(1) 1.(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በጦርነት ከተማረኩ ገንዘቦች ይጠይቁሃል። «በጦርነት የተዘረፉ ገንዘቦች የአላህና የመልዕክተኛው ናቸው:: ስለዚህ አላህን ፍሩ:: በመካከላችሁ ያለውንም ሁኔታ አሳምሩ:: ትክክለኛ አማኞች ከሆናችሁ አላህንና መልዕክተኛውን ታዘዙ።» በላቸው።
(2) 2. ፍጹም ትክክለኛ አማኞች ማለት እነዚያ አላህ በተወሳ ጊዜ ልቦቻቸው የሚፈሩ፤ በእነርሱም ላይ የቁርኣን አናቅጽ በተነበቡ ጊዜ እምነትን የሚጨምሩላቸውና በጌታቸው ላይ ብቻም የሚመኩት ብቻ ናቸው::
(3) 3. እነዚያ ሰላትንም (ወቅቱን ጠብቀውና ደንቡን አሟልተው) የሚሰግዱና ከሰጠናቸዉም ሲሳይ የሚለግሱ ናቸው::
(4) 4. እነዚያ ትክክለኛ አማኞች ማለት እነርሱው ናቸው:: ለእነርሱ በጌታቸው ዘንድ ብዙ ደረጃዎች፤ የአላህ ምሕረትና የከበረ ሲሳይ አለላቸው::
(5) 5. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ! ይህ በምርኮ ክፍያ ሂደት ላይ የታየው የከፊሉ ሰው መጥላት ምሳሌው) ከአማኞች ከፊሉ እየጠሉ ጌታህ ከቤትህ በእውነት ላይ ሆነህ እንዳወጣህ ምሳሌ ነው::
(6) 6.(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነርሱ እያዩ ወደ ሞት እንደሚነዱ ሆነው በእውነቱ ነገር ላይ በመጋደል ግዴታነት ከተገለጸላቸው በኋላ ይከራከሩሃል::
(7) 7. (እናንተ ተከራካሪዎች ሆይ!)፤ አላህ ከሁለቱ ቡድኖች አንደኛዋን ለእናንተ ናት ሲል ተስፋ በሰጣችሁና የኃይል ባለቤት ያልሆነችውን የነጋዴይቱን ቡድን ለእናንተ ልትሆን በወደዳችሁ ጊዜ አላህም በተስፋ ቃላቱ እውነቱን ማረጋገጡን ሊገልጽና የካሓዲያንንም መጨረሻ ሊቆርጥ በፈለገ ጊዜ (የሆነውን አስታውስ)::
(8) 8. ይህንንም ያደረገው አጋሪዎቹ ቢጠሉም እውነቱን ሊያረጋግጥና ክህደትን ሊያጠፋ ነው::
(9) 9. (ሙስሊሞች ሆይ!) ከጌታችሁ እርዳታን በፈለጋችሁ ጊዜ «እኔ በሺህ መላዕክት ተከታታዮች ሲሆኑ እረዳችኋለሁ።» ሲል ለእናንተ የተቀበላችሁን አስታውሱ።
(10) 10. አላህ ይህንን እርዳታ ለብስራትና ልቦቻችሁ በእርሱ ሊረኩበት እንጂ ለሌላ አላደረገዉም:: ድልም የሚገኘው ከአላህ ዘንድ ብቻ ነው:: አላህ ሁሉን አሸናፊና ጥበበኛ ነውና::
(11) 11. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ! ) ከእርሱ በሆነው ጸጥታ በጦር ግንባር በእንቅልፍ በሸፈናችሁና ውሃውንም በእርሱ ሊያጠራችሁ፤ የሰይጣንንም ጉትጎታ ከናንተ ላይ ሊያስወግድላችሁ፤ ልቦቻችሁንም በትዕግሥት ሊያጠነክርላችሁ፤ በእርሱም ጫማዎችን በአሸዋው ላይ ሊያደላድልላችሁ በእናንተ ላይ ከሰማይ ዝናብን ባወረደ ጊዜ የሆነውን አስታውስ::
(12) 12. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ ወደ መላዕክቱ «እኔ በእርዳታዬ ከናንተ ጋር ነኝና እነዚያን በእኔ ያመኑትን ሰዎች አጽናኑ:: በእነዚያ በአላህ በካዱት ልቦች ውስጥ ደግሞ ፍርሀትን እጥላለሁ:: ከአንገቶችም በላይ እራሶችን ምቱ:: ከእነርሱም የቅርንጫፎችን መለያ ( አትቆች) ሁሉ ምቱ።» ሲል ያወረደውን አስታውስ።
(13) 13. ይህ የሆነው በአላህና በመልዕክተኛው ስለካዱ ነው:: አላህንና መልዕክተኛውን ለሚቃወም ሁሉ አላህም ቅጣቱ ብርቱ ነው::
(14) 14. (ከሓዲያን ሆይ!) ይህ ቅጣታችሁ ነው:: እናም ቅመሱት:: ለከሓዲያን የገሀነም እሳት ቅጣት በእርግጥ አለባቸው::
(15) 15. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እነዚያን በአላህ የካዱትን ለጦር ሲጓዙ ባገኛቹኋቸው ጊዜ ጀርባዎችን አታዙሩላቸው::
(16) 16. ያን ጊዜ ለግድያ ለመዘዋወር ወይም ወደ ሰራዊት ለመቀላቀል ሳይሆን ጀርባውን የሚያዞርላቸው ሰው ሁሉ ከአላህ የሆነን ቁጣ አትርፏል። መኖሪያዉም ገሀነም ናት:: የገሀነም መመለሻነትም ከፋ!
(17) 17. እናንተ አልገደላችኋቸዉም:: ግን አላህ ገደላቸው:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጭብጥን አፈር በወረወርክም ጊዜ አንተ አልወረወርክም:: ግን አላህ ወረወረ። አማኞችን ሁሉ ከእርሱ የሆነን መልካም ፈተናን ለመፈተን ይህንን አደረገ። አላህም ሁሉን ሰሚ፤ ሁሉንም አዋቂ ነውና::
(18) 18. ይህ ከአላህ የተቸረ ዕውነት ነው:: አላህ የከሓዲያንን ሁሉ ተንኮል አድካሚ ነውና::
(19) 19. (ከሓዲያን ሆይ!) ፍትሕን ብትጠይቁ ፍትሁ በእርግጥ መጥቶላችኋል:: ክሕደትና መዋጋታችሁን ብትከለከሉም እርሱ ለእናንተ የተሻለ ነው:: ወደ መጋደል ብትመለሱም እንመለሳለን:: ሰራዊታችሁ ብትበዛም እንኳ ለእናንተ ምንም አትጠቅማችሁም:: አላህ ሁልጊዜም ከትክክለኛ አማኞች ጋር ነውና::
(20) 20. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህንና መልዕክተኛውን ታዘዙ:: እናንተም እየሰማችሁ ከእርሱ አትሽሹ::
(21) 21. እንደነዚያም የማይሰሙ ሲሆኑ ሰማን እንዳሉትም አትሁኑ::
(22) 22. ከተንቀሳቃሾች ፍጡራን ሁሉ አላህ ዘንድ መጥፎዎች ማለት እነዚያ ሐቅን የማይሰሙ ደንቆሮዎቹ፣ እውነትን የማይናገሩና እውነታን የማያስተውሉት ናቸው::
(23) 23. በውስጣቸው ደግ መኖሩን አላህ ባወቀ ኖሮ የመረዳትን መስማት ያሰማቸው ነበር:: ደግ የሌለባቸው መሆኑን እያወቀ ባሰማቸዉም ኖሮ እነርሱ እውነትን የተዉ ሆነው በሸሹ ነበር።
(24) 24. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! (መልዕክተኛው) ህያው ወደ የሚያደርጋችሁ (እምነት) በጠራችሁ ጊዜ ለአላህና ለመልዕክተኛው ታዘዙ:: አላህ በሰውየውና በልቡ መካከል የሚጋርድ መሆኑንና ወደ እርሱም የምትሰበሰቡ መሆናችሁንም እወቁ::
(25) 25. (እናንተ ያመናችሁ ሆይ!) ከናንተ መካከል እነዚያን የበደሉትን ብቻ ለይታ የማትጎዳን ፈተና ተጠንቀቁ:: አላህ ቅጣቱ ብርቱ መሆኑንም እወቁ::
(26) 26. (ሙስሊሞች ሆይ!) እናንተ በምድር ላይ የተናቃችሁ ጥቂቶች ሆናችሁ ሳላችሁ ሰዎች ሊነጥቋችሁ የምትፈሩ ስትሆኑ ያስጠጋችሁን፤ በእርዳታዉም ያበረታችሁን፤ ከመልካሞች ሲሳዮችም ታመሰግኑ ዘንድ የሰጣችሁን አላህን አስታውሱ::
(27) 27. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህንና መልዕክተኛውን አትካዱ:: አደራዎቻችሁንም እያወቃችሁ አትካዱ::
(28) 28. ገንዘቦቻችሁና ልጆቻችሁ ለፈተና ብቻ መሆናቸውንና አላህ ዘንድ ታላቅ ምንዳ ያለ መሆኑን ዕወቁ።
(29) 29. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ብትፈሩ የእውነት መለያ ብርሃንን ያደርግላችኋል:: ክፉ ሥራዎቻችሁንም ከናንተ ላይ ያብስላችኋል:: እናንተንም ይምርላችኃል:: አላህ የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነውና::
(30) 30. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያም በአላህ የካዱ ሰዎች ሊያስሩህ ወይም ሊገድሉህ ወይም ከመካ ሊያስወጡህ ባንተ ላይ ባሴሩብህ ጊዜ የሆነውን አስታውስ:: ያሴራሉም:: አላህም ተንኮላቸውን ይመልስባቸዋል:: አላህ ግን ከሴረኞቹ ሁሉ በላይ ነውና::
(31) 31. አናቅጻችን በነርሱ ላይ በተነበቡ ጊዜም: «በእርግጥ ሰምተናል። በሻን ኖሮ የዚህን አባባል ተመሳሳይ ባልን ነበር:: ይህ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ተረቶች እንጂ ሌላ አይደለም።» ይላሉ።
(32) 32. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ጌታችን ሆይ! ይህ እርሱ ካንተ ዘንድ የተወረደ እውነት እንደሆነ በእኛ ላይ ከሰማይ ድንጋዮችን አዝንብብን ወይም አሳማሚ ቅጣትን አምጣብን።» ባሉጊዜ (የሆነውን አስታውስ)።
(33) 33. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አንተ በመካከላቸው እያለህ አላህ የሚቀጣቸው አይደለም። እነርሱም ምሕረትን የሚለምኑት ሲሆኑ አላህ የሚቀጣቸው አይደለም።
(34) 34. እነርሱ ከተከበረው መስጊድ የሚከለክሉ ሲሆኑ አላህ የማይቀጣቸው ለመሆኑ ለእነርሱ ምን ዋስትና አላቸው? የቤቱ ጠባቂዎቹ አልነበሩም:: ጠባቂዎቹም ክሕደትን ተጠንቃቂዎቹ እንጂ ሌሎቹ አይደሉም:: ግን አብዛኛዎቹ አያውቁም::
(35) 35. በከዕባ ውስጥ ስግደታቸውም ማፏጨትና ማጨብጨብ እንጂ ሌላ አልነበረም። «ትክዱት በነበራችሁትም ነገር ቅጣትን ቅመሱ» (ይባላሉ)::
(36) 36. እነዚያ የካዱት ከአላህ መንገድ ሊከለክሉ ገንዘቦቻቸውን ያወጣሉ:: በእርግጥም ያወጡታል:: ከዚያ ግን በእነርሱ ላይ ጸጸት ይሆንባቸዋል:: ከዚያም ይሸነፋሉ:: እነዚያም የካዱት ሁሉ ወደ ገሀነም ይሰበሰባሉ::
(37) 37. አላህ መጥፎውን ነገር ከመልካሙ ሊለይ መጥፎውንም ከፊሉን በከፊሉ ላይ ሊያደርግና በአንድ ላይ ሊያነባብረው በገሀነም ውስጥም ሊያደርገው (ይሰበሰባሉ):: እነዚያ እነርሱ ከሳሪዎቹ ናቸው::
(38) 38. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለእነዚያ በአላህ ለካዱት ቢከለከሉ ለእነርሱ በእርግጥ ያለፈውን ሥራ ምሕረት እንደሚደረግላቸው፤ ወደ መጋደል ቢመለሱም (እንደምናጠፋቸው ንገራቸው)። የቀድሞዎቹ ሕዝቦች ልማድ በእርግጥ አልፏልና።
(39) 39. ሁከት እስከሚጠፋና ሃይማኖት ሁሉ ለአላህ ብቻ እስከሚሆንም ድረስ ተጋደሏቸው:: ቢከለከሉም አላህ የሚሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው::
(40) 40. (ሙስሊሞች ሆይ!) ከእምነት ቢዞሩም አላህ ረዳታችሁ መሆኑን እወቁ:: እርሱ ምን ያምር ጠባቂ! ምን ያምርም ረዳት ነው!
(41) 41.(እናንተ ያመናችሁ ሆይ!) ከማንኛዉም ነገር በጦርነት ከካሓዲያን የማረካችሁትም ሁሉ አንድ አምስተኛው ለአላህና ለመልዕክተኛው፤ ለነብዩ የዝምድና ባለቤቶች፤ ለየቲሞች፤ ለሚስኪኖች፤ ለመንገደኞችም የተገባ መሆኑን እወቁ:: በአላህና በዚያም እውነትና ውሸት በተለየበት ቀን ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙበት (በበድር) ቀን ባገልጋያችን ላይ ባወረድነውም የምታምኑ እንደ ሆናችሁ ይህንን እወቁ:: አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው።
(42) 42. (ሙስሊሞች ሆይ!) እናንተ በቅርቢቱ ዳርቻ ሁናችሁ እነርሱ ደግሞ በሩቂቱ ዳርቻ ሆነው የነጋዴዎቹም ቡድን ከናንተ በታች ሲሆኑ በሰፈራችሁ ጊዜ ያደረግንላችሁን አስታውሱ:: በተቃጠራችሁም ኖሮ ግን በቀጠሮው በተለያያችሁ ነበር:: ግን አላህ ሊሠራው የሚገባውን ነገር ሊፈጽምና የሚጠፋም ከአስረጅ መድረስ በኋላ እንዲጠፋ፤ ሕያው የሚሆንም ከአስረጅ መድረስ በኋላ ሕያው እንዲሆን ያለቀጠሮ አጋጠማችሁ:: አላህ በእርግጥ ሁሉን ሰሚና ሁሉንም አዋቂ ነውና::
(43) 43. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ በሕልምህ እነርሱን ጥቂት አድርጎ ባሳየህ ጊዜ አስታውስ:: እነርሱን ብዙ አድርጎ ባሳየህም ኖሮ በፈራችሁና በነገሩ በተጨቃጨቃችሁ ነበር ግን አላህ አዳናችሁ:: እርሱ በደረቶች ውስጥ ያለን ሁሉ አዋቂ ነውና::
(44) 44. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህም ሊሠራው የሚገባን ነገር ይፈጽም ዘንድ በተጋጠማችሁ ጊዜ እነርሱን በዓይኖቻችሁ ጥቂት አድርጎ ያሳያችሁንና በዓይኖቻቸውም ላይ ያሳነሳችሁን (አስታውሱ)፡፡ ነገሮቹም ሁሉ ወደ አላህ ብቻ ይመለሳሉ፡፡
(45) 45. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ሰራዊትን በገጠማችሁ ጊዜ እርጉ (መክቱ):: አላህንም በብዙው አውሱ:: በእርግጥ ትድናላችሁና::
(46) 46. (ሙስሊሞች ሆይ!) አላህንና መልዕክተኛውን ታዘዙ :: አትጨቃጨቁም ትፈራላችሁና ኃይላችሁም ትሄዳለችና:: ታገሡም አላህ በእርዳታው ከትዕግሥተኞች ጋር ነውና::
(47) 47. እንደ እነዚያ ለትዕቢትና ለሰዎች ይዩልኝ ሲሉ ከአላህም መንገድ ለማገድ ከሀገራቸው እንደወጡት ሰዎች አትሁኑ:: አላህ በሚሠሩት ሁሉ በእውቀቱ ከባቢ ነውና::
(48) 48. ሰይጣንም ሥራዎቻቸውን ለእነርሱ ባሳመረላቸውና «ዛሬ ለእናንተ ከሰዎች አሸናፊ የላችሁም:: እኔም ለእናንተ ረዳት ነኝ።» ባለ ጊዜም (የሆነውን አስታውስ):: ሁለቱ ቡድኖችም በተያዩ ጊዜ ወደኋላው አፈገፈገ:: «እኔ ከናንተ ንጹህ ነኝ:: እኔ እናንተ የማታዩትን አያለሁ:: እኔ አላህን እፈራለሁ:: አላህም ቅጣተ ብርቱ ነው።» አላቸው::
(49) 49. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አስመሳዮችና እነዚያ በልቦቻቸው ውስጥ በሽታ ያለባቸው ሰዎች «እነዚህን ሙስሊሞች ሃይማኖታቸው አታለላቸው።» ባሉ ጊዜ (የነበረውን አስታውስ):: በአላህ ላይ የሚጠጋ (ሁልጊዜም ያሸንፋል):: አላህ ሁሉንም አሸናፊና ጥበበኛ ነውና::
(50) 50. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያንም በአላህ የካዱትን ሰዎች መላዕክት ፊቶቻቸውንና ጀርቦቻቸውን እየመቱ «የቃጠሎን ስቃይ ቅመሱ።» እያሉ በሚገድሏቸው ጊዜ ብታይ ኖሮ (አስደንጋጭን ነገር ታይ ነበር)::
(51) 51. «ይህ እጆቻችሁ ባስቀደሙት ምክንያት አላህ ለባሮቹ በዳይ ባለመሆኑ ነው።» ይባላሉ።
(52) 52. የእነዚያ ሰዎች ልማድ እንደ ፈርዖን ቤተሰብና እንደነዚያም ከእነርሱ በፊት እንደ ነበሩት ህዝቦች ልማድ ነው:: በአላህ አናቅጽ ካዱ:: አላህም በኃጢአቶቻቸው ያዛቸው:: አላህ ሀይለኛና ቅጣተ ብርቱ ነውና::
(53) 53. ይህ ቅጣት አላህ በሕዝቦች ላይ የለገሰውን ጸጋ በነፍሶቻቸው ያለውን ነገር እስከሚለውጡ ድረስ የማይለውጥ በመሆኑ ምክንያት ነው:: አላህም ሁሉን ሰሚና ሁሉንም አዋቂ ነውና::
(54) 54. እንደ ፈርዖን ቤተሰቦችና እንደእነዚያ ከእነርሱ በፊት እንደ ነበሩት ልማድ (እስከሚለውጡ ድረስ አይለውጥባቸዉም)። በጌታቸው ታዓምራት አስተባበሉና በኃጢአቶቻቸው አጠፋናቸው:: የፈርዖንን ቤተሰቦች አስመጥናቸው:: ሁሉም በዳዮች ነበሩና::
(55) 55. ከሚንቀሳቀሱ እንስሳዎች ሁሉ አላህ ዘንድ ይበልጥ ክፉዎቹ እነዚያ የካዱት ሰዎች ናቸው:: ስለዚህ እነርሱ አያምኑም።
(56) 56. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያ ከእነርሱ ቃል ኪዳን የያዝክባቸውና ከዚያም በየጊዜው ቃል ኪዳናቸውን የሚያፈርሱ ናቸው:: እነርሱም አይጠነቀቁም::
(57) 57. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በጦር ላይ ብታገኛቸው በእነርሱ ቅጣት ምክንያት ሌሎቹ ከሓዲያን ይገሠጡ ዘንድ ከኋላቸው ያሉትን በትንባቸው::
(58) 58. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከሕዝቦችም በኩል ክህደትን ብትፈራ የቃል ኪዳኑን መፍረስ በማወቅ በኩል ተመሳሳይ ሆናችሁ ቃል ኪዳናቸውን ወደ እነርሱ ጣልላቸው:: አላህ ከዳተኞችን ሁሉ አይወድምና::
(59) 59. እነዚያም የካዱት ከአላህ ቅጣት ያመለጡ መሆናቸውን አያስቡ:: እነርሱ አያቅቱምና (አያሸንፉምና)::
(60) 60. (እናንተ ያመናችሁ ሆይ!) ለእነርሱ ከማንኛውም ኃይልና ከታጀቡ ፈረሶች የቻላችሁትን ሁሉ በእርሱ የአላህን ጠላትና ጠላታችሁን ሌሎችንም ከእነርሱ በስተቀር ያሉትን የማታውቋቸውን አላህ ብቻ የሚያውቃቸውን አስመሳዮች የምታሸብሩበት ስትሆኑ አዘጋጁላቸው:: ከማንኛዉም ነገር በአላህ መንገድ የምትለግሱት ምንዳው ወደ እናንተ በሙሉ ይሰጣል:: እናንተ ቅንጣት አትበደሉም::
(61) 61. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ወደ ዕርቅ ቢያዘነብሉ አንተም ወደ እርቁ ተዘንበልና በአላህ ላይ ብቻ ተመካ:: እነሆ እርሱ ሁሉን ሰሚ እና ሁሉን አዋቂው ነውና።
(62) 62. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሊያታልሉህ ቢፈልጉ አላህ በቂህ ነው:: እርሱ ያ በእርዳታውና በምዕምናን ያበረታህ ነውና::
(63) 63. በልቦቻቸውም መካከል ያስማማ ነው፡፡ (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በምድር ያለውን ሁሉ ሀብት ብትለገስ ኖሮ እንኳን በልቦቻቸው መካከል ባላስማማህ ነበር:: ግን አላህ በመካከላቸው አስማማ:: እርሱ ሁሉን አሸናፊና ጥበበኛ ነውና::
(64) 64. አንተ ነብይ ሆይ! ለሁሉ ነገር በቂህ አላህ ነው:: ለተከተሉህም ምዕምናን በቂያቸው አላህ ነው::
(65) 65. አንተ ነብይ ሆይ! አማኞችን ጠላቶቻቸውን በመዋጋት ላይ አደፋፍራቸው:: ከናንተ ውስጥ ሃያ ታጋሾች ቢኖሩ ሁለት መቶን ያሸንፋሉ:: ከናንተም መካከል መቶ ሰዎች ቢኖሩ ከእነዚያ ከካዱት ሕዝቦች መካከል አንድ ሺሕን ያሸንፋሉ:: ምክንያቱም እነርሱ የማይገነዘቡ ህዝቦች ናቸዉና::
(66) 66. አሁን አላህ ከናንተ ላይ አቀለለላችሁ:: በእናንተ ውስጥም ድክመት መኖሩን አወቀ:: ስለዚህ ከናንተ መካካል መቶ ታጋሾች ቢኖሩ ሁለት መቶን ያሸንፋሉ:: ከናንተም አንድ ሺህ ቢኖሩ በአላህ ፍቃድ ሁለት ሺዎችን ያሸንፋሉ:: አላህ ከታጋሾቹ ጋር ነዉና::
(67) 67. ለነብይ በምድር ላይ ጠላቶቹን እስኪያደክም ድረስ ለእርሱ ምረኮኞች ሊኖሩት አይገባም:: (አማኞች ሆይ!) የቅርቢቱን ዓለም ጠፊ ጥቅም ትፈልጋላችሁ:: አላህ መጨረሻይቱን ይሻል:: አላህም ሁሉን አሸናፊና ጥበበኛ ነው::
(68) 68. ከአላህ ያለፈ ውሳኔ ባልነበረ ኖሮ በወሰዳችሁት ቤዛ ከባድ ቅጣት በነካችሁ ነበር::
(69) 69. (አማኞች ሆይ!) ያ! ከጠላት የማረካችሁትን ሀብት የተፈቀደና መልካም ሲሆን ብሉ:: አላህንም ፍሩ:: አላህም መሓሪና አዛኝ ነውና::
(70) 70. አንተ ነብይ ሆይ! ከምርኮኞች መካከል በእጆቻችሁ ላሉት «አላህ በልቦቻቸው ውስጥ በጎን ነገር (እምነትን) ቢያውቅ ከተወሰደባችሁ የተሻለን ይሰጣችኋል:: ለእናንተም ይምራችኋል:: አላህም መሓሪና አዛኝ ነውና።» በላቸው።
(71) 71. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሊክዱህ ቢፈልጉ ከዚህ በፊት አላህን በእርግጥ ከድተዋል:: እናም ከእነርሱ አስመችቶሃል:: አላህም ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነው::
(72) 72. እነዚያ በአላህ አምነው ለእርሱም ሲሉ ከሀገራቸው የተሰደዱ በአላህ መንገድ ላይም በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው የታገሉ እና እነዚያም ስደተኞቹን ያስጠጉና የረዱ ሰዎች እነዚያ ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው:: እነዚያ አምነውም ያልተሰደዱ ሰዎች ደግሞ ለአላህ ብለው እስከሚሰደዱ ድረስ ከእነርሱ ምንም ዝምድና የላችሁም:: በሃይማኖት እርዳታን ቢፈልጉባችሁ በእናንተና በእነርሱ መካከል ቃል ኪዳን ባላችሁ ሕዝቦች ላይ ካልሆነ በስተቀር በእናንተ ላይ እነርሱን መርዳት አለባችሁ:: አላህ የምትሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነውና::
(73) 73. እነዚያም በአላህ የካዱ ሰዎች ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው:: (ከምዕምናን ጋር መረዳዳትን ከከሓዲያን መቆራረጥን) ባትሠሩት በምድር ላይ ሁከትና ታላቅ ጥፋት ይሆናል::
(74) 74. እነዚያ አምነው ለእርሱም ሲሉ የተሰደዱት፤ በአላህ መንገድ ላይም የታገሉ እና እነዚያም ያስጠጉና የረዱ እነዚያ ትክክለኛ አማኞች እነርሱው ናቸው:: ለእነርሱም ምሕረትና የከበረ ሲሳይ አለላቸው::
(75) 75. (እናንተ ያመናችሁ ሆይ!) እነዚያ በኋላ ያመኑና ከሀገራቸው የተሰደዱ ከናንተም ጋር ሆነው የታገሉ እነዚያ ከናንተው ናቸው:: የዝምድናዎች ባለቤቶች በአላህ መጽሐፍ ከፊሎቻቸው ከከፊሉ ለመውረስ የተገቡ ናቸው። አላህ ሁሉን ነገር አዋቂ ነውና::