(1) 1. አሊፍ፤ ላም፤ ሚይም፤
(2) 2. ሰዎቹ አምነናል በማለታቸው ብቻ (ከአላህ በልዩ ልዩ ነገሮች) ሳይፈተኑ የሚተው መሰላቸውን?
(3) 3. እነዚያን ከእነርሱ በፊት የነበሩትንም ህዝቦች በርግጥ ፈትነናል። እነዚያን እውነት የተናገሩትን አላህ በእርግጥ ያውቃል። ውሸታሞችንም ያውቃል።
(4) 4.ይልቁንም እነዚያ መጥፎዎችን ሥራዎች የሚሠሩት ሰዎች የሚያመልጡን መሰላቸውን? ያ የሚፈርዱት ፍርድ ከፋ::
(5) 5. የአላህን መገናኘት ተስፋ የሚያደርግ ሰው ሁሉ የአላህ ቀጠሮ በእርግጥ መጪ ነው:: እርሱም ሰሚም ሁሉን አዋቂ ነው።
(6) 6. በአላህ መንገድ ላይ የታገለ ሰው የሚታገለው ለነፍሱ ብቻ ነው:: አላህ ከዓለማት ሁሉ በእርግጥ የተብቃቃ ነውና::
(7) 7. እነዚያም በአላህና በመልዕክተኛው ያመኑና መልካም ተግባራትንም የሠሩ መጥፎ ሥራዎቻቸውን ከእነርሱ ላይ እናብስላቸዋለን። በዚያም ይሠሩት በነበሩት መልካም ሥራ በእርግጥ እንመነዳቸዋለን።
(8) 8. የሰውን ልጅ ለወላጆቹ መልካም ተግባርን ሁሉ እንዲፈጽም አዘዝነው:: ወላጆችም ላንተም በእርሱ እውቀት የሌለህን ጣኦት በእኔ እንድታጋራው ቢያስገድዱህ አትታዘዛቸው:: መመለሻችሁ ወደ እኔ ነው:: ከዚያም ትሠሩት የነበራችሁትን ሁሉ እነግራችኋለሁ::
(9) 9. እነዚያንም በአላህ ያመኑና መልካም ሥራዎችን የሠሩ ሁሉ ከደጋጎቹ ውስጥ በእርግጥ እናስገባቸዋለን::
(10) 10. ከሰዎች መካከል «በአላህ አመንን።» የሚል ሰው አለ:: ከዚያ በአላህ በማመኑ ምክኒያት በተሰቃየ ጊዜ የሰዎችን ማሰቃየት እንደ አላህ ቅጣት ያደርጋል:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከጌታህም እርዳታ ቢመጣ እኛ በእርግጥ ከናንተ ጋር ነበርን ይላሉ:: አላህ በዓለማት ሕዝብ ልቦች ውስጥ ያለውን ሁሉ አዋቂ አይደለምን?
(11) 11. አላህ እነዚያንም በትክክል ያመኑትን በእርግጥ ያውቃል:: መናፍቆቹንም ያውቃል::
(12) 12. እነዚያንም የካዱት ሰዎች ለእነዚያ ላመኑት «መንገዳችንን ተከተሉ:: ኃጢአቶቻችሁንም እንሸከማለን» አሉ:: እነርሱም ከኃጢአቶቻቸው ምንንም ተሸካሚዎች አይደሉም:: እነርሱ በእርግጥ ውሸታሞች ናቸው።
(13) 13. ሸክሞቻቸውንና ከሸክሞቻቸው ጋር ሌሎች ሸክሞችንም በእርግጥ ይሸከማሉ:: በትንሳኤም ቀን ይቀጥፉት ከነበሩት ሁሉ በእርግጥ ይጠየቃሉ::
(14) 14. ኑሕንም ወደ ህዝቦቹ በእርግጥ ላክነው:: በውስጣቸዉም ሺህ ዓመትን ሀምሳ ዓመት ሲቀር ተቀመጠ:: እነርሱ በዳዮች ሆነዉም የውሃው ማዕበል አጥለቀለቃቸው::
(15) 15. ኑህንና የመርከቢቱን ጓዶች አዳንናቸው:: እርሷንም ለዓለማት ተዓምር አደረግናት::
(16) 16. መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ! ኢብራሒም ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ የሆነውን (አስታውስ)። «አላህን ተገዙ ፍሩትም ይህን ማድረጋችሁ የምታውቁት ብትሆኑ ለናንተ በላጭ ነው።
(17) 17. (ሰዎች ሆይ!) ከአላህ ሌላ የምትገዙት ጣኦታትን ብቻ ነው:: ውሸትንም ትቀጥፋላችሁ:: እነዚያ ከአላህ ሌላ የምትገዟቸው ጣዖታት ለእናንተ ሲሳይን ሊሰጧችሁ አይችሉም:: ስለዚህ ሲሳይን ከአላህ ዘንድ ብቻ ፈልጉ:: ተገዙትም:: ለርሱም አመስግኑ ወደ እርሱም ትመለሳላችሁ::
(18) 18. ብታስተባብሉም ከፊታችሁ የነበሩት ህዝቦች በእርግጥ አስተባብለዋል:: በመልዕክተኛዉም ላይ ግልጽ ማድረስ እንጂ ሌላ የለበትም::
(19) 19. አላህ መፍጠርን እንዴት እንደሚጀምርና ከዚያ እንዴት እንደሚመልሰው አይመለከቱምን? ይህ በአላህ ላይ ቀላል ነው::
(20) 20. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በምድር ላይ ሂዱ:: እናም መፍጠርን እንዴት እንደጀመረ ተመልከቱ:: ከዚያም አላህ የመጨረሻይቱን መነሳት ያስነሳል:: አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና።» በላቸው::
(21) 21. የሚሻውን ሰው ይቀጣል:: የሚሻውንም ሰው ያዝንለታል ወደ እርሱም ትመለሳላችሁ::
(22) 22. እናንተ በምድርም ሆነ በሰማይ የምታቅቱ አይደላችሁም። ከአላህም ሌላ ወዳጅም ተከላካይም ምንም የላችሁም።
(23) 23. እነዚያም በአላህ አናቅጽና በመገናኘቱ የካዱ እነዚያ ከእዝነቴ ተስፋን ቆረጡ:: እነዚያም ለእነርሱ አሳማሚ ቅጣት አለባቸው::
(24) 24. የህዝቦቹም መልስ፡- «ግደሉት ወይም አቃጥሉት።» ማለት እንጂ ሌላ አልነበረም። ከዚያም ከእሳቲቱ አላህ አዳነው። በዚህ ውስጥ ለሚያምኑ ሕዝቦች ብዙ ተዐምራት አሉበት።
(25) 25. (ኢብራሂም) አለ፡- «ከአላህ ሌላ ጣኦታትን አማልክት የያዛችሁት በቅርቢቱ ህይወት በመካከላችሁ ለመዋደድ ብቻ ነው። ከዚያም በትንሳኤ ቀን ከፊላችሁ በከፊሉ ይክዳል:: ከፊላችሁም ከፊሉን ይረግማል:: መኖሪያችሁም እሳት ናት:: ለእናንተም ከረዳቶች ምንም የላችሁም።»
(26) 26. ከዚያም ሉጥ ለእርሱ አመነ:: (ኢብራሂምም) «እኔ ወደ ጌታዬ ተሰዳጅ ነኝ:: እነሆ እርሱ አላህ ሁሉን አሸናፊና ጥበበኛ ነውና።» አለ።
(27) 27. ለእርሱም ኢስሐቅንና ያዕቆብን ሰጠነው በዘሩም ውስጥ ነብይነትንና መጽሐፍን አደረግን:: ምንዳውንም በቅርቢቱ ዓለም ሰጠነው:: እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከደጋጎቹ ነው::
(28) 28. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሉጥንም ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ አስታውስ: «እናንተ ጠያፍን ሥራ ትሰራላችሁን? በእርሷ ከዓለማት አንድም ሰው አልቀደማችሁም።
(29) 29. «እናንተ በእርግጥ ወንዶችን ትመጣላችሁን? መንገድንም ትቆርጣላችሁን? በሸንጓችሁም የሚነወርን ነገር ትሠራላችሁን?» አላቸው:: የሕዝቦቹም መልስ «ከእውነተኞቹ እንደሆንክ የአላህን ቅጣት አምጣብን።» ማለት እንጂ ሌላ አልነበረም።
(30) 30. «ጌታዬ ሆይ! በአመጸኞች ሕዝቦች ላይ እርዳኝ።» አለ::
(31) 31. መልዕክተኞቻችንም ወደ ኢብራሂም በብስራት በመጡ ጊዜ «እኛ የዚችን ከተማ ሰዎች አጥፊዎች ነን ሰዎችዋ በዳዮች ነበሩና።» አሉት።
(32) 32. «በእርሷ ውስጥ ሉጥ አለ እኮ?» አላቸው:: «እኛ በውስጧ ያለውን ካንተ ይበልጥ አዋቂ ነን:: እርሱንማ በእርግጥ እናድነዋለን:: ቤተሰቦቹንም ጭምር ሚስቱ ብቻ ስትቀር እርሷ በጥፋቱ ውስጥ ከሚቀሩት ናት።» አሉት::
(33) 33. መልዕክተኞቻችንም ወደ ሉጥ በመጡት ጊዜ በነሱ ምክንያት አዘነ:: በእነርሱም ልቡ ተጨነቀ። አሉትም: «አትፍራ። አትዘንም። እኛ አዳኞችህ ነን:: ቤተሰቦችህንም ሚስትህ ብቻ ስትቀር:: እርሷ ግን በጥፋቱ ውስጥ ከቀሪዎቹ ናት።
(34) 34. «እኛ በዚህ ከተማ ሰዎች ላይ ያምጹ በነበሩበት ምክንያት ከሰማይ ቅጣትን አውራጆች ነን።» (አሉት)
(35) 35. በእርግጥም ለሚያስቡ ሰዎች ሁሉ ከእርሷ ግልጽ ምልክትን ተውን (አስቀረን)::
(36) 36. ወደ መድየንም ወንድማቸውን ሹዐይብን ላክን። «ህዝቦቼ ሆይ! አላህን ተገዙ:: የመጨረሻውንም ቀን ፍሩ:: በምድርም ውስጥ የምታጠፉ ሆናችሁ አታበላሹ።» አላቸው።
(37) 37. እናም አስተባበሉትና የምድር መንቀጥቀጥ ያዘቻቸው፡፡ ባገራቸዉም ውስጥ ተንከፍረው አደሩ (አነጉ)።
(38) 38. ዓድንና ሠሙድንም አጠፋን:: የመኖሪያዎቻቸውን ፍርስራሾች በማየት መጥፋታቸው ለእናንተ በእውነት ተገለጠላችሁ:: ሰይጣንም ሥራዎቻቸውን ለእነርሱ ሸለመላቸው:: ከመንገድም አገዳቸው:: የማስተዋልም ባለቤቶች ነበሩ:: ግን አላስተዋሉም::
(39) 39. ቃሩንንም ፈርዖንንም ሃማንንም አጠፋን:: ሙሳም በተዐምራት በእርግጥ መጣባቸው:: በምድርም ላይ ኮሩ:: አምላጮችም አልነበሩም::
(40) 40. ሁሉንም በኃጢአቱ ያዝነው:: ከእነርሱም ውስጥ ጠጠርን ያዘለ ነፍስን የላክንበት አለ:: ከእነርሱም ውስጥ ጩኸት የያዘችው አለ:: ከእነርሱም ውስጥ በእርሱ ምድርን የደረባንበት አለ:: ከእነርሱም ውስጥ ያሰመጥነው አለ:: አላህ የሚበድላቸው አልነበረም:: ግን ነፍሶቻቸውን የሚበድሉ ነበሩ::
(41) 41. የእነዚያ ከአላህ ሌላ ረዳቶችን (ጣኦታትን) የያዙ ሰዎች ምሳሌ ቤትን እንደሠራች ሸረሪት ብጤ ነው:: ከቤቶችም ሁሉ በጣም ደካማው የሸረሪት ቤት ነው:: ቢያውቁ ኖሮ አማልክት አድርገው አይገዟቸዉም ነበር::
(42) 42. አላህ ያንን ከእርሱ ሌላ የሚገዙትን ማንኛውንም ያውቃል:: እርሱም ሁሉን አሸናፊዉና ጥበበኛው ነው::
(43) 43. እነዚህንም ምሳሌዎች ለሰዎች እንገልጻቸዋለን:: ከሊቃውንቶቹም በስተቀር ሌሎችአያውቋትም፡፡
(44) 44. አላህም ሰማያትንና ምድርን እውነተኛ ሆኖ ፈጠረ፤ በዚህ ውስጥ ለአማኞች ተዐምር አለበት።
(45) 45. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከመጽሐፉ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ:: ሶላትንም ደንቡን ጠብቀህ ስገድ:: ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና:: አላህን ማውሳት ከመልካም ነገር ሁሉ በላጭ ነው:: አላህም የምትሠሩትን ስራ ሁሉ ያውቃል::
(46) 46. (እናንተ ያመናችሁ ሆይ!) ከእነርሱ እነዚያን የበደሉትን ሲቀር የመጽሐፉ ባለቤቶችን በዚያች እርሷ መልካም በሆነችው ክርክር እንጂ አትከራከሩ:። በሉም፡- «በዚያ ወደ እኛ በተወረደው ወደ እናንተም በተወረደው አመንን:: አምላካችንም አምላካችሁም አንድ ነው:: እኛም ለእርሱ ታዛዦች ነን።»
(47) 47. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እንደዚሁም ወደ አንተ መጽሐፍን አወረድን:: እነዚያም መጽሐፍን የሰጠናቸው በእርሱ ያምናሉ:: ከእነዚህም (ከመካ) ሰዎች በእርሱ የሚያምኑ አሉ:: በተዓምራታችንም ከሓዲያን እንጂ ማንም አይክድም::
(48) 48. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከእርሱ በፊትም መጽሐፍን የምታነብ በቀኝህም የምትጽፈው አልነበርክም:: ያን ጊዜ አጥፊዎቹ በእርግጥ በተጠራጠሩ ነበር::
(49) 49. አይደለም:: እርሱ (ቁርኣን) በእነዚያ እውቀትን በተሰጡት ሰዎች ልቦች ውስጥ የጠለቀ ግልፆች አናቅጽ ነው:: በአናቅጻችንም በዳዮቹ እንጂ ሌላው አይክድም::
(50) 50. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከሓዲያን «በእርሱ ላይ ከጌታው ዘንድ ተዐምራት ለምን አልተወረዱም?» አሉ:: »ተዐምራት ከአላህ ዘንድ ብቻ ናቸው:: እኔም ግልጽ አስፈራሪ ብቻ ነኝ።» በላቸው::
(51) 51. እኛ መጽሐፉን በእነርሱ ላይ የሚነበብ ሆኖ ባንተ ላይ ማውረዳችን አይበቃቸዉምን? በዚህ ውስጥ ለሚያምኑ ሕዝቦች ሁሉ ችሮታና ግሳጼ አለበት::
(52) 52. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በእኔና በእናንተ መካከል መስካሪ በአላህ በቃ:: በሰማያትና በምድር ያለውን ሁሉ ያውቃል።» በላቸው:: እነዚያም በብላሽ ነገር ያመኑና በአላህ የካዱ እነዚያ እነርሱ ከሳሪዎቹ ናቸው።
(53) 53. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በቅጣትም ያስቸኩሉሃል! የተወሰነም ጊዜ ባልነበረ ኖሮ ቅጣቱ በመጣባቸው ነበር:: እነርሱ የማያውቁ ሲሆኑም በድንገት በእርግጥ ይመጣባቸዋል::
(54) 54. በቅጣት ያስቸኩሉሃል! ገሀነምም ከሓዲያንን በእርግጥ ከባቢ ናት::
(55) 55. ቅጣቱ ከበላያቸው ከእግሮቻቸዉም ሥር በሚሸፍናቸው ቀን «ትሰሩት የነበራችሁትን ቅመሱ።» በሚላቸዉም ቀን ትከባቸዋለች።
(56) 56. እናንተ ያመናችሁ ባሮቼ ሆይ! ምድሬ በእርግጥ ሰፊ ናት:: ብትቸገሩ ተሰደዱ እኔንም ብቻ ተገዙኝ::
(57) 57. ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት:: ከዚያም ወደ እኛ ትመለሳላችሁ::
(58) 58. እነዚያም በአላህ ያመኑና መልካም ስራዎችን የሠሩ ከገነት በስሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው ሰገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲሆኑ በእርግጥ እናሰፍራቸዋለን:: የሠራተኞችም ምንዳ ምንኛ አማረ!
(59) 59. እነርሱ እነዚያ የታገሱ በጌታቸዉም ላይ የሚመኩ ናቸው፡
(60) 60. ከተንቀሳቃሽ ፍጡራን ምግባቸውን የማይሸከሙ ብዙ ናቸው:: አላህ ይመግባቸዋል:: እናንተንም ይመግባል:: እርሱ ሰሚና አዋቂ ነውና::
(61) 61. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ጸሐይንና ጨረቃንም የገራ ማን እንደሆነ ብትጠይቃቸው በእርግጥ ”አላህ ነው“ ይሉሃል:: ታዲያ እንዴት ይመለሳሉ።
(62) 62. አላህ ከባሮቹ ለሚሻው ሲሳይን ያሰፋል:: ለእርሱም ያጠባል:: አላህ በነገሩ ሁሉ አዋቂ ነውና::
(63) 63. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከሰማይ ውሃን ያወረደና በእርሱም ምድርን ከሞተች በኋላ ሕያው ያደረጋት ማን እንደሆነ ብትጠይቃቸው "አላህ ነው" ይሉሃል:: "ስለዚህ ምስጋና ሁሉ ለአላህ ነው።“ በላቸው:: ግን አብዛኞቻቸው ይህን አያውቁም።
(64) 64. ይህም የቅርቢቱ ሕይወት መታለያና ጨዋታ እንጂ ሌላ አይደለም:: የመጨረሻይቱም አገር እርሷ በእርግጥ የዘላለም ህይወት አገር ናት:: የሚያውቁ ቢሆኑ ኖሮ ጠፊይቱን ሕይወት አይመርጡም ነበር::
(65) 65. በመርከቦች ውስጥ በተሳፈሩ ጊዜም አላህን መገዛትን ለእርሱ ብቻ ያጠሩ ሆነው ይጠሩታል:: ወደ የብስ በማውጣት ባዳናቸው ጊዜ ግን ወዲያውኑ እነርሱ ጣዖትን ያጋራሉ::
(66) 66. በሰጠናቸው ጸጋ ሊክዱና ሊጠቃቀሙ ያጋራሉ፤ ወደ ፊትም የሚጠብቃቸውን ያውቃሉ።
(67) 67. ሰዎቹ ከየዙሪያቸው ሲነጠቁ እኛ አገራቸውን ጸጥተኛ ክልል ማድረጋችንን አያዩምን? በውድቅ ነገር ያምናሉን? በአላህም ጸጋ ይክዳሉን?
(68) 68. በአላህ ላይ ውሸትን ከቀጣጠፈ ሰው ወይም እውነት በመጣለት ጊዜ ከአስዋሸ ሰው ይበልጥ ራሱን በዳይ ማነው? በገሀነም ውስጥ ለከሓዲያን መኖሪያ የለምን?(አለ)
(69) 69. እነዚያም በእኛ መንገድ የታገሉ ህዝቦችን መንገዳችንን በእርግጥ እንመራቸዋለን:: አላህ በእርግጥ ከበጎ ሰሪዎች ጋር ነውና፡: