ከፍሬዎች ሁሉ ለእናንተ ሲሳይን ያወጣላችሁ፤ መርከቦችንም በፈቃዱ በባህር ላይ ይንሳፈፉ ዘንድ ለእናንተ ያገራ፤ ወንዞችንም ለናንተ ያገራ ነው።
(33) 33. ጸሓይንና ጨረቃንም ዘወትር ሒያጆች ሲሆኑ ለእናንተ የገራ፤ ሌሊትንና ቀንንም ለእናንተ የገራላችሁ ነው::
(34) 34. ከለመናችሁትም ሁሉ የሰጣችሁ ነው:: የአላህንም ጸጋ ብትቆጥሩ እንኳ አትዘልቁትም:: ሰው በጣም በደለኛና ከሓዲ ነው::
(35) 35. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ኢብራሂም ባለ ጊዜ አስታውስ: «ጌታዬ ሆይ! ይህንን ሀገር መካን ጸጥተኛ አድርገው:: እኔንና ልጆቼንም ጣኦታትን ከመገዛት አርቀን።
(36) 36. «ጌታዬ ሆይ! እነርሱ (ጣኦታቱ) ከሰዎች ብዙዎችን አሳስተዋልና:: የተከተለኝም ሰው እርሱ ከእኔ ነው:: ትዕዛዜን የጣሰ ሰው ግን አንተ መሓሪና አዛኝ ነህ።
(37) 37. «ጌታችን ሆይ! እኔ አዝመራ በሌለው ሸለቆ ውስጥ በተከበረው ቤትህ በካዕባ አጠገብ ከዘሮቼ አስቀመጥኩ:: ጌታችን ሆይ! ሶላትን ደንቡን ጠብቀው ይሰግዱ ዘንድ አስቀመጥኳቸው:: ከሰዎችም ልቦችን ወደ እነርሱ የሚናፍቁ አድርግ:: ያመሰግኑህም ዘንድ ከፍሬዎች ስጣቸው::
(38) 38. «ጌታችን ሆይ! አንተ የምንደብቀውንም የምንገልጸውንም ሁሉ በእርግጥ ታውቃለህ:: በአላህ ላይ በምድርም በሰማይም ምንም ነገር አይደበቅም::
(39) 39. «ለእዚያ ከሽምግልና በኋላ ኢስማኢልንና ኢስሐቅን ለሰጠኝ አላህ ምስጋና ሁሉ ይገባው። ጌታዬ ልመናን ሰሚ ነውና::
(40) 40. «ጌታዬ ሆይ! ሶላትን አዘውትሬ የምሰግድ አድርገኝ:: ከዘሮቼም አድርግ ጌታችን ሆይ! ጸሎቴንም ተቀበለኝ።
(41) 41. «ጌታችን ሆይ! ለእኔም ለወላጆቼም ለአማኞችም ሁሉ ምርመራ በሚደረግበት ቀን ማረን።»
(42) 42. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህንም በደለኞች ከሚሠሩት ግፍ ዘንጊ አድርገህ አታስብ። የሚያቆያቸው ዓይኖች እስከሚፈጡበት ቀን ድረስ ብቻ ነው::
(43) 43. ወደ ጠሪው መልአክ ቸኳዮች ራሶቻቸውንም አንጋጣጮች ሆነው ዓይኖቻቸው ይፈጣሉ። ዓይኖቻቸው ወደ እነርሱ አይመለሱም:: ልቦቻቸው ባዶዎች ናቸው::
(44) 44. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሰዎችንም ቅጣቱ የሚመጣባቸውን ቀን አስፈራራቸው:: እነዚያም የበደሉትማ «ጌታችን ሆይ! እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አቆየን:: ጥሪህንም እንቀበላለንና መልዕክተኞቹንም እንከተላለንና።» ይላሉ። ይባላሉም: «ከአሁን በፊት በምድረ ዓለም ለእናንተ ምንም መወገድ የላችሁም በማለት የማላችሁ አልነበራችሁምን?
(45) 45. «በእነዚያም ነፍሶቻቸውን በበደሉት ሰዎች መኖሪያ ውስጥ ተቀመጣችሁ:: በእነርሱም እንዴት እንደሠራንባቸው ለእናንተም ተገለጸላችሁ፤ ለእናንተ ምሳሌዎችንም ገለጽንላችሁ።»
(46) 46. በነብዩ ላይ ሴራቸውንም በእርግጥ አሴሩ:: ሴራቸዉም ቅጣቱ አላህ ዘንድ ነው:: ሴራቸዉም ኮረብታዎች በእርሱ የሚወገዱበት አልነበረም::
(47) 47. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህንም ለመልዕክተኞቹ የገባላቸውን ቃል ኪዳኑን አፍራሽ አድርገህ አታስብ:: አላህ ሁሉን አሸናፊና የመበቀል ባለቤት ነው::
(48) 48. ምድር በሌላ ምድር የምትለወጥበትን ሰማያትም እንደዚሁ በሌላ ሰማያት የሚለወጥበትን እና አንድ ብቸኛና አሸናፊ ለሆነው አላህ ፍጡራን ሁሉ የሚገለጹበትን ቀን የሚሆነውን አስታውስ::
(49) 49. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አመጸኞችንም በዚያ ቀን በሰንሰለቶች ተቆራኝተው ታያቸዋለህ::
(50) 50. ቀሚሶቻቸው ከካትራሜ የተሰሩ ናቸው:: ፊቶቻቸውንም እሳት ትሸፍናቸዋለች::
(51) 51. አላህ ይህንን ያደረገው ነፍስ ሁሉ የሠራችውን ትመነዳ ዘንድ ነው:: አላህ ምርመራው ፈጣን ነው::
(52) 52. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ይህ ቁርኣን ለሰዎች ገሳጭና መድረስ ያለበት ነው:: ሊመከሩበት በእርሱም ሊስፈራሩበት፤ እርሱም አንድ አምላክ ብቻ መሆኑን ሊያውቁበት፤ የአእምሮ ባለቤቶችም ሊገሰጹበት የተወረደ ነው::