(1) 1. ያ ንግስና በእጁ የሆነው አምላክ ችሮታው በዛ:: እርሱም በሁሉም ነገር ላይ ቻይ ነው::
(2) 2. ያ የየትኛችሁ ስራ ይበልጥ ያማረ መሆኑን ሊሞክራችሁ ሞትንና ህይወትን የፈጠረ ነው:: እርሱም አሸናፊና መሀሪ ነው::
(3) 3. ያ ሰባቱን ሰማያት የተነባበሩ ሆነው የፈጠረ ነው:: በአል ረህማን አፈጣጠርም ውስጥ ምንም ቅንጣት ያህል መዛነፍን (መቃረንና መበላሸት) አይታይም:: ዓይንህንም መልስ:: ከስንጥቆች አንዳችን ታያለህን?
(4) 4. ከዚያም ዓይንህን መላልስ:: ዓይንህ ተዋርዶ (ተናንሶ)፤ እርሱም የደከመ ሆኖ ወደ አንተ ይመለሳል::
(5) 5. ቅርቢቱን ሰማይም በእርግጥ በመብራቶች (በከዋክብት) አጌጥናት:: ለሰይጣናትም መቀጥቀጫዎች አደረግናት፤ ለእነርሱም ተንቀልቃይ የእሳትን ቅጣት አዘጋጀንላቸው::
(6) 6. ለእነዚያም በጌታቸው ለካዱት የገሀነም ቅጣት አላቸው:: መመላሻይቱም ገሀነም ከፋች!
(7) 7. በውስጧ በተጣሉ ጊዜ እርሷ የምትፈላ ስትሆን ከእርሷ እንደ (አህያ) ማናፋትን ይሰማሉ::
(8) 8. ከቁጭቷ የተነሳ ልትቆራረጥ ትቀርባለች:: በውስጧ ቡድኖች በተጣሉ ቁጥር «ዘበኞቿ (ስለዚህ ቀን) አስፈራሪ (ነብይ) አልመጣላችሁም ነበርን?» በማለት ይጠይቋቸዋል::
(9) 9. «አይደለም በእርግጥ አስፈራሪ መጥቶልናል:: አስተባበልንም:: አላህም ምንንም አላወረደም:: እናንተ አውርዷል ስትሉ፤ በትልቅ ስህተት ውስጥ እንጂ አይደላችሁም አልን» ይላሉ::
(10) 10. «የምንሰማ ወይም የምናስብ በነበርን ኖሮ የእሳት ጓዶች ባልሆን ነበር» ይላሉ::
(11) 11. በኃጢአታቸዉም ያምናሉ:: ለእሳት ጓዶችም (ከእዝነት) መራቅ ተገባቸው::
(12) 12. እነዚያ ጌታቸውን በሩቁ የሚፈሩ ለእነርሱ ምህረትንና ታላቅ ምንዳ አለላቸው::
(13) 13. (ሰዎች ሆይ!) ቃላችሁንም መስጥሩ:: ወይም በእርሱ ጩሁ:: እርሱ በልቦች ውስጥ ያለን ሁሉ አዋቂ ነው::
(14) 14. የፈጠረን አምላክ እርሱ እውቀተ ረቂቁ ውስጠ አዋቂው ሲሆን (ሚስጢርን) ሁሉ አያውቅምን?
(15) 15. እርሱ ያ ምድርን ለእናንተ የተገራች ያደረገላችሁ ነው:: በጋራዎቿና በመንገዶቿም ሂዱ:: ከሲሳዮም ብሉ:: (ኋላ) መመለሻችሁም ወደ እርሱ ብቻ ነው::
(16) 16. በሰማይ ያለው ጌታ በእናንተ ምድርን እንደማያሰምጥባችሁ ወዲያዉም እርሷም (እናንተኑ ውጣ) የምታረገርግ እንደማትሆን ትተማመናላችሁን? (አትፈሩምን?)።
(17) 17. ወይስ በሰማይ ያለው ጌታ በእናንተ ላይ ጠጠርን ያዘለች ንፋስን እንደማልክባችሁ ትተማመናላችሁ? (አትፈሩም?) ማስጠንቀቄም እንዴት እንደሆነ ወደ ፊት ታውቃላችሁ
(18) 18. እነዚያ ከእነርሱ በስተፊት የነበሩትም አስተባበሉ:: ጥላቻየም እንዴት ነበር (አስተዉል)፤
(19) 19. ከበላያቸው ሰልፍ ሰርተው ወዳሉ ወፎች አይመለከቱምን? ክንፎቻቸውን ያጥፋሉ:: ከአር-ረህማን ሌላ የሚይዛቸው የለም:: እርሱ ሁሉን ነገር አዋቂ ነው::
(20) 20. በእውነት ያ እርሱ ከአር-ረህማን ሌላ የሚረዳችሁ ለእናንተ የሆነ ሰራዊት ማነው? ከሓዲያን በመታለል ውስጥ እንጂ በሌላ ላይ አይደሉም::
(21) 21. ወይም ሲሳዮን ቢይዝባችሁ ያ ሲሳይን የሚሰጣችሁ ማነው? በእውነት እነርሱ በሞገድና በመደንበር ውስጥ ጸኑ::
(22) 22. በፊቱ ላይ ተደፍቶ የሚሄድ ሰው ይበልጥ የተቀና ነውን? ወይስ በቀጥተኛው መንገድ ላይ ተስተካክሎ የሚሄድ?
(23) 23. እርሱ! ያ አላህ የፈጠራችሁ፤ ለእናተም መስሚያና ማያዎች፤ ልቦችንም ያደረገላችሁ ነው:: ጥቂትንም አታመሰግኑምን በላቸው::
(24) 24. እርሱ ያ በምድር ላይ የበተናችሁ ነው:: ወደ እርሱም ትሰበሰባላችሁ በላቸው::
(25) 25. «እውነተኞችም እንደሆናችሁ ይህ ቀጠሮ መቼ ነው ተፈፃሚ የሚሆነው?» ይላሉ::
(26) 26. እውቀቱ ከአላህ ዘንድ ብቻ ነው:: እኔ ግልጽ አስፈራሪ እንጂ ሌላ አይደለሁም በላቸው::
(27) 27. (ቅጣቱ) ቅርብ ሆኖ ባዩትም ጊዜ የእነዚያ የካዱት ሰዎች ፊቶች ይከፋሉ:: ይህ ያ በእርሱ ትከራከሩበት የነበራችሁት ነው ይባላሉም::
(28) 28. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አያችሁን? እስኪ ንገሩኝ? አላህ ቢገድለኝ ከእኔ ጋር ያሉትንም (እንደዚሁ) ወይም በማቆየት ቢያዝንልን ከሓዲያንን ከአሳማሚ ቅጣት የሚያድን ማን ነው? በላቸው::
(29) 29. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እርሱ ያ (እመኑበት የምላችሁ) አር-ረህማን ነው:: እኛ በእርሱ አመንን:: በእርሱም ላይ ተጠጋን:: ወደ ፊትም በግልጽ መሳሳት ውስጥ የሆነው እርሱ ማን እንደሆነ በእርግጥ ታውቃላችሁ በላቸው::
(30) 30. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አያችሁ (እስኪንገሩኝ?) ውሃችሁ ሰራጊ ቢሆን (ወደ መሬት ቢሰርግ) ፈሳሽን (ምንጭን) ውሃ የሚያመጣላችሁ ማን ነው? በላቸው::