61 - As-Saff ()

|

(1) 1. በሰማያትና በምድር ውስጥ ያሉ ሁሉ አላህን አጠሩ:: እርሱ አሸናፊና ጥበበኛው ነው::

(2) 2. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የማትሰሩትን ነገር ለምን ታወራላችሁ?

(3) 3. የማትሰሩትን ነገር መናገራችሁ በአላህ ዘንድ በመጠላት እጅግ ከበደ::

(4) 4. አላህ እነዚያን ልክ እንደተለሰነ ግንብ የተሰለፉ ሆነው በሃይማኖቱ የሚፋለሙትን ይወዳል::

(5) 5. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሙሳም ለህዝቦቹ፡- «ህዝቦቼ ሆይ! እኔ ወደ እናንተ የአላህ መልዕክተኛ መሆኔን እያወቃችሁ ለምን ታሰቃዩኛላችሁ?» ባለ ጊዜ የሆነውን አስታውስ:: ከእውነት በተዘነበሉ ጊዜ አላህም ልቦቻቸውን አዘነበለባቸው:: አላህ አመጸኞችን ህዝቦች አያቀናምና::

(6) 6. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የመርየም ልጅ ዒሳም፡- «የኢስራኢል ልጆች ሆይ! እኔ ከተውራት በፊት ያለውን የማረጋግጥና ከእኔ በኋላ በሚመጣው መልዕክተኛ ስሙ አህመድ በሆነውም የማበስር ስሆን ወደ እናንተ የተላኩ የአላህ መልዕክተኛ ነኝ» ባለ ጊዜ የሆነውን አስታውስ:: ግልጽ ታዐምራቶችን ባመጣላቸው ጊዜ «ይህ ግልጽ ድግምት ነው» አሉ::

(7) 7. እርሱ ወደ ኢስላም የሚጠራ ሲሆን በአላህ ላይ ውሸትን ከቀጣጠፈ ይበልጥ በደለኛ ማን ነው? አላህ በዳዮችን ህዝቦች አይመራም::

(8) 8. የአላህን ብርሃን በአፎቻቸው ሊያጠፉ ይሻሉ:: ከሓዲያን ቢጠሉም እንኳ አላህ ብርሀኑን ገላጭ ነው::

(9) 9. አላህ ያ አጋሪዎቹ ቢጠሉም መልዕክተኛውን በመምሪያ መጽሐፍና በእውነተኛ ሃይማኖት (በኢስላም) ከሃይማኖት ሁሉ በላይ ይፋ ሊያደርገው የላከ ነው፡፡

(10) 10. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከአሳማሚ ቅጣት የሚያድናችሁን ትርፋማ ንግድ ላመላክታችሁን?» በላቸው።

(11) 11. እርሱም በአላህና በመልዕክተኛው ታምናላችሁ:: በአላህ መንገድ በገንዘቦቻችሁና በነፍሶቻችሁ ትታገላለችሁ:: ይህ ተግባር የምታውቁ ከሆናችሁ ለእናንተ የተሻለ ነው::

(12) 12. ኃጢአቶቻችሁን ይምራል:: ከስሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸዉም ገነቶች ያስገባችኋል:: በመኖሪያ ገነቶችም በሚያምሩ ቤቶች ውስጥ ያስቀምጣችኋል:: ይህ ታላቅ እድል ነው::

(13) 13. ሌላይቱንም የምትወዷትን ጸጋ ይሰጣችኋል:: እርሷም ከአላህ የሆነ እርዳታና ቅርብ የሆነ አገር መክፈት ነው:: አማኞችንም አብስር::

(14) 14. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የመርየም ልጅ ዒሳ ለሐዋሪያቱ፡- «ወደ አላህ ረዳቴ ማን ነው» እንዳለና ሐዋርያቶቹም፡- «እኛ የአላህ ረዳት ነን» እንዳሉት ሁሉ እናንተም የአላህ ረዳቶች ሁኑ፤ ከኢስራኢል ልጆችም አንደኛዋ ቡድን አመነች:: ሌላይቱም ቡድን ካደች:: እነዚያን ያመኑትንም በጠላታቸው ላይ አበረታናቸው:: ከዚያ እነርሱም አሸናፊዎች ሆኑ::