19 - Maryam ()

|

(1) 1. ካፍ፤ ሃ፤ ያ፤ ዐይን፤ ሷድ፤

(2) 2. ይህ ጌታህ ባርያውን ዘከሪያን በችሮታው ያወሳበት ነው::

(3) 3. ጌታውን የሚስጢርን ጥሪ በተጣራ ጊዜ የሆነውን አስታውስ::

(4) 4. (እንዲህም) አለ: «ጌታዬ ሆይ! እኔ አጥንቴም ደከመ:: ራሴም በሽበት ተንቀለቀለ። ጌታዬ ሆይ! አንተንም በመለመኔ፤ ምንጊዜም ዕድለ ቢስ እልሆንኩም።

(5) 5. «እኔም ከበኋላዬ (ከሞትኩ በኋላ) ዘመዶቼን (ከእምነት እንዳይወጡ) ፈራሁ:: ሚስቴም መካን ነበረች:: ስለዚህ ካንተ ዘንድ ለእኔ ልጅን ስጠኝ::

(6) 6. «የሚወርሰኝ ከየዕቁብ ቤተሰቦችም የእምነትን ሃላፊነት የሚወርስን ልጅ ስጠኝ:: ጌታዬ ሆይ! ተወዳጅም አድርገው።» አለ።

(7) 7. «ዘከሪያ ሆይ! እኛ ስሙ የሕያ በሆነና ከዚያ በፊት ሞክሼን ባላደረግንለት ወንድ ልጅ እናበስርሃለን።» አለው።

(8) 8. «ጌታዬ ሆይ! ሚስቴ መካን እኔም ከእርጅና የተነሳ ድርቀትን የደረስኩ ስሆን እንዴት ልጅ ይኖረኛል?» አለ።

(9) 9. (ጅብሪልም) አለ: «ነገሩ ልክ እንደዚሁ ነው። ጌታህ ‹ከዚህ በፊት ምንም ያልነበርከውን የፈጠርኩህ ስሆን እርሱ በእኔ ላይ ቀላል ነው።› ብሏል።»

(10) 10. እርሱም «ጌታዬ ሆይ! እንግዲያውስ ምልክት አድርግልኝ።» አለ። «ምልክትህ (ጤናማ ሆነህ ሳለህ) ሶስት ሌሊት ከነቀናቸው ሰዎችን ማነጋገር አለመቻልህ ነው።» አለው።

(11) 11. እርሱም ከምኩራቡ ወደ ህዝቦቹ ወጣ:: ጧትና ማታ ጌታችሁን አውሱ አጥሩትም በማለትም ወደ እነርሱ ጠቀሰ።

(12) 12. «የሕያ ሆይ! መጽሐፉን በጥብቅ ያዝ።» አልነው:: ጥበብንም በሕጻንነቱ ሰጠነው።

(13) 13. ከእኛም የሆነን ርህራሄና ንጽህናንም (ሰጠነው):: ጥንቁቅም ነበር::

(14) 14. ለወላጆቹም በጎ ሠሪ ነበር:: ትዕቢተኛና አመጸኛም አልነበረም::

(15) 15. በተወለደበት ቀንና በሚሞትበት ቀን ህያው ሆኖ በሚነሳበትም ቀን ሰላም በእሱ ላይ ይሁን ::

(16) 16. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) መርየም ከቤተሰቧ ወደ ምስራቃዊ ስፍራ በተለየች ጊዜ የሆነውን ታሪኳን በመጽሐፉ ውስጥ አውሳ::

(17) 17. ከእነርሱም መጋረጃን አደረገች:: መንፈሳችንንም (መልዐኩ ጂብሪልን) ወደ እርሷ ላክን:: ለእርሷም ትክክለኛ ሰው ሆኖ ተመሰለላት::

(18) 18. «ካንተ በአር-ረህማን እጠበቃለሁ። ጌታህን ፈሪ ከሆንክ (አትቅረበኝ)።» አለች።

(19) 19. «እኔ ንጹሕ የሆነን ልጅ ላንቺ ልሰጥ የመጣሁ የጌታሽ መልዕክተኛ ነኝ።» አላት።

(20) 20. «በጋብቻ አንድም ሰው ያልነካኝ ሆኜ አመንዝራ ዝሙትኛ ሳልሆን ለእኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል!» አለች።

(21) 21. (መልአኩም) «ነገሩ ልክ እንደዚሁ ነው የሚፈጸመው። ጌታሽ ‹እርሱ በእኔ ላይ ገር ነው:: ለሰዎችም ተዓምር ከእኛም ችሮታ ልናደርገው ይህንን ሰራን፤ ነገሩ የተወሰነም ነው።› ብሏል።» አለ።

(22) 22. ወዲያውኑም አረገዘችው:: እርሱንም በሆድዋ ይዛው ወደ ሩቅ ስፍራ ገለል አለች::

(23) 23. ምጡ ወደ ዘንባባይቱ ግንድ አስጠጋት:: እርሷም «ወይኔ! ምነው ከዚህ በፊት በሞትኩና የተረሳሁ በሆንኩ።» አለች።

(24) 24. ከበታቿም እንዲህ ሲል ጠራት: «አትዘኝ። ጌታሽ ከበታችሽ ትንሽን ወንዝ በእርግጥ አድርጓልና።

(25) 25. «የዘምባባይቱን ግንድ ወደ አንቺ ወዝውዢው:: በአንቺ ላይ የበሰለን የተምር እሸት ያረግፍልሻልና።

(26) 26. «ብይ፤ ጠጭም። ተደሰችም ከሰዎች አንድንም ብታይ እኔ ለአዛኙ አምላክ ዝምታን ተስያለሁ:: እናም ዛሬ ማንንም ሰው በፍጹም አላነጋግርም በይ።» አላት።

(27) 27. እርሱን ተሸክማው ወደ ዘመዶቿ መጣች (እንዲህም) አሏት: «መርየም ሆይ! ከባድ ነገርን በእርግጥ ፈጸምሽ።

(28) 28. «አንቺ የሃሩን እህት ሆይ! አባትሽ መጥፎ ሰው አልነበረም:: እናትሽም አመንዝራ ዝሙተኛ አልነበረችም።» አሏት።

(29) 29. እርሷም ወደ ህፃኑ አመለከተች:: እነርሱም «በአንቀልባ ያለን ህፃን እንዴት እናናግራለን?» አሉ።

(30) 30. ህፃኑም አለ: «እኔ የአላህ አገልጋይ ነኝ፤ መጽሐፍን ሰጥቶኛል። ነብይም አድርጎኛል።

(31) 31. «በየትም ስፍራ ብሆን የተባረኩኝ አድርጎኛል። በህይወትም እስካለሁ ሶላትንና ዘካን አዞኛል።

(32) 32. «ለእናቴም ታዛዥ አድርጎኛል:: ትዕቢተኛ እድለቢስ አላደረገኝም።

(33) 33. «በተወለድሁበት ቀን በምሞትበት ቀንና ሕያው ሆኜ በምቀሰቀስበትም ቀን ሰላም በእኔ ላይ ይስፈን።» አለ።

(34) 34. የመርየም ልጅ ዒሳ ይሀው ነው፤ ያ በእርሱ የሚጠራጠሩበት እውነተኛ ቃል ይህ ነው።

(35) 35. ለአላህ ልጅን መያዝ አይገባዉም:: ከጉድለት ሁሉ ጠራ:: አንድን ነገር በወሰነ ጊዜ ለእርሱ የሚለው «ሁን» ብቻ ነው:: ወዲያዉም ይሆናል።

(36) 36. ዒሳ ለህዝቦቹ «አላህ የእኔም ጌታዬ የእናንተም ጌታችሁ ነውና ተገዙት:: ይህ ቀጥተኛው መንገድ ነው።» አለ።

(37) 37. ከመካከላቸዉም አንጃዎች በእርሱ ነገር ላይ ተለያዩ:: ለእነዚያም ለካዱት ሰዎች ከታላቁ ቀን መጋፈጥ ክስተት ወዮላቸው::

(38) 38. ወደ እኛ በሚመጡ ቀን ምን ያህል ሰሚ ምን ያህል ተመልካች አደረጋቸው:: ግን አመጸኞች በዳዮች ዛሬ በዚህች ዓለም በግልጽ ስህተትና ጥመት ውስጥ ናቸው::

(39) 39. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በሚፈረድበት ጊዜ የቁጭትን ቀን አስፈራራቸው እነርሱ አሁን በመዘንጋት ላይ ናቸው:: እነርሱ አያምኑምና::

(40) 40. ምድርንና በእርሷም ላይ ያለውን ፍጡር ሁሉ እኛ እንወርሳለን:: ወደ እኛም ይመለሳሉ::

(41) 41. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በመጽሐፉ ውስጥ ኢብራሂምን አውሳ:: እርሱም በጣም እውነተኛ ነብይ ነበርና::

(42) 42. ለአባቱ (እንዲህ) ባለው ጊዜ የሆነውን አስታውስ: «አባቴ ሆይ! የማይሰማንና የማያይን ላንተም ምንንም የማይጠቅምህን (የማይፈይድህን) ጣዖት ለምን ታመልካለህን?

(43) 43. «አባቴ ሆይ! እኔ አንተ ያልደረሰህን እውቀት መጥቶልኛልና ተከተለኝ:: ቀጥተኛውን መንገድ እመራሃለሁና።

(44) 44. «አባቴ ሆይ! ሰይጣንን አትገዛ \አታምልክ\:: ሰይጣን ለአር-ረህማን አመጸኛ ነውና።

(45) 45. «አባቴ ሆይ! እኔ የአር-ረህማን ቅጣት ሊያገኝህ እና ከዚያ የሰይጣን ጓደኛ ልትሆን እፈራለሁ:

(46) 46. አባቱም «ኢብራሂም ሆይ! አንተ አምላኮቼን ትተህ የምትዞር ነህን? ከዚህ ተግባርህ ባትከለከል በእርግጥ እወግርሃለሁ:: ረዥም ጊዜንም ተወኝ።» አለ።

(47) 47. ኢብራሂምም አለ: «ደህና ሁን (ሰላም ላንተ ይሁን):: ከጌታዬ ምህረትን እለምንልሃለሁ:: እርሱ ለእኔ በጣም ሩህሩህ ነውና።

(48) 48. «እናንተንና ከአላህ ሌላ የምትገዙትን ሁሉ እርቃለሁ:: ጌታዬንም ብቻ እገዛለሁ፤ ጌታዬን በመገዛት የማፍር አለመሆኔን እከጅላለሁ (ተስፋ አደርጋለሁ)።» አለ።

(49) 49. እነርሱንና ከአላህ ሌላ የሚገዙትን በራቀ ጊዜ ኢስሐቅንና የዕቁብን ሰጠነው:: ሁለቱንም ነብይ አደረግናቸው::

(50) 50. ለእነርሱም ከችሮታችን ሰጠናቸው:: ለእነርሱም ከፍ ያለ ምስጉን ዝናን አደረግንላቸው::

(51) 51. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በመጽሐፉ ውስጥ ሙሳን አውሳ:: እርሱ ምርጥ ነበርና:: መልዕክተኛ ነብይም ነበርና::

(52) 52. ከጡር ጋራ በስተቀኝ ጎን በኩልም ጠራነው። በሚስጥር ያነጋገርነውም ስንሆን አቀረብነው።

(53) 53. ከእዝነታችንም (ከችሮታችንም) ወንድሙን ሃሩንን ነብይ አደረግንለት።

(54) 54. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በመጽሐፉ ውስጥ ኢስማዒልንም አውሳ:: እርሱ ቀጠሮን አክባሪ ነበርና። መልዕክተኛ ነብይም ነበር።

(55) 55. ቤተሰቦቹንም በሶላትና በዘካ ያዝ ነበር:: በጌታዉም ዘንድ ተወዳጅ ነበር::

(56) 56. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በመጽሐፉ ውስጥ ኢድሪስንም አውሳ:: እርሱ እውነተኛ ነብይ ነበርና::

(57) 57. (ኢድሪስን) ወደ ከፍተኛም ስፍራ አነሳነው::

(58) 58. እነዚህ (አሥሩ) እነዚያ አላህ በእነርሱ ላይ ችሮታውን የለገሰላቸው ከነብያት ከአዳም ዘር ከኑሕ ጋር በመርከቢቱ ላይ ከጫንናቸዉም ዘሮች ከኢብራሂምና ከኢስራኢልም ዘሮች ከመራናቸውና ከመረጥናቸዉም የሆኑት የአር-ረህማን አናቅጽ በእነርሱ ላይ በተነበቡ ጊዜ ሰጋጆችና አልቃሾች ሆነው ወደ መሬት የሚወድቁ (የሚደፉ) ናቸው። {1}
{1} እዚህ ሱጁዱ ትላዋ ይደረጋል።

(59) 59. ከእነርሱም በኋላ ሶላትን ያጎደሉ ከንቱ ፍላጎቶችንም የተከተሉ መጥፎ ትውልዶች ተተኩ:: «ገይ» የሚባልን የገሀነምንም ሸለቆ በእርግጥ ያገኛሉ::

(60) 60. ግና ከእነርሱ የተጸጸቱ በአላህ ያመኑ በጎንም ስራ የሰሩ ሰዎች ወደ ገነት ይገባሉ:: አንዳችንም አይበደሉም::

(61) 61. የመኖሪያን ገነቶች ያችን አር-ረህማን ለባሮቹ በሩቅ ሆነው ሳሉ ተስፋ ቃል የገባላቸውን ይገባሉ:: እርሱ ተስፋው ሁልጊዜም ተፈጻሚ ነውና::

(62) 62. በእርሷ ሰላምን እንጂ ውድቅን ነገር አይሰሙም:: ለእነርሱም በእርሷ ውስጥ ጧትም ማታም ሲሳያቸው አላቸው::

(63) 63. ይህ ያቺ ከባሮቻችን ጥንቁቆች ለሆኑት ሁሉ የምናወርሳት ገነት ናት::

(64) 64. (ጂብሪልም ለነቢዩ) «በጌታህ ትእዛዝ እንጂ አንወርድም:: በፊታችን፤ በኋላችንና በዚህም መካከል ያለው ሁሉ የእርሱ ብቻ ነው:: ጌታህም ረሺ አይደለም።» አለ።

(65) 65. እርሱ የሰማያትና የምድር በሁለቱም መካከል ላለው ሁሉ ጌታ ነውና ተገዛው:: እርሱን በመገዛትም ላይ ታገሥ:: ለእርሱ ሞክሼን ታውቃለህን?

(66) 66. ሰው «በሞትኩ ጊዜ ወደ ፊት ህያው ሆኜ ከመቃብር እወጣለሁን?» ይላል።

(67) 67. ሰው ከዚህ በፊት ምንም ነገር ያልነበረ ሲሆን የፈጠርነው መሆኑን አያስታውስምን?

(68) 68. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በጌታህ እንምላለን ሰይጣናት ጋር በእርግጥ እንሰበስባቸዋለን:: ከዚያም በገሀነም ዙሪያ የተንበረከኩ ሆነው እናቀርባቸዋለን::

(69) 69. ከዚያም ከየቡድኖቹ ሁሉ ከእነርሱ ያንን በአር-ረህማን ላይ በድፍረት በጣም ብርቱ የሆነውን መዘን እናወጣለን::

(70) 70. ከዚያም እነዚያን በእርሷ ለመቃጠል ይበልጥ ተገቢ የሆኑትን ሰዎች እናውቃለን::

(71) 71. (ሰዎች ሆይ!) ከናንተ መካከል ወደ ገሀነም የማይወርድ አንድም የለም:: መውረዱም ጌታህ የፈረደው ግዴታና አይቀሬ ዉሳኔ ነው:: {1}
{1} ይህ ጀሀነም መውረድ ትርጉሙ ሙስሊሞች በርሷ ላይ በተዘረገው ሲራጥ በተባለ በጣም ቀጭን ድልድይ ላይ ያልፋሉ ማለት ነው፣ ሰው ያለ ጥፋት ገሀነም የማይገባ መሆኑ የተወቀ ነው [ተፍሲር ኢብኑጀሪር አጥጠበሪ]

(72) 72. ከዚያም እነዚያን አላህን የፈሩትን ብቻ እናድናለን:: አመጸኞችን ደግሞ የተንበረከኩ ሆነው በውስጧ እንተዋቸዋለን::

(73) 73. በእነርሱም ላይ አናቅጻችን ግልጽ ማስረጃዎች ሆነው በተነበቡላቸው ጊዜ እነዚያ የካዱት ለእነዚያ ላመኑት «ከሁለቱ ክፍሎች መኖሪያው የበለጠውና ሸንጎዉም ይበልጥ የሚያምረው ማንኛው ነው?» ይላሉ።

(74) 74. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከእነርሱ በፊት ከክፍለ ዘመናት ህዝቦች እነርሱ በእይታ በጣም ያማሩትን ብዙዎችን አጥፍተናል::

(75) 75. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በስህተት ውስጥ የሆነውን አዛኙ አምላክ ለእርሱ ጥመትን ይጨምርለት (ማዘግየትን ያዘግየው::) የሚዛትባቸውንም ቅጣትን ወይም ሰዓቲቱን ባዩ ጊዜ እርሱ ስፍራው መጥፎና ሰራዊቱ ደካማ ማን እንደሆነ በእርግጥ ያውቃሉ።» በላቸው::

(76) 76. እነዚያንም የቀኑትን ሰዎች አላህ ቅንነትን ይጨምርላቸዋል:: መልካም ቀሪ ስራዎች በጌታህ ዘንድ በምንዳ በላጭ ናቸው:: በመመለሻነትም የተሻሉ ናቸው::

(77) 77. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ያንን በአናቅጻችን የካደውንና «በትንሣኤ ቀን ገንዘብም ሆነ ልጅ በእርግጥ እሰጣለሁ» ያለውን አየህን?

(78) 78. ሩቁን ምስጢር አወቀን ? ወይስ አዛኙ አምላክ ዘንድ ቃል ኪዳንን ያዘ?

(79) 79. ከዚህ አቋሙ ይታቀብ:: አይሰጠዉም:: የሚለውን ሁሉ በእርግጥ እንጽፋለን:: ለእርሱም ከቅጣት ጭማሬን እንጨምርለታለን::

(80) 80. አለኝ የሚለውንም ሁሉ እንወርሰዋለን ወደ እኛም ብቻውን ሆኖ ይመጣል::

(81) 81. ከአላህ ሌላ አማልክትን ለእነርሱ መከበሪያ አማላጅ እንዲሆኗቸው ያዙ::

(82) 82. ከዚህ ተግባራቸው ይከልከሉ (ይታቀቡ):: መገዛታቸውን በእርግጥ ወደፊት ይከዷቸዋል:: በእነርሱም ላይ ተቃራኒ (ባላጋራ) ይሆኑባቸዋል::

(83) 83. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሰይጣናትን በከሓዲያን ላይ በመጥፎ ሥራ የሚገፋፏቸው ሲሆኑ የላክንባቸው መሆናችንን አላየህምን::

(84) 84. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በእነርሱም መቀጣት ላይ አትቸኩል:: ለእነርሱ ቀንን እንቆጥርላቸዋለንና::

(85) 85. ትክክለኛ አማኞችን የተከበሩ ቡድኖች ሆነው ወደ አዛኙ አምላክ የምንሰበሰብበትንና:

(86) 86. ከሓዲያንን የተጠሙ ሆነው ወደገሀነም የምንነዳበትን ቀን አስታውስ።

(87) 87. አዛኙ አምላክ ዘንድ ቃል ኪዳንን የያዘ ቢሆን እንጂ ሌሎች ማማለድን አይችሉም::

(88) 88. አጋሪዎች «አዛኙ አምላክ አላህ ልጅ ወለደ።» አሉ።

(89) 89.(አጋሪዎች ሆይ!) እጅግ ከባድና መጥፎን ነገር በእርግጥ አመጣችሁ::

(90) 90. ከዚህ ንግግራቸው ሰማያት ሊቀደዱ፤ ምድርም ልትሰነጠቅ፤ ጋራዎችም ተንደው ሊወድቁ ይቃረባሉ::

(91) 91. ይህም ለአዛኙ አምላክ ልጅ አለው ስላሉ ነው::

(92) 92. አዛኙ ጌታ ልጅን መያዝ አይገባዉም::

(93) 93. በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ በትንሣኤ ቀን (ለአር-ረህማን) ለአዛኙ ጌታ ባሪያ ሆነው የሚመጡ እንጂ ሌላ አይደሉም::

(94) 94. አላህ በእርግጥ በዕውቀቱ ከቧቸዋል:: መቁጠርንም ቆጥሯቸዋል::

(95) 95. ሁሉም በትንሳኤ ቀን ለየብቻ ሆነው ወደ እርሱ መጪዎች ናቸው::

(96) 96. እነዚያ በአላህ ያመኑና በጎ ስራዎችን የሰሩ ሁሉ አር-ረህማን ለእነርሱ ውዴታን ይሰጣቸዋል::

(97) 97. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በምላስህም ቁርኣንን ያገራነው በእርሱ ጥንቁቆችን ልታበስርበትና በእርሱ ተከራካሪ ሕዝቦችን ልታስፈራራበት ዘንድ ነው::

(98) 98. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከእነርሱም በፊት ከክፍለ ዘመናት ህዝቦች ብዙ ትውልዶችን አጥፍተናል:: ከእነርሱ አንድን እንኳ ታያለህን? ወይንስ ለእነርሱ ሹክሹክታን ትሰማለህን? (አታይም፣ አጸማምም)