12 - Yusuf ()

|

(1) 1.አሊፍ፤ ላም፤ ራ፤ እነዚህ አናቅጽ ግልጽና የተብራራ ከሆነው መጽሐፍ አናቅጽ ናቸው።

(2) 2. እኛ ይህንን ቁርኣንን ትረዱት ዘንድ በዐረበኛ ቋንቋ አወረድነው።

(3) 3.(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ይህንን የቁርኣን ወደ አንተ በማውረዳችን እጅግ ውብና ማራኪ የሆነ ታሪክ እንተርክልሃለን:: ከዚህ በፊት አንተም ይህንን ታሪክ ከማያውቁት ነበርክ::

(4) 4. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ነብዩ ዩሱፍ በልጅነቱ ለአባቱ «አባቴ ሆይ! እኔ አስራ አንድ ኮከቦችን፤ ጨረቃንና ጸሐይን ሲሰግዱልኝ በሕልሜ አየሁኝ።» ባለ ጊዜ የሆነውን ታሪክ ለህዝቦችህ አስታውስ።

(5) 5. አባቱም አለ: «ልጄ ሆይ! ይህን ህልምህን ለወንድሞችህ አትንገር። ባንተ ላይ ተንኮል እንዳያሴሩ። ምክንያቱም ሰይጣን ለሰው ልጅ ሁልጊዜም ግልጽ ጠላት ነውና።

(6) 6. «ጌታህ ልክ ይህን ህልም እንዳሳየህ ሁሉ ለነብይነትም ይመርጥሃል:: የንንግግሮችን ፍፃሜ ያስተምርሃል:: ጸጋውንም ቀደም ሲል ለአባቶችህ ለኢብራሂምና ለኢስሃቅ እንደሞላ ሁሉ ላንተና ለያዕቁብ ቤተሰቦችም ይሞላል:: ጌታህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነውና።»

(7) 7. በዩሱፍና በወንድሞቹ ታሪክ ዉስጥ እውቀትን በመሻት ለሚጠይቁ ሁሉ እያሌ ተዓምራት አሉ::

(8) 8. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ! እንዲህ) ባሉ ጊዜ: «እኛ በቁጥር ብዙዎች ሁነን እያለ ዩሱፍና ወንድሙ (ብንያም) ከአባታችን ዘንድ ከእኛ ይበልጥ ተወዳጆች ናቸው:: በእውነቱ አባታችን ግልጽ ስህተት ውስጥ ነው።

(9) 9. «ዩሱፍን ግደሉት ወይም እሩቅ ቦታ ጣሉት:: ይህን ካረጋችሁ የአባታችሁን ፊት ትኩረትና ውዴታ የራሳችሁ ብቻ ታደርጋላችሁ:: ከዚህ በኋላ ከኃጥያታችሁ በመመለስ መልካም ሰዎች ትሆናለችሁ።

(10) 10. ከእነሱ አንድ ተናጋሪ «ዩሱፍን አትግደሉ ግን በጉድጓድ አዘቅት ጨለማ ውስጥ ጣሉት፤ ከተጓዢዎች አንዱ ያነሳዋልና፡፡ ሠሪዎች ብትኾኑ (በዚሁ ተብቃቁ) አላቸው፡፡

(11) 11. አሉም: «አባታችን ሆይ! በዩሱፍ ጉዳይ እኛ ለእርሱ ቅን አሳቢዎች ሁነን ሳለ ለምን አታምነንም?

(12) 12. «እስቲ ይዝናና ይጫወት ዘንድ ነገ ከእኛ ጋር አብረህ ላከው::እኛም ለእርሱ ጠባቂዎች ነን።»

(13) 13. አባቱም «እርሱን መውሰዳችሁ ያሳዝነኛል። ዘንግታችሁት ተኩላ እንዳይበላዉም እፈራለሁ።» አለ።

(14) 14. እነርሱም «እኛ እንዲህ ጭፍሮች ሆነን ተኩላ ከበላውማ ከሳሪዎቹ እኛ ነን።» አሉ።

(15) 15. እርሱንም ወስደውት በጉድጓድ ወለል ላይ ሊጥሉት በወሰኑ ጊዜ «እነርሱ ሳያውቁ ይህን ጸያፍ ተግባራቸውን ወደ ፊት ትነግራቸዋለህ» የሚል መልዕክት ላክንለት።

(16) 16. አባታቸውንም በምሽት እያለቀሱ መጡት።

(17) 17. «አባታችን ሆይ! እኛ ለሩጫና ለውርወራ ልንሽቀዳደም ሄድን። ዩሱፍንም እቃችን ዘንድ ተውነው:: ወዲያዉም ተኩላ በላው:: አንተም እውነተኞች ብንሆንም የምታምነን አይደለህም።» አሉ።

(18) 18. በቀሚሱም ላይ የውሸትን ደም አመጡ:: አባታቸውም: «ይህ ትክክል አይደለም። ይልቁን ነፍሶቻችሁ ውሸት ነገርን ለናንተ ሸለሙላችሁ:: ስለዚህ መልካም ትዕግስት ማድረግ አለብኝ:: በምትሉትም ነገር ላይ መታገዣው አላህ ብቻ ነው።» አለ።

(19) 19. መንገደኞችም መጡ:: ውሃ ቀጂያቸውንም ላኩ:: አኮሌውንም ወደ ጉድጎዱ ሰደደ:: የምስራች:: «ይህ ልጅ ነው።» አለ:: ሸቀጥ አድርገዉም ደበቁት:: አላህ የሚሠሩትን ሁሉ አዋቂ ነው::

(20) 20. በርካሽ ዋጋና በሚቆጠሩ ዲርሃሞች ሸጡት:: በእርሱም ላይ ከቸልተኞቹ ነበሩ::

(21) 21. ያም ከምስር የገዛው ሰው ለሚስቱ «ይህ ልጅ መኖሪያውን አክብሪ ሊጠቅመን ወይም ልጅ አድርገን ልንይዘው ይከጅላልና።» አላት:: ልክ እንደዚሁ ለዩሱፍ ገዥ ልናደርገውና የሕልሞችንም ፍች ልናስተምረው በምድር ላይ አስመቸነው:: አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ አሸናፊ ነው። ግን አብዛኞቹ ሰዎች ይህን አያውቁም::

(22) 22. ጥንካሬውንም በደረሰ ጊዜ ጥበብንና ዕውቀትን ሰጠነው:: ልክ እንደዚህም መልካም ሠሪዎችን ሁሉ እንመነዳለን::

(23) 23. ያችም እርሱ በቤትዋ የነበረባት ሴት ከነፍሱ አባበለችው:: ደጃፎቹንም ዘጋችና «ይኸው ላንተ ተዘጋጂቼልሃለሁና ቶሎ በል» አለችው:: እሱም «ከዚህ ጸያፍ ተግባር በአላህ እጠበቃለሁ:: እርሱ የገዘኝ ጌታዬ ኑሮዬን ያሳመረልኝ ነውና አልከዳዉም:: እነሆ በደለኞች ሁሉ አይድኑምና» አላት።

(24) 24. በእርሱም በእርግጥ አሰበች፡፡ በእርሷም አሰበ ፡፡የጌታውን ማስረጃ ባላዬ ኖሮ (በእርሷም ባሰበ ነበር) ፡፡ልክ እንደዚሁ መጥፎ ነገርንና ኃጢአትን ከእርሱ ላይ ልንመልስለት አስረጃችንን አሳየነው ፡፡እርሱ ከተጠበቁት ባሮቻችን አንዱ ነዉና ፡፡

(25) 25. እርሱና እርሷ በሩን ተሸቀዳደሙና ቀሚሱን ከኋላው ቀደደችው። ባለቤትዋን እበሩ አጠገብ አገኙት:: እርሷም ቀደም ብላ «በባለቤትህ መጥፎን ያሰበ ሰው ቅጣቱ መታሰር ወይም አሳማሚ ስቃይ እንጂ ሌላ አይደለም።» አለችው።

(26) 26. ዩሱፍም «እርሷ ናት ከነፍሴ ያባበለችኝ።» አለ:: ከቤተሰቦቿም አንድ መስካሪ (እንዲህ) መሰከረ: «ቀሚሱ ከበስተፊት ተቀዶ ከሆነ እርሷ እውነት ተናገረች:: እርሱ ከውሸታሞቹ አንዱ ነው።

(27) 27. «ቀሚሱም ከበስተኋላው ተቀዶ እንደሆነ ዋሸች:: እርሱም ከእውነተኞቹ ነው።»

(28) 28. ቀሚሱንም ከበስተኋላ ተቀዶ ባየ ጊዜ አለ: «እርሱ የተናገርሽው ከተንኮላችሁ ነው። የእንናንተ የሴቶች ተንኮል በእርግጥ ብርቱ ነው።

(29) 29. «ዩሱፍ ሆይ! አንተም ከዚህ ወሬ ተከልከል:: አንቺም ለኃጢአትሽ ማርታን ለምኝ። አንቺ ከስሕተተኞቹ ሆነሻልና።» አለ::

(30) 30. በከተማው ያሉ ሴቶችም «የዐዚዝ ሚስት ሰራተኛዋን ከነፍሱ ታባብለዋለች:: በእውነቱ ፍቅሩ ልቧን መቷታል:: እኛ በግልጽ ስሕተት ውስጥ ሆና በእርግጥ እናያታለን።» አሉ።

(31) 31. እርሷም ሐሜታቸውን በሰማች ጊዜ ወደነሱ ላከችባቸው:: ግብዣንም ለእነርሱ አዘጋጀችላቸው:: ለያንዳንዳቸዉም ቢላዋን ሰጠችና «በእነርሱም ላይ ውጣ።» አለችው:: እነርሱም በተመለከቱት ጊዜ በጣም አደነቁት:: እጆቻቸዉንም ቆረጡ። «ለአላህ ጥራት ይገባው:: ይህ ሰው አይደለም:: ይህ የተከበረ መልአክ እንጂ ሌላ አይደለም።» አሉ።

(32) 32. በዚህ ጊዜ «ይህ እኮ ነው ያ በእርሱ ፍቅር ያማችሁኝ ሰው:: በእርግጥም ከነፍሱ አባባልኩት ግና እርሱ እንቢ አለ:: ወደፊትም የማዘውን ነገር ባይሠራ በእርግጥ ይታሰራል ከወራዶቹም ይሆናል።» አለች።

(33) 33. «ጌታዬ ሆይ! ወደ እርሱ ከሚጠሩኝ ነገር (ከዝሙት) ይልቅ መታሰር ለእኔ የተወደደ ነው:: ተንኮላቸውንም ከእኔ ላይ ባትመልስልኝ ወደ እነርሱ እዘነበላለሁ:: ከስሕተተኞቹም እሆናለሁ።» አለ።

(34) 34. ጌታዉም ጸሎቱን ተቀበለው፤ ተንኮላቸውንም ከእርሱ መለሰለት:: እነሆ እርሱ ሁሉን ሰሚና ሁሉን አዋቂ ነውና።

(35) 35. ከዚያም ማስረጃዎችን ካዩ በኋላ እስከ ጊዜ ድረስ እንዲያስሩት ለእነርሱ ታያቸው::

(36) 36. ከእሱም ጋር ሁለት ወጣቶች እስር ቤቱ ገቡ:: አንደኛቸው «እኔ በሕልሜ የወይን ጠጅን ስጠምቅ አየሁ።» አለ:: ሌላው ደግሞ «እኔ በራሴ ላይ ቂጣን ተሸክሜ ከእሱ በራሪ አሞራ ስትበላ አየሁ ፍችውን ንገረን እኛ ከአሳማሪዎች ሁነህ እናይሃለንና።» አሉት።

(37) 37. ዩሱፍም አለ: «ማንኛዉም የምትሰጡት ምግብ ለእናንተ ከመምጣቱ በፊት ፍችውን የምነግራችሁ ቢሆን እንጂ አይመጣላችሁም:: ይህ ጉዳይ ጌታዬ ካሳወቀኝ ነገር ነው:: እኔም በአላህ የማያምኑትንና በመጨረሻይቱ ዓለም ከሓዲያን የሆኑ ሕዝቦችን ሃይማኖት ትቻለሁ::

(38) 38. «የአባቶቼንም የኢብራሂምን፤ የኢስሐቅንና የያዕቁብን ሃይማኖት ተከትያለሁ:: ለእኛ በአላህ ምንንም ማጋራት አይገባንም:: ያ አለማጋራት በእኛ ላይና በሰዎች ላይ የአላህ ችሮታ ነው:: ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያመሰግኑም::

(39) 39. «የእስር ቤት ጓደኞቼ ሆይ! የተለያዩ አምላኮች ይሻላሉን ወይስ አሸናፊውና አንዱ አላህ?

(40) 40. «ከእርሱ ሌላ እናንተና አባቶቻችሁ አማልክት ብላችሁ የጠራችኋቸውን ስሞች እንጂ አትገዙም። አላህ በእርሷ ምንም አስረጂ አላወረደም። ፍርዱ የአላህ እንጂ ሌላ አይደለም:: እርሱን እንጂ ሌላን እንዳትገዙም አዟል:: ይህ ትክክለኛው ሃይማኖት ነው:: ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም::

(41) 41. «የአስር ቤት ጓደኞቼ ሆይ! አንደኛችሁማ ንጉሡን ጠጅ ያጠጣል። ሌላውም ይሰቀላል:: ከራሱም በራሪ አሞራ ትበላለች:: ያ ፍቹን የምትጠይቁት ነገር ተፈጸመ።» አላቸው።

(42) 42. ለዚያም ከሁለቱ እርሱ የሚድን መሆኑን ለተጠራጠረው እጌታህ ዘንድ አስታውሰኝ አለው፡፡ ጌታውንም ከማስታወስ ሰይጣን አስረሳው፡፡ ለጥቂት ዓመታትም በወህኒ ቤቱ ውስጥ ቆየ፡፡

(43) 43. ንጉሡም «እኔ ሰባት የሰቡ ላሞችን ሰባት የከሱ ላሞች ሲበሉዋቸው፤ ሰባት ለምለም ዘለላዎችም ሌሎች ሰባት ደረቆችን ስብርብር ሲያደርጉ በሕልሜ አየሁ:: እናንተ ታላላቅ ሰዎች ሆይ! ሕልም መፍታት የምታውቁ ከሆናችሁ ሕልሜን ፍቱልኝ።» አላቸው።

(44) 44. «ሕልሞችህ ቅዠቶች ናቸው:: እኛም የሕልሞችን ፍች አዋቂዎች አይደለንም።» አሉት።

(45) 45. ያም ከሁለቱ መካከል የዳነውና ከብዙ ጊዜ በኋላ ዩሱፍን ያስታወሰው ሰው «እኔ ፍቹን እነግራችኋለሁና ላኩኝ።» አለ።

(46) 46. «አንተ እውነተኛው ዩሱፍ ሆይ! ሰባትን የሰቡ ላሞች ሰባት ከሲታዎች ላሞች ሲበሏቸው፤ ሰባትን ለምለም ዘለላዎችም ሌሎች ሰባት ደረቆች በእነርሱ ላይ ስብርብር ሲያደርጉ ያየን ሰው ሕልም ፍች እስቲ ተችልን:: ያውቁ ዘንድ ወደ ሰዎቹ ልመለስ እከጅላለሁና።» አለው።

(47) 47. እርሱም አለ: «ሰባትን የተከታተሉ ዓመታት ትዘራላችሁ ያጨዳችሁትንም ሁሉ ከምትበሉት ጥቂት በስተቀር በዘለላው ውስጥ ተውት።

(48) 48. «ከዚያም ከነዚያ በኋላ ካደለባችሁት ጥቂት ሲቀር ለእነርሱ ያደለባችሁትን ሁሉ የሚበሉ ሰባት የችግር ዓመታት ይመጣሉ።

(49) 49. «ከዚያ ከእነዚያ በኋላ ሰዎቹ በእርሱ ዝናብ የሚያገኙበትና በእርሱም ወይንን የሚጨምቁበት ዓመት ይመጣል።»

(50) 50. ንጉሡም «እርሱን አምጡልኝ።» አለ። መልእክተኛዉም ወደ ዩሱፍ በመጣ ጊዜ ዩሱፍ: «ወደ ጌታህ ተመለስና የእነዚያን እጆቻቸውን የቆረጡትን ሴቶች ሁኔታ ጠይቀው ጌታዬ ተንኮላቸውን አዋቂ ነውና።» አለው።

(51) 51. ንጉሡም «ዩሱፍን ከነፍሱ ባባበላችሁት ጊዜ ነገራችሁ ምንድን ነው?» አላቸው። «ለአላህ ጥራት ይገባው በእርሱ ላይ ምንም መጥፎን ነገር አላወቅንም (አላየንም)።» አሉት። የዐዚዝ ሚስትም አለች: «አሁን እውነቱ ተገለጸ እኔ አባበልኩት እርሱም ከእውነተኞቹ ነው።

(52) 52. «ይህ ጌታዬ ሩቅ ሆኖ ሳለ ያልከዳሁት መሆኔንና አላህም የከዳተኞችን ተንኮል የማያቃና መሆኑን እንዲያውቅ ነው።»

(53) 53. «ነፍሴንም ከስሕተት አላጠራም:: ነፍስ ሁሉ ጌታዬ ያዘነላት (የጠበቃት) ካልሆነች በስተቀር በመጥፎ ነገር በእርግጥ አዛዥ ናትና:: ጌታዬ በጣም መሐሪና አዛኝ ነው።»

(54) 54. ንጉሡም «እርሱን አምጡልኝ ለራሴ የግሌ አደርገዋለሁና።» አለ። ባናገረዉም ጊዜ «አንተ ዛሬ እኛ ዘንድ ባለሟልና ታማኝ ነህ።» አለው።

(55) 55. «በምድር ግምጃ ቤቶች ላይ ሹም አድርገኝ እኔ ጠባቂ አዋቂ ነኝና።» አለ።

(56) 56. እንደዚሁም ለዩሱፍ በምድር ላይ ከእርሷ በፈለገው ስፍራ የሚሰፍር ሲሆን አስመቸነው:: በችሮታችን የምንሻውን ሰው እንለያለን። የበጎ ሠሪዎችንም ዋጋ አናጠፋም።

(57) 57. የመጨረሻይቱም ዓለም ምንዳ ለእነዚያ ላመኑትና ይጠነቀቁ ለነበሩት የበለጠ ነው::

(58) 58. የዩሱፍ ወንድሞችም መጡ በእርሱም ላይ ገቡ:: እነርሱም እርሱን የሳቱት ሲሆኑ አወቃቸው::

(59) 59. ጉዳያቸውን ፈጽሞ ስንቃቸውንም ባዘጋጀላቸው ጊዜ አለ: «ከአባታችሁ በኩል የሆነውን ወንድማችሁን አምጡልኝ እኔ ከአስተናጋጆች ሁሉ በላጭ ስሆን ስፍርን የምሞላ መሆኔን አታዩምን?

(60) 60. «እርሱንም ባታመጡልኝ። እኔ ዘንድ ለእናንተ ስፍር የላችሁም:: አትቀርቡኝምም።» አለ

(61) 61. «ስለ እርሱ አባቱን በጥብቅ እንጠይቃለን፤ እኛም ይህንን በእርግጥ ሰሪዎች ነን።» አሉት።

(62) 62. ለአሽከሮቹም፡- «ወደ ቤተሰቦቻቸው በተመለሱ ጊዜ ሸቀጣቸውን (ገንዘባቸውን) ያውቋት ዘንድ በየጓዞቻቸው ውስጥ አድርጉላቸው ሊመለሱ ይከጀላልና።» አላቸው።

(63) 63. ወደ አባታቸዉም በተመለሱ ጊዜ፡- «አባታችን ሆይ! (ወንድማችንን እስከምንወስድ) ስፍር ከኛ ተከልክሏል። ስለዚህ ወንድማችንን ከእኛ ጋር ላከው፤ ይሰፈርልናልና እኛም ለእርሱ ጠባቂዎች ነን።» አሉ::

(64) 64. «ከአሁን በፊት በወንድሙ ላይ እንዳመንኳችሁ እንጂ በእርሱ ላይ አምናችኋለሁን? አላህም በጠባቂነት ከሁሉ የበለጠ ነው:: እርሱም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነው።» አላቸው።

(65) 65. እቃቸውንም በከፈቱ ጊዜ ሸቀጣቸውን ወደ እነርሱ ተመልሶ አገኙት። «አባታችን ሆይ! ምን እንፈልጋለን? ይህች ሸቀጣችን ናት ወደ እኛ ተመልሳልናለች እንረዳባታለን:: ለቤተሰቦቻችንም እንሸምታለን። ወንድማችንንም እንጠብቃለን:: የአንድ ግመልን ጭነትም እንጨምራለን:: ይህ በንጉሱ ላይ ቀላል ስፍር ነው።» አሉ።

(66) 66. «ካልተከበባችሁ በስተቀር እርሱን በእርግጥ የምታመጡልኝ ለመሆናችሁ ከአላህ የሆነን ቃልኪዳን (መተማመኛ) እስከምትሰጡኝ ድረስ ከናንተ ጋር ፈጽሞ አልከዉም።» አላቸው። መተማመኛቸውንም በሰጡ ጊዜ «አላህ በምንለው ሁሉ ላይ ዋስ ነው።» አላቸው።

(67) 67. አለም፡- «ልጆቼ ሆይ! በአንድ በር አትግቡ:: ግን በተለያዩ በሮች ግቡ:: ከአላህም ፍርድ በምንም አልጠቅማችሁም (አልመልስላችሁም)። ፍርዱ የአላህ እንጂ የሌላ አይደለም:: በእርሱ ላይ ብቻ ተመካሁ:: ተመኪዎችም ሁሉ በእርሱ ላይ ብቻ ይመኩ።»

(68) 68. አባታቸው ካዘዛቸው ስፍራ በገቡ ጊዜ ከአላህ ፍርድ ምንም ነገር ከእነርሱ የሚከለክልላቸው አልነበረም:: ግን በየዕቁብ ነፍስ ውስጥ የነበረች ጉዳይ ናት:: ፈጸማት። እርሱም ስላሳወቅነው የእውቀት ባለቤት ነው። ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም::

(69) 69. በዩሱፍ ላይ በገቡ ጊዜም ወንድሙን ወደ እርሱ አስጠጋውና «እነሆ እኔ ወንድምህ ነኝ:: ይሰሩት በነበሩትም ሁሉ አትበሳጭ።» አለው።

(70) 70. እቃቸውን ባዘጋጀላቸው ጊዜ ዋንጫይቱን በወንድሙ እቃ ውስጥ አደረገና ከዚያ «እናንተ ባለ ግመሎች ሆይ! እናንተ በእርግጥ ሌቦች ናችሁ።» ሲል ጠሪ ተጣራ።

(71) 71. ወደ እነርሱ ዞረዉም: «ምንድን ጠፋችሁ?» አሉ።

(72) 72. «የንጉሱ መስፈሪያ ጠፍቶናል እርሱንም ላመጣ ሰው የአንድ ግመል ጭነት አለው። እኔም በእርሱ ተያዥ ነኝ።» አለ።

(73) 73. «በአላህ እንምላለን! በምድር ላይ ለማጥፋት እንዳልመጣን በእርግጥ አውቃችኋል ሌቦችም አልነበርንም።» አሉ።

(74) 74. «ውሸታሞች ብትሆኑስ ቅጣቱ ምንድን ነው?» አሏቸው።

(75) 75. «ቅጣቱ በየዕቁብ ሕግ እቃው በጓዙ ውስጥ የተገኘበት ሰው ራሱ ባሪያ ተደርጎ መውሰድ ነው። እርሱም ቅጣቱ ነው:: ልክ እንደዚሁ በደለኞችን እንቀጣለን።» አሉ።

(76) 76. ምርመራውን ከወንድሙ እቃ በፊትም በእቃዎቻቸው ጀመረ:: ከዚያ ዋንጫይቱን ከወንድሙ እቃ ውስጥ አወጣት። ልክ እንደዚሁ ለዩሱፍ ብልሃትን አስተማርነው:: አላህ ባልሻ ኖሮ በንጉሱ ሕግ ወንድሙን ሊይዝ አይገባዉም ነበር:: የምንሻውን ሰው በደረጃዎች ከፍ እናደርጋለን። ከእውቀት ባለቤቶች ሁሉ በላይም አዋቂ አለ::

(77) 77. «እርሱ ቢሰርቅ ከአሁን በፊት የእርሱው ወንድም በእርግጥ ሰርቋል።» አሉ። ዩሱፍም ይህችን (አስቀያሚ ንግግር) በነፍሱ ውስጥ ደበቃት:: ለእነርሱም አልገለጣትም። በልቡ «እናንተ ሥራችሁ የከፋ ነው:: አላህ የምትሉትን ሁሉ ይበልጥ አዋቂ ነው።» አለ።

(78) 78. «አንተ የተከበርከው ሆይ! ለእርሱ በእርግጥ ታላቅ ሽማግሌ አባት አለው:: ስለዚህ በእርሱ ስፍራ አንደኛችንን ያዝ:: እኛ ከመልካም ሠሪዎች ሆነህ እናይሃለንና።» አሉት።

(79) 79. «ዕቃችንን እርሱ ዘንድ ያገኘንበትን ሰው እንጂ ሌላን ከመያዝ በአላህ እንጠበቃለን:: እኛ ያን ባደረግን ጊዜ በእርግጥ በዳዮች ነን።» አለ።

(80) 80. ከእርሱም ተስፋን በቆረጡ ጊዜ የሚመካከሩ ሆነው ገለል አሉ:: ታላቃቸውም አለ: «አባታችሁ በእናንተ ላይ ከአላህ የሆነን መተማመኛ ቃል ኪዳን በእርግጥ የያዘባችሁ መሆኑንና ከዚህም በፊት በዩሱፍ ላይ ግፍ የሠራችሁትን አታውቁምን? ስለዚህ አባቴ ለእኔ እስከሚፈቅድልኝ ወይም አላህ ለእኔ እስከሚፈርድልኝ ድረስ የምስርን (የግብጽን) ምድር አልለይም:: እርሱ ከፈራጆች ሁሉ በላጭ ነው።

(81) 81. «ወደ አባታችሁ ተመለሱ:: በሉትም: ‹አባታችን ሆይ ልጅህ ሰረቀ፤ ባወቅነዉም ነገር እንጂ አልመሰከርንም:: ሩቁንም ነገር ምስጢሩን አዋቂዎች አልነበርንም።

(82) 82. «‹ያችንም በውስጧ የነበርንባትን ከተማ ያችንም በውስጧ የመጣነውን ባለ ግመል ጓድ ጠይቅ እኛም በእርግጥ እውነተኞች ነን።›»

(83) 83. ያዕቁብም፡- «አይደለም። ነፍሶቻችሁ አንዳች ነገርን ለእናንተ ሸለሙላቸሁና ሠራችሁት እንጂ:: እናም መልካም ትዕግስት ማድረግ አለብኝ:: እነርሱን ሁሉንም የተሰበሰቡ ሆነው አላህ ሊያመጣልኝ ይከጀላል:: እነሆ እርሱ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነውና።» አላቸው።

(84) 84. ከነርሱም ዞር አለና፡- «በዩሱፍ ላይ ዋ ሐዘኔ!» አለ:: ዓይኖቹም ከሐዘን የተነሳ ነጡ:: እርሱም በትካዜ የተሞላ ነው።

(85) 85. እነርሱም፡- «በአላህ እንምላለን! ለጥፋት የቀረብክ እስከምትሆን ወይም ከጠፊዎቹ እስከምትሆን ድረስ ዩሱፍን ከማውሳት አትወገድም።» አሉ።

(86) 86. «ጭንቀቴንና ሐዘኔን የማሰሙተው ወደ አላህ ብቻ ነው። ከአላህ በኩል የማታውቁትን ነገር እኔ አውቃለሁና።» አላቸው።

(87) 87. «ልጆቼ ሆይ! ሂዱ ከዩሱፍና ከወንድሙም ወሬ ተመራመሩ:: ከአላህም እዝነት ተስፋ አትቁረጡ:: እነሆ ከአላህ እዝነት ከሓዲያን ህዝቦች እንጂ ማንም ተስፋ አይቆርጥም።» አለ።

(88) 88. በእርሱም ላይ በገቡ ጊዜ: «አንተ የተከበርከው ሆይ! እኛንም ቤተሰቦቻችንንም ጉዳት ደረሰብን። እርካሽ ሸቀጥም ይዘን መጥተናል:: ስፍርንም ለእኛ ሙላልን:: በእኛም ላይ መጽውት:: አላህ መጽዋቾችን ይመነዳልና።» አሉት።

(89) 89. «እናንተ የማታውቁ በነበራችሁ ጊዜ በዩሱፍና በወንድሙ ላይ የሠራችሁትን ግፍ አወቃችሁን?» አላቸው።

(90) 90. «አንተ በእርግጥ አንተ ዩሱፍ ነህን?» አሉት። «አዎ እኔ በትክክል ዩሱፍ ነኝ:: ይህም ወንድሜ ነው:: አላህ በእኛ ላይ በእርግጥ ለገሰልን:: እነሆ የሚጠነቀቅና የሚታገስ ሰው አላህ ይክሰዋል:: አላህ የበጎ አድራጊዎችን ዋጋ አያጠፋምና።» አለ።

(91) 91. «በአላህ እንምላለን! አላህ በእኛ ላይ በእርግጥ አበለጠህ፤ እኛም በእርግጥ አጥፊዎች ነበርን።» አሉ::

(92) 92. እርሱም አላቸው: «ዛሬ በእናንተ ላይ ምንም ወቀሳ የለባችሁም። አላህ ለእናንተ ይምራል። እርሱም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነውና።»

(93) 93. «ይህንን ቀሚሴን ይዛችሁ ሂዱ:: በአባቴ ፊትም ጣሉት:: የሚያይ ሆኖ ይመጣልና:: ቤተሰቦቻችሁንም በሙሉ ሰብስባችሁ አምጡልኝ።» አላቸው።

(94) 94. ግመል ጫኞችም ከግብጽ በወጡ ጊዜ አባታቸው «እኔ የዩሱፍን ሽታ በእርግጥ አገኛለሁ:: ባታቄሉኝ ኖሮ ታምኑኝ ነበር።» አለ።

(95) 95. «በአላህ እንምላለን! አንተ በእርግጥ እስካሁንም በዚያው በቀድሞው ስህተትህ ውስጥ ነህ።» አሉት።

(96) 96. አብሳሪዉም በመጣ ጊዜ ቀሚሱን በፊቱ ላይ ጣለው፤ ወዲያዉም የሚያይ ሆነ:: «እኔ ለእናንተ ከአላህ በኩል የማታውቁትን አውቃለሁ አላልኳችሁም ነበርን?» አላቸው።

(97) 97. «አባታችን ሆይ! ለኃጢያቶቻችን ምሕረትን ለምንልን:: እኛ ጥፋተኞች ነበርንና።» አሉ::

(98) 98. «ወደ ፊት ለእናንተ ጌታዬን ምሕረትን እለምንላችኋለሁ:: እነሆ እርሱ መሓሪ አዛኝ ነውና።» አላቸው።

(99) 99. በዩሱፍ ላይም በገቡ ጊዜ ወላጆቹን ወደ እርሱ አስጠጋቸው፤ «በአላህም ፈቃድ ጥብቆች ስትሆኑ ሚስርን (ግብጽ) ግቡ።» አላቸው::

(100) 100. ወላጆቹንም በዙፋኑ ላይ አወጣቸው ለርሱም ሰጋጆች ሆነው ወረዱለት። «አባቴም ሆይ! ይህ ፊት ያየኋት ሕልሜ ፍች ነው፡፡ ጌታዬ በእርግጥ እውነት አደረጋት፡፡ ከወህኒ ቤትም ባወጣኝና ሰይጣንም በእኔና በወንድሞቼ መካከል ካበላሸ በኋላ እናንተን ከገጠር ባመጣችሁ ጊዜ በእርግጥ ለእኔ መልካም ዋለልኝ:: ጌታዬ ለሚሻው ነገር እዝነቱ ረቂቅ ነው:: እነሆ እርሱ አዋቂውና ጥበበኛው ነው።» አለ።

(101) 101. «ጌታዬ ሆይ! ከንግስና በእርግጥ ሰጠኸኝ:: ከህልሞችም ፍች አስተማርከኝ:: የሰማያትና የምድር ፈጣሪ ሆይ! አንተ በቅርቢቱና በመጨረሻይቱ ዓለም ረዳቴ ነህ:: ሙስሊም ሆኜ ግደለኝ:: ወደ መልካም ሰሪዎችም አስጠጋኝ።» አለ።

(102) 102. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ይህ ወደ አንተ የምናወርደው ሲሆን ከሩቅ ወሬዎች ነው:: አንተም እነርሱ በዩሱፍ ላይ የሚያሴሩ ሆነው ነገራቸውን በቆረጡ ጊዜ እነርሱ ዘንድ አብረህ አልነበርክም::

(103) 103. አብዛኛዎቹ ሰዎች ለማመናቸው ብትጓጓም የሚያምኑ አይደሉም::

(104) 104. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በቁርኣን ላይ ምንም ዋጋን አትጠይቃቸዉም:: እርሱ ለዓለማት ግሳጼ እንጂ ሌላ አይደለም::

(105) 105. በሰማያትና በምድር ካለችው ምልክት ብዙይቱ እነርሱ ከእርሷ ዘንጊዎች ሆነው በእርሷ ላይ ያልፋሉ::

(106) 106. አብዛኞቻቸዉም እነርሱ አጋሪዎች ሆነው እንጂ በአላህ አያምኑም::

(107) 107. ከአላህ ቅጣት ሽፋኝ አደጋ የምትመጣባቸው ወይም ሰዓቲቱ እነርሱ የማያውቁ ሲሆኑ በድንገት የምትመጣባቸው መሆኑዋን አይፈሩምን?

(108) 108. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ይህ መንገዴ ነው:: ወደ አላህ እጠራለሁ:: እኔም የተከተለኝም ሰው በግልጽ ማስረጃ ላይ ነን:: ጥራትም ለአላህ ብቻ ይገባው:: እኔም ከአጋሪዎች አይደለሁም።» በል::

(109) 109. ካንተ በፊትም ከከተሞች ሰዎች ወደነርሱ ራዕይ የምናወርድላቸው የሆኑን ወንዶችን እንጂ አላክንም:: በምድር ላይ አይሄዱምና የእነዚያን ከእነርሱ በፊት የነበሩትን ሰዎች መጨረሻ እንዴት እንደሆነ አይመለከቱምን? የአኺራ ደስታ ለተጠነቀቁት ሰዎች ሁሉ በእርግጥ የተሻለች ናት:: አታውቁምን?

(110) 110. መልዕክተኞች ተስፋ በቆረጡና እነርሱ በእርግጥ የተዋሹ መሆናቸውን በተጠራጠሩ ጊዜ እርዳታችን መጣላቸው:: ከዚያ እኛ የምንፈልገው ሰው እንዲድን ተደረገ:: ቅጣታችንም ከአመፀኞቹ ህዝቦች ላይ አይመለስም::

(111) 111. በታሪካቸው ውስጥ ለአዕምሮ ባለቤቶች ሁሉ በእርግጥ መገሰጫ ነበረ:: ይህ ቁርኣን የሚቀጣጥፍ ወሬ አይደለም:: ይልቁንም ያንን በስተፊቱ ያለውን አረጋጋጭ፤ ሁሉን ጉዳዮች ገላጭና ለሚያምኑ ህዝቦችም ሁሉ መሪ፤ ችሮታ ነው::