(1) 1. (ነፍስን (ሩህን)) በኃይል መንጫቂዎች በሆኑት፤
(2) 2. በቀስታ መምዘዝን መዛዦች በሆኑትም፤
(3) 3. መዋኘትንም ዋኚዎች በሆኑት፤
(4) 4. መቅደምንም ቀዳሚዎች በሆኑት፤
(5) 5. ጉዳይንም አስተናባሪዎች በሆኑት መላዕክት እምላለሁ (በእርግጥ ትቀሰቀሳላችሁ)።
(6) 6. (ይህም የሚሆነው) ተርገፍጋፊይቱ (ምድር) በምትርገፈገፍበት ቀን፤
(7) 7. ተከታይቱም በምትከተላት ቀን (ትቀሰቀሳላችሁ)።
(8) 8. በዚያ ቀን ልቦች ተሸባሪዎች ናቸው::
(9) 9. ዓይኖቻቸው ተዋራጆች (አቀርቃሪዎች) ናቸው።
(10) 10. «እኛ ወደ መጀመሪያይቱ ሁኔታ ተመላሾች ነን እንዴ?» ይላሉ።
(11) 11. የበሰበሱ አጥንቶች በሆንን ጊዜ እንደገና እንቀሰቀሳለን?
(12) 12. «እንዲያማ ከሆነ ያች የኪሳራ መመለስ ናታ!» ይላሉ።
(13) 13. እርሷን (እውን የምታደርጋት) አንዲት ጩኸት ብቻ ናት።
(14) 14. ወዲያውኑ በንቃት ላይ ናቸው።
(15) 15. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የሙሳ ወሬ መጣልህን?
(16) 16. ጌታው በተቀደሰው ጡዋ ሸለቆ በጠራው ጊዜ፤
(17) 17. ወደ ፈርዖን ሂድ፤ ወሰን አልፏልና::
(18) 18. (እንዲህም) በለው: «እራስህን ለማጥራት ታስባለህን?
(19) 19. ጌታህንም ትፈራ ዘንድ መንገዱን ልመራህ፤ (ታስባለህን?)»
(20) 20. (ሙሳ ለፈርዖን) ታላቁንም ተዐምር አሳየው።
(21) 21. አስተባበለም፤ አመጸም፤
(22) 22. ከዚያ ለመጥፋት የሚተጋ ሆኖ ዞረ::
(23) 23. (ህዝቡን) ሰበሰበም ተጣራም።
(24) 24. እኔ «ታላቁ ጌታችሁ ነኝ» አለም።
(25) 25. አላህም በኋለኛይቱና በፊተኛይቱ ቃል ቅጣት ያዘው::
(26) 26. በዚህ ውስጥ አላህን ለሚፈሩ በእርግጥ ማስጠንቀቂያ አለበት።
(27) 27. በአፈጣጠር እናንተ ይበልጥ የበረታችሁ ናችሁን? ወይስ ሰማይ? (አላህ) ገነባት::
(28) 28. ከፍታዋን አጓነ አስተካከላትም።
(29) 29. ሌሊቷንም ሸፈነ፤ ቀኗንም ግልጽ አደረገ።
(30) 30. ምድርንም ከዚያ በኋላ ዘረጋት።
(31) 31. ውሃዋንና ግጦሿን ከእርሷ አወጣ::
(32) 32. ጋራዎችንም አደላደላቸው።
(33) 33. ለእናንተም ለእንስሶቻችሁም መጣቀሚያ ይሆን ዘንድ (ይሄን አደረገ)።
(34) 34. ታላቂቱም መዓት በመጣች ጊዜ፤
(35) 35. ሰው ሁሉ የሰራውን የሚያስታውስበት ቀን፤
(36) 36. ገሀነምም ለሚያይ ሰው በተገለጠች ጊዜ፤
(37) 37. የካደ ሰውማ፤
(38) 38. ቅርቢቱንም ሕይወት የመረጠ፤
(39) 39. በእርግጥ መኖሪያው ጀሀነም ናት።
(40) 40. በጌታው ፊት መቆምን የፈራና ነፍሱንም ከዝንባሌዋ የከለከለማ፤
(41) 41. በእርግጥ መኖሪያው ገነት ናት።
(42) 42. ስለሰዓቲቱም መነሻዋ መቼ እንደሆነ ይጠይቁሃል።
(43) 43. (ለመሆኑ አንተ ስለዚያች እለት) በመወሳቷ ምን ላይ አለህበትና?
(44) 44. የእርሷ ጉዳይ የሚመለሰው ወደ ጌታህ ብቻ ነው::
(45) 45. አንተ ያለብህ ለሚፈራት ሰው ሁሉ ስለ እርሷ (ከወዲሁ) ማስጠንቀቅ ነው።
(46) 46. እነርሱ የሚያይዋት ቀን የአንዲትን ቀን ምሽት ወይም ረፋዷን እንጂ ያልቆዩ ይመስላሉ::