(1) 1. (ሁኔታው ከሓዲያን እንደሚሉት አይደለም):: በትንሳኤ ቀን እምላለሁ::
(2) 2. (ሁኔታው ከሓዲያን እንደሚሉት አይደለም):: ራሷን ወቃሽ በሆነች ነፍስም እምላለሁ::
(3) 3. (በእርግጥ ትቀሰቀሳላችሁ።) ሰው አጥንቶችን ለመሰብሰባችን ይጠራጠራልን?
(4) 4. እንዴታ ጣቶቹንም ፊት እንደነበሩት በማስተካከል ላይ ቻዮች ስንሆን (እንሰበስባቸዋለን)።
(5) 5. ይልቁን ሰው በፊቱ ባለ ነገር በትንሳኤ ቀን ሊያስተባብል ይፈልጋል::
(6) 6. «የትንሳኤው ቀን መቼ ነው?» ሲል ይጠይቃል።
(7) 7. ዓይንም በዋለለ ጊዜ::
(8) 8. ጨረቃም በጨለመ ጊዜ::
(9) 9. ጸሐይና ጨረቃም በተሰበሰቡ ጊዜ፤
(10) 10. ሰው በዚያን ቀን «መሸሻው የት ነው?» ይላል።
(11) 11. «ይከልከል፤ ምንም መጠጊያ የለም።
(12) 12. በዚያ ቀን መርጊያው ወደ ጌታህ ብቻ ነው።» ይባላል።
(13) 13. ሰው በዚያን ቀን ያስቀደመውም ያስቆየውም ሁሉ ይነገረዋል።
(14) 14. በእርግጥ ሰው በነፍሱ ላይ አስረጅ ነው::
(15) 15. ምክንያቶቹን ሁሉ ቢያመጣ እንኳን (አይሰማም)።
(16) 16. በቁርኣን ንባብ ልትቸኩል ብለህ ምላስህን አታላውስ::
(17) 17. በልብህ ውስጥ መሰብሰቡና ማስነበቡ በኛ ላይ ነውና::
(18) 18. ባነበብነው ጊዜ (ካለቀ በኋላ) ንባቡን ተከተል።
(19) 19. ከዚያም (ላንተ) ማብራራቱ በእኛ ላይ ነው።
(20) 20. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከመጣደፍ ተከልከል፤ ይልቁንም (ሰዎች ስትባሉ) ፈጣኒቱን ዓለም ትወዳላችሁ::
(21) 21. የመጨረሻይቱን ዓለም (ግን) ትተዋላችሁ።
(22) 22. (የተወሰኑ) ፊቶች በዚያ ቀን አብሪዎች ናቸው።
(23) 23. ወደ ጌታቸው ተመልካቾችም ናቸው::
(24) 24. (ሌሎች) ፊቶች ደግሞ በዚያ ቀን አጨፍጋጊዎች ናቸው።
(25) 25. በእነርሱም ላይ አደጋ እንደሚሰራባቸው ያረጋገጣሉ::
(26) 26. (ሙስሊሞች አስተውሉ።) (ነፍስ) ወደ ጉሮሮ በደረሰች፤
(27) 27. «አሻሪው ማነው?» በተባለም ጊዜ፤
(28) 28. (የሰፈረበት ነገር ከዚህ ዓለም) መለየት መሆኑን ባረጋገጠ ጊዜ፤
(29) 29. ባትም ከባት በተጣበቀች ጊዜ፤
(30) 30. በዚያ ቀን መነዳት ወደ ጌታህ (ፍርድ) ብቻ ነው።
(31) 31. እናም (ከሀዲው) አላመነምም፤ አልሰገደምም።
(32) 32. ግን በአላህ አስተባበለ፤ ከእምነት ዞረም::
(33) 33. ከዚያም እየተንጎማለለ ወደ ቤተሰቡ ሄደ።
(34) 34. (የምትጠላውን ነገር) ላንተው ይሁን፤ ላንተ ተገቢህም ነው።
(35) 35. ከዚያም ጥፋት ይጠጋህ ላንተ የተገባህም ነው።
(36) 36. ሰው እንደፈለገ እንዲኖር ልቅ ሆኖ የሚተው ይመስለዋልን?
(37) 37. የሚፈስ ከሆነ የፍትወት ጠብታ አልነበረምን?
(38) 38. ከዚያ የረጋ ደም ሆነ:: ከዚያ አላህ ሰው አድርጎ ፈጠረው፤ አስተካከለዉም::
(39) 39. ከእርሱም ሁለት ዓይነቶች ወንድና ሴትን አደረገ።
(40) 40. (ታዲያ) ይህ ሀያል (ጌታ) ሙታንን ሕያው በማድረግ ላይ ቻይ አይደለምን?