49 - Al-Hujuraat ()

|

(1) 1. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልዕክተኛው ፊት ነፍሶቻችሁን አታስቀድሙ:: አላህንም ፍሩ:: አላህ ለሚባለው ሁሉ ሰሚ ለሚፈጸመው ነገር ሁሉ አዋቂ ነውና::

(2) 2. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ድምፆቻችሁን ከነብዩ ድምጽ በላይ ከፍ አታድርጉ:: ከፊላችሁ ለከፊሉ እንደሚጮህም ሁሉ በንግግር ለርሱ ስትናገሩ አትጩሁ:: እናንተ የማታውቁ ስትሆኑ ስራዎቻችሁ እንዳይበላሹ (ከዚህ ተከልከሉ)::

(3) 3. እነዚያ በአላህ መልዕክተኛ ዘንድ ድምፆቻቸውን ዝቅ የሚያደርጉ እነዚህ እነዚያ አላህ ልቦቻቸውን ለፍርሃት የፈተናቸው ናቸው:: ለእነርሱም ምህረትና ታላቅ ምንዳ አለላቸው::

(4) 4. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያ ከመኖሪያ ክፍሎቹ ውጭ ሆነው የሚጠሩህ አብዛሀኞቻቸው አያውቁም::

(5) 5. ወደ እነርሱም እስክትወጣ ድረስ ዝምብለው በታገሱ ኖሮ ለእነርሱ በላጭ በሆነ ነበር:: አላህም እጅግ መሀሪና አዛኝ ነውና::

(6) 6. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ነገረኛ ወሬ ቢያመጣላችሁ በስህተት ላይ ሆናችሁ ህዝባችሁን እንዳትጎዱና ከዚያም በሰራችሁት ነገር ላይ ተጸፃቾች እንዳትሆኑ አረጋግጡ::

(7) 7. በውስጣችሁም የአላህ መልዕክተኛ መኖሩን እወቁ:: ከነገሩ በብዙው ነገሮች ቢከተላችሁ ኖሮ በእርግጥ በተቸገራችሁ ነበር:: ግን አላህ እምነትን ወደ እናንተ አስወደደ :: በልቦቻችሁም ውስጥ አስዋበው። ክህደትን፣ አመፅንና እምቢተኝነትንም ለናንተ የተጠላ አደረገ። እነዚያ እምነትን የወደዱና ክሕደትን የጠሉ ሰዎች እነርሱ ትክክለኛ ቅኖቹ ናቸው።

(8) 8. ከአላህ በሆነው ችሮታና ጸጋ ሲሆን ቅኖች ናቸው። አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነው።

(9) 9. ሁለት የምዕምናን ቡድኖች እርስ በእርስ ቢጋደሉ በመካከላቸው አስታርቁ:: ከሁለት አንደኛይቱ በሌላኛይቱ ላይ ወሰን ብታልፍ ያችን ወሰን የምታልፈውን ወደ አላህ ትዕዛዝ እስከምትመጣ ድረስ ተጋደሏት፤ ብትመለስ ግን በመካከላቸው በትክክል አስታርቁ:: በነገሩ ሁሉ አስተካክሉ:: አላህ አስተካካዮችን ይወዳልና።

(10) 10.(አማኞች ሆይ!) ምዕመናኖች ወንድማማቾች ናቸውና በሁለት ወንድሞቻችሁ መካከል አስታርቁ:: ይታዘንላችሁም ዘንድ አላህን ፍሩ::

(11) 11.እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ወንዶች በወንዶች አይሳለቁ:: ከእነርሱ የበለጡ ሊሆኑ ይከጀላልና:: ሴቶችም በሴቶች አይሳለቁ:: ከእነርሱ የበለጡ ሊሆኑ ይከጀላልና:: ነፍሶቻችሁንም አታነዉሩ በመጥፎ ሰሞችም አትጠራሩ:: ከእምነት በኋላ መጥፎ ስም ከፋ:: ያልተጸጸተ ሰው በእውነት እነርሱ በዳዮቹ ናቸው።

(12) 12. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከጥርጣሬ ብዙን ራቁ:: ከጥርጣሬ ከፊሉ ኃጢአት ነውና:: ነውርንም አትከታተሉ። ከፊላችሁም ከፊሉን አይማው። አንደኛችሁ የወንድሙን ስጋ የሞተ ሆኖ ሊበላ ይወዳልን? (መብላቱን) ጠላችሁት (ሀሜቱንም ጥሉት):: አላህንም ፍሩ:: አላህ ጸጸትን ተቀባይና አዛኝ ነውና::

(13) 13. እናንተ ሰዎች ሆይ! እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ:: እንድትተዋወቁም ጎሳዎችና ነገዶች አደረግናችሁ:: አላህ ዘንድ በላጫችሁ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ብቻ ነው:: አላህ ግልጽን አዋቂ ውስጥንም አዋቂ ነው::

(14) 14. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የዐረብ ዘላኖች አምነናል አሉ:: «አላመናችሁም ግን ሰልመናል በሉ እምነቱም በልቦቻችሁ ውስጥ ገና ጠልቆ አልገባም:: አላህንና መልዕክተኛውን ብትታዘዙ ከስራዎቻችሁ ምንም አይጎድልባችሁም:: አላህ መሀሪና አዛኝ ነውና» በላቸው::

(15) 15. አማኞች እነዚያ በአላህና በመልዕክተኛው ያመኑትና ከዚያም ያልተጠራጠሩት በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸዉም በአላህ መንገድ ላይ የታገሉት ሰዎች ብቻ ናቸው:: እነዚያ እነርሱ እውነተኞቹ ናቸው::

(16) 16. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «አላህ በሰማያት ውስጥ ያለውንና በምድር ውስጥ ያለውን ሁሉ የሚያውቅ ሲሆን አላህን በሃይማኖታችሁ ታስታውቁታላችሁን?» በላቸው:: አላህም በነገሩ ሁሉ አዋቂ ነው::

(17) 17. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በመስለማቸው ባንተ ላይ ይመፃደቃሉ። «በእስልምናችሁ በእኔ ላይ አትመጻደቁ:: ይልቁንም አላህ ወደ ትክክለኛው እምነት ስለመራችሁ ፀጋውን ውሎላችኋል:: እውነተኞች ብትሆኑ (መመፃደቅ የሚገባው ለአላህ) ብቻ ነው» በላቸው።

(18) 18. አላህ የሰማያትንና የምድርን ሩቅ ሚስጥር ሁሉ ያውቃል:: አላህ የምትሰሩትን ሁሉ ተመልካችም ነው::