18 - Al-Kahf ()

|

(1) 1-ምስጋና ሁሉ ለዚያ መጽሐፉን በውስጡ ቅንጣት መጣመምን ሳያደርግ በባሪያው (በሙሐመድ) ላይ ላወረደው ለአላህ ብቻ ይገባው::

(2) 2. ቀጥተኛ ሲሆን ከርሱ ዘንድ የሆነን ብርቱን ቅጣት ሊያስፈራራበት፤ እነዚያንም በጎ ሰሪዎችን ለእነርሱ መልካም ምንዳ ያላቸው መሆኑን ሊያበስርበት (አወረደው)

(3) 3. በውስጡም ዘለዓለም የሚቆዩ መሆናቸውን ሊያበስርበት አወረደው።

(4) 4. እነዚያንም «አላህ ልጅን ይዟል።» ያሉትን ሊያስፈራራበት (ቁርኣንን አወረደው።)

(5) 5.ለእነርሱም ሆነ ለአባቶቻቸው ስለ አላህ ልጅ መኖር ምንም እውቀት የላቸዉም:: ከአፎቻቸው የሚወጣው ቃል ምን አከበደው! ውሸትን እንጂ ሌላን አይናገሩም::

(6) 6. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በዚህም ንግግር በቁርኣን ካላመኑ በፈለጎቻቸው ላይ በቁጭት ነፍስህን አጥፊ ልትሆን ይፈራልሀል::

(7) 7.እኛ ማንኛቸው ሥራው ያማረ መሆኑን ልንፈትናቸው በምድር ላይ ያለን ሁሉ የእርሷ ጌጥ አደረግን::

(8) 8. እኛ በእርሷ ላይ ያለውን ሁሉ በመጨረሻ ቡቃያ የሌለበት ምልጥ አፈር አድራጊዎች ነን::

(9) 9-(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የዋሻውና የሰሌዳው ባለቤቶች ከተዓምራታችን ሲሆኑ ግሩም መሆናቸውን አሰብክን?

(10) 10. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ወጣቶቹ ወደ ዋሻው በተጠጉና: «ጌታችን ሆይ! ካንተ ዘንድ እዝነትን ስጠን:: ለእኛም ከነገራችን ቅንን ነገር አዘጋጅልን።» ባሉ ጊዜ (የሆነውን ታሪክ አስታውስ።)

(11) 11. በዋሻዉም ውስጥ የተቆጠሩን ዓመታት በጆሮዎቻቸው ላይ መታንባቸው (አስተኛናቸው)::

(12) 12.ከዚያም ከሁለቱ ክፍሎች ለቆዩት ጊዜ ልክ ያረጋገጠው ማንኛው መሆኑን ልናውቅ ከተኙበት አስነሳናቸው::

(13) 13. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እኛ ወሬያቸውን ባንተ ላይ በእውነት እንተርክልሃለን:: እነርሱ በጌታቸው በትክክል ያመኑ ወጣቶች ናቸው:: ወደ ቀናው መንገድ መመራትንም ጨመርንላቸው::

(14) 14. በንጉሳቸው ፊት በቆሙና እንዲህም ባሉ ጊዜ ልቦቻቸውን በእምነት አጠነከርን: «ጌታችን የሰማያትና የምድር ጌታ ነው:: ከእርሱ ሌላ አምላክን አንገዛም:: ከእሱ ሌላን ብናመልክማ ወሰን ያለፈን ንግግር በእርግጥ ተናገርን።

(15) 15. «እነዚህ ህዝቦቻችን ከእርሱ ሌላ አማልክትን ያዙ:: እውነተኞች ከሆኑ በእነርሱ ላይ ግልጽ ማስረጃን ለምን አያመጡም? በአላህ ላይ ውሸትን ከሚቀጣጥፍ ይበልጥ በዳይ ማን ነው?» አሉ።

(16) 16. «እነርሱንና ያንን ከአላህ ሌላ የሚገዙትን በተለያችሁ ጊዜ ወደ ዋሻው ተጠጉ። ጌታችሁ ለእናንተ ከችሮታው ይዘረጋላችኋልና፤ ከነገራችሁም ለእናንተ መጠቃቀሚያ ያዘጋጅላችኋልና።» (ተባባሉ)

(17) 17.ጸሐይዋ በወጣች ጊዜ ከዋሻቸው ወደ ቀኝ ጎን ስታዘነብል ታያታለህ:: በገባችም ጊዜ ከሰፊው ዋሻ ውስጥ እያሉ በግራ በኩል ትተዋቸዋለች:: ይህ ከአላህ ተዓምራት አንዱ ነው:: አላህ ያቀናው በእርግጥም የተቀናው እርሱ ብቻ ነው:: እርሱ ያጠመመውን ደግሞ ቅኑን መንገድ የሚመራው ረዳት ማንንም አታገኝለትም::

(18) 18. እነርሱ በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ እያሉ የነቁ ይመስሉሃል:: ወደቀኝና ወደ ግራ ጎናቸው እናገላብጣቸዋለን:: ውሻቸዉም በዋሻቸው በር ላይ የፊት እግሩን ዘርግቷል:: ብታያቸው ኖሮ ከእነርሱ በእርግጥ የምትሸሽ ኾነህ በዞርክ ነበር:: በፍርሀትም በተሞላህ ነበር::

(19) 19. ልክ እንዳስተኛናቸውም ሁሉ በመካከላቸው እንዲጠያየቁም ቀሰቀስናቸው:: ከእነርሱ አንድ ተናጋሪ «ምን ያህል ቆያችሁ አለ?» ሌሎቹም «አንድን ቀን ወይም የቀንን ከፊል ቆየን።» አሉ። ተባባሉም: «ጌታችሁ የቆያችሁትን ጊዜ ልክ አዋቂ ነው:: ከዚህም ገንዘባችሁ ጋር አንዳችሁን ወደ ከተማይቱ ላኩ:: ከምግብ የትኛዋ ንጹህ መሆኗንም ይመልከት:: (ከንጹሑ) ምግብን ያምጣላችሁ:: ቀስም ይበል:: በእናንተም አንድንም ሰው አያሳውቅ።

(20) 20. «እነርሱ በእናንተ ላይ ቢዘልቁ ይቀጠቅጧችኋል:: ወይም ወደ ሃይማኖታቸው ይመልሷችኋል፤ ያን ጊዜም በፍጹም ፍላጎታችሁን አታገኙም።» ተባባሉ።

(21) 21. ልክ እንደዚሁም የአላህ ቀጠሮ እርግጠኛ መሆኑን ሰዓቲቱም በእርሷ ጥርጣሬ የሌለ መሆኑን ያውቁ ዘንድ በእነርሱ ላይ ሰዎችን አሳወቅን:: አማኞቹና ከሓዲያን ነገራቸውን በመካከላቸው ሲከራከሩ የሆነውን አስታውስ:: ከሓዲያን «በእነርሱ ላይ ግንብን ገንቡ።» አሉ:: ጌታቸው ለእነርሱ ይበልጥ አዋቂ ነው:: እነዚያ በነገራቸው ላይ ያሸነፉት ግን «በእነርሱ ላይ በእርግጥ መስጊድን እንሰራለን።» አሉ።

(22) 22. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) (ስለ እነርሱ የተወሰኑ ቡድኖች በጥርጣሬ) «ሶስት ናቸው አራተኛው ውሻቸው ነው።» ይላሉ:: (ሌሎች ቡድኖች) «አምስት ናቸው ስድስተኛው ውሻቸው ነው።» ይላሉ። በሩቅ ወርዋሪዎች ሆነው (ባላወቁት አለም) ሲገምቱ። (ሶስተኛው ቡድን ደግሞ) «ሰባት ናቸው ስምንተኛቸው ውሻቸው ነዉ።» ይላሉ:: «ጌታዬ ብቻ ቁጥራቸውን አዋቂ ነው:: ጥቂት ሰው እንጂ አያውቃቸዉም።» በላቸው:: እናም በእነርሱ ነገር ግልጽን ክርክር እንጂ ጠልቀህ አትከራከር:: በእነርሱም ጉዳይ ከመጽሐፉ ሰዎች አንድንም አትጠይቅ::

(23) 23 ለማንኛዉም ነገር «እኔ ይህንን ነገ ሠሪ ነኝ።» አትበል።

(24) 24. «አላህ ቢሻ እሠራዋለሁ።» ብትል እንጂ። በረሳህ ጊዜም ጌታህን አውሳ። «ጌታዬም ከዚህ ይበልጥ ለቀጥታ የቀረበን ሊመራኝ ይከጀላል» በላቸው።

(25) 25. በዋሻቸዉም ውስጥ ሶስት መቶ ዓመታትን ቆዩ:: ዘጠኝ አመታትንም ጨመሩ::

(26) 26.(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «አላህ ብቻ የቆዩትን ልክ በትክክል አዋቂ ነው። የሰማያትና የምድር ሚስጢር የእሱ ብቻ ነዉ። እርሱ (አላህ) ሁሉን ተመልካች ሁሉን ሰሚ መሆኑ ይግረምህ። ለእነርሱ ከእርሱ በስተቀር ምንም ወዳጅ የላቸዉም:: በፍርዱም አንድንም አያጋራም።» በላቸው።

(27) 27.(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከጌታህ መጽሀፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ:: ለቃሎቹ ለዋጭ የላቸዉም:: ከርሱም በስተቀር መጠጊያን በፍጹም አታገኝም።

(28) 28. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ነፍስህንም ከእነዚያ ጌታቸውን ፊቱን የሚሹ ሆነው በጥዋትና በማታ ከሚገዙት ጋር አስታግስ:: የቅርቢቱንም ህይወት ሽልማት የምትሻ ሆነህ አይኖችህ ከእነርሱ ወደ ሌላ አይለፉ:: ያ ልቡን እኛን ከማስታወስ ያዘነጋነውንና የግል ፍላጎቱን የተከተለውን ነገሩ ሁሉ ወሰን ማለፍ የሆነውን ሰው አትታዘዝ።

(29) 29. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ሰዎች ሆይ! እውነቱ ሁሉ ከጌታችሁ ነው:: ስለዚህ የፈለገም ሰው በእውነቱ ይመን:: የፈለገም ሰው ይካድ።» በላቸው:: እኛ ለበደለኛ ከሓዲያን አጥሯ በእነርሱ ላይ የከበበ የሆነችውን እሳት አዘጋጅተናል:: ከጥም ለመዳን እርዳታን ቢፈልጉ እንደ ዘይት ዝቃጭ ባለ ፊቶችን በሚጠብስ ውሃ ይረዳሉ:: መጠጡም ከፋ፤ መደገፊያይቱም ምንኛ አስከፋች!

(30) 30. እነዚያ በአላህ ያመኑና መልካም ሥራዎችን የሠሩ እኛ ሥራ ያሳመረን ምንዳ አናጠፋም።

(31) 31.እነዚያ ለእነርሱ የመኖሪያ ገነቶች ከስሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው አሏቸው:: በእርሷ ውስጥ ከወርቅ የሆኑን አምባሮች ይሸለማሉ:: ከቀጭን ሀርና ከወፍራም ሀርም አረንጓዴ ልብሶችን ይለብሳሉ:: በውስጧ በባለ አጎበር አልጋዎች ላይ የተደገፉ ሆነው ይቀመጣሉ:: እነዚህ ሰዎች ምንዳቸው ምን ያምር! መኖሪያቸው ገነትም ምንኛ አማረች!

(32) 32. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለከሓዲያን የሁለትን ሰዎችን ምሳሌ ግለጽላቸው:: ለአንደኛው ከሓዲ ሁለት የወይን አትክልቶች አደረግንለት። በዘንባባም ከበብናቸው። በመካከላቸውም አዝመራን አደረግን።

(33) 33. ሁለቱም አትክልቶች ሰብላቸውን ሰጡ፤ ከርሱም ምንም አላጎደሉም። በመካከላቸዉም ወንዝን አፈሰስን።

(34) 34.ለእርሱ ከአትክልቶቹ ሌላ ፍሬያማ ሀብት ነበረው:: ለአማኙ ጓደኛዉም የሚወዳደረው ሲሆን «እኔ ካንተ በገንዘብ ይበልጥ የበዛሁ በወገንም ይበልጥ የበረታሁ ነኝ።» አለው።

(35) 35. እርሱም ነፍሱንም በዳይ ሆኖ ወደ አትክልቱ ገባ። (እንዲህም) አለ: «ይህች አትክልት መቸም ትጠፋለች ብዬ አልጠረጥርም።

(36) 36. «ሰዓቲቱንም ትከሰታለች ብዬ አልጠረጥርም፤ እንደምትለው ወደ ጌታዬም ብመለስ ከእርሷ የበለጠን መመለሻ በእርግጥ አገኛለሁ።» አለው።

(37) 37. አማኙ ጓደኛውም ለእርሱ የሚመላለሰው ሲሆን (እንዲህ) አለው: «በዚያ ከአፈር ከዚያም ከፍትወት ጠብታ በፈጠረህ ከዚያም ሰው ባደረገህ ሃያል አምላክ ካድክን?

(38) 38. «እኔ ግን አላህ ጌታዬ ነው እላለሁ። በጌታዬም አንድንም አላጋራም።

(39) 39. «እኔን በገንዘብም ሆነ በልጅ ካንተ በጣም ያነስኩ ሆኜ ብታየኝም ወደ አትክልትህ በገባህ ጊዜ ‹አላህ የሻው ሆኗል። በአላህ ቢሆን እንጂ ብልሃትም የለም› አትልም ኖሯልን?

(40) 40. «ጌታዬ ከአትክልትህ የበለጠን ሊሰጠኝ በአትክልትህ ላይ ደግሞ በሰማይ መብረቆችን ሊልክባትና የምታንዳልጥ ምልጥ ምድር ልትሆንም ይቻላል።

(41) 41. «ወይም ውሀው ሰራጊ ሊሆንብህ ይችላል። ያን ጊዜ እርሱን መፈለጉን ፈጽሞ አትችልም።» አለው።

(42) 42. ሀብቱም ተጠፋ:: እርሷ በዳሶችዋ ላይ የወደቀች ሆና በእርሷ ባወጣው ገንዘብ ላይ የተጸጸተ መዳፎቹን የሚያገላብጥና «ወይ ጸጸቴ! በጌታዬ አንድንም ባላጋራሁ።» የሚል ሆነ።

(43) 43.እርሱም ከአላህ ሌላ የሚረዱት ቡድኖች አልነበሩትም:: ተረጂም አልነበረም::

(44) 44.እዚያ ዘንድ በትንሳኤ ቀን ስልጣኑ እውነተኛ ለሆነው ለአላህ ብቻ ነው:: እርሱ በመመንዳት የበለጠ ፍጻሜንም በማሳመር የበለጠ ነው::

(45) 45. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለእነርሱም የቅርቢቱን ህይወት ምሳሌ አውሳላቸው:: እርሷ ከሰማይ እንዳወረድነው ውሃ በእርሱም የምድር ቡቃያ እንደተቀላቀለበት፤ ከተዋበ በኋላም ደርቆ ንፋሶች የሚያበኑት ደቃቅ እንደሆነ ብጤ ናት:: አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው::

(46) 46. ገንዘብና ልጆች የቅርቢቱ ህይወት ጌጦች ብቻ ናቸው:: መልካም ቀሪ ሥራዎች ግን በጌታህ ዘንድ በምንዳ በላጭ ናቸው:: በተስፋም በላጭ ናቸው::

(47) 47. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ተራራዎችን የምናስኬድበትን ቀን አስታውስ:: ምድርንም ግልጽ ሆና ታያታለህ:: እንሰበስባቸዋለንም:: ከእነርሱ አንድንም አንተዉም::

(48) 48. የተሰለፉ ሆነው በጌታህ ላይ ይቀርባሉ:: ይባላሉም «በመጀመሪያ ጊዜ እንደፈጠርናችሁ በእርግጥ ወደ እኛ መጣችሁ:: በእውነቱ ለእናንተ የመቀስቀሻ ጊዜን አናደርግም መስሏችሁ ነበር።»

(49) 49 ለሰው ሁሉ መጽሐፉ ይቀርባል:: ወዲያዉም ከሓዲያንን በውስጡ ካለው ነገር ፈሪዎች ሆነው ታያቸዋለህ። «ዋ ጥፋታችን! ይህ መጽሐፍ ከሥራ ትንሽንም ትልቅንም የቆጠራት ቢሆን እንጂ የማይተወው ምን አለው?» ይላሉ:: የሠሩትንም ነገር ሁሉ ቅርብ ሆኖ ያገኙታል:: ጌታህም አንድንም አይበድልም::

(50) 50. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለመላዕክት «ለአደም ስገዱ።» ባልናቸው ጊዜ (የሆነውን አስታውስ):: ወዲያዉም ዲያብሎስ ብቻ ሲቀር ሁሉም ሰገዱ:: ከአጋንንት ጎሳ ነበርና:: ከጌታዉም ትዕዛዝ ወጣ:: እርሱንና ዘሮቹን እነርሱም ለእናንተ ጠላቶች ሲሆኑ ከኔ ሌላ ረዳቶች ታደርጋላችሁን? ለበዳዮች ልዋጭነቱ ከፋ::

(51) 51.የሰማያትና የምድርም አፈጣጠር አላሰየኋቸዉም:: የነፍሶቻቸውንም አፈጣጠር እንደዚሁ አሳሳቾችንም ረዳቶች አድርጌ የምይዝ አይደለሁም::

(52) 52. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እነዚያንም አምላክ የምትሏቸውን ተጋሪዎቼን ጥሩ።» የሚልበትን ቀን አስታውስ:: ይጠሯቸዋልም። ግን አይመልሱላቸዉም:: በመካከላቸዉም መጥፊያን ስፍራ ገሀነምንም አደረግን።

(53) 53. ከሓዲያንም እሳትን ያያሉ፤ እነርሱም በውስጧ ወዳቂዎች መሆናቸውን ያረጋግጣሉ:: ከእርሷም መሸሻን አያገኙም።

(54) 54. በዚህም ቁርኣን ውስጥ ከየምሳሌው ሁሉ ለሰዎች መላልሰን ገለጽን፤ ሰዉም ከነገሩ ሁሉ ይበልጥ ክርክረ ብዙ ነው::

(55) 55.ሰዎችንም መመሪያ በመጣላችሁ ጊዜ ከማመንና ጌታቸውንም ምህረትን ከመለመን የከለከላቸው የመጀመሪያዎቹ ህዝቦች ልማድ መጥፋት ልትመጣባቸው ወይም ቅጣቱ በየዓይነቱ ሊመጣባቸው መጠባበቅ ብቻ እንጂ ሌላ አይደለም::

(56) 56. መልዕክተኞችንም አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች ሆነው እንጂ አንልክም:: እነዚያ የካዱትም በውሸት እውነቱን በእሱ ሊያበላሹ ይከራከራሉ:: አንቀፆቼንና በእርሱ የተስፈራሩበትንም ነገር ማላገጫ አድርገው ያዙ::

(57) 57.በጌታዉም አናቅጽ ከተገሰጸና ከእርሷም ከዞረ፤ ሁለት እጆቹም ያስቀደሙትን ነገር ከረሳቸዉም ይበልጥ በዳይ ማን ነው? እኛ በልቦቻቸው ላይ እንዳያውቁት ሽፋኖችን፤ በጆሮዎቻቸዉም ውስጥ ድንቁርናን አደረግን። (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ወደ መመራትም ብትጠራቸው ያን ጊዜ ፈጽሞ አይመሩም::

(58) 58. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህም በጣም መሀሪው የእዝነት ባለቤት ነው:: በሠሩት ሥራ ቢይዛቸው ኖሮ ቅጣቱን ለእነርሱ ባስቸኮለባቸው ነበር:: ግን ለእነርሱ ከእርሱ ሌላ መጠጊያን ፈጽሞ የማያገኙበት ቀጠሮ አላቸው::

(59) 59.እነዚህ ከተሞችም በበደሉ ጊዜ አጠፋናቸው፤ ለመጥፊያቸዉም የተወሰነ ጊዜ አደረግን::

(60) 60. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሙሳ ለወጣቱ «የሁለቱን ባህሮች መገናኛ እስከምደርስ ወይም ብዙን ጊዜ እስከምሄድ ድረስ ከመጓዝ አልወገድም።» ያለውን (አስታውስ)

(61) 61. የሁለቱን ባህር መገናኛ በደረሱም ጊዜ ዓሳቸውን ረሱ፤ ዓሳውም መንገዱን በባህር ውስጥ ቀዳዳ አድርጎ ያዘ።

(62) 62. ባለፉም ጊዜ ለወጣቱ «ምሳችንን ስጠን ከዚህ ጉዟችን በእርግጥ ድካምን አግኝተናልና።» አለ።

(63) 63. «አየህን? ወደ ቋጥኟ በተጠጋን ጊዜ እኔ ዐሳውን ረሳሁ፤ ሰይጣን እንጂ ሌላ አላስረሳኝም፤ በባህሩም ውስጥ መንገዱን አስደናቂ መንገድ አድርጎ ያዘ።» አለ።

(64) 64. ሙሳም «ይህ እኮ እንፈልገው የነበረው ነው።» አለው። ከዚያ በኮቴዎቻቸው (ዱካቸው) ላይ እየተከተሉ ተመለሱ።

(65) 65.ከባሮቻችንም ከእኛ ዘንድ ችሮታን የሰጠነውን ከኛም ዘንድ እውቀትን ያስተማርነውን አንድን ባሪያችንን አገኙ::

(66) 66. ሙሳ «ለእርሱ ከተማርከው ነገር ቀጥተኛን እውቀት ታስተምረኝ ዘንድ ልከተልህ?» አለው።

(67) 67. ባሪያዉም አለ: «አንተ ከእኔ ጋር መታገስን በጭራሽ አትችልም።

(68) 68. «በእውቀት ባልደረስክበት ነገር ላይስ እንዴት ትታገሳለህ?»

(69) 69. ሙሳም «አላህ የፈለገ እንደሆነ ታጋሽና ላንተ ትዕዛዝን የማልጥስ ሆኜ ታገኘኛለህ።» አለው።

(70) 70. «ብትከተለኝም ላንተ ከእርሱ ማውሳትን እስከምጀምርልህ ድረስ ከምንም ነገር እንዳትጠይቀኝ።» አለው።

(71) 71. ሄዱም:: በመርከቢቱም በተሳፈሩ ጊዜ መርከቢቱን ቀደዳት። «ባለቤቶችዋን ልታሰምጥ ቀደድካትን? ትልቅን ጥፋት በእርግጥ ሠራህ።» አለው።

(72) 72. «አንተ ከእኔ ጋር ትዕግስትን ፈጽሞ አትችልም አላልኩምን?» አለ።

(73) 73. «በረሳሁት ነገር አትያዝብኝ:: ከነገሬም ችግርን አታሸክመኝ።» አለው።

(74) 74. ወርደው ተጓዙም ወጣቱንም ልጅ ባገኘውና በገደለው ጊዜ «ነፍስን ያልገደለችን ንጹህን ነፍስ ገደልክን? በእርግጥ መጥፎን ነገር ሰራህ።» አለው።

(75) 75. «አንተ ከእኔ ጋር ትዕግስትን ፈጽሞ አትችልም አላልኩህምን?» አለ።

(76) 76. «ከአሁኒቱ በኋላ ከምንም ነገር ብጠይቅህ አትጎዳኘኝ:: ከእኔ የይቅርታን መጨረሻ በእርግጥ ደርሰሃል።» አለው።

(77) 77. ሄዱም። ወደ አንዲት ከተማ ሰዎች ዘንድ ደረሱ ከነዋሪዎች ምግብን ጠየቁ:: (እንደ እንግዳ) ማስተናገዳቸዉንም እምቢ አሉ:: በእርሷም ውስጥ ለመውደቅ የተቃረበን የቤት ግድግዳ አገኙ:: አቆመው:: ሙሳም «ብትፈልግ ኖሮ በእርሱ ላይ ዋጋን በተቀበልክ ነበር።» አለው።

(78) 78. አለም: «ይህ በእኔና ባንተ መካከል መለያያችን ነው። በእርሱ ላይ መታገስን ያልቻለክበትን ፍቺ እነግርሃለሁ።

(79) 79. «መርከቢቱማ በባህር ውስጥ ለሚሠሩ ምስኪኖች ነበረች:: ከኋላቸው መርከብን ሁሉ በቅሚያ የሚወስድ ክፉ ንጉስ ነበረና እንዳይቀማቸው ላስነውራት ፈልጌ ነው።

(80) 80. «ያ ወጣቱም ልጅ ወላጆቹ አማኞች ነበሩ:: ቢያድግ በትዕቢትና በክህደት ወላጆቹን የሚያስገድዳቸው መሆኑን ፈራን።

(81) 81. «ጌታቸው በንጹሕነት ከእርሱ በላጭን፤ በእዝነትም ከእርሱ በጣም ቀራቢን ልጅ ሊለውጥላቸው ፈለግን።

(82) 82. «ግድግዳዉም በከተማይቱ ውስጥ የነበሩ የሁለት የቲሞች ወጣቶች ነበር:: በስሩም ለእነርሱ የሆነ የተቀበረ ድልብ ነበረና አባታቸዉም መልካም ሰው ነበር:: ጌታህም ለአካለ መጠን እንዲደርሱና ከጌታህ ችሮታ ድልባቸውን እንዲያወጡ ፈቀደ:: በፈቃዴም አልሠራሁትም:: ይህ ያ በእርሱ ላይ መታገስን ያልቻልከው ነገር ፍቹ ነው።» አለው።

(83) 83. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ስለ ዙልቀርነይንም ይጠይቁሀል:: «በእናንተ ላይ ከእርሱ ወሬን (ማስታወሻን) አነባለሁ።» በላቸው።

(84) 84.እኛ እርሱን በምድር ላይ አስመቸነው:: በነገሩም ሁሉ መዳረሻ መንገድን ሰጠነው::

(85) 85. መንገድንም (ወደ ምዕራብ) ተከተለ::

(86) 86. ወደ ጸሐይ መግቢያም በደረሰ ጊዜ ጥቁር ጭቃማ ምንጭ ውስጥ ስትጠልቅ አገኛት:: በአጠገቧም ህዝቦችን አገኘ:: «ዙልቀርነይን ሆይ! ወይም በመግደል ትቀጣለህ፤ ወይም በእነርሱ መልካም ነገርን ትሠራለህ።» አልነው።

(87) 87. (እርሱም) አለ: «የበደለውንማ ወደፊት እንቀጣዋለን ከዚያ ወደ ጌታው ይመለሳል:: ብርቱንም ቅጣት ይቀጣዋል።

(88) 88. «ያመነና መልካምን ሥራ የሰራ ለእርሱ ከምንዳ በኩል መልካሚቱ ገነት አለችው:: ለእርሱም ከትዕዛዛችን ገርን ነገር እናዘዋለን።» አለ።

(89) 89-. ከዚያ መንገድን (ወደ ምስራቅ) ቀጠለ::

(90) 90.ወደ ጸሐይ መውጫ በደረሰም ጊዜ ለእነርሱ ከበታቹ መከለያን ባላደረግንላቸው ህዝቦች ላይ ስትወጣ አገኛት::

(91) 91.ነገሩ ልክ እንደዚሁ ነው:: እርሱም ዘንድ ባለው ነገር ሁሉ በእርግጥ በእውቀት ከበብን::

(92) 92. ከዚያ (ወደ ሰሜን አቅጣጫ) መንገድን ቀጠለ::

(93) 93.በሁለቱ ጋራዎችም መካከል በደረሰ ጊዜ በአቅራቢያቸው ንግግርን ለማወቅ የማይቃረቡ ህዝቦችን አገኘ::

(94) 94. «ዙልቀርነይን ሆይ! የዕጁጅና መዕጁጅ በምድር ላይ አበላሾች ናቸው። ግብር እናድርግልህና በእኛና በእነርሱ መካከል ግድብን ታደርግልን?» አሉ።

(95) 95. (እርሱም) አለ: «ጌታዬ ያስመቸብኝ ሀብት ከናንተ ግብር በላጭ ነው:: እናም በጉልበት ብቻ እገዙኝ:: በእናንተና በእነርሱ መካከል ብርቱን ግድብ አደርጋለሁና።

(96) 96. «የብረትን ታላላቅ ቁራጮች ስጡኝ።» አላቸው:: በሁለቱ ኮረብታዎች ጫፍ መካከልም ባስተካከለ ጊዜ «አናፉ» አላቸው። ብረቱን እሳትም ባደረገው ጊዜም: «የቀለጠውን ነሀስ ስጡኝ በእርሱ ላይ አፈስበታለሁና።» አላቸው።

(97) 97. የእጁጅና መእጁጅ ይህን መከላከያ ሊወጡት አልቻሉም:: ለእርሱ መሸንቆሩንም እንኳን አልቻሉም።

(98) 98. «ይህ ግድብ ከጌታዬ ችሮታዎች ነው:: የጌታዬ ቀጠሮ በመጣ ጊዜ እንኩትኩት ያደርገዋል:: የጌታዬም ቀጠሮ የተረጋገጠ ነው።» አለ።

(99) 99. በዚያን ቀን ከፊላቸውን በከፊሉ የሚቀላቀሉ አድርገን እንተዋቸዋለን:: በቀንዱም ይነፋል:: መሰብሰብንም እንሰበስባቸዋለን::

(100) 100. ገሀነምንም በዚያ ቀን ለከሓዲያን በጣም ማቅረብን እናቀርባታለን::

(101) 101.ለእነዚያ አይኖቻቸው ከግሳጼዬ በሽፋን ውስጥ ለነበሩትና መስማትንም የማይችሉ ለነበሩት እናቀርባታለን::

(102) 102. እነዚያ በእኔ የካዱት ባሮቼን ከኔ ሌላ አማልክት አድርገው መያዛቸውን የማያስቆጣኝ አድርገው አሰቡን? እኛ ገሀነምን ለከሓዲያን መስተንግዶ አዘጋጅተናል::

(103) 103. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) (እንዲህ) በላቸው: «በሥራዎች በጣም ከሳሪዎቹን እንንገራችሁን?

(104) 104. «እነዚያ እነርሱ ሥራን የሚያሳምሩ የሚመስላቸው ሲሆኑ በቅርቢቱ ህይወት ሥራቸው የጠፋባቸው ናቸው።»

(105) 105. እነዚያ እነርሱ በጌታቸው ተዓምራትና መገናኘት የካዱ ናቸው። ሥራዎቻቸዉም ተበላሸ:: ለእነርሱም በትንሳኤ ቀን ሚዛንን አናቆምላቸዉም::

(106) 106. ነገሩ ይህ ነው:: በክህደታቸው፣ አንቀፆቼንና መልዕክተኞቼንም መሳለቂያ አድርገው በመያዛቸው ፍዳቸው ገሀነም ነው::

(107) 107. እነዚያ በአላህ ያመኑና መልካም ሥራዎችን የሠሩ ፊርደውስ የተባለው የገነት ክፍል ለእነርሱ መስፈሪያ ናቸው::

(108) 108. በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች፤ ከእርሷም መዛወርን የማይፈልጉ ሲሆኑ መስፈሪያቸው ነው።

(109) 109. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ባህሩ ለጌታዬ ቃላት መጻፊያ ቀለሞችን ቢሆን ኖሮ ብጤውን ጭማሪ ብናመጣም እንኳ የጌታዬ ቃላት ከማለቋ በፊት ባህሩ ባለቀ ነበር።» በላቸው።

(110) 110. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እኔ መሰላችሁ ሰው ነኝ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው የሚል መልዕክት ወደ እኔ የሚወረድልኝ:: እናም ከጌታው ጋር መገናኘት የሚፈልግ ሰው ሁሉ መልካም ሥራን ይሥራ:: በጌታዉም መገዛት ላይ አንድንም አያጋራ።» በላቸው።