31 - Luqman ()

|

(1) 1. አሊፍ፤ ላም፤ ሚይም፤

(2) 2. እነዚህ አናቅጽ ጥበብ ከተሞላው መጽሐፍ ናቸው።

(3) 3. ለበጎ አድራጊዎች ሁሉ መሪ፣ እዝነት ሲሆን፤

(4) 4. ለእነዚያ ሶላትን አስተካክለው ለሚሰግዱ፤ ዘካንም ለሚሰጡት፤ በመጨረሻይቱም ዓለም የሚያረጋግጡ ለሆኑት፤

(5) 5. እነዚያ (የተጠቀሱትን ባህሪያት የሚላበሱ ሰዎች ሁሉ) በጌታቸው መመሪያ ላይ የሚጓዙ ናቸው። እነዚያ ፍላጎታቸውንም ያገኙትም እነርሱ ብቻ ናቸው::

(6) 6. ከሰዎች መካከል ያለ ምንም እውቀት ሰዎችን ከአላህ መንገድ ሊያሳስትና የአላህን መንገድ ማላገጫ ሊያደርግ አታላይ ወሬን የሚገዛ አለ:: እነዚያ ይህን የሚያደርጉ ሁሉ ለእነርሱ አዋራጅ ቅጣት አለባቸው::

(7) 7. አናቅጻችን በእርሱ ላይ በሚነበቡ ጊዜ እንዳልሰማትና በጆሮቹ ድንቁርና እንዳለበት የኮራ ሆኖ ይዞራል:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ይህን ሰው በአሳማሚ ቅጣት አብስረው::

(8) 8. እነዚያ ያመኑና መልካሞችን ተግባራት የሰሩ ሁሉ ለእነርሱ የጸጋ ገነቶች አሏቸው::

(9) 9. በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ሲሆኑ አላህ እውነተኛን የተስፋ ቃል ገባላቸው:: እርሱም ሁሉንም አሸናፊና ጥበበኛ ነውና::

(10) 10. ሰማያትን የምታዮዋት ምሰሶ ሳያደርግላት ፈጠረ:: በምድርም ውስጥ በእናንተ እንዳታረገርግ ተራራዎችን ጣለ:: በእርሷም ላይ ከተንቀሳቃሽ ነገሮች ሁሉ በተነ:: ከሰማይም ውሃን አወረድን:: በእርሷ ውስጥ ከመልካም ዓይነት ሁሉ አበቀልን::

(11) 11. ይህ ሁሉ የአላህ ፍጡር ነው:: እነዚያ ከእርሱ ሌላ ያሉት ምንን እንደ ፈጠሩ እስኪ አሳዩኝ:: በዳዮች በእውነት በግልጽ ጥመት ውስጥ ናቸው::

(12) 12. ለሉቅማንም ጥበብን በእርግጥ ሰጠነው:: አላህን አመስግን አልነዉም:: ያመሰገነም ሁሉ የሚያመሰግነው ለራሱ ብቻ ነው:: የካደም ሰውም (በራሱ ላይ ነው::) አላህ ተብቃቂና ምስጉን ነውና::

(13) 13. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሉቅማንም ለልጁ እርሱ የሚገስጸው ሲሆን «ልጄ ሆይ! በአላህ አታጋራ። ማጋራት ታላቅ በደል ነውና።» ያለውን አስታውስ።

(14) 14. ሰውንም በወላጆቹ በጎ እንዲያደርግ በጥብቅ አዘዝነው:: እናቱ ከድካም በላይ በሆነ ድካም አረገዘችው:: ጡት መጣያዉም በሁለት ዓመት ውስጥ ነው:: «ለእኔም ለወላጆችህም አመስግን" በማለትም አዘዝነው። መመለሻው ወደ እኔ ብቻ ነው።

(15) 15. ላንተ በእርሱ እውቀት የሌለህን ነገር በእኔ እንድታጋራ ቢያስገድዱህ አትታዘዛቸው:: በቅርቢቱም ዓለም በመልካም ስራ ተወዳጃቸው:: ወደ እኔም የተመለሰን ሰው መንገድ ተከተል:: ከዚያ መመለሻችሁ ወደ እኔ ነው:: ትሰሩት የነበራችሁትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ (አልነው)

(16) 16. (ሉቅማንም አለ:) «ልጄ ሆይ! የእርሷ (መጥፎም ይሁን በጎ) የሰናፍጭ ቅንጣት ክብደት ያህል እንኳን ብትሆንና በቋጥኝ ውስጥ ወይም በሰማያት ውስጥ ወይም በምድር ውስጥ ብትሆን አላህ ያመጣታል:: አላህ ሩህሩህና ውስጠ አዋቂ ነውና።

(17) 17. «ልጄ ሆይ! ሶላትን አስተካክለህ ስገድ፤ በበጎ ነገርም እዘዝ ከሚጠላም ሁሉ ከልክል፤ በሚያገኝህም መከራ ላይ ታገስ ይህ በምር ከሚያዙ ወሳኝ ነገሮች ነው።

(18) 18. «ጉንጭህንም በኩራት ከሰዎች አታዙር:: በምድርም ላይ ተንበጥርረህ አትሂድ:: አላህ ተንበጥራሪን (ኮራተኛ) ጉረኛን ሁሉ አይወድምና::

(19) 19. «በአካሄድህም መካከለኛ ሁን:: ከድምጽህም ዝቅ አድርግ:: ከድምፆች ሁሉ አስከፊው የአህዮች ድምጽ ነውና።»

(20) 20. (ሰዎች ሆይ!) አላህ በሰማያት እና በምድር ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ለእናንተ ያገራላችሁ፤ ጸጋዎችንም ግልጽም ይሁኑ ድብቅ የሞላላችሁ መሆኑን አታዩምን? ከስሞች መካከል ያለ በቂ እውቀትና ያለ መሪ፤ ያለ ግልጽ መጽሀፍም፤ ስለ አላህ የሚከራከር አለ::

(21) 21. ለእነርሱም «አላህ ያወረደውን ተከተሉ።» በተባሉ ጊዜ «አይደለም በእርሱ ላይ አባቶቻችንን ያገኘንበትን እንከተላለን።» ይላሉ:: ሰይጣን (ይህን ተግባር በማስዋብ) ወደ እሳት ቅጣት የሚጠራቸው ቢሆንም ይከተሏቸዋልን?

(22) 22. መልካም ሰሪ ሆኖ ፊቱን ወደ አላህ የሚሰጥ ሁሉ ጠንካራ ገመድን በእርግጥ ጨበጠ:: የነገሩ ሁሉ ፍጻሜ ወደ አላህ ብቻ ነው::

(23) 23. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በአላህ የካደም ሁሉ ክህደቱ አያሳዝንህ። መመለሻቸው ወደ እኛ ብቻ ነውና:: ከዚያም የሰሩትንም ሁሉ እንነግራቸዋለን:: አላህ በልቦች ውስጥ ያለን ሁሉ ያውቃልና፡፡

(24) 24. ጥቂትን ጊዜ እናጣቅማቸዋለን:: ከዚያም ወደ ብርቱ ቅጣት እናስገድዳቸዋለን::

(25) 25. ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ማን እንደሆነ ብትጠይቃቸው «በእርግጥ አላህ ነው።» ይላሉ። «ምስጋና ሁሉ ለአላህ ብቻ ይገባው።» በላቸው:: ይልቁንም አብዛኞቹ አያውቁም።

(26) 26. በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ብቻ ነው:: አላህ በራሱ ተብቃቂዉና ምስጉኑ ነው::

(27) 27. በምድር ያሉ ሁሉ ዛፎች ብዕሮች ቢሆኑ ኖሮ ባህሩም ከእርሱ ማለቅ በኋላ ሰባት ባህሮች የሚጨመሩለት ሆኖ ቀለም ቢሆንና ቢጻፍባቸው የአላህ ቃላት ባላለቀች ነበር:: አላህ ሁሉን አሸናፊና ጥበበኛ ነውና::

(28) 28. (ሰዎች ሆይ!) እናንተን መፍጠርና እናንተን መቀስቀስ እንደ አንዲት ነፍስ እንጂ ሌላ አይደለም:: አላህ ሁሉን ሰሚና ሁሉን ተመልካች ነውና::

(29) 29. (የሰው ልጅ ሆይ) አላህ ሌሊትን በቀን ውስጥ የሚያስገባ ቀንንም በሌሊት ውስጥ የሚያስገባ ጸሀይንና ጨረቃንም የገራ መሆኑን አታይምን? ሁሉም እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ይሮጣሉ:: አላህም በምትሰሩት ሁሉ ውስጠ አዋቂ ነው::

(30) 30. ይህም የእርሱ (የአላህ) ብቸኛ አምላክነት እውነት በመሆኑ፤ ከእርሱ ሌላ የሚገዙት ጣዖት ሁሉ ውሸት በመሆኑና አላህ የበላይ ታላቅ በመሆኑ ነው።

(31) 31. (የሰው ልጅ ሆይ!) ከአስደናቂ ምልክቶቹ ሊያሳያችሁ መርከቦች በአላህ ችሮታ በባህር ውስጥ የሚንሻለሉ መሆናቸውን አታይምን? በዚህ ውስጥ በጣም ታጋሽ አመስጋኝ ለሆኑ ሁሉ አያሌ ተዓምራት አሉበት::

(32) 32. እንደ ጥላዎች የሆነ ማዕበል በሸፈናቸው ጊዜ ሃይማኖትን ለእርሱ ብቻ ያጠሩ ሆነው አላህን ይጠሩታል:: ወደ የብስ ባዳናቸው ጊዜ ግን ከእነርሱ መካከል ትክክለኛም አለ:: (ከእነርሱም መካከል የሚክድ አለ):: በአናቅጻችንም አታላይና ከዳተኛ የሆነ ሁሉ እንጂ ሌላው አይክድም::

(33) 33. እናንተ ሰዎች ሆይ! ጌታችሁን ፍሩ:: ወላጅ ከልጁ በምንም የማይጠቅምበት ልጅም ወላጅን በምንም ጠቃሚ የማይሆንበትን ቀን ፍሩ:: የአላህ ቀጠሮ እውነት ነውና:: ቅርቢቱም ህይወት አትሸንግላችሁ:: በአላህ (መታገስም) አታላዩ (ሰይጣን) አያታልላችሁ።

(34) 34. አላህ የሰዓቲቱ እውቀት እርሱ ዘንድ ብቻ ነው:: ዝናብንም ያወርዳል:: በማህጸኖችም ውስጥ ያለን ሁሉ ያውቃል። ማንኛይቱም ነፍስ ነገ የምትሰራውን አታውቅም:: ማንኛይቱም ነፍስ በየትኛው ምድር እንደምትሞትም አታውቅም:: አላህ አዋቂና ውስጠ አዋቂ ነው::