17 - Al-Israa ()

|

(1) 1. ጥራት ለዚያ ባሪያውን (ሙሐመድን) ከተከበረው የሐረም መስጊድ ወደ እዚያ ዙሪያውን ወደ ባረክነው ሩቁ (አል አቅሷ) መስጊድ በሌሊት ለወሰደው አምላክ ለአላህ ይሁን:: ይህን ያደረግን ተዓምራታችንን ልናሳየው ነው:: እነሆ እርሱ (አላህ) ሰሚዉና ተመልካቹ ነው::

(2) 2. ለሙሳም (ተውራት የተባለውን) መጽሐፍ ሰጠነውና ለኢስራኢል ልጆች መሪ አደረግነው:: ከእኔ ሌላ ወኪል (መጠጊያ) አድርጋችሁ ማንንም አታድርጉ“ስንልም አዘዝናቸው::

(3) 3. «ከኑህ ጋር (በመርከቧ ላይ) የጫንናቸው (አማኝ )ዝርዮች ሆይ! (አላህን ተገዙ)፤ ኑህ በእርግጥ አምላኩን በብዛት አመስጋኝ ባሪያ ነበርና» አልናቸው።

(4) 4. ለኢስራኢል ልጆችም፡ “በምድር ላይ ሁለት ጊዜ ጥፋት ትፈጽማላችሁ:: አለቅጥም አምባገነን ትሆናላችሁ::” ስንል በመጽሐፉ ውስጥ ገለጽን::

(5) 5. ከሁለቱ የመጀመሪያው ጥፋት መፈጸሚያ ወቅቱ በደረሰ ጊዜ የበረታ ኃይል ያላቸውን ባሮቻችንን በእናነተ ላይ ላክንባችሁ:: እነርሱም ቤቶችን ሁሉ በረበሩ:: ይህ መፈጸሙ የማይቀር ውሳኔ ነበር::

(6) 6. (የኢስራኢል ልጆች ሆይ!) ከዚያም በኋላ በእነርሱ ላይ የድል አድራጊነትን እድል ሰጠናችሁ:: ገንዘብንና ወንዶች ልጆችንም ለገስናችሁ:: በሰው ኃይልም ብዙ አደረግናችሁ::

(7) 7. መልካምን ብትሠሩ ለነፍሶቻችሁ መልካምን ሠራችሁ:: መጥፎንም ብትሠሩ በነፍሶቻችሁ ላይ ነው:: የኋለኛይቱ ጥፋት ቀጠሮ በደረሰ ጊዜ ፊቶቻችሁን ሊያስከፉ፤ መስጊዱንም በመጀመሪያ ጊዜ እንደገቡቡት ሊገቡ፤ ያሸነፉትንም ሁሉ ፈጽመው ማጥፋትን እንዲያጠፉ እንልካቸዋለን::

(8) 8. (የኢስራኢል ልጆች ሆይ! በመጽሐፉም አልን ብትጸጸቱ) «ጌታችሁ ሊያዝንላችሁ ይከጀላል:: ወደ ማጥፋት እንደገና ብትመለሱም እኛም ወደ ቅጣቱ እንመለሳለን:: ገሀነምንም ለከሓዲያን ሁሉ ማሰሪያ አድርገናል።»

(9) 9. ይህ ቁርኣን ወደዚያች በሁሉ ነገር ቀጥተኛ ወደ ሆነችው መንገድ ይመራል:: እነዚያንም በጎ የሚሠሩትንም አማኞች ለእነርሱ ታላቅ ምንዳ ያላቸው መሆኑን ያበስራል::

(10) 10. እነዚያም በመጨረሻይቱ ዓለም የማያምኑት ለእነርሱ አሳማሚ ቅጣትን አዘጋጅተንላቸዋል::

(11) 11. ሰው መልካምን ነገር እንደሚለምን ሁሉ መጥፎንም ነገር ይለምናል:: ሰዉም ቸኳይ ነውና::

(12) 12. ሌሊትንና ቀንን ለችሎታችን ምልክቶች አደረግን:: የሌሊትን ምልክትም አበስን:: የቀንን ምልክትም የምታሳይ አደረግን:: ይህም የሆነበት ከአላህ ትርፍን ልትፈልጉበትና የዓመታትንም ቁጥርና ሒሳብን ታውቁበት ዘንድ ነው:: ነገሩንም ሁሉ ለያይተን ዘረዘርነው::

(13) 13. ሰውን ሁሉ በራሪውን (ሥራውን) በአንገቱ ላይ አስያዝነው:: ለእርሱም በትንሣኤ ቀን የተዘረጋ ሆኖ የሚያገኘው የሆነን መጽሐፍ እናወጣለታለን::

(14) 14. (ከዚያም) «መጽሐፍህን አንብብ:: ዛሬ ባንተ ላይ ተቆጣጣሪነት በነፍስህ ብቻ በቃ።» ይባላል።

(15) 15. በቀናው መንገድ የተመራ ሁሉ የሚመራው ለእራሱ ብቻ ነው:: ከቀናው መንገድ የተሳሳተም የመሳሳቱ ጉዳት በእርሱ ላይ ብቻ ነው:: ተሸካሚም ነፍስ የሌላይቱን ኃጢአት አትሸከምም:: መልዕክተኛንም እስከምንልክ ድረስ ማንንም የምንቀጣ አይደለንም።

(16) 16. ማንኛዋንም ከተማ ለማጥፋት በፈለግን ጊዜ ባለ ጸጋዎችዋን እናዛቸዋለን:: በውስጧም ያምፃሉ:: በእርሷም ላይ የቅጣት ቃሉ ይፈጸምባታል:: ከዚያም ማውደምን እናወድማታለን::

(17) 17. ከኑሕም በኋላ ከየክፍለ ዘመናት ሰዎች ያጠፋናቸው ብዙዎች ናቸው:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የባሮቹንም ኃጢአቶች ውስጠ አዋቂ ተመልካች መሆን በጌታህ ብቻ በቃ::

(18) 18. ጊዜያዊቱን ዓለም (በሥራው) የሚፈልግ ሁሉ ለእርሱ ከእርሷ ውስጥ የፈለግነውን ጸጋ ብቻ ለምንፈልገውም ብቻ እናስቸኩልለታለን:: ከዚያም ለእርሱ ገሀነምን መኖሪያ አድርገንለታል:: ተወቃሽና ከአላህ እዝነት የተባረረ ሆኖ ይገባባታል።

(19) 19. የመጨረሻይቱን ዓለም የፈለገ እና እርሱ አማኝ ሆኖ ለእርሷ ተገቢ የሆነን ሥራ የሠራ ደግሞ እነዚህ ሥራቸው የተመሰገነ ይሆናል::

(20) 20. ሁሉንም እነዚህንም እነዚያንም ከጌታህ ስጦታ በዚህ ዓለም እንጨምርላቸዋለን:: የጌታህም ስጦታ በዚች ዓለም ክልክል አይደለም::

(21) 21. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ እንዴት እንዳስበለጥን ተመልከት:: የመጨረሻይቱም ሀገር በማዕረጎች በጣም የከበረችና በመብለጥም የላቀች ናት::

(22) 22. (የሰው ልጅ ሆይ!) ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ አታድርግ:: የተወቀስክ፤ ረዳት የሌለህ ትሆናለህና::

(23) 23. (የሰው ልጅ ሆይ!) ጌታህ እንዲህ ሲል አዘዘ:: እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፤ ለወላጆቻችሁም መልካምን ሥሩ፤ ባንተ ዘንድ ሆነው ከወላጆችህ አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ «ኡፍ!» እንኳን አትበላቸው:: አትገላምጣቸዉም:: ለእነርሱም መልካምን ቃል ብቻ ተናገራቸው::

(24) 24. (ልጅ ሆይ!) ለሁለቱም የመተናነስ ክንፍን ዝቅ አድርግላቸው። «ጌታዬ ሆይ! በሕጻንነቴ በርህራሄ እንዳሳደጉኝ ሁሉ ለእነርሱም እዘንላቸው።» በልም።

(25) 25. (ሰዎች ሆይ!) ጌታችሁ በነፍሶቻችሁ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ይበልጥ አዋቂ ነው:: ታዛዦችም ብትሆኑ ወይም ብታጠፉ እርሱ ለተመላሾች ሁሉ መሓሪ ነው::

(26) 26. (የሰው ልጅ ሆይ!) ለዝምድና ባለቤት ሁሉ ተገቢ መብቱን ስጥ:: ለምስኪንና ለመንገደኛም እንዲሁ መብቱን ስጥ:: (በሁሉም ነገር ላይ) ማባከንንም አታባክን::

(27) 27. አባካኞች የሰይጣናት ወንድሞች ናቸውና:: ሰይጣንም ለጌታው ብርቱ ከሓዲ ነው::

(28) 28. ከጌታህም የምትከጅላትን ጸጋ ለማምጣት በማሰብ ከእነርሱ ብትዞር ለእነርሱ ልዝብን ቃል ተናገራቸው::

(29) 29. እጅህን ወደ አንገትህ ታጥፋ የታሠረች አታድርግ:: መዘርጋትንም ሁሉ አትዘርጋት:: የተወቀስክና የተቆጨህ ትሆናለህና::

(30) 30. ጌታህ ሲሳይን ለሚፈልገው ሁሉ ያሰፋል። ለሚፈልገውም ያጠባል። እርሱ በባሮቹ ሁኔታ ውስጠ አዋቂና ተመልካች ነውና።

(31) 31. (ሰዎች ሆይ!) ልጆቻችሁንም ድህነትን በመፍራት አትግደሉ:: እኛ እንመግባቸዋለን:: እናንተንም እንመግባችኃለን:: እነርሱን መግደል ታላቅ ኃጢአት ነውና::

(32) 32. (ሰዎች ሆይ!) ዝሙትንም አትቅረቡ:: እርሱ በእርግጥ መጥፎ ሥራ ነውና:: መንገድነቱም ከፋ!

(33) 33. (ሰዎች ሆይ!) ያቺንም አላህ ያከበራትን ነፍስ ያለ ሕግ አትግደሉ:: የተበደለ ሆኖ ለተገደለም ሰው ዘመዱ በገዳዩ ላይ ስልጣንን አድርገንለታል:: በመግደል ወሰንን አይለፍ:: እርሱ እገዛ ያለው ነውና::

(34) 34. (ሰዎች ሆይ!) የየቲምንም ገንዘብ የብርታቱን ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በዚያች እርሷ መልካም በሆነች ሁኔታ እንጂ አትቅረቡ:: በቃል ኪዳናችሁም ሙሉ:: ቃል ኪዳን የሚጠየቁበት ጉዳይ ነውና::

(35) 35. (ሰዎች ሆይ!) በሰፈራችሁም ጊዜ ስፍርን ሙሉ:: በትክክለኛው ሚዛንም መዝኑ:: ይህ መልካም ነገር ነው:: መጨረሻዉም ያማረ ነው::

(36) 36. (የሰው ልጅ ሆይ!) ላንተ በእርሱ እውቀት የሌለህንም ነገር አትከተል:: መስሚያ፤ ማያ፤ ማሰቢያም እነዚህ ሁሉ ባለቤታቸው ከእነርሱ ተጠያቂ ነውና::

(37) 37. (የሰው ልጅ ሆይ!) በምድር ላይ የተንበጣረርክ ሆነህም አትሂድ:: አንተ ፈጽሞ ምድርን አትሰረጉድምና:: በርዝመትም ፈጽሞ ጋራዎችን አትደርስምና::

(38) 38. (የሰው ልጅ ሆይ!) ይህ ሁሉ ክፋቱ ከጌታህ ዘንድ የተጠላ ነው።

(39) 39. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ይህ ጌታህ ከጥበብ ወደ አንተ ካወረደው ነገር ነው:: ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ አታድርግ:: የተወቀስክ፤ የተባረርክ ሆነህ በገሀነም ውስጥ ትጣላለህና::

(40) 40. (ጣኦታዊያን ሆይ!) ጌታችሁ በወንዶች ልጆች መረጣችሁና ከመላዕክት ሴቶችን ልጆች ለራሱ ያዘን? እናንተ ከባድ ቃልን በእርግጥ ትናገራላችሁ::

(41) 41. ይገሰጹ ዘንድ በዚህ ቁርኣን ውስጥ ደጋግመን በእርግጥ ገለጽን:: ለእነርሱ ግን ከትክክለኛው መንገድ መበርገግን እንጂ ሌላን አይጨምርላቸዉም::

(42) 42. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እነርሱ እንደሚሉት ከእርሱ ጋር ሌላ አማልክት በነበሩ ኖሮ ያን ጊዜ ወደ ዐርሹ ባለቤት መንገድን በፈለጉ ነበር።» በላቸው።

(43) 43. ጥራት ይገባው:: አላህ እነርሱ ከሚሉት ነገር ሁሉ ከፍ ያለን ልቅና ላቀ::

(44) 44. ሰባቱ ሰማያትና ምድር እንዲሁም በውስጣቸውም ያለው ሁሉ እርሱን ያጠራሉ:: ከነገሩ ሁሉ እሱን ከማመስገን ጋር የሚያጠራው እንጂ አንድም የለም:: ማጥራታቸውን ግን አታውቁትም:: እርሱ ታጋሽና መሓሪ ነው::

(45) 45. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ቁርኣንን ባነበብክ ጊዜ ባንተና በእነዚያ በመጨረሻይቱ ዓለም በማያምኑት ሰዎች መካከል የሚሸሸግን ግርዶሽ አድርገናል::

(46) 46. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እንዳያውቁትም በልቦቻቸው ላይ ሽፋንን፤ በጆሮቻቸዉም ውስጥ ድንቁርናን አደረግን:: ጌታህንም ብቻውን ሆኖ በቁርኣን ባወሳሀው ጊዜ የሚሸሹ ሆነው በጀርባዎቻቸዉ ላይ ይዞራሉ::

(47) 47. እኛ ወደ አንተ በሚያዳምጡ፤ በሚንሾካሸኩ፤ በዳዮችም እርስ በእርሳቸው «የተደገመበትን ሰው እንጂ አትከተሉም።» በሚሉ ጊዜ የሚያዳምጡበትን ምክንያት አዋቂ ነን።

(48) 48. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ላንተ ምሳሌዎችን እንዴት እንዳደረጉልህና ከዚያም እንዴት እንደ ተሳሳቱ ተመልከት:: ወደ እውነቱ ለመድረስ ትክክለኛውን መንገድ መከተል አይችሉም።

(49) 49. አሉም፡- «አጥንቶችና ብስብሶች በሆን ጊዜ እኛ እንዴት እንደገና አዲስ ፍጥረት ሆነን በእርግጥ ተቀስቃሾች እንሆናለን?»

(50) 50. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) (እንዲህ) በላቸው: «ድንጋዮች ወይም ብረትም ሁኑ፤

(51) 51. ወይም በልቦቻቸሁ ውስጥ የሚተልቅን ፍጥረትም ሁኑ (መቀስቀሳችሁ አይቀርም።)» «የሚመልሰንም ማነው?» ይላሉም። «ያ በመጀመሪያ ጊዜ የፈጠራችሁ ነው።» በላቸው:: ወደ አንተም ራሶቻቸውን ይነቀንቃሉ። «እርሱም መቼ ነው?» ይላሉም:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ! እንዲህ) በላቸው: «እርሱ በቅርብ ቀን ሊሆን ይችላል።

(52) 52. «እርሱም የሚጠራችሁንና አላህን አመስጋኞቹ ሆናችሁ ጥሪውን የምትቀበሉበት፤ ጥቂትን ቀናት እንጂ ያልቆያችሁ መሆናችሁን የምትጠራጠሩበት ቀን ነው።» በላቸው::

(53) 53. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለባሮቼም ንገራቸው:: መልካም የሆነችውን ቃል ብቻ ይናገሩ:: ሰይጣን በመካከላቸው ያበላሻልና:: ሰይጣን ለሰው ልጆች ግልጽ ጠላት ነውና::

(54) 54. (ሰዎች ሆይ!) ጌታችሁ በእናንተ ሁኔታ አዋቂ ነው:: ቢፈልግ ያዝንላችኋል፤ ቢፈልግም ይቀጣችኃል። (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በእነርሱ ላይ ሀላፊ ሆነህ አላክንህም:: አታስገድዳቸዉም::

(55) 55. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ በሰማያትና በምድር ያለውን ሁሉ አዋቂ ነው:: ከፊሉን ነብያት በከፊሉ ላይ አብልጠናል:: ዳውድንም ዘቡርን ሰጥተነዋል::

(56) 56. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በለቸው (ጣዖታዊያን ሆይ!) « እነዚያን ከእርሱ ሌላ አማልዕክት የምትሏቸውን እስቲ ጥሯቸው:: ከናንተም ላይ ጉዳትን ማስወገድን ወደ ሌላ ማዞርንም አይችሉም።»

(57) 57. እነዚያ እነርሱ የሚገዟቸው ማንኛቸዉም (ወደ አላህ) በጣም ቀራቢያቸው እንኳን ለራሳቸው ወደ ጌታቸው መቃረቢያን ሥራ ይፈልጋሉ:: እዝነቱንም ይከጅላሉ:: ቅጣቱንም ይፈራሉ:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የጌታህ ቅጣት የሚፈራ ነውና::

(58) 58. አንዲትም ከተማ የለችም እኛ ከትንሳኤ ቀን በፊት አጥፊዎችዋ ወይም ብርቱን ቅጣት ቀጭዎችዋ ብንሆን እንጂ:: ይህም በመጽሐፍ የተጻፈ ነው::

(59) 59. ተዓምራትን ከመላክ የቀድሞዎቹ ሰዎች በእርሷ ማስተባበልና መጥፋት እንጂ ሌላ አልከለከለንም። ለሠሙድም ግመልን ግልጽ ተዓምር ሆና ሰጠናቸው:: በእርሷም በደሉ፤ ተዓምራትንም ለማስፈራራት እንጂ አንልክም::

(60) 60. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ላንተም ጌታህ በእውቀቱ ሰዎችን ያካበበ መሆኑን በነገርንህ ጊዜ የሆነውን አስታውስ:: በሌሊቱ ጉዞ በዓይንህ ያሳየንህም ትርኢት ለሰዎች ፈተና እንጂ አላደረግነዉም:: በቁርኣንም የተረገመችውን ዛፍ እንደዚሁ ፈተና እንጂ አላደረግንም፤ እናስፈራራቸዋለንም፤ ትልቅንም ጥመት እንጂ አይጨምርላቸዉም::

(61) 61. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለመላዕክትም «ለአደም ስገዱ» ባልናቸው ጊዜ የነበረውን ሁኔታ አስታውስ:: ወዲያዉም ሰገዱ ዲያብሎስ ብቻ ሲቀር «ከጭቃ ለፈጠርከው ሰው እሰግዳለሁን?» አለ።

(62) 62. «እስቲ ንገረኝ ይህ ያ በእኔ ላይ ያበለጥከው ነውን? እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ ብታቆየኝ ዘሮቹን ጥቂቶች ሲቀሩ ወደ ስህተት በእርግጥ እስባቸዋለሁ።» አለ።

(63) 63. አላህም አለው: «ሂድ ከእነርሱም የተከተለህ ገሀነም የተሟላች ቅጣት ስትሆን ፍዳችሁ ናት።

(64) 64. «ከእነርሱ የቻልከውንም ሰው በድምጽህ ገፋፋ:: በእነርሱም ላይ በፈረሰኞችህ በእግረኞችህም ሆነህ ለልብ (አውጅ)። በገንዘቦቻቸዉም በልጆቻቸዉም ተጋራቸው:: የተስፋ ቃልም ግባላቸው።» ሰይጣንም ማታለልን እንጂ ተስፋ ቃልን አይገባላቸዉም::

(65) 65. ንጹህ ባሮቼ ግን በእነርሱ ላይ ፈጽሞ ላንተ ስልጣን የለህም:: ዋስም በጌታህ በቃ።

(66) 66. (ሰዎች ሆይ!) ጌታችሁ ያ ከችሮታው ትፈልጉ ዘንድ መርከቦችን በባህር ላይ ለእናንተ የሚነዳላችሁ ነው:: እነሆ እርሱ ለእናንተ አዛኝ ነውና::

(67) 67. በባህሩ ውስጥ ሆናችሁ ጉዳት በደረሰባችሁ ጊዜ የምትጠሯቸው አማልክት ሁሉ ይጠፉባችሁና እርሱ አላህ ብቻ ይቀራል። ወደ የብስም በማድረስ ባዳናችሁ ጊዜ እምነትን ትተዋላችሁ:: ሰው ሲባል በጣም ከሓዲ ነውና::

(68) 68. (ሰዎች ሆይ!) የየብሱን በኩል ምድርን በናንተ መገልበጡን ወይም ጠጠርን የያዘ ንፋስን በእናንተ ላይ መላኩን ከዚያም ለእናንተ ጠባቂ አለማግኘታችሁን አትፈሩምን?

(69) 69. ወይስ ሌላ ጊዜ ወደ እርሱ (ወደ ባህር) የሚመልሳችሁ ወዲያውኑም በእናንተ ላይ ብርቱን ነፋስ የሚልክ፤ በክህደታችሁም ምክንያት የሚያሰምጣችሁ መሆኑን ከዚያም በእኛ ላይ በእርሱ ተከታይነት (ረዳትን) ለእናንተ የማታገኙ መሆናቸሁን አትፈሩምን?

(70) 70. የአደምን ልጆች በእርግጥ ከሌላው ፍጡር አከበርናቸው:: በየብስና በባህርም አሳፈርናቸው:: ከመልካሞችም ሲሳዮችም ሰጠናቸው፤ ከፈጠርናቸው ፍጡራንም በብዙዎቹ ላይ ማብለጥን አበለጥናቸው::

(71) 71. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሰዎችን ሁሉ በመሪያቸው የምንጠራበትን ቀን አስታውስ። ያ መጽሐፉንም በቀኙ የተሰጠ ሰው እነዚያ መጽሐፋቸውን ያነባሉ፤ በተምር ፍሬ ስንጥቅ ላይ ያለውን ክር ያክል እንኳን አይበደሉም::

(72) 72. በዚህች ዓለም ልበ እውር የሆነ ሰው ሁሉ እርሱ በመጨረሻይቱም ዓለም እውር ነው:: መንገድንም በጣም የተሳሳተ ነው::

(73) 73. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነሆ ከዚያም ወደ አንተ ካወረድነው ሌላን በእኛ ላይ ትዋሽ ዘንድ ሊፈትኑህ በእርግጥ ተቃረቡ፤ ያን ጊዜም ወዳጅ አድርገው በያዙህ ነበር::

(74) 74.(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ባላረጋጋንህም ኖሮ ወደ እነርሱ ጥቂትን ዝንባሌ ልትዘነበል በእርግጥ በተቃረብክ ነበር::

(75) 75. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ያን ጊዜ የሕይወትን ሆነ የሞትን ድርብ ቅጣት እናቀምስህ ነበር:: ከዚያም ላንተ በእኛ ላይ ረዳትን አታገኝም ነበር::

(76) 76. ከምድሪቱ (ከዓረብ) ምድር ከእርሷ ያወጡህ ዘንድ ሊያሸብሩህ በእርግጥ ተቃረቡ:: ያን ጊዜም ካንተ በኋላ ጥቂትን ጊዜ እንጂ አይቆዩም ነበር::

(77) 77. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከመልዕክተኞቻችን ካንተ በፊት በእርግጥ እንደ ላክናቸው ሰዎች ልማድ ብጤ ይጠፋ ነበር፤ ለልማዳችንም መለወጥን አታገኝም (አይለወጥም)

(78) 78. ሶላትን ከጸሐይ መዘንበል እስከ ሌሊት ጨለማ ድረስ ስገድ:: የጎህንም ሶላት ስገድ:: የጎህ ሶላት መላዕክት የሚገኙበት ነውና::

(79) 79. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከሌሊት ላንተ ተጨማሪ የሆነችን ሶላት በቁርኣን ስገድ:: ጌታህ ምስጉን በሆነ ስፍራ በእርግጥ ያቆምሃልና::

(80) 80. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በልም: «ጌታዬ ሆይ! የተወደደን መግባት አስገባኝ፤ የተወደደንም መውጣት አስወጣኝ:: ለእኔም ካንተ ዘንድ የተረዳን ስልጣን አድርግልኝ።»

(81) 81. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እውነት መጣ ውሸትም ተወገደ፤ እነሆ ውሸት ተወጋጅ ነውና።» በል።

(82) 82. ከቁርኣን ለአማኞች መድሓኒትና እዝነት የሆነን እናወርዳለን በዳዮችንም ኪሳራን እንጂ ሌላ አይጨምርላቸዉም::

(83) 83. በሰዉም ላይ ጸጋችንን በለገስን ጊዜ ከምስጋና ይዞራል ጎኑንም ከእውነት ያርቃል:: ችግርም በነካው ጊዜ ተስፋ ቆራጭ ይሆናል::

(84) 84. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ሁሉም በሚመስለው መንገድ ላይ ይሠራል:: ጌታችሁም እርሱ መንገዱ ቀጥተኛ የሆነውን አዋቂ ነው።» በላቸው።

(85) 85. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከሓዲያን ከሩህ ይጠይቁሃል። «ሩህ ከጌታዬ ነገር ነው:: ከእውቀትም ጥቂትን እንጂ አልተሰጣችሁም።» በላቸው::

(86) 86. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ብንሻ ያንን ወደ አንተ ያወረድነውን በእርግጥ እንወስድብሃለን:: ከዚያም ላንተ በእኛ ላይ በእርሱ ለማስመለስ ተያዢን አታገኝም::

(87) 87. ግን ከጌታህ በሆነው እዝነት ጠበቅነው:: ችሮታው ባንተ ላይ ታላቅ ነውና::

(88) 88. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ሰዎችና ጋኔኖች የዚህን ቁርኣን ቢጤ በማምጣት ላይ ቢሰበሰቡና ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳት ቢሆኑም እንኳ ብጤውን አያመጡም።» በላቸው።

(89) 89. በዚህም ቁርኣን ውስጥ ከምሳሌው ሁሉ ለሰዎች በእርግጥ መላልሰን አብራራን:: አብዛኞቹም ሰዎች ክህደትን እንጂ ሌላን እምቢ አሉ::

(90) 90. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አሉም: «ለእኛ ከምድር ምንጭን እስከምታፈልቅልን ድረስ ላንተ አናምንም።

(91) 91. «ወይም ከዘንባባዎችና ከወይን የሆነች አትክልት ላንተ እስከምትኖርህና በመካከሏም ጅረቶችን በብዛት እስከምታንቧቧ ድረስ

(92) 92. «ወይም እንደምትለው ከሰማይ ቁራጮችን በእኛ ላይ እስከምታወርድ ወይም አላህንና መላዕክትን በግልጽ እስከምታመጣ ድረስ

(93) 93 «ወይም ከወርቅ የሆነ ቤት ላንተ እስከሚኖርህ ወይም በሰማይ እስከምትወጣ፤ ለመውጣትህም በእኛ ላይ የምናነበው የሆነን መጽሐፍ እስከምታወርድልን ድረስ ፈጽሞ አናምንልህም።» አሉ:: «ጌታዬ ጥራት ይገባው:: እኔ መልዕክተኛ (የሆንኩ) ሰው እንጂ ሌላ ነገር ነኝ እንዴ?!» በላቸው::

(94) 94. ሰዎችን መሪ ቁርኣን በመጣላቸው ጊዜ በሱ ከማመን «አላህ ሰውን መልዕክተኛ አድርጎ ላከን?» ማለታቸው ብቻ እንጂ ሌላ አልከለከላቸዉም።

(95) 95. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በምድር ላይ ተረጋግተው የሚጓዙ መላእክት ቢኖሩ ኑሮ ከሰማይ የመልአክ መልዕክተኛ እናወርድላቸው እንደነበር ንገራቸው።

(96) 96. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በእኔና በእናንተ መካከል ላለን ልዩነት መስካሪ በአላህ በቃ:: ምክኒያቱም እርሱ ባሮቹን ጠንቅቆ አዋቂና ተመልካች ነውና።» በላቸው።

(97) 97. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ ያቀናው በእርግጥም የተቀና ማለት እርሱው ነው:: እርሱ ያጠመማቸውን ግን ከቅጣቱ የሚያድናቸው ማንም ወዳጅ አታገኝላቸዉም:: የትንሳኤ ቀንም እውር፤ ዲዳና፤ ደንቆሮ አድርገን በፊቶቻቸው እየተጎተቱ እንሰበስባቸዋለን:: መኖሪያቸዉም ገሀነም ናት:: ሀይሏ በደከመ ጊዜም ግለትን እንጨምርላቸዋለን::

(98) 98. ይህ ቅጣት የሚጠብቃቸው ቅጣታቸው ነው:: ምክንያቱም በመልዕክተኞቻችን ክደው «የበሰበሰ አጥንት ከሆንና (ወደ አቧራነት) ከተቀየርን በኋላ እንደ አዲስ እንቀሰቀሳለን?» በማለታቸውም ነው።

(99) 99. ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ አላህ ብጤያቸውን በመፍጠር ላይ ቻይ መሆኑን በእርሱ ጥርጣሬ የሌለበትንም ጊዜ ለሞትም ለትንሳኤም ለእነርሱ የወሰነ መሆኑን አላወቁምን? በደለኞችም ከክህደት በስተቀር እምቢ አሉ::

(100) 100. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እናንተ የጌታዬን የችሮታ መካዚኖች ብትይዙ ኖሮ ያን ጊዜ በማውጣታችሁ ማለቋን በመፍራት በጨበጣችሁ ነበር:: ሰው በጣም ንፉግ ነውና።» በላቸው።

(101) 101. ለሙሳ ግልጽ የሆኑን ዘጠኝ ተዓምራት በእርግጥ ሰጠነው:: በመጣቸዉም ጊዜ የኢስራኢልን ልጆች ከፈርዖን እንዲለቀቁ ጠይቅ አልነው:: ፈርዖንም፡- «ሙሳ ሆይ! እኔ የተደገመብህ መሆንህን በእርግጥ እጠረጥርሃለሁ።» አለው።

(102) 102. ሙሳም፡- «እነዚህን ተዓምራት መግሰጫዎች ሲሆኑ የሰማያትና የምድር ጌታ እንጂ ሌላ እንዳላወረዳቸው በእርግጥ አውቀሀል:: እኔም ፈርዖን ሆይ! የምትጠፋ መሆንህን በእርግጥ እጠረጥርሃለሁ።» አለው።

(103) 103. ከምድርም ሊያባርራቸው አሰበ:: እርሱንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ሁሉንም አሰመጥናቸው::

(104) 104. ከእርሱም በኋላ ለኢስራኢል ልጆች «ምድሪቱን ተቀመጡባት:: የኋለኛይቱም ሰዓት ቀጠሮ በመጣ ጊዜ እናንተን የተከማቻችሁ ስትሆኑ እናመጣችኋለን።» አልናቸው።

(105) 105. ቁርኣንን በእውነትም አወረድነው:: በእውነትም ወረደ:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አንተንም አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን እንጂ አልላክንህም::

(106) 106. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ቁርኣንንም በሰዎች ላይ ሁነህ በዝግታ ታነበው ዘንድ ከፋፈልነው:: ቀስ በቀስ ማውረድንም አወረድነው::

(107) 107. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በእርሱ እመኑ ወይም አትመኑ።» በላቸው:: እነዚያ ከእርሱ በፊት እውቀትን የተሰጡት በእነርሱ ላይ በተነበበ ጊዜ ሰጋጆች ሆነው በሸንጎበቶቻቸው ላይ ይወድቃሉ::

(108) 108. ይላሉም: «ጌታችን ጥራት ይገባው። እነሆ የጌታችን ተስፋ ተፈጻሚ ነው።» ይላሉ።

(109) 109. እያለቀሱም በአሸንጎበቶቻቸው (በአገጮቻቸው) ላይ ይወድቃሉ:: አላህም ፍርሃትን ይጨምርላቸዋል::{1}
{1} አዚህ የንባብ ሱጁድ (ሱጁድትላዋ) ይደረጋል።

(110) 110. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «አላህን ጥሩ ወይም አር-ረህማንን ጥሩ:: ማንኛውንም ስም ብትጠሩ መልካም ነው:: ለእርሱ ብዙ መልካም ስሞች አሉትና።» በላቸው። በስግደትህም ስታነብ በጣም ድምጽህን አትጩህ:: በእርሷም በጣም ድምጽህን ዝቅ አታድርግ:: በሁለቱ መካከል የሆነ መንገድን ፈልግ::

(111) 111. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ምስጋና ሁሉ ለዚያ ልጅን ላልያዘው ለእርሱም በንግስናው ተጋሪ ለሌለው ለእርሱም ከውርደት የሚያድነው ወዳጅ ለሌለው ለአላህ ብቻ ይገባው።» በል። እርሱን ማክበርንም አክብረው።