(1) 1. አንተ ነብይ ሆይ! አላህ ላንተ የፈቀደልህን ነገር ሚሰቶችህን ማስወደድን የምትፈልግ ስትሆን (ባንተ ላይ) ለምን እርም ታደርጋለህ? አላህ እጅግ መሀሪና አዛኝ ነው::
(2) 2. አላህ ለእናንተ የመሐሎቻችሁን መፍቻ ደነገገላችሁ፤ አላህ ረዳታችሁ ነው:: እርሱም ሁሉን አዋቂና እጅግ ጥበበኛ ነው።
(3) 3. ነብዩ ከሚስቶቹ ወደ አንዷ ወሬን በመሰጠረ ጊዜ (አስታውስ):: እርሱንም በነገረችና አላህ እርሱን ማውራቷን ባሳወቀው ጊዜ ከፊሉን አሳወቀ፤ ከፊሉንም ተወ፤ በእርሱም ባወራት ጊዜ «ይህን ማን ነገረህ?» አለች፤ «ሁሉን አዋቂው እና ውስጠ አዋቂው ነገረኝ» አላት::
(4) 4. (ሁለታችሁም) ወደ አላህ ብትመለሱ ልቦቻችሁ በእርግጥ ተዘንብለዋልና (ትስማማላችሁ):: በእርሱ (ጥቃት) ላይ ብትረዳዱ ግን ረዳቱ አላህ ነው። ጂብሪልም ከምእምናንም መልካሙ ከዚህም በኋላ መላእክቱ ረዳቶቹ ናቸው፡፡
(5) 5. ሁላችሁንም ቢፈታችሁ ከናንተ የበለጡ ሚስቶች ሙስሊሞች፤ ትክክለኛ አማኞች፤ ታዛዦች፤ ተጸፃቾች፤ ለአላህ ተገዢዎች፤ ጿሚዎች፤ ፈቴዎችም ደናግልም የሆኑትን ጌታው ሊለውጠው ይከጅላል::
(6) 6. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! መቀጣጠያዋ ሰዎችና ደንጋዮች ከሆነች እሳት ነፍሶቻችሁንም ቤተሰቦቻችሁንም ጠብቁ፤ በእርሷ ላይ ጨካኝና ኃይለኛ የሆኑ መላዕክት አሉ:: አላህን ያዘዛቸውን ነገር በመጣስ አያምጹም፤ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሰራሉ::
(7) 7. እናንተ በአላህ የካዳችሁ ሰዎች ሆይ! ዛሬ አታመካኙ፤ የምትመነዱት ያንን ትሰሩት የነበራችሁትን ብቻ ነው (ይባላሉ)::
(8) 8. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህ ነብዩን እነዚያንም ከእርሱ ጋር ያመኑትን በማያሳፍርበት፤ ብርሃናቸው በፊቶቻቸውና በቀኞቻቸው የሚሮጥ ሲሆን፡- «ጌታችን ሆይ! ብርሃናችንን ሙላልን፤ ለእኛ ምህረትንም አድርግልን፤ አንተ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነህና» በሚሉበት ቀን ጌታችሁ ከናንተ ኃጢአቶቻችሁን ሊሰርዝላችሁ፤ ከስሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶችም ሊያስገባችሁ ይከጅላልና ንጹህ የሆነችን ጸጸት በመጸጸት ወደ አላህ ተመለሱ።
(9) 9. አንተ ነብይ ሆይ! ከሓዲያን እና አስመሳዮችን ታገል፤ በእነርሱም ላይ በርታ፤ መኖሪያቸዉም ገሀነም ናት:: ምን ትከፋም መመለሻ!
(10) 10. አላህ ለእነዚያ ለካዱት ሰዎች የኑህን ሚስት እና የሉጥን ሚስት ምሳሌ አደረገ፤ ባሮቻችን ከሆኑ ሁለት መልካም ባሪያዎች ስር ነበሩ ከዷቸዉም፤ ኑሕም ሉጥም ከሚስቶቻቸው ምንም የአላህን ቅጣት አልገፈተሩላቸዉም፤ «ከገቢዎችም ጋር እሳትን ግቡ» ተባሉ::
(11) 11. ለእነዚያ ለአመኑትም አላህ የፈርዖንን ሚስት ምሳሌ አደረገ:: «ጌታየ ሆይ! አንተ ዘንድ በገነት ውስጥ ለእኔ ቤት ገንባልኝ፤ ከፈርዖንና ከስራዉም አድነኝ፤ ከበደለኞች ህዝቦችም አድነኝ» ባለች ጊዜ።
(12) 12. የዒምራን ልጅ መርየምንም ያችን ብልቷን የጠበቀችውን ምሳሌ አደረገ:: በእርሷም ውስጥ ከመንፈሳችን ነፋን:: በጌታዋ ቃላትና በመጽሐፍቱም አረጋገጠች፤ ከታዛዦችም ነበረች::