(1) 1. አር-ረህማን
(2) 2. ቁርኣንን አስተማረ::
(3) 3. ሰውን ፈጠረ::
(4) 4. መግለፅንም አስተማረው::
(5) 5. ጸሐይና ጨረቃ በተወሰነ (በየሂሳባቸው) ልክ ይሄዳሉ::
(6) 6. የሰማይ ከዋክብትና የምድር ዛፎችም ለእርሱ ይሰግዳሉ::
(7) 7. ሰማይንም ከፍ አደረጋት:: የትክክለኛነትን ሚዛንንም አስቀመጠ::
(8) 8. በሚዛን ስትመዝኑም እንዳትበድሉ::
(9) 9. መመዘንንም በትክክል መዝኑ:: ስትመዝኑም አታጉድሉ::
(10) 10. ምድርንም ለፍጡር አደላደላት::
(11) 11. በውስጧ እሸትም ባለ ሽፍን የሆኑ ዘንባባዎችም ያሉባት ስትሆን፤
(12) 12. ባለቅርፊት ቅንጣትና ባለ መልካም መዓዛ ቅጠሎችም ያሉባት ስትሆን፤
(13) 13. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች መካከል በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(14) 14. ሰውን እንደ ሸክላ ከሚቅጨለጨል ደረቅ ጭቃ ፈጠረው::
(15) 15. ጂንንም ከጭስ አልባ የእሳት ነበልባል ፈጠረው::
(16) 16. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ ?
(17) 17. የሁለቱ ምስራቆችና የሁለቱ ምዕራቦች ጌታ ነው::
(18) 18. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(19) 19. ሁለቱም ባህሮች የሚገናኙ ሲሆኑ ለቀቃቸው::
(20) 20. እንዳይዋሀዱ በመካከላቸው የማይታይ መጋረጃ አለ:: አንዱ በሌላው ላይ ወሰን አያልፉም::
(21) 21. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(22) 22. ሉልና መርጃን የተባሉት ማዕድናት ከሁለቱ (ባህሮች) ይወጣሉ::
(23) 23. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(24) 24. እንደ ጋራዎች ሆነው በባህር ውስጥ የተሰሩት ተንሻላዮችም (ታንኳዎች) የእርሱ ናቸው::
(25) 25. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(26) 26. በእርሷ (በምድር) ላይ ያለው ሁሉ ጠፊ ነው::
(27) 27. የልቅና እና የልግስና ባለቤት የሆነው የጌታህ ፊት ብቻ ይቀራል (አይጠፋም)::
(28) 28. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(29) 29.በሰማያትና በምድር ውስጥ ያሉት ሁሉ ይለምኑታል። በየቀኑ ሁሉ እርሱ በስራ ላይ ነው።
(30) 30. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(31) 31. እናንተ ሁለት ከባዶች (ሰዎችና ጋኔኖች) ሆይ! ለእናንተ መቆጣጠር በእርግጥ እንገኛለን::
(32) 32. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(33) 33. የአጋንንትና የሰው ስብስቦች ሆይ! ከሰማያትና ከምድር ቀበሌዎች መውጣትን ከቻላችሁ ውጡ:: በአላህ ስልጣን እንጂ አትወጡም::
(34) 34. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(35) 35. በሁለታችሁም ላይ ከእሳት ነበላባልና ጭስን ይላክባችኋል:: ሁለታችሁም ድል አታደርጉም::
(36) 36. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ !) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(37) 37. ሰማይ በተሰነጠቀችና እንደጽጌረዳ እንደታረበ ቆዳ በሆነች ጊዜ (ጭንቁን ምን አበረታው)::
(38) 38. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(39) 39. በዚያ ቀን ሰዉም ጂንም ከሐጢአት አይጠየቅም::
(40) 40. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(41) 41. ከሓዲያን በምልክታቸው ይታወቃሉ:: ከዚያ አናቶቻቸውንና እግሮቻቸውን ይያዛሉ::
(42) 42. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(43) 43. "ይህች ያቺ አመጸኞች በእርሷ ያስተባብሉባት የነበረችው ገሀነም ናት" (ይባላሉ)::
(44) 44. በእርሷና በጣም ሞቃት በሆነ ፍል ውሃ መካከል ይመላለሳሉ::
(45) 45. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(46) 46. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታዉም ፊት መቆምን ለፈራ ሰው ሁሉ ሁለት ገነቶች አሉት፡
(47) 47. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(48) 48. የቀንዘሎች ባለቤቶች የሆኑ ገነቶች፤
(49) 49. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(50) 50. በሁለቱ ውስጥ የሚፈሱ ሁለት ምንጮች አሉ፤
(51) 51. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(52) 52. በሁለቱ ውስጥ ከየፍራፍሬው ሁለት ዓይነቶች (እርጥብና ደረቅ) አሉ፤
(53) 53. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(54) 54. የውስጥ ጉዝጉዛቸው ከወፍራም ሀር በሆኑ ምንጣፎች ላይ የተመቻቸ ሲሆን ይንፈላሰሳሉ፤ የሁለቱም ገነቶች ፍሬ ለለቃሚ ቅርብ ነው።
(55) 55. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(56) 56. በውስጣቸው ከባሎቻቸው በፊት ሰዉም ጂንም ያልዳሰሳቸው (ያልገሰሳቸው) ዓይኖቻቸውን (በባሎቻቸው ላይ ብቻ) አሳጣሪዎች ሴቶች አሉ::
(57) 57. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(58) 58. ልክ የያቁትንና የመርጃንን ማዕድናት ይመስላሉ::
(59) 59. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(60) 60. የበጎ ስራ ዋጋ በጎ እንጂ ሌላ ነውን?
(61) 61. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(62) 62. ከሁለት ገነቶች ሌላም ሁለት ገነቶች አሉ::
(63) 63. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(64) 64. ከልምላሜዎቻቸው የተነሳ ወደ ጥቁረት ያዘነበሉ ናቸው::
(65) 65. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(66) 66. በውስጣቸው ሁለት የሚንፏፉ ምንጮች አሉ::
(67) 67. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(68) 68. በውስጣቸው ፍራፍሬ ዘንባባና ሩማን አለ::
(69) 69. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(70) 70. በውስጣቸው ጸባየ መልካሞችና መልከ ውብ ሴቶች አሉ::
(71) 71. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(72) 72. በድንኳኖች ውስጥ የተጨጎሉ የዓይኖቸቻቸው ጥቁረትና ንጣት ደማቅ የሆኑ ናቸው::
(73) 73. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(74) 74. ከእነርሱ በፊት ሰዉም ሆነ ጃን አልዳሰሳቸዉም (አልገሰሳቸዉም) ::
(75) 75. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(76) 76. በሚያረገርጉ አረንጓዴ ምንጣፎችና በሚያማምሩ ስጋጃዎች ላይ የተደላደሉ ሲሆኑ ይቀመጣሉ::
(77) 77. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁ ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
(78) 78. የግርማ የመከበር ባለቤት የሆነው ጌታህ ስም ላቀ።