(1) 1. ተጨባጪቱ (ቂያማ) እውን በሆነች ጊዜ፤
(2) 2. (ቂያማ) እውን ለመሆኗ አንዲትም አስተባባይ ነፍስ የለችም።
(3) 3. እርሷ (ገሚሱን) ዝቅ አድራጊና (ገሚሱን) ደግሞ ከፍ አድራጊ ናት::
(4) 4. ምድር መናወጥን በተናወጠች ጊዜ::
(5) 5. ተራራዎች (እንደተፈጨ ዱቄት) መፈርፈርን በተፈረፈሩ ጊዜ።
(6) 6. የተበተነ ብናኝ በሆኑም ጊዜ::
(7) 7. እናንተ (ሰዎች) ሶስት ዓይነቶችም በሆናችሁ ጊዜ (ገሚሱን ዝቅ እና ገሚሱን ከፍ ታደርጋለች)::
(8) 8. እናም በዚያ ቀን የቀኝ ጓዶች ለመሆን የበቁ ሁሉ ምን (የተከበሩ) የቀኝ ጓዶች ናቸው::
(9) 9. የግራ ጓዶች ምን (የተዋረዱ) የግራ ጓዶች ናቸው::
(10) 10. እነዚያ (ለበጎ ስራ) ቀዳሚዎች የሆኑ ሁሉ (ለገነትም) ቀዳሚዎች ናቸው::
(11) 11. እነዚያ (በአላህ ዘንድም) ባለሟሎች ናቸው
(12) 12. በመደሰቻ ገነቶች ውስጥ ሲሆኑ
(13) 13. (የዚህ እድል ባለ ቤቶች) ከፊተኞቹ ብዙ ቡድኖች ናቸው::
(14) 14. ከኋለኞቹ ግን ጥቂቶች ናቸው::
(15) 15. በተሸሞኑ አልጋዎች ላይ ይሆናሉ::
(16) 16. በእርሷ ላይ የተመቻቹና ፊት ለፊት የተቅጣጩ ሲሆኑ።
(17) 17. እነርሱን (ለማገለገል) በእነርሱ ዙሪያ ሁልጊዜ የማያረጁ ወጣት ልጆች ይዘዋወራሉ።
(18) 18. ከ(ጠጅ) ምንጭ በብርጨቆዎች፣ በኩስኩስቶችና (እብሪቆች) በጽዋም በእነርሱ ዙሪያ እንዲዞሩ ይደረጋሉ።
(19) 19. ከእርሷ የራስ ምታት እንኳን አያገኛቸዉም:: አይሰክሩምም::
(20) 20. ከእሸቶች ከሚመርጡት ዓይነት
(21) 21. ከሚፈልጉት የበራሪ ስጋ ይዘው ይዞሩላቸዋል::
(22) 22. ዓይናማዎች የሆኑ ነጫጭ ቆንጆ ሴቶችም አሏቸው::
(23) 23. ልክ እንደተሸፈነ ሉል የሚመስሉ::
(24) 24. ለዚያ ይሰሩት በነበሩት መልካም ተግባር ምክንያት ዋጋ ይሆን ዘንድ ይህንን አደረግንላቸው።
(25) 25. በውስጧ ውድቅ ንግግርንና መወንጀልንም አይሰሙም።
(26) 26. ሰላም ሰላም መባባልን ግን ይሰማሉ::
(27) 27. የቀኝ ጓዶች ምንኛ የከበሩ የቀኝ ጓዶች ናቸው::
(28) 28. በተቀፈቀፈ (እሾህ በሌለው) ቁርቁራ ውስጥ ናቸው::
(29) 29. ፍሬው በተነባበረ ሙዝ ዛፍም ውስጥ ናቸው።
(30) 30. በተዘረጋ ጥላ ስርም ናቸው::
(31) 31. በሚንቧቡ ውሃ አጠገብም ናቸው::
(32) 32. በብዙ ዓይነት ፍራፍሬዎችም ውስጥ ናቸው።
(33) 33. ምንጊዜም የማትቋረጥ የማትከለከልም የሆነች፤
(34) 34. ከፍ በተደረጉ ምንጣፎች ላይም ናቸው።
(35) 35. እኛ (የገነት ሴቶችን) አዲስ ፍጥረት አድርገን ፈጠርናቸው::
(36) 36. እናም ደናግሎችም አደረግናቸው::
(37) 37. ለባሎቻቸው ተሽሞርሟሪዎችና እኩያዎች አደረግናቸው::
(38) 38. ለቀኝ ጓዶች አዘጋጀናቸው::
(39) 39. ከፊተኞቹ ብዙ ቡድኖች ናቸው::
(40) 40. ከኋለኞቹም ብዙ ቡድኖች ናቸው::
(41) 41. የግራ ጓዶችም ምንኛ የተዋረዱ የግራ ጓዶች ናቸው::
(42) 42. በመርዛም ንፋስና በጣም በፈላ ውሃም ውስጥ ናቸው::
(43) 43. ከጥቁር ጭስም በሆነ ጥላ ውስጥ
(44) 44. ቀዝቃዛም መልካምም ያልሆነ
(45) 45. እነርሱ ከዚህ በፊት የነብያትን አስተምህሮት ወደ ጎን የተው የዱንያ ቅምጥሎች ነበሩና::
(46) 46. በከባድ ኃጢአትም ላይ ይዘወትሩ ነበሩና::
(47) 47. (እንዲህ) ይሉ ነበርም፡ "ሞተን አፈር፣ አጥንቶችም በሆን ጊዜ እኛ የምንቀሰቀስ ነን?
(48) 48. "የፊተኞቹ አባቶቻችንንም (ይቀሰቀሳሉን)?" (ይሉ ነበር)
(49) 49. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) "ፊተኞቹም ሆኑ ኋለኞቹ
(50) 50. "በተወሰነ ቀን ቀጠሮ በእርግጥ ተሰብሳቢዎች ናቸው" በላቸው::
(51) 51. ከዚያም እናንተ ጠማሞችና አስተባባዩች ሆይ!
(52) 52. ከዘቁም ዛፍ በእርግጥ በይዎች ናችሁ::
(53) 53. ከእርሷም ሆዶቻችሁን ሞይዎች ናችሁ::
(54) 54. በእርሱ ላይም ከፈላ ውሃ ጠጪዎች ናችው::
(55) 55. የተጠሙንም ግመሎች አጠጣጥ ብጤ ጠጪዎች ናቸው::
(56) 56. ይህ የፍርዱ ቀን መስተንግዷቸው ነው::
(57) 57. (ሰዎች ሆይ!) እኛ ፈጠርናችሁ አታምኑምን?
(58) 58. በሴቶች ማህጸኖች የምታፈሱትን (የምትረጩትን ፍትወት) አያችሁን?
(59) 59. እናንተ ትፈጥሩታላችሁን! ወይስ እኛ ነን ፈጣሪዎቹ?
(60) 60. እኛ ሞትን (ጊዜውን) በመካከላችሁ ወሰንን እኛም ተሸናፊዎች አይደለንም::
(61) 61. ብጤዎቻችሁን በመለወጥና በዚያ በማታውቁትም ቅርጽ እናንተኑ በመፍጠር ላይ (አንሸነፍም)።
(62) 62. የፊተኛይቱን አፈጣጠር በእርግጥ አውቃችኋል አትገነዘቡምን?
(63) 63. የምትዘሩትን (አዝርአት) አያችሁን
(64) 64. እናንተ ታበቅሉታላችሁን? ወይስ እኛ አብቃዮቹ ነን?
(65) 65. ብንሻ ኖሮ ደረቅ ስብርብር ባረደግነው እና የምትደነቁም በሆናችሁ ነበር::
(66) 66. "እኛ በእዳ ተያዥዎች ነን::
(67) 67. "በእርግጥም እኛ (ከመጠቀም) የተከለክልን ነን" ትሉ ነበር።
(68) 68. ያንን ምትጠጡትን ውሃ አያችሁን?
(69) 69. እናንተ ከደመናው አወረዳችሁትን? ወይስ እኛ አውራጆቹ ነን?
(70) 70. ብንፈልግ ኖሮ መርጋጋ ባደረግነው ነበር:: አታመሰግኑምን?
(71) 71. ያችንም የምትሰብቋትን እሳት አያችሁን?
(72) 72. እናንተ ዛፏን ፈጠራችሁን? ወይስ እኛ ፈጣሪዎቹ ነን?
(73) 73. እኛ ለገሀነም ማስታወሻ ለመንገደኞችም መጠቀሚያ አደረግናት::
(74) 74. የታላቁን ጌታህንም ስም አጥራው::
(75) 75. በከዋክብትም መጥለቂያዎች እምላለሁ::
(76) 76. እርሱም ብታውቁ ታላቅ መሀላ ነው::
(77) 77. እርሱ የተከበረ ቁርኣን ነው::
(78) 78. በተጠበቀ መጽሐፍ ውስጥም ነው::
(79) 79. የተጥራሩት እንጂ ሌላ አይነካዉም::
(80) 80. ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው::
(81) 81. በዚህ ንግግር እናንተ ቸልተኞች ናችሁን?
(82) 82. ሲሳያችሁንም (ዝናብን) እናንተ የምታስተባበሉት ታደርጋላችሁን?
(83) 83. ነፍስ ጉሮሮንም በደረሰች ጊዜ::
(84) 84. እናንተ ያን ጊዜ የምታዩ ስትሆኑ፤
(85) 85. እኛም ግን እናንተ አታዩም እንጂ ከናንተ ይልቅ ወደ እርሱ የቀረብን ነን::
(86) 86. የማትዳኙም ከሆናችሁ
(87) 87. እውነተኞች እንደሆናችሁ ነፍሲቱን ወደ አካል ለምን አትመልሷትም?
(88) 88. እናም ሟቹ ከባለሟሎቹ ከሆነም፤
(89) 89. ለእርሱ እረፍት መልካም ሲሳይና የመጠቀሚያ ገነት አለው::
(90) 90. ሟቹ ከቀኝ ጓዶችም ከሆነ
(91) 91."ከቀኝ ጓዶች ስለሆንክ ላንተ ሰላም ነው የሚገባህ" ይባላል።
(92) 92. ሟች ከእነዚያ ከሚያስተባብሉት ጠማማዎች ከሆነ ደግሞ
(93) 93. ከፈላ ውሃ የሆነ መስተንግዶ አለለት::
(94) 94. በገሀነም መቃጠልም አለለት::
(95) 95. ይህ እርሱ እርግጠኛው እውነት ነው::
(96) 96. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የታላቁ ጌታህን ስም አጥራው::