(1) 1. አሊፍ፤ ላም፤ ራ፤ እነዚህ ጥበብ ከተሞላው መፅሀፍ አንቀፆች ናቸው።
(2) 2. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ሰዎችን (ከሓዲያንን) አስፈራራ፤ እነዚያን ያመኑትን ደግሞ ከጌታቸው ዘንድ መልካም ምንዳ ያላቸው መሆኑን አብስር» በማለት ከእነርሱ መካከል ወደ ሆነ አንድ ሰው ራዕይን ማውረዳችን ለሰዎች ድንቅ ሆነባቸውን? ከሓዲያን «ይህ (ሰው) ግልጽ ድግምተኛ ነው።» አሉ።
(3) 3. ጌታችሁ ያ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀናት ውስጥ ብቻ የፈጠራቸው አላህ ነው:: ከዚያም ነገሩን ሁሉ የሚያስተናብር ሲሆን (ለሱ ክብር በምስማማ መልኩ) በዐርሹ ላይ ተደላደለ፡፡ ከእርሱ በጎ ፈቃድ በኋላ ቢሆን እንጂ አንድም አማላጅ የለም:: እነሆ ይህ አላህ ጌታችሁ ነው:: እናም በትክክል ተገዙት:: አትገሰጹምን?
(4) 4. (ሰዎች ሆይ!) የሁላችሁም መመለሻችሁ ወደ እርሱ ብቻ ነው:: ይህም የተረጋገጠ የአላህ ቃል ኪዳን ነው:: እርሱ መፍጠርን ይጀምራል:: ከዚያም እነዚያ ያመኑትንና መልካም የሠሩትን ሰዎች በትክክል ይመነዳ ዘንድ ፍጡራንን ከሞት በኋላ ህያው ያደርጋል:: እነዚያ የካዱት ክፍሎች ግን በክህደታቸው ምክንያት የፈላ ውሃ መጠጥና አሳማሚ ቅጣት አለባቸው::
(5) 5. እርሱ ያ ጸሐይን አንጸባራቂ ጨረቃንም አብሪ ያደረገ፤ የዓመታትን ቁጥርና ሒሳብን ታውቁ ዘንድም ለጨረቃ የተለያዩ መስፈሪያ እርከኖችን የወሰነ ነው:: አላህ ይህንን በእውነት እንጂ በከንቱ አልፈጠረዉም:: ለሚያውቁ ሕዝቦችም አናቅጽን ያብራራል::
(6) 6. ሌሊትና ቀን በመተካካታቸው አላህ በሰማያትና በምድር ውስጥ በፈጠረው ሁሉ ለሚጠነቀቁ ሕዝቦች ታላላቅ ተአምራት አሉ::
(7) 7. እነዚያ ከኛ ጋር መገናኘታቸውን ተስፋ የማያደርጉ ቅርቢቱን ሕይወት የወደዱና በእርሷም የረኩ እነርሱ ከአናቅጻችን ዘንጊዎች የሆኑት።
(8) 8. እነዚያ ይሠሩት በነበሩት ኃጢአት ምክንያት መኖሪያቸው በእሳት ውስጥ ነው::
(9) 9. እነዚያ በአላህ ያመኑትና መልካም ሥራዎችን የሠሩ ሰዎች ሁሉ ጌታቸው በእምነታቸው ምክንያት የገነትን መንገድ ይመራቸዋል:: ከሥሮቻቸው ወንዞች ይፈስሳሉ:: በመጠቀሚያ ገነቶች ውስጥም ዝንታለም ይኖራሉ::
(10) 10. በእርሷም ውስጥ ጸሎታቸው የሚሆነው «ጌታችን ሆይ! ጥራት ይገባህ።» ማለት ብቻ ነው:: በእርሷ ውስጥ መከባበሪያቸው ሰላም መባባል ነው:: የመጨረሻ ጸሎታቸዉም «ምስጋና ሁሉ ለዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ ብቻ ይገባው።» ማለት ነው።
(11) 11. አላህ ለሰዎች ደግን ነገር ለማግኘት እንደ መቻኮላቸው የሚጠይቁትንም ክፉን ነገር ቢያቻኩልባቸው ኖሮ በዚያችው ጊዜያቸው እድሜያቸው በተፈጸመ ነበር:: እነዚያን መገናኘታችንን ተስፋ የማያደርጉትን ሰዎች በጥመታቸው ውስጥ እየዋለሉ እንተዋቸዋለን::
(12) 12. የሰውን ልጅ ጉዳት ባገኘው ጊዜ በጎኑ ላይ ተጋድሞ ወይም ተቀምጦ ወይም ቆሞ ይለምንና ጉዳቱን ከእሱ ላይ በገለጥንለት ጊዜ ላገኘው ጉዳት እንዳልተማጸንን ሆኖ ያልፋል:: ልክ እንደዚሁ ለድንበር አላፊዎች ሁሉ ይሠሩት የነበሩት መጥፎ ሥራ ተሸለመላቸው::
(13) 13. ከናንተ በፊት የነበሩትን የብዙ ክፍለ ዘመናት ሰዎች መልዕክተኞቻቸው በማስረጃዎች የመጡላቸው ሲሆኑ በበደሉና የማያምኑም በሆኑ ጊዜ አጠፋናቸው:: ልክ እንደዚሁ ተንኮለኞችን ህዝቦች እንቀጣለን::
(14) 14. ከዚያ እንዴት እንደምትሠሩ ልንመለከት ከእነርሱ በኋላ በምድር ላይ ምትኮች አደረግናችሁ::
(15) 15. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አናቅጻችን ግልጽ ሆነው በእነርሱ ላይ በተነበቡላቸው ጊዜ እነዚያ መገናኘታችንን የማይፈሩት (የማይሹት) ሰዎች «ከዚህ ሌላ የሆነን ቁርኣን አምጣልን ወይም ለውጠው።» ይላሉ:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እኔ ከራሴ በኩል ልለውጠው አይገባኝም:: ወደ እኔ የሚወረደውን እንጂ አልከተልም:: እኔ በጌታዬ ትዕዛዝ ላይ ባምጽ የታላቅን ቀን ቅጣት እፈራለሁ።» በላቸው::
(16) 16. (መልዕከተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «አላህ በሻ ኖሮ በእናንተ ላይ ባላነበብኩትና አላህ እርሱን ባላሳወቃችሁ ነበር:: በእናንተም ውስጥ ከእርሱ በፊት ምንም ሳልል ብዙን እድሜ በእርግጥ ኖሬያለሁ። አታውቁምን?» በላቸው።
(17) 17. በአላህ ላይ እብለትን ከቀጣጠፈ ወይ ከአናቅ ጹ መካከል (በአንዷ እንኳን) ካስተባበለ ይበልጥ በዳይ ማን ነው? እነሆ አመጸኞች አይድኑም::
(18) 18. አጋሪዎች ከአላህ ሌላ የማይጎዳቸውንና የማይጠቅማቸውን ይገዛሉ:: «እነዚህ አላህ ዘንድ አማላጆቻችን ናቸው።» ይላሉም። (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «አላህ በሰማያትና በምድር ውስጥ የማያውቀው ነገር ኖሮ እናንተ ትነግሩታላችሁን?» በላቸው:: አላህ ከሚያጋሩት ሁሉ ጠራ:: ላቀም::
(19) 19. ሰዎች አንድ ህዝብ እንጂ ሌላ አልነበሩም:: ከዚያ ተለያዩ:: ከጌታህ ያለፈ ቃልም ባልነበረ ኖሮ በዚያ በሚለያዩበት ነገር በመካከላቸው በቶሎ በተፈረደ ነበር::
(20) 20. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በእርሱ ላይም ከጌታው የሆነች ተዓምር ለምን አትወረድለትም?» ይላሉ:: «ሩቅ ነገር ሁሉ የአላህ ብቻ ነው:: እናንተም ተጠባበቁ እኔም ከናንተው ጋር ከሚጠባበቁት ነኝ።» በላቸው።
(21) 21. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሰዎች ካገኛቸው ጉዳት በኋላ እዝነትን ምቾትን ባቀመስናቸው ጊዜ ወዲያውኑ ለእነርሱ በተዓምራቶቻችን በማላገጥ ተንኮል ይኖራቸዋል:: «አላህ ቅጣቱ ፈጣን ነው።» በላቸው። መልዕክተኞቻችን የምታሴሩትን ነገር ሁሉ በእርግጥ ይጽፋሉ።
(22) 22. (ሰዎች ሆይ!) አላህ ያ በየብስና በባሕር የሚያስኬዳችሁ ነው:: በመርከቦችም ውስጥ በሆናችሁና በእነርሱም በመልካም ነፋስ በእርሷ የተደሰቱ ሆነው መርከቦቹ በተንሻለሉ ጊዜ ሀይለኛ ነፋስ ትመጣባቸዋለች:: ከየስፍራዉም ማዕበል ይመጣባቸዋል:: እነርሱም ለጥፋት የተከበቡ መሆናቸውን ሲያረጋግጡ ያን ጊዜ አላህን «ከዚህች ጭንቀት ብታድነን ከአመስጋኞቹ እንሆናለን።» ሲሉ እምነታቸውን ለእርሱ ብቻ ፍጹም አድርገው ይለምኑታል::
(23) 23. በአዳናቸዉም ጊዜ እነርሱ ወዲያውኑ ያለ አግባብ በምድር ላይ ወሰን ያልፋሉ። እናንተ ሰዎች ሆይ ወሰን ማለፋችሁ ጥፋቱ በነፍሶቻችሁ ላይ ብቻ ነው:: እርሱ የቅርቢቱ ህይወት መጠቀሚያ ነው:: ከዚያ መመለሻችሁ ወደ እኛ ነው:: ትሠሩት የነበራችሁትንም ሁሉ እንነግራችኋለን::
(24) 24. . የቅርቢቱ ህይወት ምሳሌ ከሰማይ እንዳወረድነው ውሃ በእርሱም ሰውና እንስሳዎች ከሚበሉት የምድር በቃይ ተቀላቅሎበት እንደፋፋ ምድርም ውበትዋን በያዘችና ባጌጠች ጊዜ ባለቤቶችዋን በእርሷ ላይ እነርሱ ቻዮች መሆናቸውን ባሰቡ ጊዜ ትዕዛዛችን ሌሊት ወይም ቀን መጥቶባት ትላንት እንዳልነበረች የታጨደች እንዳደረግናት ብጤ ነው:: ልክ እንደዚሁ ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች ሁሉ አናቅጽን እናብራራለን::
(25) 25. አላህ (ሁል ጊዜም) ወደ ሰላም አገር ይጠራል:: የሚፈልገዉን ሰዉም ወደ ቀጥተኛው መንገድ ይመራል::
(26) 26. ለእነዚያ መልካም ለሠሩት ሰዎች መልካም ነገርና (ገነት) ሌላ ተጨማሪም አላቸው:: ፊቶቻቸውንም ጥቁረትና ውርደት አይሸፍናቸዉም:: እነዚያ የገነት ሰዎች ናቸው:: እነርሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው::
(27) 27. እነዚያ ኃጢአቶችን የሠሩት ደግሞ ኃጢአቲቱን የሚመጥን ቅጣት አለባቸው:: ውርደትም ትሸፍናቸዋለች :: እነርሱ ከአላህ ቅጣት ጠባቂ የላቸዉም:: ፊቶቻቸው በድቅድቅ ጨለማ ቁራጮች እንደ ተሸፈኑ ይሆናሉ:: እነዚያ የእሳት ሰዎች ናቸው:: እነርሱ በውስጧ ዘለዓለም ነዋሪዎች ናቸው::
(28) 28. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አማልክትንና አምላኪዎቻቸውን ሁሉ በአንድ የምንሰበስባቸውንና ከዚያም ለእነዚያ ላጋሩት «እናንተም ተጋሪዎቻችሁም ቦታችሁን ያዙ።» የምንልበትን ተጋሪዎቻቸዉም (እንዲህ) የሚሏቸው ሲሆኑ በመካከላቸው የምንለይበትን ቀን አስታውስ «ትገዙ የነበረው እኛን አልነበረም።
(29) 29. (ጣኦታቶቹ) «እኛን ለመገዛታችሁ ዘንጊዎች ለመሆናችን በኛና በእናንተ መካከል የአላህ መስካሪነት በቃ።» ይሏቸዋል::
(30) 30. በዚያ ቀን ነፍስ ሁሉ ያሳለፈችውን ሥራ ታውቃለች:: አጋሪዎች ወደ አላህ እውነተኛ ወደሆነው ጌታቸው ይመለሳሉ:: ያ በአላህ ላይ ይቀጣጥፋት የነበሩት ሁሉ ነገርም ይጠፋባቸዋል::
(31) 31. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ከሰማይና ከምድር ሲሳይን የሚሰጣችሁ ማን ነው? መስሚያዎችንና ማያዎችንስ የፈጠረላችሁ ማን ነው? ከሙትም ህያውን የሚያወጣ፤ ከህያዉም ሙትን የሚያወጣስ ማን ነው? ነገሩን ሁሉ የሚያስተናብርስ ማን ነው?» በላቸው:: «በእርግጥ አላህ ነው።» ይሉሃል:: «ታዲያ ለምን ታጋራላችሁ? ታዲያ አትፈሩትምን?» በላቸው።
(32) 32. እውነተኛው ጌታችሁ አላህ ብቻ ነው:: ከእውነት በኋላ ጥመት እንጂ ሌላ ምን አለ? ከእውነት እንዴት ትዞራላችሁ?
(33) 33. ልክ እንደዚሁ የጌታህ ቃል በእነዚያ ባመጹት ሰዎች ላይ ፈጽሞ የማያምኑ መሆናቸው ተረጋገጠ::
(34) 34. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ከምታጋሯቸው ጣኦታት መካከል መፍጠርን የሚጀምር ከዚያ የሚመልስ አለን?» በላቸው። «አላህ ግን መፍጠርን ይጀምራል:: ከዚያ ይመልሰዋል:: ታዲያ ከእምነት እንዴት ትዘራላችሁ?» በላቸው::
(35) 35. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ከምታጋሯቸው ጣኦታት መካከልስ ወደ እውነት መንገድ የሚመራ አለን?» በላቸው:: «አላህ ግን ወደ እውነቱ ይመራል:: ወደ እውነት የሚመራው ጌታ ነውን ሊከተሉት የተገባው? ወይስ ካልተመራ በስተቀር የማይመራው? ለእናንተ ምን ( አስረጅ) አላችሁ? እንዴት በውሸት ትፈርዳላችሁ?» በላቸው::
(36) 36. አብዛኞቻቸው ጥርጣሬን እንጂ አይከተሉም:: ጥርጣሬ ደግሞ ከእውነት በፍጹም አያብቃቃም:: አላህ የሚሠሩትን ሁሉ አዋቂ ነው::
(37) 37. ይህም (ቁርኣን) ከአላህ ሌላ ከሆነ ፍጡር የተቀጠፈ ሊሆን አይገባዉም:: ይልቁንም ያንን ከእርሱ በፊት ያለውን መጽሐፍ የሚያረጋግጥና በመጽሐፉ ውስጥ ያለውን የሚዘረዝር በእርግጥ ጥርጣሬ የሌለበት ሲሆን ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው::
(38) 38. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በእውነት ሙሐመድ ቀጣጠፈው» ይላሉን? ይህን የሚሉ ከሆነ «መሰሉን አንድ ምዕራፍ እንኳ እስቲ አምጡ:: ለዚህም ጉዳይ ከአላህ ሌላ የቻላችሁትን ሁሉ ረዳት ጥሩ:: እውነተኞች እንደሆናችሁ ለዚህ ተጋግዛችሁ አምጡ።» በላቸው::
(39) 39. ይልቁንም እውቀቱን ባላዳረሱትና ፍቹም ገና ባልመጣላቸው ነገር አስተባበሉ:: እንደዚሁ እነዚያ ከእነሱ በፊት የነበሩት አስተባብለዋል፡፡ (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የበዳዮች መጨረሻ እንዴት ይመስል እንደ ነበር በጥሞና ተመልከት::
(40) 40. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከመካከላቸው ወደፊት በቁርኣን የሚያምኑ አሉ:: ከእነርሱም መካከል በእርሱ የማያምኑ አሉ:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ አጥፊዎቹን በጣም አዋቂ ነው::
(41) 41. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ቢያስተባብሉህም ለእኔ የራሴ ሥራ አለኝ:: እናንተም የራሳችሁ ሥራ አላችሁ:: እናንተ እኔ ከምሠራው ተግባር ንጹህ ናችሁ (አትጠየቁም):: እኔም እናንተ ከምትሠሩት ነገር ንጹህ ነኝ (አልጠየቅም)።» በላቸው።
(42) 42. ከእነርሱ መካከል ወደ አንተ ንግግር የሚያዳምጡ የሚሰሙና የማያምኑ አሉ:: አንተ ደንቆሮዎችን የማያውቁ ቢሆኑም ታሰማለህን?::
(43) 43. ከእነርሱም መካከል ወደ አንተ የሚመለከቱ አሉ:: አንተ ልበ እውራንን የማያዩ ቢሆኑም ትመራለህን?
(44) 44. አላህ ሰዎችን ምንም አይበድልም:: ግን ሰዎች ነፍሶቻቸውን ይበድላሉ::
(45) 45. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከሓዲያንን ከቀን አንዲትን ሰዓት እንጂ አንዳልቆዩ መስለው በመካከላቸው የሚተዋወቁ ሲሆኑ በምንሰበስባቸው ቀን የሚከሰተውን አስታውስ:: እነዚያ በአላህ መገናኘት ያስተባበሉት ሁሉ በእርግጥ ከሰሩ:: የተመሩም አልነበሩምና::
(46) 46. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የዚያንም የምናስፈራራባቸውን ነገር ውጤት ከፊሉን (በሕይወትህ ሳለህ) ብናሳይህ (መልካም ነው):: ወይም ሳናሳይህ ብንገድልህ (ጉዳዩ የእኔ ነው):: መመለሻቸው ወደ እኛ ነውና:: ከዚያ አላህ በሚሠሩት ሥራ ላይ ሁሉ አዋቂ ነው::
(47) 47. ለሕዝቦችም ሁሉ መልዕክተኛ አላቸው:: መልዕክተኛቸው በመጣ ጊዜ (ሲያስተባብሉት) በመካከላቸው በትክክል ይፈረዳል:: እነርሱም ፍጹም አይበደሉም::
(48) 48. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እውነተኞች ከሆናችሁ የቅጣቱ ቀጠሮ መቼ ነው?» ይላሉ::
(49) 49. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ለራሴ ጉዳትን ማድረስም ሆነ ጥቅምን ማስከበር አላህ ከሻው በስተቀር አልችልም:: ለህዝቦች ሁሉ የተወሰነ ጊዜ አላቸው:: ጊዜያቸው በደረሰ ወቅት አንዲትን ሰዓት እንኳን አይቆዩም:: አይቀደሙምም።» በላቸው::
(50) 50. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እስቲ ንገሩኝ ቅጣቱ በሌሊት ወይም በቀን ቢመጣባችሁ አጋሪዎቹ የሚያስቸኩላቸው ነገር ምንድን ነው?» በላቸው::
(51) 51. «ከዚያም ቅጣቱ በወደቀ ጊዜ በእርሱ አመናችሁበትን? በእርግጥ በእርሱ የምትቻኮሉ የነበራችሁ ስትሆኑ አሁን ነው የምታምኑትን?» ይባላሉ።
(52) 52. ከዚያ ለእነዚያ ለበደሉት ሰዎች «ዘውታሪውን ቅጣት ቅመሱ። ትሠሩ የነበራችሁትን እኩይ ተግባር ዋጋ እንጂ ትመነዳላችሁን? (አትመነዱም)።» ይባላሉ::
(53) 53. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «(ከሞት በኋላ መቀስቀስ) እውነት ነውን?» ሲሉ ይጠይቁሃል:: «አዎን! በጌታዬ እምላለሁ እርሱ እውነት ነው:: እናንተም የምታቅቱ አይደላችሁም።» በላቸው።
(54) 54. ለበደለች ነፍስ ሁሉ በምድር ላይ ያለው ሀብት ሁሉ የእርሷ ቢሆንላት በእርግጥ ቤዛ ባደረገችው ነበር:: ቅጣቱንም ባዩ ጊዜ ጸጸትን ይደብቃሉ (ይገልጻሉ):: በመካከላቸዉም በትክክል ይፈረዳል:: እነርሱም ቅንጣት ያህል አይበደሉም::
(55) 55. አስተውሉ! በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ብቻ ነው:: አስተዉሉ! የአላህ የተስፋ ቃል እርግጥ ነው:: ግን አብዛኞቻቸው አያውቁም::
(56) 56. እርሱ ሕያው ያደርጋል:: ይገድላልም:: ወደ እርሱም ትመለሳላችሁ::
(57) 57. ሰዎች ሆይ! ከጌታችሁ ዘንድ ግሳጼ በደረቶች ውስጥ ላለው በሽታም ፍቱን መድሀኒት፤ ለአማኞችም ብርሃንና እዝነት የሆነ መልዕክት በእርግጥ መጣላችሁ።
(58) 58. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በአላህ ችሮታና በእዝነቱ ተደሰቱ:: በዚህም ምክንያት ይደሰቱ:: እርሱ ከሚሰበስቡት ሀብት ሁሉ በላጭ ነው።» በላቸው::
(59) 59. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «አላህ ከሲሳይ ለእናንተ ያወረደው ከእርሱም ከፊሉን እርም ከፊሉን የተፈቀደ ያደረጋችሁትን አያችሁን?» በላቸው:: «አላህ ይህንን ለእናንተ ፈቀደላችሁን? ወይስ በአላህ ላይ ትቀጣጥፋላችሁ?» በላቸው::
(60) 60. እነዚያ በአላህ ላይ ውሸትን የሚቀጣጥፉ ሰዎች በትንሳኤ ቀን በአላህ ጥርጣሬያቸው ምንድን ነው? አይቀጡም ይመስላቸዋልን? አላህ በሰዎች ላይ ቅጣትን ባለማቻኮል የልግስና ባለቤት ነው:: ግን አብዛኛዎቹ አያመሰግኑትም::
(61) 61. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በማንኛዉም ነገር ላይ አትሆንም፤ ከእርሱም ከቁርኣን ትንሽም አታነብም፤ ማንኛውንም ሥራ አንተም ሆንክ ሰዎቹ አትሠሩም፤ በገባችሁበት ጊዜ በናንተ ተግባር ላይ ተጠባባቂዎች ብንሆን እንጂ :: በምድርም ሆነ በሰማይ የብናኝ ክብደት ያክል እንኳን ከጌታህ እውቀት አይርቅም:: ከዚያም ያነሰም ሆነ የተለቀ ነገር በግልጹ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈ ቢሆን እንጂ የለም::
(62) 62. አስተውሉ! የአላህ ወዳጆች ፍርሀት የለባቸዉም። አይተክዙምም።
(63) 63. እነርሱም እነዚያ ያመኑትና አላህን የሚፈሩት ናቸው::
(64) 64. ለእነርሱ በቅርቢቱ ህይወትም ሆነ በመጨረሻይቱ ዓለም ብስራት አለላቸው:: የአላህ ቃል አይለወጥም:: ይህ እርሱ ታላቅ እድል (ስኬታማነት) ነው::
(65) 65. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ንግግራቸዉም አያሳዝንህ:: ኃይል በሙሉ የአላህ ብቻ ነውና:: እርሱም ሰሚውና ሁሉን አዋቂው ነው::
(66) 66. አስተውሉ! በሰማያት ያሉትና በምድርም ያሉት ሁሉ በእርግጥ የአላህ ናቸው፤ እነዚያ ከአላህ ሌላ ተጋሪዎችን የሚጠሩ ምንን ይከተላሉ? ጥርጣሬን እንጂ ሌላ አይከተሉም፡፡ እነርሱም የሚዋሹ እንጂ አይደሉም፡፡
(67) 67. (ሰዎች ሆይ!) እርሱ ያ ሌሊትን በውስጡ ልታርፉበት ጨለማ ቀንንም ልትሠሩበት ብርሃን ያደረገላችሁ ነው:: በዚህ ውስጥ ለሚሰሙ ህዝቦች ሁሉ በእርግጥ ብዙ ተአምራት አሉ::
(68) 68. «አላህ ልጅን ወለደ።» አሉ። ከሚሉት ሁሉ ጥራት ተገባው:: እርሱ በራሱ ተብቃቂ ነው:: በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የእርሱ ብቻ ነው:: እናንተ ዘንድ በዚህ በምትሉት ምንም አስረጂ የላችሁም:: በአላህ ላይ የማታውቁትን ትናገራላችሁን?
(69) 69. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እነዚያ በአላህ ላይ ውሸትን የሚቀጣጥፉ ሰዎች ፈጽሞ አይድኑም።» በላቸው
(70) 70. እነርሱ በቅርቢቱ ዓለም ጥቂት ጊዜ ይጠቀሙና ከዚያም መመለሻቸው ወደ እኛ ነው:: ከዚያም ይክዱ በነበሩበት ምክንያት ብርቱን ቅጣት እናቀምሳቸዋለን::
(71) 71. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የኑህንም ወሬ በእነርሱ ላይ አንብብላቸው:: ለህዝቦቹ ባለ ጊዜ አስታውሱ «ህዝቦቼ ሆይ! በእናንተ ውስጥ ብዙን ጊዜ መቆየቴ የአላህንም ተዓምራት ለእናንተ ማስታወሴ በእናንተ ላይ የከበደ ቢሆንባችሁም በአላህ ላይ ተጠግቻለሁ:: ነገራችሁንም ከምታጋሯቸው ጣኦታት ጋር ሆናችሁ እስቲ ቁረጡ:: ከዚያም ነገራችሁ በእናንተ ላይ ድብቅ አይሁን ግለጹት:: ከዚያም የሻችሁትን ወደ እኔ አድርሱ:: ጊዜም አትስጡኝ (ከምንም አልቆጥራችሁም)::
(72) 72. «ብትሸሹም (አትጎዱኝም::) ከምንዳ ምንንም አለመንኳችሁምና:: ምንዳዬ በአላህ ላይ እንጂ በሌላ ላይ አይደለምና:: ከሙስሊሞች እንድሆንም ታዝዣለሁ።»
(73) 73. አስተባበሉት እርሱንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች በታንኳይቱ ውስጥ አዳንናቸው:: ለጠፉት ምትኮች አደረግናቸው:: እነዚያንም በአናቅጻችን ያስተባበሉትን አሰመጥን:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የተስፈራሩት ህዝቦች መጨረሻ እንዴት እንደ ነበር እስቲ ተመልከት::
(74) 74. ከዚያም ከእርሱ በኋላ መልዕክተኞችን ወደየ ህዝቦቻቸው ላክን:: በግልጽ ማስረጃዎችም መጡላቸው:: ከመላካቸው በፊት ባስተባበሉት ነገር የሚያምኑ አልሆኑም:: ልክ እንደዚሁ በወሰን አላፊዎች ልቦች ላይ እናትማለን::
(75) 75. ከዚያም ከእነርሱ በኋላ ሙሳንና ሃሩንን ወደ ፈርዖንና ወደ መማክርቱ በተአምራታችን ላክን:: ኮሩም:: ትእቢተኞች ህዝቦችም ነበሩ::
(76) 76. ከእኛም ዘንድ እውነቱ በመጣላቸው ጊዜ «ይህ በእርግጥ ግልጽ ድግምት ነው።» አሉ።
(77) 77. ሙሳ አለ፡- «እውነቱን በመጣላችሁ ጊዜ ድግምተኞች የማይድኑ ሲኾኑ (እርሱ ድግምት ነው) ትላላችሁን?ይህ ድግምት ነውን?»
(78) 78. እነርሱም «አባቶቻችንን ካገኘንበት ሃይማኖት ልታዞሩንና በምድር ውስጥ ለእናንተም ኩራት ሹመት ልትኖራችሁ መጣህብን:: እኛ ለእናንተ በፍጹም አማኞች አይደለንም።» አሉ::
(79) 79. ፈርዖን፡- «አዋቂ ድግምተኛን ሁሉ አምጡልኝ።» አለ::
(80) 80. ድግምተኞቹ በመጡ ጊዜም ሙሳ ለእነርሱ፡- «እናንተ የምትጥሉትን ነገር ጣሉ።» አላቸው::
(81) 81. በጣሉም ጊዜ ሙሳ፡- «ያ በእርሱ የመጣችሁበት ነገር ድግምት ነው:: አላህ በእርግጥ ያፈርሰዋል:: አላህ የአጥፊዎችን ሥራ ፈጽሞ አያበጅምና።» አለ::
(82) 82. አላህም ከሓዲያን ቢጠሉም እውነትን በቃላቱ ያረጋግጣል::
(83) 83. ለሙሳም ከፈርዖንና ከሹማምንቶቻቸው ማሰቃየትን በመፍራት ከወገኖቹ ጥቂት ትውልዶች ብቻ እንጂ አላመኑለትም:: ፈርዖንም በምድር ላይ በእርግጥ ይኮራ ነበር። እርሱም በእርግጥ ወሰን ካለፉት ነበር።
(84) 84. ሙሳም፡- «ህዝቦቼ ሆይ! በአላህ አምናችሁ እንደ ሆነ በእርሱ ላይ ብቻ ተጠጉ:: ታዛዦች እንደ ሆናችሁም በአላህ ላይ ብቻ ተመኩ።» አለ::
(85) 85. አሉ፡- «በአላህ ላይ ተጠጋን:: ጌታችን ሆይ! ለበደለኞች ህዝቦች መፈተኛ አታድርገን::
(86) 86. «በእዝነትህም ከከሓዲያን ህዝቦች ግፍ አድነን።»
(87) 87. ወደ ሙሳና ወደ ወንድሙ፡ «ለህዝቦቻችሁ በግብጽ ውስጥ ቤቶችን ሥሩ:: ቤቶቻችሁንም መስገጃ አድርጉ:: ሶላትንም በደንቡ ስገዱ:: ምዕመናኖቹንም አብስር።» ስንል ላክን::
(88) 88. ሙሳም: «ጌታችን ሆይ! አንተ ለፈርዖንና ለሹሞቹ በቅርቢቱ ህይወት ጌጥን ብዙ ገንዘቦችንም በእርግጥ ሰጠህ:: ጌታችን ሆይ! ከመንገድህ ያሳስቱ ዘንድ ሰጠሃቸው:: ጌታችን ሆይ! ገንዘቦቻቸውን አጥፋ:: በልቦቻቸዉም ላይ አትም:: አሳማሚን ቅጣት አስከሚያዩ አያምኑምና።» አለ።
(89) 89. (አላህም) ፡- «ጸሎታችሁ ተሰምታለች:: ቀጥም በሉ:: የእነዚያን የማያውቁትን ሰዎች መንገድ አትከተሉ።» አላቸው::
(90) 90. የኢስራኢል ልጆችን ባህሩን አሳለፍናቸው:: ፈርዖንና ሰራዊቱም ወሰን ለማለፍና ለመበደል ተከተሏቸው:: የመስመጥ አደጋ ባገኘውም ጊዜ «አመንኩ:: እነሆ ከዚያ የእሥራኤል ልጆች ካመኑበት አምላክ በስተቀር ሌላ የእውነት አምላክ የለም:: እኔም ከታዛዦቹ (ሙስሊሞች) አንዱ ነኝ።» አለ::
(91) 91. «ከአሁን በፊት በእርግጥ ያመጽክና ከአጥፊዎችም የነበርክ ስትሆን አሁን ታምናለህን?» ተባለ።
(92) 92. እናም ዛሬ ከኋላህ ለሚመጡ ትውልዶች ተዓምር ትሆን ዘንድ አካልህን (ከባሕሩ) እናወጣሀለን ከሰዎችም ብዙዎቹ ከተዐምሮቻችን በእርግጥ ዘንጊዎች ናቸው::
(93) 93. የኢስራኢልን ልጆችም ምስጉንን ስፍራ በእርግጥ አሰፈርናቸው:: ከመልካም ሲሳዮችም ሰጠናቸው:: እውቀትም እስከመጣላቸው ድረስ አልተለያዩም:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ በእርሱ ይለያዩበት በነበሩት ነገር በትንሳኤ ቀን በመካከላቸው ይፈርዳል::
(94) 94. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!)) ወደ አንተ ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ከሆንክ እነዚያን ካንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ሰዎች ጠይቅ:: እውነቱ ከጌታህ ዘንድ መጥቶልሃል:: እናም ከተጠራጣሪዎች አትሁን::
(95) 95. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከእነዚያ የአላህን አናቅጽ ካስተባበሉት ሰዎች አትሁን:: ከከሳሪዎቹ ትሆናለህና::
(96) 96. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያ የጌታህ ቃል የተረጋገጠባቸው ሰዎች አያምኑም::
(97) 97. ተዓምራት ሁሉ ቢመጣላቸዉም አሳማሚን ቅጣት እስከሚያዩ ድረስ(አያምኑም)::
(98) 98. ከነብዩ ዩኑስ በፊት ካለፉት ከተሞች ያመነችና እምነት የጠቀማት ከተማ ለምን አልኖረችም? ግን የነብዩ ዩኑስ ህዝቦች ባመኑ ጊዜ በቅርቢቱ ህይወት የውርደትን ቅጣት ከእነርሱ ላይ አነሳንላቸው:: እስከ ጊዜም ድረስ አጣቀምናቸው::
(99) 99. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ በሻ ኖሮ በምድር ያሉት ሁሉ በአንድ የተሰበሰቡ ሆነው ባመኑ ነበር:: ታዲያ አንተ ሰዎችን አማኞች እንዲሆኑ ታስገድዳለህን?
(100) 100. ማንኛዋም ነፍስ በአላህ ፈቃድ ቢሆን እንጂ የምታምን አይደለችም:: ከእነዚያ በማያውቁት ላይ ርክሰትን ያደርጋል::
(101) 101. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በሰማያትና በምድር ውስጥ ያሉትን ተዓምራት ተመልከቱ።» በላቸው:: ሆኖም ተዓምራትና አስፈራሪዎች ለማያምኑ ህዝቦች ምንም አይጠቅሙም::
(102) 102. የእነዚያን ከእነርሱ በፊት ያለፉትን ህዝቦች ቀኖች ብጤ ያገኟቸውን አይነት ቀናትን እንጂ ሌላን ይጠባበቃሉን? (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እናንተም ተጠባበቁ እኔም ከናንተው ጋር ከሚጠባበቁት ነኝ።» በላቸው::
(103) 103. መልዕክተኞቻችንንና እነዚያን ያመኑትንም ከጭንቅ ሁሉ እናድናለን:: እንደዚሁም ምእምናንን (ከጭንቅ ሁሉ) እናድናለን፡፡ ይህ በእኛ ላይ ተረጋገጠ::
(104) 104. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ሰዎች ሆይ! ከእኔ ሃይማኖት በመጠራጠር ውስጥ ከሆናችሁ እነዚያን ከአላህ ሌላ የምትገዟቸውን አልገዛም:: ይልቁንም ያንን የሚገድላችሁን አላህን ብቻ እገዛለሁ:: ከትክክለኛ አማኞች እንድሆንም ታዝዣለሁ።» በላቸው።
(105) 105. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ፊትህን ወደ ቀጥታው መንገድ ያዘነበልክ ስትሆን ለሃይማኖት ቀጥ አድርግ:: ከአጋሪዎቹም አትሁን::
(106) 106. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ከአላህ በስተቀር የማይጠቅምህንና የማይጎህዳን አትገዛ:: ይህን ብትሠራ ግን ያን ጊዜ ከበደለኞቹ ትሆናለህ (ተብያለሁ» በላቸው)::
(107) 107. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ ጉዳትን ቢያደርስብህ ከእርሱ ሌላ ለእርሱ ገላጭ የለዉም:: በጎ ነገርም ቢሻልህ ለችሮታው መላሽ ማንም የለም:: ከባሮቹ የሚሻውን በእርሱ ይለይበታል:: እርሱም መሓሪውና አዛኙ ነው::
(108) 108. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ሰዎች ሆይ! እውነቱ ከጌታችሁ በእርግጥ መጣላችሁ:: በእርሱ የተመራም የሚመራው ለራሱ ብቻ ነው:: የተሳሳተም የሚሳሳተው ጉዳቱ በራሱ ላይ ብቻ ነው:: እኔ በእናንተ ላይ ተጠባባቂ አይደለሁም።» በላቸው::
(109) 109. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ወደ አንተ የሚወረደውን ነገር ተከተል:: አላህ በእነርሱና ባንተ መካከል ባለው ጉዳይ ላይ እስከሚፈርድ ድረስ ታገሥ:: እርሱም ከፈራጆቹ ሁሉ በላጭ ፈራጅ ነውና::