(1) 1.ምስጋና ሁሉ ለዚያ ሰማያትንና ምድርን ለፈጠረ ጨለማዎችንና ብርሃንን ላደረገው ለአላህ የተገባ ነው:: ከዚያም እነዚያ በእርሱ የካዱ ሁሉ ጣዖታትን ከጌታቸው ጋር ያስተካክላሉ::
(2) 2. (ሰዎች ሆይ!) እርሱ ያ ከጭቃ የፈጠራችሁ ከዚያም የሞት ጊዜን የወሰነ ነው:: እርሱም ዘንድ ለትንሳኤ የተወሰነ ጊዜ አለ:: ከዚያም እናንተ በመቀስቀሳችሁ ትጠራጠራላችሁን?
(3) 3. እርሱም ያ በሰማያትም በምድርም ሊገዙት የሚገባው አላህ ነው:: (ሰዎች ሆይ!) ሚስጥራችሁንም ሆነ ግልፃችሁን ጠንቅቆ ያውቃል። የምትሰሩትን ሁሉ ጠንቅቆ ያውቃል::
(4) ⒋ ከጌታቸው አናቅጽ አንዱም አይመጣላቸዉም ከእርሱ የሚሸሹ ቢሆኑ እንጂ::
(5) 5. ቁርኣን በመጣላቸው ጊዜም በእርግጥ አስተባበሉ:: ግን የእዚያ በእርሱ ይሳለቁበት የነበሩት ነገር ዜናዎች ቅጣት ይመጣባቸዋል።
(6) 6. ከበፊታቸው ከክፍለ ዘመናት ህዝቦች መካከል ብዙዎቹን ማጥፋታችንን አላዩምን? ለእናንተ ያላስመቸነውን ለእነርሱ በምድር ውስጥ አስመቸናቸው:: በእነርሱም ላይ ዝናብን የተከታተለ ሲሆን ላክን:: ወንዞችንም በስራቸው እንዲፈሱ አደረግን:: በኃጢአቶቻቸዉም ምክንያት አጠፋናቸው:: ከኋላቸዉም ሌሎችን ሰዎች በየክፍለ ዘመኑ አስገኘን::
(7) 7. በእነርሱ ላይ በወረቀት የተፃፈን መጽሐፍ ባወረድንና በእጆቻቸው በነኩት ኖሮ እነዚያ ከሓዲያን «ይህ ግልጽ ድግምት እንጂ ሌላ አይደለም።» ባሉ ነበር::
(8) 8. «በእርሱ (በሙሐመድ) ላይ መልአክ ለምን አይወረድለትም?» አሉ። ነገር ግን መላዕክን ባወረድንለትና (ባያምኑ ኖሮ) የጥፋታቸው ነገር በተፈረደ ነበር:: ከዚያም አይቆዩም ነበር::
(9) 9. መልዕክተኛውን ከመላዕክት መካከል ባደረግነው ኖሮ ወንድ ሰው አድርገን በመላክ በእነርሱ ላይ የሚያመሳስሉትን ነገር ባመሳሰልንባቸው ነበር።
(10) 10. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ካንተ በፊት በነበሩ መልዕክተኞችም ላይ ተላግጧል:: እናም በእነዚያ ባላገጡት ላይ ያላገጡበት ውጤት በእነርሱ ላይ ተፈጽሟል::
(11) 11. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ! ከሓዲያንን) «በምድር ላይ ሂዱና የእነዚያን የአስተባባዮችን መጨረሻ እንዴት እንደነበረ ተመልከቱ።» በላቸው::
(12) 12. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በላቸው: «በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የማን ነው?» በላቸውም: «የአላህ ብቻ ነው። አላህ በራሱ ላይ እዝነትን ፃፈ:: በዚያ ጥርጥር በሌለበት በትንሳኤ ቀን ይሰበስባችኋል:: እነዚያ ነፍሶቻቸውን ያከሰሩ ማለት እነርሱው ናቸው። እናም አያምኑም።
(13) 13. «በሌሊትም ሆነ በቀን ጸጥ ያለው ሁሉ የእርሱው ነው:: እርሱም ሰሚውና አዋቂው ነው።»
(14) 14. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ ከሆነው አላህ እርሱ ፍጡርን የሚመግብና ለራሱ የማይመገብ አምላክ ሲሆን ሌላን አምላክ እይዛለሁን?» በላቸው። «እኔ መጀመሪያ ትዕዛዝን ከተቀበለ ሰው እንድሆን ታዘዝኩ:: ‹ከአጋሪዎችም ፈጽሞ አትሁን።› ተብያለሁ።» በላቸው::
(15) 15. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እኔ በጌታዬ ላይ ባምጽ የዚያን የታላቁን ቀን ቅጣት እፈራለሁ።» በላቸው።
(16) 16. በዚያ ቀን ከእርሱ ላይ ቅጣት የሚመለስለት ሰው ሁሉ በእርግጥ አላህ አዘነለት:: ይህም ግልጽ ስኬት ነው።
(17) 17. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ ችግር ቢያደርስብህ ከእርሱ በስተቀር ሌላ ማንም አስወጋጅ የለም:: በጎ ነገርን ቢሰጥህም እርሱ በሁሉ ነገር ላይ ቻይ ነው::
(18) 18. እርሱ ከባሮቹ በላይ ሲሆን ሁሉን አሸናፊ ነው:: እርሱ ጥበበኛውና ውስጠ አዋቂው ነው።
(19) 19. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ከምስክርነት ሁሉ ይበልጥ ታላቁ የትኛው ነው?» በላቸው። «አላህ፤ በእኔና በእናንተ መካከል መስካሪ ነው። ይህም ቁርኣን እናንተንና የደረሰውንም ሁሉ ላስፈራራበት ወደ እኔ ተወረደ:: ከአላህ ጋር ሌሎች አማልክት መኖራቸውን እናንተ ትመሰክራላቸሁን?» በላቸው:: «እኔ ግን ፈጽሞ በዚህ አልመሰክርም።» በላቸው:: «እርሱ አንድ አምላክ ብቻ ነው:: እኔም በአላህ ከምታጋሩት ሁሉ ንጹህ ነኝ።» በላቸው።
(20) 20. እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው አይሁድና ክርስቲያኖች ልክ ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ ሁሉ ሙሐመድንም በትክክል ያውቁታል:: እነዚያ ነፍሶቻቸውን ያከሰሩት እነርሱ ፈጽሞ አያምኑም::
(21) 21. በአላህ ላይ ውሸትን ከቀጣጠፈ ወይም በአናቅጽ ካስተባበለ ይበልጥ በደለኛ ማን ነው? እነሆ በደለኞች አይድኑም።
(22) 22. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሁላቸውንም በምንሰበሰብበትና ከዚያም ለእነዚያም በአላህ ላጋሩት፤ «‹እነዚያም ለአላህ ተጋሪዎች ናቸው› ብላችሁ ታስቧቸው የነበሩት ተጋሪዎቻችሁ የት ናቸው?» የምንልበትን ቀን (አስታውስ)።
(23) 23. ከዚያም የፊትና መልሳቸው «በጌታችን በአላህ ይሁንብን አጋሪዎች አልነበርንም።» ማለት እንጂ ሌላ አይሆንም።
(24) 24. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በነፍሶቻቸው ላይ እንዴት እንደዋሹና ይቀጣጥፉት የነበሩት ነገር ሁሉ ከእነርሱ እንዴት እንደተሰወረባቸው ተመልከት::
(25) 25. ከእነርሱ መካከል ወደ አንተ የሚያዳምጥ ሰው አለ:: በልቦቻቸው ላይ እንዳያውቁት ሽፋኖችን፤ በጆሮዎቻቸዉም ላይ እንዳይሰሙት ድንቁርናን አደረግን:: ተዐምርን ሁሉ እንኳን ቢያዩ በእርሷ አያምኑም:: ወደ አንተ በመጡ ጊዜ የሚከራከሩህ ሆነው እነዚያ በአላህ የካዱ ሰዎች «ይህ ቁርኣን የቀድሞዎቹ ሰዎች ጹሑፍ ተረቶች ስብስብ እንጂ ሌላ አይደለም።» ይላሉ::
(26) 26. እነርሱም ሰዎችን ከእርሱ ይከልክላሉ፤ ከእርሱም ይርቃሉ፤ በዚህም ተግባራቸው ነፍሶቻቸውን እንጂ ሌላን አያጠፉም:: ግን አያውቁም::
(27) 27. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በእሳትም ላይ እንዲቆሙ በተደረጉ ጊዜ «ምን ነው ወደ ምድረ ዓለም በተመለስንና በጌታችን አናቅጽ ባላስተባበልን ከትክክለኛ አማኞችም ጋር በሆንን ዋ! ምኞታችን።» ባሉ ጊዜ ብታይ ኖሮ (የሚያስደነግጥህን ነገር ባየህ ነበር)
(28) 28. ይልቁንስ ከዚህ በፊት ይደብቁት የነበሩት ነገር ሁሉ ለእነርሱ ተገለጸ:: ወደ ምድረ ዓለም በተመለሱም ኖሮ ወደ ተከለከሉት ነገር በተመለሱ ነበር:: እነርሱ ሐሰተኞች ናቸው።
(29) 29. «ሕይወት ማለት ቅርቢቱ ሕይወታችን እንጂ ሌላ አይደለችም:: እኛም ፈጽሞ ተቀስቃሾች አይደለንም።» አሉ።
(30) 30. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በጌታቸው ዘንድ ለምርመራ እንዲቆሙ በተደረጉ ጊዜ ብታይ ኖሮ (አስደንጋጭን ነገር ባየህ ነበር::) «ይህ እውነት አይደለምን?» ይላቸዋል:: እነርሱም «በጌታችን ይሁንብን እውነት ነው።» ይላሉ:: «እናም ትክዱት በነበራችሁት ምክንያት ቅጣቱን ቅመሱ።» ይላቸዋል::
(31) 31. እነዚያ ከአላህ ጋር መገናኘትን ያስተባበሉ ሁሉ በእርግጥ ከሰሩ:: ስዓቲቱም በድንገት በመጣችባቸው ጊዜ እነርሱ ኃጢአቶቻቸውን በጀርባዎቻቸው ላይ የሚሸከሙ ሲሆኑ «በምድረ ዓለም ባጓደልነው ነገር ላይ ዋ ጥፋታችን!» ይላሉ። አዋጅ ያ የሚሸከሙት ነገር ምንኛ ከፋ!
(32) 32. የቅርቢቱ ሕይወት ማለት ጨዋታና ላግጣ እንጂ ሌላ አይደለችም። የመጨረሻይቱ አገር (ገነት) ግን ለእነዚያ ለሚጠነቀቁት ሰዎች ሁሉ በጣም በላጭ ናት። አታውቁምን? (አትገነዘቡምን)?
(33) 33. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ያ የሚሉህ ነገር እንደሚያሳዝንህ በእርግጥ እናውቃለን:: እነርሱ በእርግጥ አያስተባብሉህም:: ግን በዳዮች በአላህ አናቅጽ ይክዳሉ::
(34) 34. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከበፊትህ የነበሩት መልዕክተኞች ተስተባብለዋል:: በተስተባበሉበትም ነገርና በተሰቃዩት ላይ እርዳታችን እስከመጣላቸው ድረስ ታገሱ:: የአላህን ቃላት የሚለዉጥ የለም:: ከመልዕክተኞቹም ወሬ (የምትረጋጋበት) በእርግጥ መጣልህ::
(35) 35. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ኢስላምን መተዋቸው ባንተ ላይ ከባድ ቢሆንብህም በምድር ውስጥ ቀዳዳን ወይም በሰማይ ውስጥ መሰላልን ልትፈልግና ተዓምር ልታመጣላቸው ከቻልክ ሞክር:: አላህ በፈለገ ኖሮ ሁሉንም በቅኑ መንገድ ላይ በሰበሰባቸው ነበር:: ስለዚህ ከተሳሳቱት ሰዎች በፍጹም አትሁን::
(36) 36. ጥሪን የሚቀበሉት እነዚያ የሚሰሙት ብቻ ናቸው:: ሙታንማ አላህ ይቀሰቅሳቸዋል:: ከዚያም ወደ እርሱ ብቻ ይመለሳሉ::
(37) 37. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከሓዲያን «ከጌታው በእርሱ ላይ ለምን ተአምር አልተወረደለትም?» አሉ:: «አላህ ተአምርን ለማውረድ ቻይ ነው:: ግን አብዛኞቻቸው ይህን እውነታ አያውቁም።» በላቸው::
(38) 38. በምድር ላይ የሚሄድ ተንቀሳቃሽም ሆነ በሁለት ክንፎቹ የሚበር ሁሉ መሰሎቻችሁ ሕዝቦች እንጂ ሌላ አይደሉም:: በመጽሐፉ ውስጥ ምንንም ነገር አልተውንም:: ከዚያ ሁሉም ወደ ጌታቸው ይሰበሰባሉ::
(39) 39. እነዚያ በአናቅጻችን ያስተባበሉ ሁሉ እውነትን የማይሰሙ ደንቆሮዎች፤ ሐቅን የማይናገሩ ዲዳዎችና በጨለማዎች ውስጥ ያሉ ናቸው:: አላህ መጥመሙን የሚሻበትን ሰው ያጠመዋል:: ወደ ቀናው መንገድ መመራቱን የሚሻለትን ሰው ደግሞ በቀጥተኛው መንገድ ላይ ያደርገዋል::
(40) 40. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «የአላህ ቅጣት ቢመጣባችሁ ወይም ትንሳኤ ብትመጣባችሁ ከአላህ ሌላ ትጠራላችሁን? እውነተኞች ከሆናችሁ (እስኪ ንገሩኝ።)» በላቸው።
(41) 41. «በፍፁም። እውነታው እርሱን ብቻ ትጠራላችሁ:: ቢሻ ወደ እርሱ የምትጠሩበትን ነገር ያስወግድላችኋልና የምታጋሩትንም ሁሉ ትረሱታላችሁ።» በላቸው::
(42) 42. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ካንተ በፊት ለነበሩት ሕዝቦች አያሌ መልዕክተኞችን በእርግጥ ላክን:: (ከዚያም እንቢተኛ ሆኑ::) ለእኛ ይተናነሱም ዘንድ በድህነትና በችግር ቀጣናቸው::
(43) 43. ታዲያ ቅጣታችን በመጣባቸው ጊዜ አይተናነሱም ኖሯልን? ነገር ግን ልቦቻቸው ደረቁ:: ይሰሩት የነበሩትንም መጥፎ ነገር ሰይጣን መልካም ነገር አስመስሎ አሳያቸው።
(44) 44. በእርሱ ይገሰጹበት የነበረውን ነገር በዘነጉ ጊዜ ለእነርሱ የሁሉን ነገር ደጃፎችን ከፈትንላቸውና በኑሮ አስመቸናቸው:: በተሰጡትም ነገር በተደሰቱ ጊዜ በድንገት ያዝናቸው:: ወዲያውኑም እነርሱ ተስፋ ቆራጮች ሆኑ።
(45) 45. የእነዚያ የበደሉት ሕዝቦች መጨረሻ ተቆረጠ:: ምስጋና ሁሉ ለዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ ብቻ ይገባው::
(46) 46.(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እስቲ ንገሩኝ አላህ መስሚያችሁንና ማያዎቻችሁን ቢወሰድባችሁና በልቦቻችሁ ላይ ቢያትም ከአላህ ሌላ እርሱኑ የሚያመጣላችሁ አምላክ ማን ነው?» በላቸው:: አናቅጽን እንዴት እንደምናብራራና ከዚያም እነርሱ እንዴት መንገዱን እንደሚስቱ ተመልከት::
(47) 47. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እስቲ ንገሩኝ የአላህ ቅጣት ድንገት ወይም በይፋ ቢመጣባችሁ ከአመጸኛ ህዝቦች ሌላ ይጠፋልን?» በላቸው::
(48) 48. መልዕክተኞችንም በመልካም አብሳሪና ከመጥፎ አስፈራሪ አድርገን እንጂ አንልክም:: እናም በእነርሱ ያመኑና በጎ ተግባርን የሰሩ ሁሉ ስጋት የለባቸዉም። አይተክዙምም።
(49) 49. እነዚያ አናቅጻችንን ያስተባበሉት ደግሞ በአመፃቸው ምክንያት ቅጣት ያገኛቸዋል።
(50) 50. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «የአላህ ግምጃ ቤቶች እኔ ዘንድ ናቸው አልላችሁም:: ሩቅ ሚስጥርንም አላውቅም:: መልዓክ ነኝም አልልም:: ወደ እኔ የሚወርድልኝን መልዕክት ብቻ እንጂ ሌላን አልከተልም።» በላቸው። «እውርና የሚያይ ይስተካከላሉን? አታስተነትኑምን!» በላቸው።
(51) 51. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያ ከአላህ ሌላ ወዳጅና አማላጅ የሌላቸው ሲሆኑ ወደ ጌታቸው መሰብሰብን የሚፈሩትን ሰዎች ይጠነቀቁ ዘንድ በእርሱ(ቁርኣን) አስፈራራ::
(52) 52. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያን የጌታቸውን ፊት የሚሹ ሆነው በጧትና በማታ የሚጠሩትን አማኞች ከአጠገብህ አታባር:: እነርሱን መቆጣጠር ባንተ ላይ ምንም የለብህም:: አንተንም መቆጣጠር በእነርሱ ላይ ምንም የለባቸዉም::ታባርራቸውና ከበደለኞችም ትኾን ዘንድ (አታባር)።
(53) 53. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ልክ እንደዚሁም «ከመካከላችን አላህ በእነርሱ ላይ ችሮታውን የለገሳቸው እነዚህ ናቸውን?» ይሉ ዘንድ ከፊላቸውን በከፊሎች ሞከርን:: አላህ አመስጋኞቹን ከሁሉም በላይ አዋቂ አይደለምን?
(54) 54. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያም በተዐምራታችን የሚያምኑት ሰዎች ሁሉ ወደ አንተ በመጡ ጊዜ «ሰላም በእናንተ ላይ ይሁን:: ጌታችን በራሱ ላይ እዝነትን ፃፈ:: እነሆ ከናንተ ውስጥ ስህተትን ስራ የሰራና ከዚያ ተጸጽቶ ወዲያውኑ ስራውን ላሳመረ እርሱ (አላህ) መሀሪና አዛኝ ነው።» በላቸው።
(55) 55. ልክ እንደዚሁም እውነቱ እንዲገለጽና የወንጀለኞችም መንገድ ትብራራ ዘንድ አናቅጽን እንገልፃለን::
(56) 56. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እኔ እነዚያን ከአላህ ሌላ የምትጠሯቸውን (ባዕድ አማልክት) ከመገዛት ተከልክያለሁ።» በላቸው። «ዝንባሌያችሁንም አልከተልም:: ያን ካደረኩኝ በእርግጥ ተሳሳትኩ:: እኔም ከተመሪዎቹ አይደለሁም።» በላቸው።
(57) 57. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ሰዎች ሆይ! እኔ ከጌታዬ በመጣልኝ ግልጽ ማስረጃ ላይ ነኝ:: እናንተ ግን በእርሱ አስተባበላችሁ:: ያ የምትቻኮሉበት ቅጣት ውሳኔ እኔ ዘንድ አይደለም:: ፍርዱ ለአላህ ብቻ ነው:: አላህ እውነቱን ይፈርዳል:: እርሱም ከፈራጆች ሁሉ በላጭ ነውና።» በላቸው።
(58) 58. «ያ የምትቻኮሉበት ቅጣት እኔ ዘንድ በሆነ ኖሮ በእኔና በእናንተ መካከል ነገሩ (ቅጣታችሁ) በተፈጸመ ነበር:: አላህ በደለኞችን አዋቂ ነው።» በላቸው::
(59) 59. የሩቅ ሚስጥሮች መክፈቻዎች ሁሉ እርሱ ዘንድ ብቻ ናቸው:: ከእርሱ በስተቀር ማንም አያውቃቸዉም:: በየብስና በባህር ውስጥ ያለውን ሁሉ ያውቃል:: አንዲትም ቅጠል አትረግፍም አላህ የሚያውቃት ብትሆን እንጂ:: በመሬት ጨለማዎች ውስጥ ቅንጣት እርጥብም ሆነ ደረቅ አንድም ነገር የለም ግልጽ በሆነው መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ ቢሆን እንጂ::
(60) 60. እርሱ (አላህ) ያ በሌሊት የሚያስተኛችሁ በቀን የሰራችሁትንም ሁሉ የሚያውቅ ከዚያም የተወሰነው ጊዜ ይፈጸም ዘንድ በቀን ውስጥ የሚቀሰቅሳችሁ ነው:: ከዚያም መመለሻችሁ ወደ እርሱ ብቻ ነው:: ከዚያም ትሰሩት የነበራችሁትን ነገር ሁሉ ይነግራችኋል::
(61) 61. እርሱ ከባሮቹ በላይ ሲሆን ሁሉን አሸናፊ ነው:: በእናንተ ላይም ተጠባባቂዎች መላዕክትን ይልካል:: አንዳችሁንም የሞት ሰዓቱ በመጣበት ጊዜ የሞት መልዕክተኞቻችን ትዕዛዛትን የማያጓድሉ ሲሆኑ ይገድሉታል::
(62) 62. ከዚያም እውነተኛ ወደ ሆነው ጌታቸው ወደ አላህ ይመለሳሉ:: (ሰዎች ሆይ!) አስትዉሉ! አዋጅ ፍርዱ ለእርሱ ብቻ ነው:: እርሱም ከተቆጣጣሪዎች ሁሉ ይበልጥ ፈጣን ነው::
(63) 63. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ያ ከየብስና ከባህር ጨለማዎች በግልጽና በሚስጢር ‹ከዚህ ቢያድነን ከአመስጋኞች እንሆናለን› ስትሉ የምትጠሩት ስትሆኑ የሚያድናችሁ ማን ነው?» በላቸው።
(64) 64. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «አላህ ከእርሷና ከጭንቅም ሁሉ ያድናችኋል:: ከዚያ እናንተ በእሱ ባዕድ አምላክን ታጋራላችሁ።» በላቸው።
(65) 65. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እርሱ (አላህ) ከበላያችሁ ወይም ከእግሮቻችሁ በታች ቅጣትን በእናንተ ላይ ሊልክ ወይም የተለያዩ ሕዝቦች ስትሆኑ ሊያደባልቃችሁና ከፊላችሁን የከፊሉን ጭካኔ ሊያቀምስ ቻይ ነው።» በላቸው። ይገነዘቡ ዘንድ አናቅጽን እንዴት እንደምናብራራ ተመልከት።
(66) 66. እርሱ(ቁርኣን) ከአላህ የመጣ እውነት ሲሆን ህዝቦችህ ግን አስተባበሉት:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በናንተ ላይ ጠባቂ አይደለሁም።» በላቸው::
(67) 67. ለየወሬ ሁሉ የሚደርስበት መፈጸሚያ ጊዜ አለው:: ወደ ፊትም በትክክል ታውቁታላችሁ::
(68) 68. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያ አናቅጻችንን ለማስተባበል ወደ ክርክር የሚገቡትን ሰዎች በምታይ ጊዜ በሌላ ወሬ እስከሚገቡ ድረስ ተዋቸው:: ሰይጣንም መከልከልህን ቢያስረሳህና አብረሀቸው ሆነህ እንኳን ካስታወስክ በኋላ ከበደለኞች ሕዝቦች ጋር አትቀመጥ::
(69) 69. እነዚያም በሚጠነቀቁት ህዝቦች ላይ በሂሳባቸው ምንም የለባቸዉም:: ግን ይጠነቀቁ ዘንድ መገሰጽ አለባቸው::
(70) 70. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያንም ሃይማኖታቸውን ጨዋታና ቀልድ አድርገው የያዙትንና ቅርቢቱ ሕይወት ያታለለቻቸውን ተዋቸው:: ነፍስ ሁሉ በሰራችው ስራ እንዳትጠፋ በእርሱ (በቁርአን) አስታውስ:: ለእርሷ ከአላህ ሌላ ወዳጅም ሆነ አማላጅ ማንም የላትም:: ፊዳ የተባለን ሁሉ ብትከፍል እንኳን ተቀባይነት የላትም:: እነዚያ በሰሩት ስራ የተጠፉት ናቸው:: በክህደታቸው ምክንያት ከፈላ ውሃ መጠጥና አሳማሚ ቅጣት አለባቸው::
(71) 71. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ከአላህ ሌላ የማይጠቅምንና የማይጎዳን እንገዛለን? አላህ በቀናው መንገድ ከመራን በኋላ የኋሊት እንመለሳለን? እንደዚያ በምድር ላይ የዋለለ ሲሆን ሰይጣናት አሳስተውት ለእርሱ ‹ወደ እኛ ና› እያሉ ወደ ቅን መንገድ የሚጠሩ ወዳጆች ቢኖሩትም (እንደማይከተላቸው) እንሆናለንን?» በላቸው:: «የአላህ መንገድ ቀጥተኛው መንገድ ነው:: ለዓለማት ጌታ ልንገዛም ታዘዝን።» በላቸው::
(72) 72. «ሶላትን በትክክል ስገዱ አላህን ፍሩትም።» (ተብለን ታዘናል በላቸው።) እርሱ ወደ እርሱ የምትሰበሰቡበት አምላክ ነው።
(73) 73. እርሱም ያ ሰማያትንና ምድርን በትክክል የፈጠረ ነው:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ሁን» የሚልበትንና ወዲያዉም የሚሆንበትን ቀን አስታውስ:: ቃሉም እውነት ነው:: በቀንዱ በሚነፋበት ቀንም ንግስናው የእርሱ ብቻ ነው:: ሩቁንና ቅርቡን አዋቂ ነው:: እርሱም ጥበበኛውና ውስጠ አዋቂው ነው::
(74) 74. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ኢብራሂም ለአባቱ ለአዘር፡- «ጣኦትን አማልክት ታደርጋለህን? እኔ አንተንም ወገኖችህንም ግልጽ ጥመት ውስጥ ሆናችሁ አየኋችሁ።» ባለው ጊዜ የሆነውን አስታውስ::
(75) 75. ልክ በዚህ አኳኋን ኢብራሂም ጽኑ እምነት ይኖረው ዘንድ የሰማያትንና የምድርን ግዛት አሳየነው::
(76) 76. ሌሊቱ በጽልመቱ በሸፈነው ጊዜ አንድ ኮከብ አየ። «ይህ ጌታዬ ነው» አለም:: ኮከቡ በጠለቀ ጊዜም፡- «ጠላቂዎችን አልወድም» አለ::
(77) 77. ጨረቃውን ደምቆ ባየ ጊዜም፡- «ይህ ጌታዬ ነው።» አለ:: ጨረቃውም በጠለቀ ጊዜ፡- «ጌታዬ ቅኑን ጎዳና ካልመራኝ መንገድ ከተሳሳቱ ሰዎች እሆናለሁ።» አለ።
(78) 78. ጸሐይዋንም ደምቃ ጮራዋን ባየ ጊዜ፡- «ይህ ጌታዬ ነው። ይህ በጣም ትልቅ ነው።» አለ:: በጠለቀችም ጊዜ (አንዲህ) አለ፡- «ወገኖቼ ሆይ! እኔ ከምታጋሩት ሁሉ የጠራሁ ነኝ።
(79) 79. «እኔ ወደ ቀጥተኛው ሃይማኖት የተዘነበልኩ ስሆን ፊቴን ሰማያትንና ምድርን ወደ ፈጠረው አምላክ አላህ አዙሬያለሁ:: እናም ከአጋሪዎችም አይደለሁም።» (አለ)።
(80) 80. ወገኖቹም ተከራከሩት። (እርሱም) አላቸው: «በእርግጥ የመራኝ ስሆን በአላህ ጉዳይ ትከራከሩኛላችሁን? በእርሱም የምታጋሩትን ነገር አልፈራም:: ግን ጌታዬ ቢሻ (ያገኘኛል):: ጌታዬም ሁሉንም ነገር በእውቀቱ ሰፋ። አትገነዘቡምን?
(81) 81. «በእናንተ ላይ በእርሱ ማስረጃ ያላወረደበትን እናንተ ማጋራታችሁን የማትፈሩ ስትሆኑ የምታጋሩትን ጣዖት እንዴት እኔ እፈራለሁ?! የምታውቁም ብትሆኑ ከሁለቱ ክፍሎች ደህና ለመሆን ይበልጥ ተገቢው ማንኛው ነው?» አለ።
(82) 82. እነዚያ በአላህ ያመኑና እምነታቸውን በእሱ በማጋራት ያልቀላቀሉ ሁሉ እነዚያ ለእነርሱ የተሟላ ደህንነት አለላቸው:: ወደ ቀናው መንገድ የተመሩም እነርሱው ናቸው::
(83) 83. እነዚህ ማስረጃዎቻችን ናቸው:: ለኢብራሂም በህዝቦቹ ላይ አስረጅ እንዲሆኑ ሰጠነው:: የምንፈልገውን ሰው በደረጃዎች ከፍ እናደርጋለን:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ ጥበበኛና አዋቂ ነውና::
(84) 84. ለእርሱም ልጁን ነብዩ ኢስሀቅንና የልጅ ልጁን ነብዩ የዕቆብን ሰጠነው:: ሁሉንም ወደ ቀናው መንገድ መራናቸው:: ኑህንም ከእነርሱ በፊት ወደ ቀናው መንገድ መራነው:: ከዘሮቹም ነብዩ ዳውድንም፤ ነብዩ ሱለይማንንም፤ ነብዩ አዩብንም፤ ነብዩ ዮሱፍንም፤ ነብዩ ሙሳንና፤ ነብዩ ሀሩንንም መራን:: በጎ ሰሪዎችን ሁሉ ልክ እንደዚሁ እንመነዳለን::
(85) 85. ዘከርያን፤ ያህያን፤ ዒሳን፤ ኢልያስንም ወደ ቀናው መንገድ መራን:: ሁሉም ከመልካሞቹ ናቸው::
(86) 86. ነብዩ ኢስማኢልንም፤ ነብዩ አል የሰዕንም፤ ነብዩ ዩኑስንም፤ ነብዩ ሉጥንም መራን:: ሁሉንም በዓለማት ላይ አበለጥናቸው::
(87) 87. ከአባቶቻቸዉም፣ ከዘሮቻቸዉም፣ ከወንድሞቻቸዉም ብዙዎችን መራን:: መረጥናቸዉም:: ወደ ቀጥታኛዉም መንገድ መራናቸው::
(88) 88. ይህ የአላህ መመሪያ ነው:: በእርሱ ከባሮቹ የሚሻውን ወደ ቀናው መንገድ ይመራበታል:: በአላህ ባጋሩም ኖሮ ይሰሩት የነበሩት መልካም ተግባር ሁሉ ከእነርሱ በታበሰባቸው ነበር::
(89) 89. እነዚህ እነዚያ መጽሐፍትንና ጥበብን ነብይነትንም የሰጠናቸው ሰዎች ናቸው:: እነዚህ የመካ ከሓዲያን በእርሷ ቢክዱም በእርሷ የማይክዱ ሕዝቦችን አዘጋጅተንላታል::
(90) 90. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚህ ነብያት እነዚያ አላህ የመራቸው ናቸው:: ስለሆነም ፈለጋቸውን ተከተል:: «በእርሱ (በቁርኣን) ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም:: እርሱ ለዓለማት ግሳጼ ሊሆን የወረደ እንጂ ሌላ አይደለም።» በላቸው::
(91) 91. (ከሓዲያን) «አላህ በሰው ላይ ምንም አላወረደም።» ባሉ ጊዜ አላህን ተገቢውን ክብሩን አላከበሩትም:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እንዲህ በላቸው «ያንን ለሰዎች ብርሃንና ቅን መመሪያ ሆኖ ሙሳ ያመጣውን መጽሐፍ ክፍልፍሎች የምታደርጉት ስትሆኑ ማን አወረደው? (የወደዳችኋትን) ትገልጿታላችሁ ብዙውንም ትደብቃላችሁ፤ እናንተም ሆናችሁ አባቶቻችሁም ያላወቃችሁትን ተስተማራችሁ::» (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «አላህ አወረደው።» በላቸው:: ከዚያም በውሸታቸው ውስጥ የሚጫወቱ ሲሆኑ ተዋቸው::
(92) 92. ይህ ያወረድነው ብሩክና ያንንም በፊት የነበረውን (መጽሐፍ) አረጋጋጭ መጽሐፍ ነው:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የከተሞችንም እናት (መካን) ኗሪዎችን እና በዙሪያዋ ያሉትንም ሰዎች ልታስጠነቅቅበት አወረድነው:: እነዚያም በመጨረሻይቱ ዓለም የሚያምኑት ሰዎች እነርሱ በሶላታቸው የሚጠባበቁ ሲሆኑ በእርሱ ያምናሉ::
(93) 93. በአላህ ላይ ውሸትን ከቀጣጠፈ ወይም ወደ እርሱ ምንም ያልተወረደለት ሲሆን «ወደ እኔ ተወረደልኝ።» ካለና «አላህ ያወረደውን አይነት ማውረድም በእርግጥ እችላለሁ።» ካለ ይበልጥ እራሱን በዳይ ማን ነው? በደለኞችን በሞት መከራዎች ውስጥ በሆኑ ጊዜ መላዕክት እጆቻቸውን ዘርጊዎች ሆነው (ለቅጥጥብ) «ነፍሶቻችሁን አውጡ:: ከአላህ ላይ እውነትን ያልሆነን ነገር ትናገሩም የነበራችሁና በአናቅጽም ላይ ትኮሩ በነበራችሁት ምክንያት ዛሬ የውርደት ቅጣት ትመነዳላችሁ» በሚሏቸው ጊዜ ብታይ ኖሮ (አስደንጋጭን ነገር ባየህ ነበር)::
(94) 94. «በመጀመሪያ ጊዜ ልክ እንደፈጠርናችሁ ሆናችሁ የሰጠናችሁን ሁሉ ከጀርባዎቻችሁ ኋላ የተዋችሁ ስትሆኑ ለየብቻችሁ ሆናችሁ በእርግጥ ወደ እኛ መጣችሁ:: እነዚያንም እነርሱ በእናንተ (ጉዳይ) ለአላህ ተጋሪዎቹ ናቸው:: የምትሏቸውን አማላጆቻችሁን ከናንተ ጋር አናይም:: ግንኙነታችሁ በእርግጥ ተቋረጠ:: ከናንተም ያ ያማልደናል የምትሉት ሁሉ ጠፋ» (ይባላሉ።)
(95) 95. አላህ የፍሬና የዛፍ ቅንጣትን ፈልቃቂ ነው:: ከሙት ነገር ሕያውን ያወጣል:: ከሕያዉም ነገር ሙትን አውጭ ነው:: ይህ አላህ ጌታችሁ ነው:: ታዲያ እንዴት ከእውነት ትሸሻላችሁ (ትርቃላችሁ)?
(96) 96. ጎሕን ከጽልመት ጨለማ ፈልቃቂ፤ ሌሊቱን ማረፊያ፤ ጸሐይንና ጨረቃን ለጊዜ ስሌት መጠቀሚያ ያደረገ አምላክ ነው:: ይህ የዚያ የአሸናፊውና የሁሉን አዋቂው አምላክ ውሳኔ ነው::
(97) 97. አላህ ያ በየብስና በባህር ጨለማዎች ውስጥ ራሳችሁን መምራት ትችሉ ዘንድ ከዋክብትን የፈጠረላችሁ አምላክ ነው:: ለሚያውቁ ሁሉ አናቅጽን በሚገባ አብራርተናል::
(98) 98. (ሰዎች ሆይ! ) እርሱ (አላህ) ያ ከአንዲት ነፍስ ያስገኛችሁ አምላክ ነው:: በማሕጸን ውስጥ ማረፊያንና ምድር ላይም መኖሪያን አመቻቸላችሁ:: መገንዘብ ለሚችሉ ሁሉ አናቅጽን በሚገባ አብራርተናል::
(99) 99. እርሱ (አላህ) ያ ከሰማይ ውሃን ያወረደ አምላክ ነው:: በእርሱም የሁሉንም ዓይነት እጽዋት አበቀልን:: የተደራረበን ቅንጣት የምናወጣበትን ለምለም አዝመራም ከርሱ አወጣን:: ከዘንባባ እንቡጥም የተቀራረቡ የሆኑ ዘለላዎችን አወጣን:: የወይን አትክልት ቦታዎችን አዘጋጀን:: ቅጠሎቻቸው የሚመሳሰሉ ፍሬዎቻቸው ግን የማይመሳሰሉ የሆኑትን የዘይቱን(ወይራ) እና የሩማን እጽዋትም ከሰማይ ባወረድነው ዝናብ አበቀልን:: (የሰው ልጆች ሆይ!) ፍሬውን ባፈራና በበሰለ ጊዜ እስቲ ተመልከቱት:: እጅግ አስደናቂ ሆኖ ታገኙታላችሁ:: በእነዚህ ክስተቶች ውስጥ በትክክል በአላህ ለሚያምኑ ሰዎች ሁሉ በርካታ ተአምራት አሉበት::
(100) 100. (ሰዎች) የፈጠራቸው አላህ ሲሆን አጋንንትን በመታዘዝ ለእርሱ ተጋሪዎች አደረጉ:: ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆች አለው በማለት ያለ ዕውቀት በእርሱ ላይ ቀጠፉ:: አላህ ጥራት የተገባውና ከሚሉት ነገር ሁሉ የላቀ ነው::
(101) 101. እርሱ ሰማያትንና ምድርን ያለ ብጤ ፈጣሪ ነው:: ለእርሱም ሚስት የሌለው ሲሆን እንዴት ለእርሱ ልጅ ይኖረዋል? ሁሉንም ነገር ፈጠረ:: እርሱ ሁሉንም ነገር አዋቂ ነውና::
(102) 102. ይህ ጌታችሁ አላህ ነው:: ከእርሱ በስተቀር አምላክ የለም:: ሁሉን ነገር ፈጣሪ ነው:: ስለዚህ እርሱን ብቻ ተገዙት:: እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነውና::
(103) 103. አይኖች አያገኙትም:: እርሱ ግን አይኖችን ያያል:: እርሱም ሩህሩህና ውስጠ አዋቂ ነው::
(104) 104. (ሰዎች ሆይ!) «ከጌታችሁ ዘንድ ብርሃኖች በእርግጥ መጡላችሁ:: እውነቱን የተመለከተ ሰው ጥቅሙ ለነፍሱ ብቻ ነው:: የታወረም ሰው ጉዳቱ በራሱ ላይ ብቻ ነው:: እኔ በእናንተ ላይ ጠባቂ አይደለሁም።» በላቸው::
(105) 105. ልክ እንደዚሁ ገምግመው «መጽሐፍ አጥንተሃል» እንዲሉና ለሚያውቁ ህዝቦች ቁርኣንን እንድናብራራ አናቅጽን እንገልፃለን።
(106) 106. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከጌታህ ወደ አንተ የተወረደውን ብቻ ተከተል:: ከእርሱ በስተቀር ትክክለኛ አምላክ የለም:: አጋሪዎችንም ተዋቸው::
(107) 107. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ በፈለገ ኖሮ እነርሱ ጣኦትን ባላጋሩ ነበር:: በእነርሱም ላይ ጠባቂ አላደረግንህም:: አንተም በእነርሱ ላይ ኃላፊ አይደለህም::
(108) 108. (ሙስሊሞች ሆይ!) እነዚያንም ከአላህ ሌላ የሚገዟቸውን ጣዖታትን አትስደቡ:: እነርሱም ድንበርን በማለፍ ያለ እውቀት አላህን ይሰድባሉና:: ልክ እንደዚሁ ለህዝቦች ሁሉ ስራቸውን ደግ አስመሰልንላቸው:: ከዚያም መመለሻቸው ወደ ጌታቸው ብቻ ነው:: ይሰሩት የነበሩትንም ሁሉ ይነግራቸዋል::
(109) 109. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ተዐምር ብትመጣላቸው በእርሷ በቁርጥ እንደሚያምኑ ጥብቅ መሀላዎቻቸውን በአላህ ማሉ:: «ተዓምራትም ሁሉ የሚከሰቱት ከአላህ ብቻ ነው። እርሷ በመጣች ጊዜም አለማመናቸውን ወይም ማመናቸውን ምን አሳወቃችሁ?» በላቸው::
(110) 110. በመጀመሪያም ጊዜ በእርሱ እንዳላመኑ ሁሉ ልቦቻቸውንና አይኖቻቸውን እናገላብጣለን:: በጥመታቸዉም ውስጥ የሚዋልሉ ሲሆኑ እንተዋቸዋለን::
(111) 111. እኛ ወደ እነርሱ መላዕክትን ባወረድንም ኖሮ ሙታንን ባነጋገሩዋቸውና ነገሩን ሁሉ በቡድን በቡድን በእነርሱ ላይ በሰበሰብንም ኖሮ አላህ ካልሻ በስተቀር የሚያምኑ ባልሆኑ ነበር:: ግን አብዛኞቻቸው ይህንን እውነታ ይስታሉ::
(112) 112. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እንደዚሁም ለነብያት ሁሉ ከሰውና ከጋኔን የሆኑን ሰይጣናት ጠላት አደረግን:: ከፊላቸው ወደ ከፊሉ ለማታለል የተዋበን ንግግር ይጥላሉ:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ በፈለገ ኖሮ ይህን ጸያፍ ተግባር ባልሰሩት ነበር:: ከቅጥፈታቸዉም ጋር ተዋቸው::
(113) 113. ሊያታልሉ የሚጥሩትና የነዚያም በመጨረሻይቱ ህይወት የማያምኑት ሰዎች ልቦች ወደ እርሱ እንዲያዘነብሉ፤ እንዲወዱትና እነርሱ ይቀጥፉ የነበሩትንም እንዲቀጣጥፉ ነው::
(114) 114. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እርሱ ያ መጽሐፍን የተብራራ ሆኖ ወደ እናንተ ያወረደ ሲሆን ከአላህ ሌላ ዳኛን እፈልጋለሁን? በላቸው:: እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ሰዎች ቁርኣን ከጌታህ ዘንድ በእውነት የተወረደ መሆኑን በትክክል ያውቃሉ:: እናም ከተጠራጣሪዎቹ አትሁን::
(115) 115. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የጌታህ ቃላት እውነተኛና ትክክለኛ ስትሆን ተፈጸመች:: ለቃላቱ ምንጊዜም ለዋጭ የለም:: እርሱ ሰሚውና አዋቂው ነው።
(116) 116. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በምድር ካሉት መካከል አብዛኞቹን ብትከተል የአላህን መንገድ ያሳስቱሀል:: ጥርጣሬን እንጂ ሌላን አይከተሉምና:: እነርሱም የሚዋሹ እንጂ ሌላ አይደሉም::
(117) 117. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ ከመንገዱ የሚሳሳቱትን አዋቂ ነው:: እርሱም ተመሪዎቹን እንዲሁ አዋቂ ነው::
(118) 118. (ሰዎች ሆይ!) በአናቅጹም አማኞች እንደሆናችሁ ሲታረድ የአላህ ስም በእርሱ ላይ የተወሳበትን እንሰሳ ብቻ ብሉ::
(119) 119. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እርሱን መብላት ካልተገደዳችሁበት በስተቀር በእናንተ እርም የተደረገውን ለእናተ አላህ በእርግጥ የዘረዘረ ሲሆን ከዚያ በእርሱ ላይ የአላህ ስም ከተጠራበት የማትበሉት ምን ምክንያት አላችሁ? ብዙዎቹም ያለ እውቀት በዝንባሌዎቻቸው ብቻ ያሳስታሉ:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ ወሰን አላፊዎቹን አዋቂ ነውና::
(120) 120. የኃጢአትን ግልጹንም ድብቁንም ተው:: እነዚያ ኃጢአትን የሚሰሩ ሁሉ ይሰሩት በነበሩበት ነገር በእያንዳንዱ በእርግጥ ይመነዳሉ።
(121) 121. (ሙስሊሞች ሆይ!) በእርሱ ላይ የአላህ ስም ያልተወሳበትን አትብሉ:: እርሱም በእርግጥ አመጽ ነው:: ሰይጣናትም ወደ ወዳጆቻቸው በክትን በመብላት ይከራከሯችሁ ዘንድ ያሾከሹካሉ:: ታዲያ ብትታዘዟቸው በእርግጥ አጋሪዎች ናችሁ::
(122) 122. ሙት የነበረና ከዚያም ህያው አድርገነው ለርሱም በሰዎች መካከል የሚሄድበትን ብርሃን ያደረግንለት በጨለማዎች ውስጥ ምንጊዜም የማይወጣ ሆኖ እንዳለው ብጤ ነውን? ልክ እንደዚሁ ለከሓዲያን ሁሉ ይሰሩት የነበሩት ነገር ተዋበላቸው::
(123) 123. ልክ እንደዚሁ በየከተማይቱ ውስጥ ታላላቅ ወንጀለኞቿ በውስጧ እንዲያሴሩ አደረግን። በነፍሶቻቸው ላይ እንጂ በሌላ ላይ አያሴሩም:: ግን ይህን እውነታ አያውቁም።
(124) 124. ተዓምር በመጣላቸውም ጊዜ «የአላህ መልዕክተኞች የተሰጡትን ብጤ እስክንሰጥ ድረስ በፍጹም አናምንም» አሉ:: አላህ መልዕክቱን የሚያደርግበትን ስፍራ አዋቂ ነው:: እነዚያን በአላህ ያመጹ ሰዎች ይዶልቱት በነበሩት ነገር አላህ ዘንድ ውርደትና ብርቱ ቅጣት ያገኛቸዋል::
(125) 125. አላህ ሊመራው የሚሻውን ሁሉ ልቡን ለኢስላም ይከፍትለታል:: ሊያጠመው የሚሻውን ደግሞ ልቡን ጠባብና ተቸጋሪ ወደ ሰማይ ለመውጣት እንደሚታገል ያደርገዋል:: ልክ እንደዚሁ አላህ በእነዚያ በማያምኑት ሰዎች ላይ ርክሰትን ያደርጋል::
(126) 126. ይህ ያለህበት መንገድ ቀጥተኛ ሲሆን የጌታህ መንገድ ነው:: ለሚያስታውሱ ህዝቦች አናቅጽን እርግጥ ዘርዝረናል::
(127) 127. ለእነርሱም በጌታቸው ዘንድ የሰላም ሀገር አለላቸው። እርሱ ይሰሩት በነበሩት ምክንያትም ረዳታቸው ነው::
(128) 128. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሁሉንም በአንድ ቦታ በሚሰበስባቸው ቀን የሚሆነውን አስታውስ:: «የአጋንንት ቡድኖች ሆይ! ከሰዎች ቡድንን በማጥመም በእርግጥ አበዛችሁ።» ይባላሉ:: ከሰዎችም መካከል የሆኑት ወዳጆቻቸው «ጌታችን ሆይ! ከፊላችን በከፊሉ ተጠቀመ:: ያንን ለእኛ የወሰንክልንን ጊዜያችንን ደረስን።» ይላሉ:: «እሳቲቱ አላህ የሻው ጊዜ ሲቀር በውስጧ ዘወታሪዎች ስትሆኑ መኖሪያችሁ ናት።» ይላቸዋል:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ ጥበበኛና አዋቂ ነው::
(129) 129. ልክ እንደዚሁ አንዳንድ በደለኞችን ይሰሩት በነበሩት ጥፋት ምክንያት በከፊሎች ላይ እንሾማለን::
(130) 130. «የአጋንትና የሰዎች ቡድኖች ሆይ! አንቀፆቼን በእናንተ ላይ የሚተርኩ የዚህንም ቀናችሁን ቅጣት ማግኘትን የሚያስፈራሯችሁ ከናንተው የሆኑ መልዕክተኞች አልመጡላችሁም ነበርን?» ይባላሉ:: «በነፍሶቻችን ላይ መሰከርን።» ይላሉ። የዱንያ ህይወት አታለለቻቸው። በነፍሶቻቸው ላይ እነርሱ ከሓዲያን የነበሩ መሆናቸውንም በራሳቸው መሰከሩ።
(131) 131. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ይህ የሆነው ጌታህ ከተሞችን ባለቤቶችዋ (ማስጠንቀቂያ ያልመጣላቸው) ዘንጊዎች ሆነው ሳሉ በበደል ምክንያት አጥፊ ባለመሆኑ ነው።
(132) 132. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለሁሉም ከሰሩት (አንፃር) የተበላለጡ ደረጃዎች አሏቸው:: ጌታህም ከሚሰሩት ስራ ዝንጉ አይደለም::
(133) 133. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህም በራሱ ተብቃቂ የእዝነት ባለቤት ነው:: ቢሻ ከምድረ ገጽ ያጠፋችኋል:: ከሌሎች ህዝቦችም ዘሮች እንዳስገኛችሁ ሁሉ ከበኋላችሁም የሚሻውን ሰው ይተካል::
(134) 134. (ሰዎች ሆይ!) የምትቀጠሩት ሁሉ በእርግጥ መጪ ነው:: እናንተም የምታቅቱ አይደላችሁም::
(135) 135. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ህዝቦቼ ሆይ! በችሎታችሁ ላይ ስሩ እኔ በችሎታዬ ላይ ሰሪ ነኝና:: ምስጉኒቱ ሀገር ገነት ለእርሱ የምትሆንለት ሰው ማን እንደሆነ ወደፊት ታውቃላችሁ:: እነሆ በደለኞች ሁሉ ምንጊዜም አይድኑም።» በላቸው::
(136) 136. አጋሪዎች ለአላህ ከፈጠራቸው ፍጡራን ከአዝመራውም ከግመል፣ ከከብት፣ ከፍየል፤ ከበጉም ድርሻን አደረጉለት:: በሀሳባቸዉም «ይህ የአላህ ነው፤ ይህ ደግሞ ለተጋሪዎቻችን ነው።» አሉ። ለተጋሪዎቻቸው የሆነው ነገር ወደ አላህ ምንጊዜም አይደርስም:: ለአላህ የሆነው ነገር ግን ወደ ተጋሪዎቹ ይደርሳል አሉ። የሚፈርዱት ፍርድ ከፋ!
(137) 137. ልክ እንደዚሁ ከአጋሪዎች ለብዙዎቹ ሊያጠፏቸውና ሀይማኖታቸውንም በነሱ ላይ ሊያቀላቅሉባቸው ዘንድ ልጆቻቸውን መግደልን ተጋሪዎቻቸው ጣኦታቱ አሳመሩላቸው:: አላህም በሻ ኖሮ (ይህን ጸያፍ ተግባር) ባልሰሩት ነበር:: እናም ከቅጥፈታቸው ጋር ተዋቸው::
(138) 138. በሀሳባቸውም «እነዚህ እርም የሆኑ ለማዳ እንሰሳና አዝመራ ናቸው:: የምንሻለት ሰው እንጂ ሌላ ማንም አይበላቸዉም:: እነዚህ ደግሞ ጀርባዎቻቸው እርም የተደረገ ለማዳ እንሰሳ ናቸው:: አይጫኑም:: እነዚህ ሲታረዱ በእነርሱ ላይ የአላህን ስም የማይጠሩባቸዉም እንሳሳት ናቸው።» አሉ:: በእርሱ ላይ ለመቅጠፍ ነገሩን ወደ አላህ አስጠጉ:: ይቀጥፉት በነበሩት ነገር በእርግጥ ይቀጣቸዋል::
(139) 139. «በእነዚህ እንስሳት ሆዶች ውስጥ ያለው ጽንሱ ሁሉ ለወንዶቻችን ብቻ በተለይ የተፈቀደ ነው:: በሚስቶቻችን ላይ ግን እርም የተደረገ ነው:: ሙት ሆኖ ቢወለድ ግን ወንዶቹም ሆነ ሴቶች በእርሱ ላይ ተጋሪዎች ናቸው።» አሉ:: ይህን በመቅጠፋቸው አላህ በእርግጥ ይቀጣቸዋል:: እርሱ ጥበበኛና አዋቂ ነውና::
(140) 140. እነዚያ ያለ እውቀት በሞኝነት ልጆቻቸውን የገደሉና አላህም የሰጣቸውን ሲሳይ በአላህ ላይ በመቅጠፍ በራሳቸው ላይ እርም ያደረጉ ሰዎች ሁሉ በእርግጥ ከሰሩ:: ተሳሳቱም:: ወደ ትክክለኛው መንገድም የተመሩ አልነበሩም::
(141) 141. አላህ ያ (በሀረጉ) ዳስ የሚያደርግላቸውንና ዳስ የማያደርግላቸውን አትክልቶች የፈጠረ ነው:: የተምርን ዛፍ፣ አዝመራን፣ ፍሬዎቹ የተለያዩ ሲሆኑ ወይራንና ሩማንንም ቅጠላቸው ተመሳሳይና ጣዕማቸው የማይመሳሰል ሲሆኑ ፈጠረ:: (ሰዎች ሆይ!) ባፈራ ጊዜም ከፍሬው ብሉ:: ባጨዳዉም ቀን ተገቢውን (ዘካ) ለተገቢው ስጡለት:: አታባክኑም:: አላህ አባካኞችን አይወድምና::
(142) 142. ከለማዳ እንሰሳዎችም የሚጫኑትንም የማይጫኑትንም ፈጠረ:: (ሰዎች ሆይ!) አላህ ከሰጣችሁ ሲሳይ ብሉ:: የሰይጣንንም እርምጃዎች አትከተሉ:: እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና::
(143) 143. ስምንትን ዓይነቶች፤ ከበግ ሁለትን (ወንድና ሴትን) ከፍየልም ሁለትን ፈጠረ:: «ከሁለቱም ክፍሎች አላህ ወንዶችን ብቻ እርም አደረገን? ወይንስ ሴቶችን ብቻ? ወይስ በእርሱ ላይ የሁለቱ ሴቶች ማህጸኖች ያጠቃለሉትን እርም አደረገ? እውነተኞች እንደሆናችሁ በእውቀት (በአስረጂ) ንገሩኝ» በላቸው::
(144) 144. ከግመል ሁለትን፤ ከከብት ሁለትን ፈጠረ። «አላህ ከሁለቱ ወንዶችን ብቻ እርም አደረገን? ወይንስ ሴቶችን ብቻ? ወይስ የሁለቱ ሴቶች ማህጸኖች ያጠቃለሉትን? በእውነቱ አላህ በዚህ ነገር ባዘዛችሁ ጊዜ በቦታው ነበራችሁን? ሰዎችን ያለ እውቀት ሊያጠም በአላህ ላይ ውሸትን ከቀጠፈ ሰው ይበልጥ በደለኛ ማን ነው? አላህ በደለኞችን ህዝቦች ቅኑን መንገድ አይመራም::» በላቸው።
(145) 145. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ወደ እኔ በተወረደው ቁርኣን ውስጥ በክት ወይም የፈሰሰ ደም፤ ወይም የአሳማ ስጋ እርሱ እርኩስ ነውና፤ ወይም በአመጽ ከአላህ ስም ሌላ በእርሱ ላይ የተወሳበት ካልሆነ በስተቀር ተመጋቢ ላይ እርም የሆነ ነገር አላገኝም። አመጸኛና ወሰን ያለፈ ሳይሆን የተገደደ ሰው ከተወሱት ነገሮች ነፍስን የማዳን ያህል ቢበላ ኃጢአት የለበትም:: ጌታህ መሀሪና አዛኝ ነውና።» በላቸው።
(146) 146. በአይሁዳውያን ላይ የጥፍር ባለቤት እንስሳትን ሁሉ እርም አደረግንባቸው:: ከከብት፤ ከፍየልና ከበግ ሞራዎቻቸውን፤ ጀርባዎቻቸው ወይም አንጀቶቻቸው የተሸከሙት ወይም በአጥንት የተቀላቀሉ ስብ ሲቀር በእነርሱ ላይ እርም አደረግን:: በአመፃቸው ምክንያት ይህን በማድረግ ቀጣናቸው:: እኛም እውነተኞች ነን::
(147) 147. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ቢያስተባብሉልህ፡- «ጌታችሁ የሰፊ ችሮታ ባለቤት ነው:: ብርቱ ቅጣቱም ከአመጸኞች ህዝቦች ላይ አይመለስም።» በላቸው።
(148) 148. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እነዚያ በአላህ ያጋሩት ሰዎች አላህ በሻ ኖሮ እኛም ሆነ አባቶቻችን በአላህ ባላጋራንና አንዳችንም ነገር እርም ባላደረግን ነበር።» ይላሉ:: ልክ እነዚህ እንደ አስተባበሉህ ሁሉ እነዚያ ከበፊታቸው የነበሩ ሕዝቦችም ብርቱ ቅጣታችንን እስከ ቀመሱ ድረስ አስተባበሉ:: «ለእኛ ታስተምሩን ዘንድ ማጋራታችሁን ለመውደዱ እናንተ ዘንድ እውቀት አለን? ጥርጣሬን እንጂ ሌላ አትከተሉም:: እናንተ ዋሾዎች እንጂ ሌላ አይደላችሁም።» በላቸው።
(149) 149. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «የተሟላው ማስረጃ የአላህ ማስረጃ ብቻ ነው:: በፈለገ ኖሮ ሁላችሁንም ባቀናችሁ ነበር።» በላቸው።
(150) 150. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እነዚያ አላህ ይህንን እርም ማድረጉን የሚመሰክሩትን ምስክሮቻችሁን እስቲ አምጡ።» በላቸው:: ቢመሰክሩም ከእነርሱ ጋር አትመስክር:: የእነዚያን በአናቅጻችን ያስተባበሉትን፤ የእነዚያንም በጌታቸው ሌላን የሚያስተካክሉ ሲሆኑ በመጨረሻይቱ ዓለም የማያምኑትን ሰዎች ዝንባሌዎች አትከተል::
(151) 151. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በላቸውም: «ኑ ጌታችሁ በእናተ ላይ እርም ያደረገውን ነገርና (በእርሱም ያዘዛችሁን) ላንብብላችሁ። እርሱም በአላህ ምንንም ነገር አታጋሩ:: ለወላጆቻችሁም በጎ ስራን ስሩ:: ልጆቻችሁንም ድህነትን ፈርታችሁ አትግደሉ:: እኛ እናንተንም ሆነ እነርሱን እንመግባችኋለንና:: ወደ ግልፅም ይሁን ድብቅ መጥፎ ስራ አትቅረቡ:: ያችንም አላህ እርም ያደረጋትን ነፍስ በሀቅ ቢሆን እንጂ አትግደሉ:: ይሀችሁ! ታውቁ ዘንድ በእርሱ አዘዛችሁ።
(152) 152. «የየቲምንም ገንዘብ አካለ መጠን እስኪድረስ ድረስ በመልካም ሁኔታ እንጂ አትቅረቡ:: ስፍርንና ሚዛንንም በትክከል ሙሉ:: ማንኛዋም ነፍስ የችሎታዋን ያህል እንጂ አናስገድድም:: በተናገራችሁ ጊዜ በዘመዶቻችሁ ላይ ቢሆንም እንኳ እውነትን በመናገር አስተካክሉ:: በአላህ ቃል ኪዳን ሙሉ:: ይሀችሁ ትገሰጹ ዘንድ አላህ በእርሱ አዘዛችሁ።
(153) 153. «ይህ ቀጥተኛው መንገዴ ነው:: እናም እርሱን ብቻ ተከተሉ:: የተለያዩ የጥመት መንገዶችንም አትከተሉ:: ከቀጥተኛው የርሱ መንገድ እናንተን ይለያይዋችኋልና:: ይሀችሁ ትጠነቀቁ ዘንድ አላህ በእርሱ አዘዛችሁ።»
(154) 154. ከዚያ ለሙሳ መፅሀፍ ሰጠነው መልካም በሰራው ላይ ጸጋችንን ለማሟላት፤ ነገርንም ሁሉ ለመዘርዘር፤ ለህዝቦቹም መሪና እዝነት ይሆን ዘንድ:: እነርሱ ከጌታቸው በመገናኘት ጉዳይ ሊያምኑ ይከጀላልና::
(155) 155. ይህ ያወረድነው የሆነ የተባረከ መጽሐፍ ነው:: እናም ተከተሉት፤ ይታዘንላችሁም ዘንድ ከክህደት ተጠንቀቁ።
(156) 156. (ያወረድነውም) «መጽሐፍ የተወረደው ከፊታችን በነበሩ ሁለቱ ህዝቦች ላይ ብቻ ነው:: እኛም ከንባባቸው ዘንጊዎች ነበርን» እንዳትሉም ነው።
(157) 157. ወይም «እኛ መጽሐፍ በእኛ ላይ በተወረደ ኖሮ ከእነርሱ ይበልጥ የተመራን እንሆን ነበር።» እንዳትሉም ነው:: ስለዚህም ከጌታችሁ ግልጽ ማስረጃ፤ መመሪያ እና እዝነት በእርግጥ መጣላችሁ:: በአላህ አናቅጽ ካስተባበለና ከእርሱም ከዞረ ሰው ይበልጥ ራሱን በዳይ ማን ነው? እነዚያን አናቅጽን የሚተውትን ይተውት በነበሩት አንቀጽ ምክንያት ብርቱ ቅጣት በእርግጥ እንቀጣቸዋለን::
(158) 158. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከሓዲያን መላዕክት ልትመጣላቸው ወይንም ጌታህ ሊመጣ ወይም ከጌታህ ምልክቶች ከፊሉ ሊመጣ እንጂ ሌላን ይጠባበቃሉን? ከጌታህ ምልክቶች ከፊሉ የሚመጣበት ቀን ግን ከዚያ በፊት አማኝ ያልነበረች ነፍስ ሁሉ ወይም አምና በእምነቷ በጎ ያልሰራች ነፍስ ሁሉ እምነቷ (ጸጸቷ) አይጠቅማትም:: «ያን ቀን እናንተም ተጠባበቁ እኛም ተጠባባቂዎች ነን።» በላቸው::
(159) 159. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከእነዚያ ሃይማኖታቸውን ከለያዩና ቡድን ቡድን ከሆኑ (ሰዎች) ጋር አይደለህም:: ነገራቸው ወደ አላህ ብቻ ነው:: ከዚያም ይሰሩት የነበሩትን ሁሉ ይነግራቸዋል::
(160) 160. መልካምን ስራ የሰራ ሁሉ ለእርሱ አስር እጥፍ ምንዳ አሉት:: ክፉ ስራን የሰራ ግን መሰሏን ብቻ እንጂ አይመነዳም:: እነርሱም ቅንጣት አይበደሉም::
(161) 161. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እኔ ጌታዬ ወደ ቀጥተኛው መንገድ፤ የተስተካከለ ወደሆነው ሃይማኖት የኢብራሂም መንገድ መራኝ:: እሱም ከአጋሪዎች አልነበረም።» በል።
(162) 162.(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በላቸው: «ስግደቴ፤ መገዛቴ (መስዋዕቴ)፣ ሕይወቴ፤ ሞቴ የሚገባው ለዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ ብቻ ነው።
(163) 163. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ለእርሱ (ለአላህ) አጋር የለዉም:: በዚህ (አላህን ከተጋሪ በማጥራት) ታዘዝኩ:: እኔ የሙስሊሞች መጀመሪያ ነኝ።» በል።
(164) 164. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «አላህ የሁሉ ጌታ ሲሆን ከአላህ በስተቀር ሌላን ጌታ እፈልጋለሁን? ነፍስ ሁሉ በራሷ ላይ እንጂ ክፉን አትሰራም:: ወንጀለኛ ነፍስ ሁሉ የሌላይቱን ነፍስ ኃጢአት አትሸከምም:: ከዚያ መመለሻችሁ ወደ ጌታችሁ ነው:: ከዚያም ትለያዩበት የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል» በላቸው።
(165) 165. (ሰዎች ሆይ!) እርሱ (አላህ) ያ በምድር ላይ ምትኮች ያደረጋችሁ በሰጣችሁም ጸጋ ሊፈትናችሁ ከፊላችሁን በከፊሉ ላይ በደረጃዎች ከፍ ያደረገ ሃያል ጌታ ነው:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ ቅጣቱ ፈጣን ነው:: አላህ እጅግ መሀሪና ሩህሩህ ነው::