4 - An-Nisaa ()

|

(1) 1. እናንተ ሰዎች ሆይ! ያንን ከአንዲት ነፍስ (ከአደም) የፈጠራችሁን፤ ከእርሷም መቀናጆዋን (ሀዋን) የፈጠረውንና ከሁለቱም ብዙ ወንዶችንና ብዙ ሴቶችን የበተነውን ጌታችሁን (አላህን) ፍሩ:: ያንንም በእርሱ የምትጠያየቁበትን አላህን (ከሚያስቆጡ) ተግባራትና ዝምድናዎችን (ከመቁረጥ) ተጠንቀቁ:: አላህ በእናንተ ላይ ተጠባባቂ ነውና::

(2) (እናንተ ኑዛዜ ተቀባዮች ሆይ! ) ለየቲሞች ገንዘቦቻቸውን ስጡ:: (ከመሀከሉም) መጥፎውንም በመልካሙ አትለውጡ:: ገንዘቦቻቸውን ወደ ገንዘቦቻችሁ (በመቀላቀል) አትብሉ:: እርሱ ትልቅ ኃጢአት ነውና::

(3) 3. (እናንተ ሙስሊም ወንዶች ሆይ) በናንተ ስር ያሉት ሴት የቲሞችን በማግባታችሁ አለማስተካከላችሁን ብትፈሩ ከሴቶች መካከል ለእናንተ የመረጣችሁትን (ደስ ያሏችሁን) ሁለት ሁለት ሶስት ሶስትና አራት አራት አግቡ:: በሚስቶች መካከል አለማስተካከላችሁን ብትፈሩ ግን አንዲትን ሴት ብቻ ወይም ንብረታችሁ የሆኑት ሴት ባሪያዎችን ብቻ (በሚስትነት) ያዙ:: ይህም (ሴትን ልጅ) እንዳትበድሉ በጣም የቀረበ ተግባር ነው::

(4) 4. ለሴቶች መህሮቻቸውን ደስተኞች ሆናችሁ ስጧቸው። ለእናንተ ከእርሱ የተወሰነን ነገር ራሳቸው ቢለግሱላችሁ ግን በእርካታና በምቾት ሆናችሁ ብሉት (ተጠቀሙበት)

(5) 5. (ኃላፊዎች ሆይ!) ያን አላህ ለእናንተ መቋቋሚያ (መጠቃቀሚያ) ያደረገላችሁን ገንዘባችሁን (የያዛችሁላቸውን) ለቂሎች (ለአዕምሮ ደካሞች) አትስጧቸው:: ከእርሷም መግቧቸው:: ከእርሷ አልብሷቸዉም:: ለእነርሱም መልካምን ንግግር ተናገሯቸው።

(6) 6. (ሙስሊሞች ሆይ!) የቲሞችን ለጋብቻ እስከደረሱ ድረስ ፈትኗቸው:: ከእነርሱም ብልህነትን ብታውቁ ገንዘቦቻቸውን ስጧቸው:: በማባከንና ማደጋቸውን በመሽቀዳደም ገንዘቦቻቸውን አትብሉባቸው:: (ከአሳዳጊዎቹ መካከል) ሀብታም የሆነ ሰው ከገንዘቦቻቸው (ቅንጣት ያህል እንኳን ከመቅረብ) ይከልከል:: ደሃ የሆነ ሰዉም ቢሆን ለድካሙ ብቻ በአግባቡ ይብላ:: ገንዘቦቻቸውን ወደ እነርሱ በሰጣችሁም ጊዜ በእነርሱ ላይ አስመስክሩ:: በተጠባባቂነትም አላህ በቂ ነው::

(7) 7. ለወንዶች ወላጆችና የቅርብ ዘመዶች ሲሞቱ ከተውት (ጥሪት ገንዘብ የውርስ) ድርሻ አላቸው:: ለሴቶችም ወላጆችና የቅርብ ዘመዶች ከተውት ከእርሱ ይነስም ይብዛም (የውርስ) ድርሻ አላቸው:: ለሁሉም የተወሰነ ድርሻ ተደንግጓል::

(8) 8. የውርስ ክፍፍልን (ወራሽ ያልሆኑ) የዝምድና ባለቤቶች፤ የቲሞችና ሚስኪኖች በተገኙበት ጊዜ ከእርሱ ለግሱላቸው:: መልካምንም ንግግር ተናገሯቸው::

(9) 9.   እነዚያ ከኋላቸው ደካማ ዝርያዎችን ቢተው ኖሮ በእነርሱ ላይ ምን ይደርስባቸው ይሆን ብለው የሚሰጉ ሰዎች ሁሉ (በየቲሞችም ላይ) ይህንኑ ይፍሩ:: አላህንም ይፍሩ:: ትክክለኛንም ቃል ይናገሩ::

(10) 10. እነዚያ የየቲሞችን ገንዘቦች በግፍ የሚበሉ ሁሉ በሆዶቻቸው ውስጥ የሚበሉት እሳትን ብቻ ነው:: የገሀንም እሳትንም በእርግጥ ይገባሉ::

(11) 11.   (ሰዎች ሆይ) አላህ በልጆቻችሁ ውርስ (በሚከተለው መልኩ) ያዛችኋል:: ለወንዱ የሁለት ሴቶች ድርሻ ያህል አለው:: (ሁለት ወይም) ከሁለት በላይ የሆኑ ሴቶች ልጆች ብቻ ወራሽ ቢሆኑ ለእነርሱ (ሟቹ) ከተወው (ሀብት) ከሶስት ሁለት እጁ ያገኛሉ (አላቸው):: አንዲት ሴት ወራሽ ብትሆን ደግሞ ለእርሷ የሀብቱ ግማሽ አላት:: ለሟቹ ልጅ ካለው ለአባቱና ለእናቱ ከሁለቱ ለእያንዳንዱ ከስድስት አንድ አላቸው:: ለእርሱ ልጅ ባይኖረውና ወላጆቹ ብቻ ቢወርሱት ለእናቱ ሲሶው አላት:: ለእርሱም ወንድሞችና እህቶች ቢኖሩት ለእናቱ ከስድስት አንድ አላት:: (ይህም ውርስ) የሚከፋፈለው ከተናዘዘው ኑዛዜ ወይም ከእዳው ክፍያ በኋላ ነው:: አባቶቻችሁና ልጆቻችሁ ለእናንተ በመጥቀም ማንኛቸው ይበልጥ ቅርብ እንደሆኑ አታውቁም:: ይህም ከአላህ የተደነገገ ነው:: አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነዉና::

(12) 12. ለእናንተም ሚስቶቻችሁ ከተውት ንብረት ለእነርሱ ልጅ ካልኖራቸው ግማሹ አላችሁ:: ለእነርሱም ልጅ ቢኖራቸው ከተውት ሀብት ከአራት አንድ አላችሁ :: (ይህም) በእርሷ ከሚናዘዙባት ኑዛዜ ወይም ከእዳ ክፍያ በኋላ ነው:: ለእናንተም ልጅ ከሌላችሁ ከተዋችሁት ንብረት ለእነርሱ (ለሚስቶቻችሁ) አንድ አራተኛ አላቸው። ለእናንተም ልጅ ባይኖራችሁ ከተዋችሁት ንብረት ለእነርሱ (ለሚስቶቻችሁ) ከስምንት አንድ አላቸው:: (ይህም) ከምትናዘዙበት ኑዛዜ ወይም ከእዳ ክፍያ በኋላ ነው:: ወላጆችም ልጅም የሌለውና የጎን ወራሾች የሚወርሱት ወንድ ወይም ሴት ቢገኝ ለእርሱም (ለሟቹ) ከእናቱ በኩል ብቻ የሆኑ ወንድም ወይም እህት ቢኖሩት ከሁለቱ ለእያንደንዳቸው ከስድስት አንድ አላቸው:: ከአንድ የበዙ ቢሆኑ ደግሞ በሲሶው ላይ ተጋሪዎች ናቸው:: ይህም ወራሾቹን የማይጎዳ ሆኖ ከእርሷ ከሚናዘዙባት ኑዛዜ ወይም ከእዳ በኋላ ነው:: ከአላህም የሆነን ኑዛዜ ያዛችኋል:: አላህ ሁሉን አዋቂና ቻይ ነውና።

(13) 13. እነዚህ የአላህ ውሳኔዎች ናቸው:: አላህንና መልዕክተኛውን የሚታዘዙ ሰዎች ሁሉ ከስሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲሆኑ ያስገባቸዋል። ይህም ትልቅ እድል ነው።

(14) 14. በአላህና በመልዕክተኛው ላይ የሚያምጽ ወሰኖችንም የሚተላለፍ ሁሉ በውስጧ ዘውታሪ ሲሆን ወደ ገሀነም እሳት ያስገባዋል:: ለእርሱም አዋራጅ ቅጣት አለበት።

(15) 15. እነዚያ ከሴቶቻችሁ መካከል ዝሙትን የሚሰሩ በእነርሱ ላይ ከናንተ የሆነን አራት ታማኝ ወንዶችን አስመስክሩባቸው:: ከመሰከሩባቸዉም ሞት እስከሚደርስባቸው ወይም አላህ ለእነርሱ ሌላ መንገድን እስከሚያደርግ ድረስ በቤቶች ውስጥ ያዟቸው(እሰሯቸው::)

(16) 16. እነዚያ ከእናንተ ውስጥ ዝሙትን የሚሰሩትን አሰቃዩዋቸው (በሚገባ ቅጧቸው):: ቢጸጸቱና ስራቸውን ቢያሳምሩ ግን እነርሱን ተዋቸው (አታሰቃዩዋቸው።) አላህ ጸጸትን ተቀባይና አዛኝ ነውና።

(17) 17. ጸጸትን መቀበል ከአላህ በኩል ለእነዚያ ኃጢአትን በስህተት ለሚሰሩና ከዚያም ወዲያውኑ ለሚጸጸቱ ነው:: እነዚያንማ አላህ ከእነርሱ ጸጸትን ይቀበላል:: አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነውና፣

(18) 18. ጸጸትን መቀበል ለእነዚያ ኃጢአቶችን ለሚሰሩና ልክ ሞት በመጣባቸው ጊዜ «አሁን ተጸጸትኩ።» ለሚሉና ለእነዚያም ከሓዲያን ሆነው ለሚሞቱ አይደለም:: ለእነርሱማ አሳማሚን ቅጣት አዘጋጅተናል።

(19) 19. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ሴቶችን ያስገደዳችሁ ሆናችሁ ልትወርሱና ግልጽ የሆነ መጥፎ ስራ ካልሰሩ በስተቀር ከሰጣችኋቸው ከፊሉን ልትወስዱባቸውና ልታጉላሏዋቸው አይፈቀድላችሁም:: በመልካም ተኗኗሯቸው:: ብትጠሏቸዉም እንኳን ታገሱ:: አንድ ነገር ብትጠሉትም አላህ በእርሱ ዉስጥ ብዙ ደግ ነገሮችን ሊያደርግላችሁ ይችላልና::

(20) 20. (ባሎች ሆይ!) በሚስት ቦታ ሌላ ሚስትን ለመለወጥ ብትፈልጉ (ለምትፈታው ሴት ቀደም ሲል) ብዙን ገንዘብ የሰጣችኋት እንደሆነ ከእርሷ ምንንም አትውሰዱባት:: በመበደልና ግልጽ በሆነ ኃጢአት ትወስዱታላችሁን?

(21) 21. ከፊላችሁ ወደ ከፊሉ የደረሰ ሲሆንና ከናንተ ላይም (ሴቶች) የጠበቀ ቃል ኪዳንን የያዙባችሁ ሲሆኑ እንዴት ትወስዱታላችሁ?

(22) 22. (ወንዶች ሆይ!) ከሴቶች መካከል አባቶቻችሁ ያገቧቸውን አታግቡ። ያለፈው ሲቀር። እርሱ መጥፎና የተጠላ ስራ ነውና። መንገድነቱም ከፋ።

(23) 23. (ወንዶች ሆይ!) እናቶቻችሁ፤ ሴት ልጆቻችሁ፤ እህቶቻችሁ፤ አክስቶቻችሁ (የአባቶቻችሁ እህቶች)፣ አክስቶቻችሁ (የእናቶቻችሁ እህቶች)፤ የወንድም ሴት ልጆች፤ የእህት ሴት ልጆች፤ እነዚያም ያጠቧችሁ የጡት እናቶቻችሁ፤ የጡት እህቶቻችሁ፤ የሚስቶቻችሁ እናቶች፤ እነዚያም ከጉያዎቻችሁ ያሉት የእነዚያ ግብረ ስጋ ግንኙነት የፈጸማችሁባቸው ሚስቶቻችሁ ሴት ልጆች ልታገቧቸው በእናንተ ላይ እርም ተደረጉባችሁ:: ግብረ ስጋ ግንኙነት ያልፈጸማችሁባቸው የሚስቶቻችሁ ሴት ልጆቻቸውን ብታገቡ ግን በእናንተ ላይ ኃጢአት የለባችሁም:: የእነዚያ ከጀርባዎቻችሁ የሆኑት ወንዶች ልጆቻችሁ ሚስቶችም ሁለት እህትማማቾችን በአንድ መሰብሰብም እንደዚሁ እርም ነው:: ከዚህ በፊት ያለፈው ሲቀር:: እርሱንስ ተምራችኋል:: አላህ መሀሪና አዛኝ ነውና።

(24) 24. ባል ያገቡ ሴቶችም በጦርነት እጆቻችሁ በምርኮ የያዟቸው ሲቀሩ (በእናንተ ላይ እርም ናቸው):: ይህን ህግ አላህ በእናንተ ላይ ደነገገ:: ከነዚህ ከተከለከሉት ሌላ ጥብቆች ሆናችሁና ዝሙተኞች ሳትሆኑ በገንዘባችሁ ጋብቻን ልትፈለጉ ለእናንተ ተፈቀደ:: እናም ከእነርሱም መገናኘት የተጠቀማችሁባቸውን ሴቶች መህሮቻቸውን ልትሰጧቸው ግዴታ ነው:: ከመወሰን በኋላ በተዋደዳችሁበት ነገር በእናንተ ላይ ኃጢአት የለም:: አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነውና::

(25) 25. (ወንዶች ሆይ!) ከናንተ መካከል ጥብቆች ምዕመናትን ለማግባት ሀብትን ያልቻለ ሰው እጆቻችሁ ንብረት ካደረጓቸው ከምዕመናት መካከል ወጣቶቻችሁን አገልጋዬች የመረጠውን ያግባ:: አላህ የውስጥ እምነታችሁን ምንነት አዋቂ ነውና:: ከፊላችሁ ከከፊሉ የተራባ ነው:: ባሮችንም ቢሆን እንደዚሁ በአሳዳሪዎቻቸው ፈቃድ ብቻ አግቧቸው:: መህሮቻቸውንም በመልካም መንገድ ስጧቸው:: ጥብቆች ሆነው ዝሙተኛ ያልሆኑ የስርቆሽ ወዳጅንም ያልያዙ እንደሆኑ አግቧቸው:: በማግባት በተጠበቁም ጊዜ መጥፎን ስራ ቢሰሩ በእነርሱ ላይ የተደነገገው ቅጣት በነፃዎቹ ላይ ከተደነገገው ቅጣት ግማሹ ቅጣት አለባቸው:: ያ ከናንተ መካከል ዝሙትን ለፈራ ብቻ ነው:: መታገሳችሁ የተሻለ ነው:: አላህ መሀሪና አዛኝ ነውና።

(26) 26. (አማኞች ሆይ!) አላህ የሃይማኖታችሁን ህግጋት ሊያብራራላችሁ፤ ከናንተ በፊትም የነበሩትን ነብያት ፈለጎች ሊመራችሁ፤ በእናንተም ላይ ጸጸትን ሊቀበል ይሻል:: አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነው::

(27) 27. አላህ በእናንተ ላይ ጸጸትን ሊቀበል ይሻል:: እነዚያ ፍላጎታቸውን የሚከተሉ ግን ከእውነት ትልቅን መዘንበል እንድትዘነበሉ ይፈልጋሉ::

(28) 28. አላህ ከናንተ ሊያቃልልላችሁ ይሻል። ሰው ደካማ ሆኖ የተፈጠረ ነውና::

(29) 29. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ገንዘቦቻችሁን በመካከላችሁ ያለ አግባብ አትብሉ:: በእናንተ መካከል በመስማማት የሆነችውን ንግድ ካልሆነች በስተቀር (እሷን ግን ብሉ) :: ነፍሶቻችሁን በራሳችሁ አትግደሉ። አላህ ለእናንተ አዛኝ ነውና::

(30) 30. ወሰን በማለፍ እና በመበደል ይህን የሰራ ሁሉ እሳት እናስገባዋለን:: ይህም በአላህ ላይ ገር ነውና።

(31) 31. ትክክለኛ አማኞች ሆይ! ከተከለከላችሁት ወንጀሎች መካክል ታላላቆችን ብትርቁ ትናንሽ ኃጢአቶቻችሁን እናብስላችኋለን:: የተከበረውንም መግቢያ (ገነት) እናስገባችኋለን::

(32) 32. አላህ ከፊላችሁን በከፊሉ ያበለጠበትን ጸጋ አትመኙ:: ለወንዶችም ከሰሩት ስራ እድል አለላቸው:: ለሴቶችም ከሰሩት ስራ እንዲሁ እድል አለላቸው:: አላህን ከችሮታው ለምኑት:: አላህ በሁሉ ነገር አዋቂ ነውና::

(33) 33. ለሁላችሁም ወላጆችና የቅርብ ዘመዶች ከተውት ሀብት ወራሾችን አድርገናል:: እነዚያንም (ለመረዳዳትና ለመዋረስ) በመሐላዎቻችሁ የተዋዋላችኋቸውን (ከስድስት አንድ) ድርሻቸውን ስጧቸው:: አላህ በነገሩ ሁሉ አዋቂ (መስካሪ) ነው::

(34) 34. ወንዶች ለሴቶች ቋሚና የበላይ አስተዳዳሪዎች ናቸው:: አላህ ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ በማብለጡና ወንዶች ከገንዘቦቻቸው ለሴቶች በመስጠታቸው ምክኒያት ነው:: መልካሞቹ ሴቶች ማለት ለባሎቻቸው ታዛዦች፤ አላህ ባስጠበቀው ነገር ከባሎቻቸው ሩቅ የሆነውን ጠባቂዎች ናቸው:: እነዚያን ማመፃቸውን የምትፈሩትን ሴቶች መጀመሪያ ገስጿቸው:: ከዚያም በመኝታቸው ተለዩዋቸው:: ከዚያም (በአካሎቻቸው ላይ ሳካ ሳታደርሱ) ምቷቸው:: ከታዘዟችሁ ለመጨቆን ስትሉ በእነርሱ ላይ መንገድን አትፈልጉ:: አላህ የሁሉም በላይና ታላቅ ነውና::

(35) 35. በመካከላቸውም ጭቅጭቅ መኖሩን ብትፈሩ (ብታውቁ) ከቤተሰቡና ከቤተሰቦቿ የተውጣጡ የቤተ ዘመድ ጉባኤ አዋቅሩ:: ሁለቱም እርቅን ቢሹ አላህ በመካከላቸው ያስማማቸዋል:: አላህ ግልጽንም ሆነ ውስጥንም አዋቂ ነውና::

(36) 36. አላህን ተገዙ:: በእርሱ ምንንም አታጋሩ። ለወላጆች፣ ለቅርብ ዝምድና ባለቤቶች፣ ለየቲሞች፣ ለምስኪኖች፣ ለቅርብ ጎረቤት፣ ለሩቅ ጎረቤት፣ ለጎን ባልደረባ፣ ለመንገደኛ፣ እጆቻችሁ ንብረት ላደረጓቸው ባሮች መልካምን ስሩ። አላህ ኩራተኞችንና ጉረኞችን አይወድምና::

(37) 37. እነዚያ የሚሰስቱ ንፉጎችና ሰዎችንም በመሰሰት (በንፍግና) የሚያዝዙ አላህ ከችሮታው የሰጣቸውን ጸጋ የሚደብቁ ብርቱን ቅጣት ይቀጣቸዋል። ለከሓዲያንም አዋራጅን ቅጣት አዘጋጅተናል።

(38) 38. እነዚያ ለሰዎች ይዩልን ሲሉ ገንዘቦቻቸውን የሚሰጡ በአላህ እና በመጨረሻው ቀን የማያምኑ ይቀጣሉ:: ሰይጣንም የእሱ ጓደኛው የሆነለት ሁሉ ጓደኛነቱ ከፋ!

(39) 39. በአላህና በመጨረሻው ቀን ባመኑና አላህ ከሰጣቸዉም ሲሳይ በለገሱ ኖሮ በእነርሱ ላይ ምን ጉዳት ነበረ? አላህ በእነርሱ ሁኔታ አዋቂ ነውና::

(40) 40. አላህ የብናኝን ክብደት ያህል እንኳን አይበድልም:: መልካም ስራ ብትሆንም ይደራርባታል:: ከእርሱም ዘንድ ታላቅን ምንዳ ይሰጣል::

(41) 41. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከሕዝቦች ሁሉ መስካሪን ባመጣንና አንተንም በእነዚህ (ባንተ ህዝቦች) ላይ መስካሪ አድርገን በምናመጣህ ጊዜ የከሓዲያን ሁኔታ እንዴት ይሆን?

(42) 42. በዚያ ቀን እነዚያ በአላህ የካዱ ሰዎችና መልዕክተኛውን ያልታዘዙት ምድር በእነርሱ ላይ ብትደፋባቸው ይመኛሉ:: ከአላህም ወሬን አይደብቁም።

(43) 43. (እናንተ ያመናችሁ ሆይ!) የምትሉትን ነገር ለይታችሁ አስከምታውቁ ድረስ የሰከራችሁ ሆናችሁ ወደ ሶላት አትቅረቡ:: ጀናባ ስትሆኑም መንገድን አላፊዎች ካልሆናችሁ በስተቀር ሙሉ አካላታችሁን እስከምትታጥቡ ድረስ መስጊድን አትቅረቡ:: በሽተኞች ወይም በጉዞ ላይ ብትሆኑ ወይም ከናንተ አንዱ ከአይነ ምድር ቢጸዳዳ ወይም ከሴቶች ጋር ብትነካኩና ( የግብረስጋ ግንኙነት ብትፈጽሙና) ውሃን ባታገኙ ንጹህ የሆነን የምድር ገጽ (አፈርን) አብሱ:: ከዚያ ፊቶቻችሁንና እጆቻችሁን በእርሱ አብሱ:: አላህ ይቅር ባይና መሀሪ ነውና።

(44) 44. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ወደ እነዚያ ከመጽሐፉ የእውቀት ድርሻን ወደ ተሰጡት ክፍሎች አላየህም? ጥመትን በቅንነት ይገዛሉ:: መንገድንም እንድትሳሳቱ ይፈልጋሉ።

(45) 45. (ትክክለኛ አማኞች ሆይ!) አላህ ጠላቶቻችሁን ከናንተ በበለጠ አዋቂ ነው:: ጠባቂነትም በአላህ በቃ:: ረዳትነትም በአላህ በቃ።

(46) 46. ከእነዚያ ከአይሁዳውያን መካከል ንግግሮችን ከስፍራዎቹ የሚያጣምሙ አሉ። «ንግግርክን ሰማንና ትእዛዝክን አመጽን፤ የማትሰማም ስትሆን እስቲ ስማ።» ይላሉ:: በምላሶቻቸዉም ለማጣመምና ሃይማኖትንም ለመዝለፍ በማሰብ "ራዒና" ይላሉ:: እነርሱም «ሰማንና ታዘዝን፤ ስማን ተመልከተንም።» ባሉ ኖሮ ለእነርሱም መልካምና ትክክለኛ በሆነ ነበር:: ግን በክህደታቸው ምክንያት አላህ ረገማቸው:: ከእነርሱም መካከል ጥቂቶች እንጂ አያምኑም።

(47) 47. እናንተ መጽሐፉ የተሰጣችሁ ሰዎች ሆይ! ፊቶችን ሳናዞርና በጀርባዎች ላይ ሳንመልሳቸው ወይም የሠንበትን ባለቤቶች እንደረገምን ሳንረግማችሁ በፊት ከናንተ ጋር ያለውን የሚያረጋግጥ ሆኖ በአወረድነው ቁርኣን እመኑ:: የአላህም ትዕዛዝ ተፈፃሚ ነው።

(48) 48. አላህ በእርሱ ማጋራትን ፈጽሞ አይምርም:: ከዚህ በታች (ውጭ) ያለውን ኃጢአት ግን ለሚሻው ሁሉ ይምራል:: በአላህ የሚያጋራ ሁሉ ታላቅን ኃጢአት በእርግጥ ቀጠፈ::

(49) 49. ወደ እነዚያ ነፍሶቻቸውን ወደ ሚያጠሩት (ሚያወድሱት) አላየህምን? ይልቁንም አላህ ነው የሚፈልገውን የሚያጠራው። በተምር ፍሬ ስንጥቅ ላይ ያለችን ክር መሳይ ያህልም ቢሆን አይበደሉም።

(50) 50. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በአላህ ላይ ውሸትን እንዴት እንደሚቀጥፉ ተመልከት። ግልጽ ወንጀል በርሱ በቃ።

(51) 51. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ወደ እነዚያ ከመጽሐፉ ድርሻን ወደ ተሰጡት አላየህምን? በድግምትና በጣዖት ያምናሉ። ለእነዚያ በአላህ ለካዱትም እነርሱ በሃይማኖት ከእነዚያ በሙሐመድ ካመኑት ይበልጥ ቀና እንደሆኑ ይናገራሉ።

(52) 52. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያ አላህ የረገማቸው ናቸው:: አላህ የረገመውን ደግሞ ለርሱ ፈጽሞ ረዳት አታገኝለትም።

(53) 53. በእውነቱ ለእነርሱ ከንግስናው ፈንታ አላቸውን? ያን ጊዜማ ለሰዎች በተምር ፍሬ ላይ ያለችውን ነጥብ ያህል እንኳን አይሰጡም ነበር።

(54) 54. ይልቁንም ለሰዎች አላህ ከችሮታው በሰጣቸው ነገር ላይ ይመቀኛሉን? ለኢብራሂምም ቤተሰቦች መጽሐፍንና ጥበብን በእርግጥ ሰጠን:: ታላቅንም ንግስናን ሰጠናቸው::

(55) 55. ከነሱም (ከአይሁድ) መካከል በነብዩ ሙሐመድ ያመነ አለ:: ከእነርሱም ከዚህ እምነት ያፈገፈገ አለ። አቃጣይነት በገሀነም በቃ።

(56) 56. እነዚያን በተዐምራታችን የካዱትን ሁሉ በእርግጥ እሳትን እናስገባቸዋለን:: ስቃይን እንዲቀምሱም ቆዳዎቻቸው በተቃጠሉ ቁጥር ሌሎችን ቆዳዎች እንለውጥላቸዋለን:: አላህ ሁሉን አሸናፊና ጥበበኛ ነው::

(57) 57. እነዚያ በአላህ አንድነት ያመኑና መልካም ስራዎችን የሰሩ ከስራቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች ዘላለም በውስጣቸው ዘወታሪዎች ሲሆኑ በእርግጥ እናስገባቸዋለን:: ለእነርሱ በውስጧ ንጹህ ሚስቶችም አሏቸው:: የምታስጠልልን ጥላም እናስገባቸዋለን::

(58) 58. አላህ አደራዎችን ወደ የባለቤቶቻቸው እንድታደርሱና በሰዎች መካከል በፈረዳችሁ ጊዜም በትክክል እንድትፈርዱ ያዛችኋል:: አላህ በእርሱ የሚገስፃችሁ ነገር ምን ያምር ነው! አላህ ሁሉን ሰሚ እና ሁሉን ተመልካች ነውና።

(59) 59. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ታዘዙ:: መልዕክተኛውን እና ከመካከላችሁም የስልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ:: በማንኛዉም ነገር ብትከራከሩም በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ከሆናችሁ የተከራከራችሁበትን ነገር ወደ አላህና ወደ መልዕክተኛው መልሱት:: ይህ የተሻለ እና መጨረሻዉም ያማረ ነው::

(60) 60. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ወደ እነዚያ «ባንተ ላይ በተወረደውና ካንተ በፊትም በተወረደው አምነናል።» ወደ ሚሉት አላየህምን? በእርሱ እንዲክዱ በእርግጥ የታዘዙ ሲሆኑ ወደ ጣኦት መፋረድን ይፈልጋሉ:: ሰይጣንም ከእውነት የራቀን መሳሳት ሊያሳስታቸው ይፈልጋል።

(61) 61. ለእነርሱም፡- «አላህ ወደ አወረደው ቁርኣንና ወደ መልዕክተኛው ኑ።» በተባሉ ጊዜ አስመሳዮችን ካንተ በሀይል ሲሸሹ ታያቸዋለህ።

(62) 62. እጆቻቸዉም ባስቀደሙት ጥፋት ምክንያት መከራ በደረሰባቸውና ከዚያ «ደግን ሀሳብና ማስማማትን እንጂ ሌላን አልፈለግንም።» በማለት በአላህ የሚምሉ ሆነው ወደ አንተ በመጡ ጊዜ እንዴት ይሆናል?

(63) 63. እነዚያ አላህ በልቦቻቸው ውስጥ ያለውን ሁሉ የሚያውቅባቸው ናቸው:: ከእነርሱ ራስህን አግልል:: ገስፃቸዉም:: ለእነርሱም በነፍሶቻቸው ውስጥ ጠልቆ የሚገባ ጠንካራ ቃል ተናገራቸው።

(64) 64. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ማንንም መልዕክተኛ በአላህ ፈቃድ ሊታዘዙት እንጂ አልላክንም:: እነርሱም ነፍሶቻቸውን በበደሉ ጊዜ ወደ አንተ መጥተው አላህን ምህረት በለመኑና መልዕክተኛዉም ለእነርሱ ምህረትን በለመነላቸው ኖሮ አላህን ጸጸትን ተቀባይና አዛኝ ሆኖ ባገኙት ነበር።

(65) 65. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጉዳዩ እነርሱ እንዳሉት አይደለም:: በጌታህ እምላለሁ በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ የሚያስፈርዱህ ሆነው ከዚያ ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍጹም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አማኝ አይሆኑም::

(66) 66. እኛም በእነርሱ ላይ፡- «ነፍሶቻችሁን ግደሉ» ወይም «ከአገሮቻችሁ ውጡ» ማለትን በፃፍን ኖሮ ከእነርሱ ጥቂቶቹ እንጂ ባልሰሩት (ባልተገበሩት) ነበር። የሚገሰጹበትን ነገር በተገበሩት ኖሮ ለእነርሱ መልካምና በእምነታቸው ላይ ለመርጋትም በጣም የበረታ በሆነ ነበር።

(67) 67. ያን ጊዜ ደግሞ ከእኛ ዘንድ ታላቅን ምንዳ በሰጠናቸው ነበር።

(68) 68. ቀጥተኛውንም መንገድ በእርግጥ በመራናቸው ነበር::

(69) 69. አላህንና መልዕክተኛውን የሚታዘዝ ሁሉ ከእነዚያ አላህ በእነርሱ ላይ ፀጋውን ከዋለላቸው ከነብያት፤ ከፃድቃን፤ ከሰማዕታትና ከመልካሞቹ ጋር ይሆናሉ። የእነዚያም ጓደኝነት አማረ።

(70) 70. ይህ ችሮታ ከአላህ የተለገሰ ነው:: አዋቂነትም በአላህ በቃ::

(71) 71. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ጥንቃቄያችሁን ያዙ:: ክፍልፍልም ወይም በአንድ ሆናችሁ ለዘመቻ ውጡ::

(72) 72. ከናንተ ውስጥ በእርግጥ ከዘመቻ ወደ ኋላ የሚንጓደድ (የሚጎተት) ሰው አለ:: አደጋም ካገኛችሁ «ከእነርሱ ጋር ተሳታፊ ባለመሆኔ አላህ በእኔ ላይ በእርግጥ ጸጋውን ዋለልኝ።» ይላል።

(73) 73. ከአላህ የሆነ ችሮታ ካገኛችሁ ደግሞ በእናንተና በእርሱ መካከል ፍቅር አንዳልነበረ ሁኖ «ታላቅ እድል አገኝ ዘንድ ምን ነው ከእነርሱ ጋር በሆንኩ?» ይላል።

(74) 74. እናም እነዚያ ቅርቧን ህይወት በመጨረሻይቱ ሕይወት የሚለውጡ (የሚገዙ) በአላህ መንገድ ይጋደሉ:: በአላህ መንገድ የሚጋደልና ከዚያ የሚገደል ወይም የሚያሸንፍ ሁሉ ታላቅ ምንዳን በእርግጥ እንሰጠዋለን።

(75) 75. (አማኞች ሆይ!) በአላህ መንገድና ከወንዶች፣ ከሴቶችና ከልጆችም የሆኑትን እነዚያን፡- «ጌታችን ሆይ! ከዚህች ባለቤቶቿ በዳይ ከሆኑባት ከተማ አውጣን፤ ካንተም ዘንድ ለእኛ አሳዳሪን አድርግልን፤ ካንተ ዘንድም ለእኛ ረዳትን አድርግልን።» የሚሉትን ደካሞች ሰዎች ለማዳን የማትዋጉት ለምንድ ነው?

(76) 76. እነዚያ ያመኑት በአላህ መንገድ ይዋጋሉ:: እነዚያ በአላህ የካዱት ደግሞ በጣኦት መንገድ ይዋጋሉ:: እናም (እናንተ ያመናችሁ ሆይ!) የሰይጣን ቡድኖችን ተፋለሙ:: የሰይጣን ተንኮል ደካማ ነውና::

(77) 77. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ወደ እነዚያ ለእነርሱ፡- «እጆቻችሁን ከመጋደል ሰብስቡ፤ ሶላትን ደንቡን ጠብቃችሁ ስገዱ፤ ግዴታ ምጽዋትን ስጡ።» ወደ ተባሉት አላየህምን? በእነርሱ ላይ መጋደል ግዴታ በሆነባቸው ጊዜ ደግሞ ከእነርሱ መካከል ከፊሎቹ ወዲያውኑ ሰዎችን ልክ አላህን እንደሚፈሩ ወይም የበለጠ ይፈራሉ:: «ጌታችን ሆይ! በእኛ ላይ መጋደልን ለምን ደነገግህ? እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አታቆየንም ኖሯልን?» ይላሉ:: «የቅርቢቱ ሕይወት ጥቅም አነስተኛ ነው:: የመጨረሻይቱ ዓለም ጥቅም ግን አላህን ለሚፈራ ሁሉ በላጭ ነው። በተምር ፍሬ ውስጥ ያለችን ክር መሰል ያህል እንኳ አትበደሉም።» በላቸው።

(78) 78. የትም ስፍራ ብትሆኑ ሞት ያገኛችኋል:: በጠነከሩ ህንፃዎች ውስጥም ብትደብቁ እንኳን:: ደግ ነገር ካገኛቸው «ይህ ከአላህ ዘንድ የመጣ ነው።» ይላሉ:: መከራ ካገኛቸው ግን «ይህ ካንተ ዘንድ የመጣ ነው።» ይላሉ:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ሁሉም (ደጉም ክፉዉም) ከአላህ ዘንድ የመጣ ነው።» በላቸው:: እነዚህ ሰዎች ንግግርን ሊረዱ የማይቀርቡት ለምንድን ነው?

(79) 79. (የሰው ልጅ ሆይ!) ደግ ነገር የሚያገኝህ ከአላህ ችሮታ ነው:: የሚደርስብህ መከራ ግን ከራስህ ጥፋት የተነሳ ነው:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለሰዎች ሁሉ መልዕክተኛ አድርገን ላክንህ:: መስካሪነትም በአላህ በቃ::

(80) 80. መልዕክተኛውን የሚታዘዝ ሁሉ በእርግጥ አላህን ታዘዘ:: ከትዕዛዝም የሸሸው ጉዳዩ አያሳስብህ:: በእነርሱ ላይ ጠባቂ አድርገን አላክንህምና::

(81) 81. አጠገብህ ሲሆኑ የአንተ ታዛዥ ነን ይላሉ:: ካንተ ዘንድ በወጡ ጊዜ ከእነርሱ ከፊሎቹ ከዚያ በአጠገብህ ከሚሉት ሌላን በልቦቻቸው ያሳድራሉ:: አላህ በልቦቻቸው የሚያሳድሩትን ነገር ሁሉ ይጽፋል:: ስለዚህ ተዋቸውና በአላህ ላይ ብቻ ተመካ:: መመኪያነት አላህ ብቻ በቃ::

(82) 82. ቁርኣንን አያስተነትኑምን? ከአላህ ሌላ ዘንድ የመጣ በነበረ ኖሮ በውስጡ ብዙ መለያየትን ባገኙ ነበር::

(83) 83. ሰላምን ወይም ስጋትን የሚመለከት ወሬ በመጣላቸው ጊዜ እርሱን ያሰራጫሉ (ያጋንናሉ)። ወደ መልዕክተኛውና ከእነርሱ መካከል የጉዳይ ባለቤቶች ወደ ሆኑት አዋቂዎቹ በመለሱት ኖሮ እነዚያ ከእነርሱ መካከል ነገሩን በትክክል የሚረዱት ክፍሎች ባወቁት ነበር:: በእናንተ ላይ የአላህን ችሮታና እዝነቱ ባልነበረ ኖሮ ከጥቂቶቹ በስተቀር ሰይጣንን በተከተላችሁ ነበር።

(84) 84. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በአላህ መንገድ ተዋጋ:: ራስህን እንጂ ሌላን አትገደድም:: አማኞችንም በአላህ መንገድ ላይ በመዋጋት ላይ አደፋፍራቸው:: አላህ የእነዚያን የካዱትን ሰዎች ኃይል ሊከለክል ይከጀላል:: አላህ በሃይል በመያዙ የበረታና ቅጣቱም የጠነከረ ነው::

(85) 85. መልካም መታደግን የሚታደግ (ሽምግልናን የሚሸመግል) ሰው ሁሉ ለራሱ ከእርሷ እድል ይኖረዋል:: መጥፎ መታደግንም የሚታደግ ሰው ለእርሱ ከእርሷ ድርሻ ይኖረዋል:: አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው::

(86) 86.(እናንተ ያመናችሁ ሆይ!) ሰላምታ በቀረበላችሁ ጊዜ ከእርሷ ይበልጥ ባማረ ሰላምታን መልሱ። ወይም እርሷኑ ራሷን መልሷት። አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ተቆጣጣሪ ነውና።

(87) 87. አላህ ከእርሱ በስተቀር ትክክለኛ አምላከ የለም:: ወደ ትንሳኤ ቀን በእርሱ ጥርጥር የሌለበት ሲሆን በእርግጥ ይሰበስባችኋል:: በንግግርም ከአላህ ይበልጥ እውነተኛ ማን ነው?

(88) 88.(አማኞች ሆይ) አላህ በስራዎቻቸው ምክንያት ወደ ክህደት የመለሳቸው ሲሆኑ በሙናፊቆች ጉዳይ እናንተ ለሁለት ቡድን የተከፈላችሁት ምን ሆናችሁ ነው? አላህ ያጠመመውን ሰው ልታቀኑ ታስባላችሁን? (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ ያጠመመውን ሰው ለእርሱ መንገድ ፈጽሞ አታገኝለትም::

(89) 89. (አማኞች ሆይ) በአላህ እንደ ካዱ ሁሉ እናንተም እንድትክዱና ከእነርሱ ጋር እኩል እንድትሆኑ ተመኙ:: በአላህ መንገድ እስከሚሰደዱ ድረስ ከእነርሱ መካከል ወዳጆችን አትያዙ:: ከእምነት ካፈገፈጉም ማርኳቸው:: ባገኛችኋቸው ስፍራ ሁሉ ግደሏቸው:: ከእነርሱም ወዳጅንና ረዳትን አትያዙ::

(90) 90. እነዚያ በእናተና በእነርሱ መካከል ቃል ኪዳን ወዳላቸው ህዝቦች የሚጠጉ፤ ወይም እናንተን ለመጋደልም ይሁን ወገኖቻቸውን ለመጋደል ልቦቻቸው የተጨነቁ ሆነው ወደ እናንተ የመጡ ሲቀሩ እነዚያንማ አትጋደሏቸው:: አላህ በፈለገ ኖሮ በእናንተ ላይ ሀይል በሰጣቸውና በተዋጓችሁ ነበር:: ቢተዋችሁ ባይዋጓችሁ ወደ እናንተ የእርቅን ሀሳብ ቢያቀርቡ አላህ ለእናንተ በእነርሱ ላይ የመዋጋት መንገድን አላደረገም::

(91) 91. ከናንተም ሆነ ከወገኖቻቸው ለመዳን የሚፈልጉ ሌሎች ቡድኖችም ታገኛላችሁ:: ወደ እውከት እንዲመለሱ በተጠሩ ቁጥር በእርሷ ውስጥ ይዘፈቃሉ:: ባይተዋችሁና እርቅን ካላቀረቡላችሁ እጆቻቸውንም ባይሰበስቡ ባገኛችኋቸው ስፍራ ሁሉ ማርኳቸው:: ግደሏቸዉም:: እነዚያን ለእናንተ በእነርሱ ላይ ግልጽ ማስረጃን አድርገንላችኋል::

(92) 92. አማኝ በስህተት ካልሆነ በስተቀር አማኝን መግደል አይገባዉም:: አማኝን በስህተት የገደለም አማኝ ባሪያን ነፃ ማውጣትና ምህረት ካላደረጉለት በስተቀር ለቤተሰቦቹ የምትሰጥ ጉማ መክፈል አለበት:: ተገዳዩ ምዕመን ሆኖ ለእናንተ ጠላት ከሆኑ ህዝቦች ዘንድ ቢሆንም አማኝን ባሪያ ነፃ ማውጣት አለበት:: ተገዳዩ በእናንተ እና በእነርሱ መካከል ቃል ኪዳን ካላቸዉም ህዝቦች ጋር ቢሆን ለቤተሰቦቹ የምትሰጥ ጉማና አማኝን ባሪያ ነፃ ማውጣት አለበት:: ይህንን ያላገኘም በተከታታይ ሁለት ወሮችን መፆም አለበት:: ከአላህ የሆነ ጸጸት (ለመቀበል ደነገገላችሁ::) አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነው::

(93) 93. አማኝን አስቦ የሚገድል ቅጣቱ በውስጧ ዘወታሪ ሲሆን ገሀነም ናት:: አላህ በእርሱ ላይ ተቆጣ:: ረገመዉም:: ለእርሱ ከባድ ቅጣትን አዘጋጀቶለታል::

(94) 94. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህ መንገድ ለመዋጋት በተጓዛችሁ ጊዜ አረጋግጡ:: ሰላምታን ወደ እናንተ ላቀረበ ሰው የቅርቢቱን ሕይወት ጥቅም የምትፈልጉ ሆናችሁ «ትክክለኛ አማኝ አይደለህም።» አትበሉት:: አላህ ዘንድ ብዙ ምርኮዎች አሉና:: እናንተም ከዚህ በፊት ልክ እንደዚሁ ነበራችሁ:: አላህ በእናንተ ላይ ለገሰ:: ስለዚህም አረጋግጡ:: አላህ በምትሰሩት ሁሉ ውስጠ አዋቂ ነውና::

(95) 95. ከአማኞች የጉዳት ባለቤት ከሆኑት በስተቀር ተቀማጮቹ እና በአላህ መንገድ በገንዘቦቻቸውም በነፍሶቻቸውም የሚታገሉት አይስተካከሉም:: በገንዘቦቻቸውም በነፍሶቻቸውም የሚታገሉትን አላህ በተቀማጮቹ ላይ በደረጃ አበለጠ:: ለሁሉም አላህ መልካሚቱን (ገነት) ተስፋ ሰጠ (ቃል ኪዳን ገባ):: ታጋዮቹንም በተቀማጮቹ ላይ አላህ በታላቅ ምንዳ አበለጠ::

(96) 96. ከእርሱ ዘንድ በሆኑ ደረጃዎች አበለጠ:: ምህረትንም አደረገ:: እዝነትንም አዘነላቸው:: አላህ መሀሪና አዛኝ ነውና::

(97) 97. እነዚያ ለእምነት ሲሉ ባለመሰደድ ነፍሶቻቸውን በዳዮች ሆነው መላዕክት የገደሏቸው መላዕክት ለእነርሱ «በምን ነገር ላይ ነበራችሁ?» ይሏቸዋል። «በምድር ውስጥ ደካሞች ነበርን።» ይላሉ:: «የአላህ ምድር ትሰደዱባት ዘንድ ሰፊ አልነበረችምን?» ይሏቸዋል። እነዚያም መኖሪያቸው ገሀነም ናት:: ገሀነምም መመለሻነቷ ከፋች።

(98) 98. ከወንዶችና ከሴቶች ከህፃኖችም ሲሆኑ ከሀገራቸው ለመውጣት መላን የማይችሉና መንገድንም የማይመሩ ደካሞች ባለመሰደዳቸው ግን ምንም ቅጣት የለባቸዉም::

(99) 99. እነዚያ አላህ ከእነርሱ ይቅርታ ሊያደርግ ይሻል:: አላህም ይቅር ባይና መሀሪ ነውና::

(100) 100. በአላህ መንገድ የሚሰደድ ሁሉ በምድር ውስጥ ብዙ መሰደጃንና ምቾትን ያገኛል:: ወደ አላህና ወደ መልዕክተኛው ስደተኛ ሆኖ ከቤቱ የሚወጣና ከዚያ በመንገድ ላይ ሞት የሚያገኘው ምንዳው በእርግጥ በአላህ ዘንድ ተረጋገጠ:: አላህ መሀሪና አዛኝ ነውና::

(101) 101.(አማኞች) በምድር ላይ በተጓዛችሁ ጊዜ እነዚያ የካዱት ሊያውኳችሁ እንደሆነ ብትፈሩ ከሶላቶች መካከል ከፊሎችን (ባለ አራት አራት ረካአ የሆኑትን ቁጥራቸውን ወደ ሁለት ሁለት በመቀነስ) ብታሳጥሩ በእናንተ ላይ ኃጢአት የለም። ከሓዲያን ለእናንተ በእርግጥ ግልጽ ጠላቶች ናቸውና።

(102) 102.(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ) በጦርነት ላይ በመካከላቸው በሆንክና ሶላትን ለእነርሱ ባሰገድካቸው ጊዜ ከእነርሱ አንዱ ቡድን ካንተ ጋር ይቁም:: መሳሪያዎቻቸውንም ይያዙ:: ሱጁድ ባደረጉ ጊዜ ከበስተኋላችሁ ይሁኑ:: ከዚያም እነዚያ ቡድኖች ወደ ግንባር ይሂዱና ያልሰገዱት ሌሎች ቡድኖች ይምጡ :: ከዚያም ካንተ ጋር ይስገዱ:: ጥንቃቄያቸውንና መሳሪያዎቻቸውንም ይያዙ:: እነዚያ በአላህ የካዱት ከትጥቅና ስንቃችሁ ብትዘናጉና በአንድ ጊዜ ቢወሯችሁ ይመኛሉ:: ዝናብ አውኳችሁ ወይም በሽተኛ ሆናችሁ ትጥቃችሁን ብታስቀምጡ በእናንተ ላይ ኃጢአት የለባችሁም:: ጥንቃቄ አድርጉ:: አላህ ለካሐዲያን ሁሉ አዋራጅን ቅጣት አዘጋጀ::

(103) 103. ሶላትንም በፈጸማችሁ (በጨረሳችሁ) ጊዜ ቆማችሁ፣ ተቀምጣችሁና በጎኖቻችሁም ተጋድማችሁ አላህን አውሱ:: በተረጋጋችሁ ጊዜ ግን ሶላትን ደንቧን አሟልታችሁ ስገዱ:: ሶላት በአማኞች ላይ በጊዜያት የተወሰነች ግዴታ ናትና::

(104) 104.ሰዎቹንም ከመፈለግ አትስነፉ:: ስትቆስሉ የምትታመሙ ብትሆኑም እናንተ እንደምትታመሙ ሁሉ እነርሱም ይታመማሉ:: እናንተ ግን እነርሱ የማይከጅሉትን ከአላህ ትከጅላላችሁ:: አላህም ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነው::

(105) 105. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በሰዎች መካከል አላህ ባሳወቀህ ልትፈርድ ወደ አንተ መጽሐፉን በእውነት አወረድን:: እናም ለከዳተኞች ተከራካሪ አትሁን::

(106) 106. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህን ምህረት ለምነው:: አላህ መሀሪና አዛኝ ነውና::

(107) 107. ለእነዚያ ነፍሶቻቸውን ስለሚያታልሉት ሰዎች አትከራከር:: አላህ ከዳተኛንና ኃጢአተኛን ሰው አይወድምና::

(108) 108. ከሰው ይደበቃሉ:: አላህ በዕውቀቱ ከእነርሱ ጋር ሲሆን ከንግግር የማይወደውን ነገር በልቦቻቸው በሚያሳድሩ ጊዜ ከእርሱ አይደበቁም:: አላህ በሚሰሩት ሁሉ በእውቀቱ ከባቢ ነውና::

(109) 109. እነሆ እናንተ እነዚያ በቅርቢቱ ሕይወት ውስጥ ከእነርሱ ተከራከራችሁ:: በትንሳኤ ቀን አላህን ስለ እነርሱ የሚከራከርላቸው ማን ነው? ወይስ ለእነርሱ ሀላፊ የሚሆን ማን ነው?

(110) 110. መጥፎ ነገር የሚሰራ ወይም ነፍሱን የሚበድልና ከዚያም ተጸጽቶ አላህን ምህረት የሚለምን ሁሉ አላህን መሀሪና አዛኝ ሆኖ ያገኘዋል::

(111) 111. ኃጢአት የሚሰራም የሚሰራው ጥፋት ጉዳቱ በራሱ ላይ ብቻ ነው:: አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነውና::

(112) 112. ኃጢአትን ወይም ወንጀልን የሚሰራና ከዚያም በእርሱ ንጹህን የሚሰድብ ቅጥፈትንና ግልጽ ኃጢአትን በቁርጥ ተሸከመ::

(113) 113. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የአላህ ችሮታና እዝነቱ ባንተ ላይ ባልነበረ ኖሮ ከእነርሱ የሆነ ቡድኖች ሊያሳስቱህ ባሰቡ ነበር:: ነፍሶቻቸውን እንጂ ሌላ አያሳስቱም:: በምንም አይጎዱህም:: አላህ ባንተ ላይ መጽሐፍንና ጥበብን አወረደ:: የማታውቀውን ሁሉ አስተማረህ:: የአላህ ችሮታ ባንተ ላይ ታላቅ ነው::

(114) 114. ከውይይቶቻቸው መካከል በምጽዋት ወይም በበጎ ስራ ወይም በሰዎች መካከል በማስታረቅ ከሚያዙ ሰዎች ውይይት በስተቀር በብዙው ውይይት ውስጥ ደግ ነገር የለበትም:: ይህንንም የተባለውን የአላህን ውዴታ በመፈለግ ለሚሰራ ሁሉ ታላቅ ምንዳን እንሰጠዋለን::

(115) 115. ቅኑ መንገድ ለእርሱ ከተገለጸት በኋላ መልዕክተኛውን የሚቃረንና ከምዕመናኖቹ መንገድ ሌላ የሆነን የሚከተል ሁሉ በመረጠው ጥመት ላይ እንተወዋለን። ወደ ገሀነምም እናስገባዋለን:: መመለሻይቱም ገሀነም ከፋች።

(116) 116. አላህ በእርሱ ማጋራትን ፈጽሞ አይምርም:: ከሽርክ በታች (ሌላ) ያለውን ጥፋት ግን ለሚሻው ይምራል:: በአላህ የሚያጋራም ከእውነት የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ::

(117) 117. ከእርሱ ሌላ እንስት ጣኦታትን እንጂ አይገዙም:: አመጸኞች ሰይጣንንም እንጂ ሌላን አይገዙም::

(118) 118. አላህም የረገመውን (እንዲህ) ያለውንም ሰይጣን እንጂ አይከተሉም: «ከባሮችህ የተወሰነን ድርሻ በእርግጥ እይዛለሁ።

(119) 119. «በእርግጥ አጠማቸዋለሁ:: ከንቱን ምኞትም አስመኛቸዋለሁ:: አዛቸዉምና የእንስሶችን ጀሮዎች ይተለትላሉ:: አዛቸዉምና የአላህን ፍጥረት ይለውጣሉ።» (ያለውን ይከተላሉ።) ከአላህ ሌላ ሰይጣንን ረዳት አድርጎ የሚይዝ ግልጽ ኪሳራን በእርግጥ ከሰረ።

(120) 120. የማይፈጽመውን ከንቱ ተስፋ ይሰጣቸዋል:: ያስመኛቸዋልም:: ሰይጣን ለማታለል እንጂ ቃል አይገባላቸዉም::

(121) 121. እነዚያ የመጨረሻ መኖሪያቸው ገሀነም ናት:: ከእርሷም መሸሻን አያገኙም::

(122) 122. እነዚያ በአላህ ያመኑትና በጎ ስራዎችን የሰሩ ሁሉ በስራቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች ዘላለም በውስጣቸው ዘወታሪዎች ሲሆኑ እናስገባቸዋለን:: አላህ እውነተኛን ተስፋ ሰጣቸው:: በንግግርም ከአላህ ይበልጥ እውነተኛ ማን ነው?

(123) 123. ነገሩ በምኞታችሁና በመጽሐፉ ሰዎች ምኞት አይደለም:: መጥፎን የሚሰራ ሁሉ በእርሱ ይመነዳል:: ለእርሱም ከአላህ ሌላ ጠባቂን ረዳትንም አያገኝም::

(124) 124. ከወንድ ወይም ከሴት አማኝ ሆነው ከበጎ ስራዎች አንድንም ነገር የሚሰሩ ገነት ይገባሉ:: በተምር ፍሬ ላይ ያለችን ነጥብ ያክል እንኳን አይበደሉም።

(125) 125. መልካም ሰሪ ሆኖ ፊቱን ለአላህ ከሰጠና የኢብራሂምን መንገድ ቀጥተኛ ሲሆን ከተከተለ ሰው ይበልጥ ሃይማኖቱ ያማረ ማን አለ? አላህ ኢብራሂምን ፍጹም ወዳጅ አድርጎ ያዘው::

(126) 126. በሰማያትና በምድር ያለው ነገር ሁሉ የአላህ ነው:: አላህ በነገሩ ሁሉ በእውቀት ከባቢ ነው::

(127) 127. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ) ስለ ሴቶች ጉዳይ ይጠይቁሃል። «አላህ ስለነሱ ይነግራችኋል:: ያም በመጽሐፍ ውስጥ በእናንተ ላይ የሚነበበው ሲሆን በእነዚያ ከውርስ የተደነገገላቸውን ድርሻ በማትሰጧቸው ሴቶችና ልታገቧቸው በማትፈልጉት የቲሞች ሴቶች ይህንን እንዳታደርጉ፤ ህፃናት ለሆኑትም ደካሞች መብታቸውን እንድትሰጡ፤ ለየቲሞች በትክክል እንድትቆሙ ይነገራችኋል።» በላቸው:: ከበጎም ስራ የሆነን ማንኛውንም ስራ ብትሰሩ አላህ እርሱን አዋቂ ነው::

(128) 128. ሴት ልጅ ከባሏ ጥላቻን ወይም ከእርሷ ፊቱን ማዞሩን ብታውቅ እና ከዚያ በመካከላቸው እንደገና ቢስማሙ በሁለቱ ላይ ኃጢአት የለባቸዉም:: መታረቅ መልካም ነውና:: ነፍሶች ሁሉ ንፍገት ተጣለባቸው:: (ባሎች ሆይ!) መልካም ነገር ብትሰሩና ብትጠነቀቁ ግን አላህ በምትሰሩት ነገር ሁሉ ውስጠ አዋቂ ነው::

(129) 129. (ባሎች ሆይ! ) በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሴቶች መካከል ምንም እንኳን ብትጓጉ በፍቅር ለማስተካከል አትችሉም። ሆኖም እንደተንጠለጠለች (ገመድ) አድርጋችሁ ትተዋት ዘንድ ወደምትወዷት ሴት ሙሉ መዘንበልን አትንዘንበሉ:: ብታበጁና ብትጠነቀቁ አላህ መሀሪና አዛኝ ነው::

(130) 130. ባልና ሚስት በመሀከላቸው በተፈጠረው ችግር ቢለያዩ አላህ ሁሉንም በችሮታው ያብቃቃቸዋል:: አላህ ችሮታው ሰፊና ጥበበኛ ነውና::

(131) 131. በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ነው:: እነዚያንም ከበፊታችሁ መጽሐፍ የተሰጡትን እናንተንም አላህን ፍሩ በማለት በእርግጥ አዘዝን:: ብትክዱም በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ነው አትጎዱትም:: አላህ በራሱ ተብቃቂና ምስጉን ነውና::

(132) 132. በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ብቻ ነው:: መመኪያነትም በአላህ በቃ::

(133) 133. (እናንተ ሰዎች ሆይ!) አላህ ቢሻ ያስወግዳችሁና ሌሎችን በቦታችሁ ላይ ይተካል:: አላህም በዚህ ላይ ቻይ ነው::

(134) 134. የቅርቢቱን አለም ምንዳ የሚፈልግ ሁሉ አላህ ዘንድ የቅርቢቱና የመጨረሻይቱ ምንዳ አለ:: አላህ ሁሉን ሰሚ እና ሁሉን ተመልካች ነውና::

(135) 135. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በነፍሶቻችሁ ወይም በወላጆችና በቅርብ ዘመዶች ላይ ቢሆንም እንኳ በትክክል ለፍትህ ቋሚዎች ለአላህ መስካሪዎች ሁኑ:: ሀብታም ወይም ድሃ ቢሆንም አላህ ከእነርሱ ለእናንተ ይበልጥ ተገቢ ነው:: እንዳታዳሉም ዝንባሌን አትከተሉ:: ምስክርን ብታጣምሙ ወይም መመስከርን ብትተው አላህ በምትሰሩት ነገር ላይ ሁሉ ውስጠ አዋቂ ነው::

(136) 136. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልዕክተኛው በዚያ በመልዕክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍም ከዚያ በፊትም ባወረደው መጽሐፍ እመኑ:: በአላህ፣ በመላዕክቱ፣ በመጽሐፍቱ፣ በመልዕክተኞቹና በመጨረሻውም ቀን የካደ ሁሉ ከእውነት የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ።

(137) 137. እነዚያ ያመኑና ከዚያም የካዱ ከዚያም ያመኑ ከዚያም የካዱ ከዚያም ክህደትን የጨመሩ አላህ ለእነርሱ የሚምራቸውና ቅኑን መንገድም የሚመራቸው አይደሉም።

(138) 138. አስመሳዮችን ለእነርሱ አሳማሚ ቅጣት ያላቸው መሆኑን አብስራቸው::

(139) 139. እነዚያ ከአማኞች ሌላ ከሓዲያንን ወዳጆች አድርገው የሚይዙ ሰዎች እነርሱ ዘንድ ልቅናን ይፈልጋሉን? ልቅና ሁሉ ለአላህ ብቻ ነው::

(140) 140. በእናንተ ላይ በመጽሐፉ ውስጥ የአላህን አናቅጽ በእርሷ ሲካድባት በእርሷም ሲላገጥባት በሰማችሁ ጊዜ በሌላ ወሬ ውስጥ እስከሚገቡ ድረስ ከእነርሱ ጋር አትቀመጡ ማለትን በእርግጥ አወረደ:: እናንተ ያን ጊዜ ቢጤያቸው ናችሁና:: አላህ አስመሳዮችንም ከሓዲያንንም በገሀነም ውስጥ ሰብሳቢ ነውና::

(141) 141. እነዚያ (አስመሳዮች) በእናንተ ላይ የጊዜ መዘዋወርን የሚጠባበቁ ናቸው:: ለእናንተም ከአላህ የሆነ አሸናፊነት ሲኖራችሁ «ከናንተ ጋር አልነበርንምን?» ይላሉ:: ለከሓዲያን እድል ሲኖር ደግሞ «ከአሁን በፊት እኛ በእናንተ ላይ አልተሾምንባችሁምና (አልተውናችሁምን?) ከአማኞች አደጋስ አልከለከልናችሁምን?» ይላሉ:: አላህ በትንሳኤ ቀን በመካከላችሁ ይፈርዳል:: አላህ ለከሓዲያን በአማኞች ላይ መንገድን በፍጹም አያደርግም::

(142) 142. አስመሳዮች አላህን ያታልላሉ:: እርሱም አታላያቸው ነው:: ወደ ሶላትም በቆሙ ጊዜ ታካቾችና ሰዎችን የሚያሳዩ ሆነው ይቆማሉ:: አላህንም ጥቂትን እንጂ አያወሱም።

(143) 143. በዚህ መካከል ወላዋዮች ሆነው ይታያሉ:: ወደ እነዚህም ወደ እነዚያም አይደሉም:: አላህም ያሳሳተውን ለእርሱ የቅንነት መንገድን በፍጹም አታገኝለትም::

(144) 144. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከአማኞች ሌላ ከሓዲያንን ወዳጆች አድርጋችሁ አትያዙ:: ለአላህ በእናንተ ላይ ግልጽ ማስረጃዎችን ልታደርጉ ትፈልጋላችሁን?

(145) (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አስመሳዮች በእርግጥ ከእሳት በታችኛዋ አዘቅት ውስጥ ናቸው:: እናም ለእነርሱ ረዳትን አታገኝላቸዉም::

(146) 146. እነዚያ የተመለሱና ስራቸውን ያሳመሩ በአላህ የተጠበቁ ሃይማኖታቸውንም ለአላህ ፍጹም ያደረጉት ሲቀሩ:: እነዚያስ ከአማኞች ጋር ናቸው:: ለአማኞችም አላህ ታላቅን ምንዳ በእርግጥ ይሰጣል::

(147) 147. ብታመሰግኑና ብታምኑ አላህ እናንተን በመቅጣት ምን ያደርጋል? አላህም ወረታን መላሽ አዋቂ ነው::

(148) 148. አላህ በክፉ ንግግር መጮህን ከተበደለ ሰው ጩኸት በስተቀር አይወድም:: አላህ ሁሉን ሰሚ እና ሁሉን አዋቂ ነውና::

(149) 149. ደግ ነገርን ብትገልጹ ወይም ብትደብቁት ወይም ከመጥፎ ነገር (በደል) ይቅርታ ብታደርጉ አላህ ይቅር ባይ እና ቻይ ነው::

(150) 150. እነዚያ በአላህና በመልዕክተኞቹ የሚክዱ፤ በአላህና በመልዕክተኞቹም መካከል መለየትን የሚፈልጉና «በከፊሉ እናምናለን በከፊሉ ደግሞ እንክዳለን» የሚሉ ሁሉ በዚህ መካከል መንገድን ሊይዙ የሚፈልጉ፣

(151) 151. በእውነቱ እነዚያ ከሓዲያን እነርሱው ናቸው:: ለከሓዲያንም አዋራጅን ቅጣት አዘጋጅተናል::

(152) 152. እነዚያ በአላህና በመልዕክተኞቹ ያመኑ፤ ከእነርሱም መካከል በአንዱም ያልለዩ ሰዎች እነዚያ ምንዳዎቻቸው በእርግጥ ይሰጣቸዋል:: አላህ መሀሪና አዛኝ ነውና::

(153) 153. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የመጽሐፉ ባለቤቶች እነርሱ ላይ ከሰማይ መጽሐፍን እንድታወርድ ይጠይቁሃል:: ከዚህም የከበደን ጥያቄ ከዚህ በፊት ሙሳን በእርግጥ ጠይቀዋል:: «አላህን በግልጽ አሳየን።» ብለዋል:: በበደላቸዉም ምክንያት መብረቅ ያዘቻቸው:: ከዚያም ተዓምራት ከመጡላቸው በኋላ ወይፈኑን አምላክ አድረገው ያዙ:: ከዚያ ያንን ይቅር አልን:: ሙሳንም ግልጽ ስልጣን ሰጠነው::

(154) 154. በቃል ኪዳናቸው ምክንያት የጡር ተራራን ከበላያቸው አነሳን:: ለእነርሱም «ደጃፍን ስትገቡ አጎንብሳችሁ ግቡ።» አልን:: ለእነርሱም «በሰንበት ቀን ትዕዛዝን አትተላለፉ።» አልን:: ከእነርሱም ከባድን ቃል ኪዳን ያዝን::

(155) 155. ቃል ኪዳናቸውን በማፍረሳቸው፤ በአላህ አናቅጽ በመካዳቸው፤ ነብያትን ያለ አግባብ በመግደላቸውና «ልቦቻችን ሽፍን ናቸው።» በማለታቸውም ምክንያት ረገምናቸው:: በእውነቱ በክህደታቸው ምክንያት አላህ በእርሷ ላይ አተመ:: ስለዚህ ጥቂትን እንጂ አያምኑም::

(156) 156. በመካዳቸዉም በመርየም ላይ ከባድ ቅጥፈትን በመናገራቸው ምክንያት ረገምናቸው::

(157) 157. «እኛ የአላህ መልዕክተኛ የመርየም ልጅ አል መሲህ ዒሳን ገደልን።» በማለታቸውም ረገምናቸው:: አልገደሉትም:: አልሰቀሉትምም:: ግን የተገደለው ሰው ለእነርሱ በዒሳ ተመሰለባቸው:: እነዚያ በእርሱ ጉዳይ የተለያዩት በእርሱ መገደል በመጠራጠር ውስጥ ናቸው:: ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በእርሱ ነገር ምንም እርግጠኛ እውቀት የላቸዉም:: በእርግጥም አልገደሉትም::

(158) 158. ይልቁንስ አላህ ወደ እርሱ አነሳው:: አላህም አሸናፊና ጥበበኛ ነው::

(159) 159. ከመጽሐፉ ባለቤቶች መካከልም ከነብዩ ዒሳ ሞት በፊት በነብዩ ዒሳ በእርግጥ በትክክል የሚያምን እንጂ አንድም የለም:: በትንሳኤ ቀንም ዒሳ በእነርሱ ላይ መስካሪ ይሆናል::

(160) 160. ከእነዚያ ከአይሁዳውያን መካከል በፈጸሙት በደልና ሰዎችን ከአላህ መንገድ በብዙ በመከላከላቸው ምክንያት ለእነርሱ ተፈቅደው የነበሩ ጣፋጮች ምግቦችን እርም አደረግንባቸው::

(161) 161. ከእርሱ በቁርጥ የተከለከሉ ሲሆኑ አራጣን በመያዛቸውና የሰዎችን ገንዘቦች ያለ አግባቡ በመብላታቸዉም ምክንያት የተፈቀደላቸውን እርም አደረግንባቸው:: ከእነርሱም መካከከል ለከሓዲያን አሳማሚ ቅጣት አዘጋጀን::

(162) 162. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ግን ከእነርሱ ውስጥ በእውቀት የጠለቁት ክፍሎችና ትክክለኛ ምዕመናኖቹ ባንተ ላይ በተወረደውና ካንተ በፊት በተወረደው መጽሐፍ ያምናሉ። ሶላትንም ደንቡን ጠብቀው ሰጋጆቹ፣ ዘካንም ሰጪዎቹ በአላህና በመጨረሻው ቀንም ትክክለኛ አማኞቹን እነዚያ ታላቅ ምንዳን በእርግጥ እንሰጣቸዋለን::

(163) 163. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እኛ ወደ ኑህና ከእርሱ በኋላ ወደ ነበሩት ነብያት መልዕክታችንን እንዳወረድን ሁሉ ወደ አንተም ቁርኣንን አወረድን:: ወደ ነብዩ ኢብራሂም፤ ወደ ነብዩ ኢስማኢልም፤ ወደ ነብዩ ኢስሃቅም፤ ወደ ነብዩ የዕቆብም፤ ወደ ነገዶችም፤ ወደ ነብዩ ዒሳም፤ ወደ ነብዩ አዩብም፤ ወደ ነብዩ ዩኑስም፤ ወደ ነብዩ ሃሩንና ወደ ነብዩ ሱለይማን አወረድን:: ለነብዩ ዳውድም ዘቡርን ሰጠነው::

(164) 164. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከዚህም በፊት በአንተ ላይ በእርግጥ የተረክናቸውን መልዕክተኞች ባንተ ላይም ያልተረክናቸውንም መልዕክተኞች እንደላክን ሁሉ አንተን ላክንህ:: አላህ ነብዩ ሙሳንም ማነጋገርን አነጋገረው::

(165) 165. ከመልዕክተኞች በኋላ ለሰዎች በአላህ ላይ ምንም አስረጂ እንዳይኖራቸው አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች አድርገን መልዕክተኞችን ላክን:: አላህ ሁሉን አሸናፊ፤ ጥበበኛ ነውና::

(166) 166. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ ግን ባንተ ላይ ባወረደው ቁርኣን ይመሰክራል:: በእውቀቱ አወረደው:: መላዕክቱም ይመሰክራሉ:: መስካሪነትም በአላህ ብቻ በቃ::

(167) 167. እነዚያ በአላህ የካዱና ከአላህ መንገድም ሰዎችን ያገዱ ሰዎች ከእውነት የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳቱ::

(168) 168. እነዚያ የካዱና የበደሉ አላህ የሚምራቸውና ቅን መንገድን የሚመራቸው አይደለም::

(169) 169. ግን በውስጧ ለዘልዓለም ዘወታሪዎች ሲሆኑ የገሀነምን መንገድ ይመራቸዋል:: ይህም በአላህ ላይ ገር ነው::

(170) 170. እናንተ ሰዎች ሆይ! መልዕክተኛው እውነትን ከጌታችሁ አመጣላችሁ:: እናም ባመጣው እመኑ ለእናንተ የተሻለ ይሆናል:: በአላህ ብትክዱም እሱን (ቅንጣት) አትጎዱትም:: በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ነውና:: አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነው::

(171) 171. እናንተ የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ:: በአላህም ላይ እውነትን እንጂ አትናገሩ:: የመርየም ልጅ አል መሲህ ዒሳ የአላህ መልዕክተኛ ወደ መርየም የጣላት የሁን ቃሉና ከእርሱ የሆነ መንፈስ ብቻ ነው:: በአላህና በመላዕክተኞቹ እመኑ:: «አማልዕክት ሶስት ናቸው።» አትበሉ:: ተከልከሉ:: ለእናንተ የተሻለ ይሆናልና:: አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው:: ለእርሱም ልጅ ያለው ከመሆን የጠራ ነው:: በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የእርሱ ብቻ ነው:: መመኪያነትም በአላህ በቃ::

(172) 172. አል መሲህ ለአላህ ባሪያ ከመሆን ፈጽሞ አይጸየፍም:: ቀራቢዎች የሆኑ መላዕክትም እንዲሁ ለአላህ ባሪያ ከመሆን ፈጽሞ አይጸየፉም:: ወደ አላህ እርሱን ከመገዛት የሚጸየፉና የሚኮሩ ሁሉ አላህ ሁሉንም ወደ እርሱ በእርግጥ ይሰበስባቸዋል::

(173) 173. እነዚያ በአላህ ያመኑና መልካም ተግባራትን የሰሩትን ምንዳዎቻቸውን ይሞላላቸዋል:: ከችሮታዉም ይጨምርላቸዋል:: እነዚያን የተጸየፉትና የኮሩትን ግን አሳማሚውን ቅጣት ይቀጣቸዋል:: ከአላህ ሌላ ለእነርሱ ዘመድና ረዳት አያገኙም::

(174) 174. እናንተ ሰዎች ሆይ! ከጌታችሁ ዘንድ በእርግጥም አስረጅ መጣላችሁ:: ወደ እናንተም ገላጭ የሆነን ብርሃንን (ቁርኣንን) አወረድን::

(175) 175. እነዚያማ በአላህ ያመኑና በእርሱ የተጠበቁ ሰዎች ከእርሱ በሆነው እዝነትና ችሮታ ውስጥ እርግጥ ያስገባቸዋል:: ወደ እርሱም ቀጥተኛ መንገድን ይመራቸዋልም::

(176) 176. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ይጠይቁሃል: «ወላጆችና ልጅ ሳይኖረው በሚወረስ ሟች ሰው ጉዳይ አላህ ይነግራችኋል።» በላቸው፡፡ ልጅ የሌለው ሰው ቢሞትና ለእርሱ እህት ብትኖረው ለእርሷ ከተወው ንብረት ግማሽ አላት፡፡ እርሱም ለእርሷ ልጅ የሌላት እንደሆነች በሙሉ ይወርሳታል፡፡ ሁለት እህቶች ወይም ከሁለት በላይ ቢሆኑ ግን ከተወው ንብረት ከሶስት ሁለት እጅ አላቸው ፡፡ ወንድሞችና እህቶች ወንዶችና ሴቶች ቢሆኑ ደግሞ ለወንድ የሁለት ሴቶች ድርሻ ያህል አለው ፡፡ አላህ እንዳትሳሳቱ ህግጋትን ለእናንተ ያብራራል ፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ አዋቂ ነውና፡፡