(1) 1. ፊቱን አጨፈገገ፤ ዞረም፤
(2) 2. ዓይነስውሩ ወደ እርሱ ስለመጣ።
(3) 3. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ምን ያሳውቅሃል? ምን አልባትም (ይህ አይነስውር ሰው ካንተ በሚሰማው ምክር ከኃጢአቶቹ) ሊጥራራ ይከጀላል::
(4) 4. ወይም ሊገሰጽና ግሳጼይቱም ልትጠቅመው ይከጀላል::
(5) 5. ያ! ከአላህ የተብቃቃውን ሰውማ፤
(6) 6. አንተ ለእርሱ ትዘጋጃለህ።
(7) 7. ባይጥራራ (ባያምን)፤ ባንተ ላይ ምንም የሌለብህ ስትሆን፤
(8) 8. ያ! እየገሰገሰ የመጣህ ሰውማ፤
(9) 9. እርሱ አላህን የሚፈራ ሲሆን፤
(10) 10. አንተ ከእርሱ ትዘናጋለህ::
(11) 11. ተከልከል፤ (ቁርኣን) ማስገንዘቢያ ነው::
(12) 12. የፈለገ ሰው ሁሉ (ቁርኣኑን) ያስታውሰዋል::
(13) 13. በተከበሩት ጹሑፎች ውስጥ ነው::
(14) 14. ከፍ በተደረገች፤ ንጹህም በተደረገች (ጹሑፍ ውስጥ ነው)።
(15) 15. በጸሐፊዎች መላዕክት እጆች (ንጹህ የተደረገ)::
(16) 16. የተከበሩና ታዛዦች በሆኑት ጸሐፊዎች (እጆች)፤
(17) 17. ሰው ተረገመ። ምን ከሓዲ አደረገው?
(18) 18. (ጌታው) ከምን ነገር ፈጠረው?
(19) 19. (አያስብምን?) ከፍትወት ጠብታ ፈጠረው፤ መጠነዉም::
(20) 20. ከዚያም (መውጫ) መንገዱን አገራው::
(21) 21. ከዚያም ገደለው:: እንዲቀበርም አደረገው፤
(22) 22. ከዚያ ማንሳቱን በፈለገ ጊዜ ያስነሳዋል::
(23) 23. በእውነት ያንን ጌታው ያዘዘውን ገና አልፈጸመም::
(24) 24. ሰው ወደ ምግቡ ይመልከት፤
(25) 25. እኛ ውሃን ማንቧቧትን ያንቧቧን መሆናችንን፤
(26) 26. ከዚያ ምድርን በደካማ ቡቃያ መሰንጠቅን የሰነጠቅን፤
(27) 27. በውስጧም እህልን ያበቀልን
(28) 28. ወይንም እርጥብ ሳርንም፤
(29) 29. የዘይት ወይራንም ዘንባባንም፤
(30) 30. ጭፍቆች አትክልቶችንም፤
(31) 31. ፍራፍሬንና፤ ገለባንም (ያበቀልን መሆናችንን ይመልከት)።
(32) 32. ለእናንተም ለእንሰሶቻችሁም መጠቀሚያ ይሆን ዘንድ (ይህን ሰራን)::
(33) 33. አደንቋሪይቱ (መከራ) በመጣች ጊዜ፤
(34) 34. ሰው ከወንድሙ በሚሸሽበት ቀን፤
(35) 35. ከእናቱም፤ ከአባቱም፤ (በሚሸሽበት ቀን)
(36) 36. ከሚስቱና ከልጁም፤ (በሚሸሽበት ቀን)
(37) 37. ከእነርሱ ለየሰው ሁሉ በዚያ ቀን ከሌላው የሚያብቃቃው ሁኔታ አለው::
(38) 38. ፊቶች በዚያ ቀን አብሪዎች፤
(39) 39. ሳቂዎችና ተደሳቾች ናቸው::
(40) 40. ፊቶች ደግሞ በዚያ ቀን በላያቸው ላይ ትብያ አለባቸው።
(41) 41. ጥቁረት ትሸፍናቸዋለች፤
(42) 42. እነዚያ እነርሱ በአላህ ከሓዲያን እና በትዕዛዙ ላይ አመጸኞቹ ናቸው።