22 - Al-Hajj ()

|

(1) 1.እናንተ ሰዎች ሆይ! ጌታችሁን (አላህን) ፍሩ:: የሰዓቲቱ እንቅጥቃጤ በጣም ከባድ ነገር ነውና::

(2) 2. በምታዩዋት ቀን ሁኔታው አጥቢ ሁሉ ያጠባችውን ልጅ ትዘነጋዋለች። እርጉዝ ሴት ሁሉ እርጉዝዋን ትጨነግፋለች:: ሰዎቹንም በድንጋጤ ብርታት የሰከሩ መስለው ታያቸዋለህ:: እነርሱ ከመጠጥ የሰከሩ ሁው ሳይሆን ግን የአላህ ቅጣት ብርቱ ስለሆነ ነው።

(3) 3. ከሰዎች መካከል ያለ ምንም ዕውቀት በአላህ ነገር የሚከራከር፤ ሞገደኛ ሰይጣንንም የሚከተል ሰው አለ::

(4) 4. እነሆ የተከተለውን ሰው እርሱ ያጠመዋል:: ወደ አቃጣይ እሳት ስቃይም ይመራዋል ማለት በእርሱ ላይ ተጽፏል:: (ተወስኖባቸዋል)

(5) 5. ሰዎች ሆይ! ከሞት በኋላ ከመቀስቀስ በመጠራጠር ጉዳይ እንደ ሆናችሁ የመጀመሪያውን (አፈጣጠራችሁን ተመልከቱ። እኛም) ከአፈር ፈጠርናችሁ:: ከዚያ ከፍትወት ጠብታ፤ ከዚያም ከረጋ ደም፤ ከዚያም ከቁራጭ ስጋ ፍጥረትዋ ሙሉ ከሆነችና ሙሉ ካልሆነች (ችሎታችንን) ለእናንተ ልንገልጽላችሁ ፈጠርናችሁ። የምንሻውንም እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ በማህጸን ውስጥ እናረጋዋለን። ከዚያም ህፃን ሆናችሁ እናወጣችኋለን:: ከዚያም ሙሉ ጥንካሪያችሁን ትደርሱ ዘንድ (እናሳድጋችኋለን):: ከናንተም መካከል በወጣትነቱ የሚሞት ሰው አለ:: ከናንተም መካከል ከዕውቀት በኋላ ምንንም ላያውቅ ወደ ጃጀ ዕድሜ የሚመለስ ሰው አለ:: ምድርንም ደረቅ ሆና ታያታለህ:: በእርሷም ላይ ውሃን ባወረድን ጊዜ ትላወሳለች \ትነቃነቃለች\:: ትነፋለችም:: ውበት ካለው የእጽዋት አይነት ሁሉ ታበቅላለችም።

(6) 6. ይህ ሁሉ አላህ ፍፁም እውነት፤ እርሱም ሙታንን ህያው የሚያደርግ፤ በሁሉ ነገር ላይ ቻይ በመሆኑ ነው።

(7) 7. የሰዓቲቱም መከሰት ፈጽሞ ጥርጣሬ የሌለበት በመሆኑና አላህ በመቃብሮች ውስጥ ያለን ሁሉ የሚቀሰቅስ በመሆኑም ነው።

(8) 8. ከሰዎች መካከል ያለ ምንም ዕውቀት ያለ አንዳች ማስረጃም ያለ አብራሪ መጽሐፍም ጎኑን ያጠፈ ሆኖ ከአላህ መንገድ ሊያሳስት በአላህ ነገር የሚከራከር ሰው አለ::

(9) 9. ጎኑን ያጠፈ ሆኖ ከአላህ መንገድ ሊያሳስት (ይከራከራል)። በቅርቢቱ ዓለም ለርሱ ውርደት አለው:: በትንሳኤ ቀንም አቃጣይን (የእሳት) ቅጣት እናቀምሰዋለን::

(10) 10. «ይህ እጆችህ ባስቀደሙት ኃጢአት ነው፣ አላህም ለባሮቹ ፈጽሞ በዳይ አይደለም።» (ይባላል።)

(11) 11. ከሰዎችም መካከል በሃይማኖት ጫፍ ላይ ሆኖ አላህን የሚገዛ ሰው አለ:: እናም መልካም ነገር ካገኘው በእምነቱ ላይ ይረጋል:: መከራ ካገኘው ግን በፊቱ ላይ ይገለበጣል (ይክዳል):: ይህ አይነቱ ሰው የቅርቢቱን ዓለምም ሆነ የመጨረሻይቱን ዓለም ከሰረ:: ይህ ነው ግልጽ ኪሳራ ማለት።

(12) 12. ከአላህ ሌላ የማይጎዳውንና የማይጠቅመውን ይገዛል:: ይህ እርሱ ከእውነት የራቀ ስህተት ነው::

(13) 13. ያንን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ወደ እሱ የሚቀርብን ይገዛል:: ረዳቱ ምንኛ ከፋ! ወዳጁም ምንኛ ከፋ!

(14) 14. አላህ እነዚያን በትክክል ያመኑትንና መልካም ስራዎችን የሰሩትን ሰዎች በስሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች ያስገባቸዋል:: አላህም የሚሻውን ነገር ሁሉ በእርግጥ ይሰራልና።

(15) 15. አላህ (መልዕክተኛውን) ሙሐመድን በቅርቢቱም ሆነ በመጨረሻይቱ ዓለም አይረዳዉም ብሎ የሚያስብ ሰው ካለ ገመድን ወደ ሰማይ ይዘርጋና ከዚያ (ትንፋሹ እስኪቆረጥ) ይታነቅ:: ይህ ተግባሩ ተንኮሉ የሚያስቆጨውን ነገር ያስወግደለት እንደሆነም ይመልከት።

(16) 16. ልክ እንደዚሁ (ቁርኣንን) የተብራሩ አናቅጽ አድርገን አወረድነው:: አላህ የሚሻውን ሁሉ ይመራልና።

(17) 17. እነዚያ በአላህ ያመኑ እነዚያ አይሁዳውያን፤ እነዚያ ምንም እምነት የሌላቸው ሳቢያኖች፤ ክርስቲያኖችም፤ መጁሶችም እነዚያም (ጣዖታትን በአላህ) ያጋሩ ሁሉ አላህ በትንሳኤ ቀን በመካከላቸው በፍርድ ይለያል:: አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ በእርግጥ አዋቂ ነውና::

(18) 18. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ ጸሐይና፤ ጨረቃም፤ ከዋክብትም፤ ተራሮችም፤ ዛፎችም፤ ተንቀሳቃሾችም ፍጡራንና ከሰዎች ብዙዎችም ለእርሱ የሚሰግዱለት መሆኑን አታውቅምን? ብዙዉም በእርሱ ላይ የአላህ ቅጣት ተረጋገጠበት:: አላህ የሚያዋርደው ሰው ለእርሱ ምንም አክባሪ የለዉም:: አላህ የሻውን ይሰራልና:: {1}
{1} እዚህ የንባብ ሱጁድ (ሱጁዱ ትላዋ) ይደረጋል።

(19) 19. እነዚህ በጌታቸው ጉዳይ የተከራከሩ ሁለት ባላጋራዎች ናቸው:: እነዚያ በአላህ የካዱት የእሳት ልብሶች ተለክተውላቸዋል፤ እንዲቀልጥ ከራሶቻቸው ላይ የፈላ ውሃ ይምቧቧባቸዋል።

(20) 20. በሆዶቻቸው ውስጥ ያለውና ቆዳዎቻቸው በእርሱ ይቀለጣል::

(21) 21. ለእነርሱም (መቅጫ) ከብረት የሆኑ መዶሻዎች አሉ::

(22) 22. ከጭንቀት ብርታት የተነሳ ከእርሷ ለመውጣት በፈለጉ ቁጥር በእርሷ ውስጥ እንዲመለሱ ይደረጋሉ። «ያን በጣም የሚያቃጥለውን ቅጣት ቅመሱ።» (ይባላሉ።)

(23) 23. አላህ እነዚያን በትክክል ያመኑትንና መልካም ስራዎችን የሰሩትን ሰዎች በስሮቻቸው ጅረት ወንዞች በሚፈሱባቸው ገነቶች ያስገባቸዋል:: በእርሷ ውስጥ የወርቅ አንባሮችና ሉልን ይሸለማሉ:: በእርሷ ውስጥ ልብሶቻቸዉም ከሐር የተሰሩ ናቸው::

(24) 24. ወደ መልካም ንግግር ተመሩ፣ ወደ ምስጉን መንገድም ተመሩ።

(25) 25. እነዚያ በአላህ የካዱ ሰዎችን ከአላህ መንገድና ከዚያም በውስጡ ነዋሪ ለሆኑትም ሆነ ከሩቅ ለሚመጡት (ሰዎች) እኩል ካደረግነው ከተከበረው መስጊድ የሚከለክሉ ሁሉ (አሳማሚ ቅጣት እንቀጣቸዋልን::) በእርሱም ውስጥ ከትክክለኛ መንገድ በመዘንበል ራሱን በዳይ ሆኖ (ማንኛውንም ነገር) የሚያስብ ከአሳማሚ ቅጣት እናቀምሰዋለን::

(26) 26. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለኢብራሂም የቤቱን የከዕባን ስፍራ መመለሻ ባደረግንለት (እንዲህ) ባልነውም ጊዜ (የሆነውን አስታውስ): «በኔ ምንንም አታጋራ:: ቤቴንም ለሚዞሩትና ለሚቆሙበት (ለኢባዳ) ለሚያጎነብሱትና በግንባራቸዉም ለሚደፉት (ሩኩዕና ሱጁድ ለሚያደርጉት) ንጹህ አድርግላቸው።

(27) 27. «ኢብራሂም ሆይ! በሰዎች መካከል የሐጅን ትእዛዝ አሰማ:: እግረኞችና ከየሩቅ መንገድ በሚመጡ ከሲታ ግመሎች ሁሉ ላይም ሆነዉም ይመጡልሃልና።

(28) 28. «ለእነርሱ የሆኑ ጥቅሞችን ያገኙ ዘንድና በእነዚያ በታወቁ ቀናትም ውስጥ ከለማዳ እንስሳዎች በሰጣቸው ሲሳይ ላይ የአላህን ስም ያወሱ ዘንድ ይመጡልሃል:: ከእርሷም ብሉ:: ችግረኛ ድሀንም አብሉ።

(29) 29. «ከዚያም (እንደ ጠጉርና ጥፍር ያሉትን) ትርፍ አካላቸውንና እድፋቸውን ያስወግዱ:: ስለቶቻቸውንም በትክክል ይሙሉ:: በጥንታዊዉም ቤት በካዕባ ዙሪያ ይዙሩ።» አልን።

(30) 30. ይሀው ነው። የአላህንም ህግጋት የሚያከብር ሁሉ እርሱ እጌታው ዘንድ ለእርሱ በጣም የተሻለ መልካም ነው:: የቤት እንስሳትም በእናንተ ላይ እርም መሆኑ ከሚነበብላችሁ በስተቀር ለእናንተ ተፈቅዳላችኋለች:: ከጣዖታትም ርክሰት ተጠንቀቁ:: ሐሰትንም ቃል ራቁ::

(31) 31. ለአላህ ታዛዦች፤ በእርሱ የማታጋሩና ወደ ቀጥተኞች መንገድ የተዘነበላችሁ ሁኑ:: በአላህ የሚያጋራ ሁሉ ከሰማይ እንደ ወደቀና በራሪ እንደምትነጥቀው ወይም ንፋስ በሩቅ ስፍራ እንደምትጥለው ነው::

(32) 32. (ነገሩ) ይህ ነው። የአላህን ሃይማኖታዊ ምልክቶች የሚያከብር ሁሉ ይህ ድርጊቱ አላህን ከሚፈሩ ልቦች የሚፈጸም ጥንቃቄ ነው።

(33) 33. ለእናንተ በእርሷ እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ጥቅሞች አሏችሁ:: ከዚያም የ(ኡዱሂያ)ማረጃ ስፍራ እጥንታዊው ቤት አጠገብ ነው::

(34) 34. ከቤት እንስሳት በሰጣቸው ሲሳይ ላይ የአላህን ስም ብቻ ያወሱ ዘንድ ለህዝቦች ሁሉ (ወደ አላህ) መስዋዕት ማቅረብን ሀይማኖታዊ ሥርአቶችን ደነገግን:: አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው:: እርሱንም ብቻ ታዘዙ:: ለአላህ ተዋራጆችንም በመልካም ነገር አብስራቸው::

(35) 35. እነዚያን አላህ በተወሳ ጊዜ ልቦቻቸው የሚጨነቁትን (የሚፈሩትን)፤ በደረሰባቸዉም መከራ ላይ ታጋሾችን፤ ሰላትንም አስተካክለው ሰጋጆችን፤ ከሰጠናቸዉም ሲሳይ የሚለግሱትን በገነት አብስር::

(36) 36. ግመሎችንም ለእናንተ ከአላህ ሃይማኖት ምልክቶች አደረግናቸው:: በእነርሱ ለእናንተ ብዙ መልካም ጥቅሞች አሏችሁ:: በእርሷም ላይ ስታርዷት በሦስት እግሮቿ ቆማ የተሰለፈች ሆና የአላህን ስም አውሱ:: ጎኖቻቸዉም በወደቁ ጊዜ ከእርሷ ብሉ:: በግልጽ ለማኝንም ለልመና የሚያገዳድምንም አብሉ:: ልክ እንደዚሁ ታመሰግኑ ዘንድ ለእናንተ ገራናት::

(37) 37. አላህን ስጋዎቿም ሆኑ ደሞቿ ፈጽሞ አይደርሰዉም:: ግን ከእናንተ የሆነው ፍራቻ ይደርሰዋል:: እንደዚሁ አላህን በመራችሁ ላይ ልታከብሩት ለእናንተ ገራት:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በጎ ሰሪዎችንም አብስር::

(38) 38. አላህ ከእነዚያ በእርሱ ካመኑት ላይ ይከላከልላቸዋል። አላህ ከዳተኛንና ውለታ ቢስን ሁሉ አይወድምና።

(39) 39. ለእነዚያ በከሓዲያን ለሚገደሉት ትክክለኛ አማኞች የተበደሉ በመሆናቸው መጋደል ተፈቀደላቸው:: አላህ እነርሱን በመርዳት ላይ በእርግጥ ቻይ ነውና::

(40) 40. ለእነዚያ «ጌታችን አላህ ነው።» ከማለታቸው በስተቀር ያለ አግባብ ከየቀያቸው የተባረሩ ለሆኑት ከራሳቸው ላይ መከላከል ተፈቀደ:: አላህ ሰዎችን ከፊላቸውን በከፊሉ መገፍተሩ ባልነበረ ኖሮ ገዳማት፣ ቤተክርስቲያኖችም፣ ምኩራቦችና በውስጣቸው የአላህ ስም በብዛት የሚወሳባቸው መስጊዶችም በተፈረሱ ነበር:: አላህም ሃይማኖቱን የሚረዳውን ሁሉ በእርግጥ ይረዳዋል:: አላህ ብርቱና ሁሉን አሸናፊ ነውና::

(41) 41. እነርሱ ማለት እነዚያ በምድር ላይ ብናስመቻቸው (የበላይነትን ሰጥተን ባጎናጸፍናቸው ኖሮ) ሶላትን እንደሚገባ የሚያስተካክሉ፤ ዘካንም የሚሰጡ፤ በደግ ነገርም የሚያዝዙ፤ ከመጥፎ ነገርም የሚከለከሉ ናቸው:: የነገሮች ሁሉ መጨረሻ ወደ አላህ ብቻ ነው::

(42) 42. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ቢያስተባብሉህም ከእነርሱ በፊት የኑሕ ህዝቦች፣ የዓድና የሰሙድም በእርግጥ አስተባብለዋል።

(43) 43. የኢብራሂምም ህዝቦች የሉጥም ህዝቦች እንደዚሁ አስተባብለዋል፤

(44) 44. የመድየንም ሰዎች እንዲሁ አስተባብለዋል:: ሙሳም ተስተባብሏል:: ለከሓዲያንም ጊዜን ሰጠኋቸው:: ከዚያ ያዝኳቸው። ጥላቻዬም እንዴት ነበረ (ተመልከቱ)

(45) 45. ከከተሞች መካከል በደለኛ ሆነው ያጠፋናቸው እና በጣሪያዎቻቸው ላይ ወዳቂ የሆኑ ብዙ ናቸው:: ከተራቆተም የውሃ ጉድጓድ ከተገነባም ህንፃ ያጠፋነው ብዙ ነው::

(46) 46. ለእነርሱም የሚያውቁባቸው ልቦች፤ ወይም የሚሰሙባቸው ጆሮዎች ይኖሯቸው ዘንድ በምድር ላይ አይሄዱምን? እነሆ ዓይኖች አይታወሩም:: እነዚያ በደረቶች ውስጥ ያሉት ልቦች ናቸው የሚታወሩት።

(47) 47. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ! ) አላህ ቀጠሮውን በፍጹም የማይጥስ ሲሆን ቅጣትን እንድታመጣ ያቻኩሉሃል (ያጣድፉሃል):: በጌታህ ዘንድ አንዱ ቀን ከምትቆጥሩት ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት የሚመጥን ነው::

(48) 48. ከከተማ በዳይ ሆና ጊዜ የሰጠኋትና ከዚያ የያዝኳት የቀጣኋት ብዙ ናት:: የመጨረሻው መመለሻም ወደ እኔ ብቻ ነው::

(49) 49. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እናንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ለእናንተ ግልጽ አስፈራሪ ብቻ ነኝ።» በላቸው።

(50) 50. እነዚያም በትክክል ያመኑና መልካም ስራዎችን የሰሩ ለእነርሱ ምህረትና ያማረ ሲሳይ አላቸው::

(51) 51. እነዚያ ከአላህ የሚያመልጡ መስሏቸው ተዓምራታችንን በመንቀፍ የተጉ ሁሉ እነርሱ የእሳት ጓዶች ናቸው።

(52) 52. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ካንተ በፊት አንድንም መልዕክተኛ ወይም ነብይ አላክንም ባነበበ ጊዜ ሰይጣን በንባቡ ውስጥ የማጥመሚያን ሀሳብ የሚጥል ቢሆን እንጂ:: ወዲያዉም አላህ ሰይጣን የሚጥለውን ማጥመሚያ ቃል ያስወግዳል:: ከዚያም አላህ አናቅጽን ያጠነክራል (ያጸናል):: አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነውና::

(53) 53. ሰይጣን የሚጥለውን ነገር ለእነዚያ በልቦቻቸው ውስጥ በሽታ ላለባቸውና ልቦቻቸው ደረቆች ለሆኑት ፈተና ሊያደርግ ይጥላል:: በዳዮችም ከእውነት በራቀ ጭቅጭቅ (ውዝግብ) ውስጥ ናቸው::

(54) 54. እነዚያም እውቀትን የተሰጡት እርሱ (ቁርኣን) ከጌታህ የሆነ እውነት መሆኑን እንዲያውቁና በእርሱ እንዲያምኑ ልቦቻቸዉም በእርሱ እንዲረኩ (ያጠነክራል):: አላህም እነዚያን በትክክል ያመኑትን ሁሉ ወደ ቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ መሪ ነው::

(55) 55. እነዚያ የካዱት ሰዎች ሰዓቲቱ በድንገት እስከምትመጣባቸው ወይም ከደግ ነገር መካን የሆነው ቀን ቅጣት እስከሚመጣባቸው ድረስ በቁርኣን ጉዳይ ከመጠራጠር አያቆሙም::

(56) 56. በዚያ ቀን ንግስናው የአላህ ብቻ ነው:: በመካከላቸውም ይፈርዳል:: እነዚያም ያመኑትና መልካም ስራዎችን የሰሩት በመደሰቻ ገነቶች ውስጥ ናቸው።

(57) 57. እነዚያም የካዱትና በአናቅጻችንም ያስተባበሉት ሁሉ እነዚያ ለእነርሱ አዋራጅ ቅጣት አለባቸው::

(58) 58. እነዚያም ለአላህ ሀይማኖት ሲሉ የተሰደዱና ከዚያም ሲታገሉ የተገደሉ ወይም የሞቱ አላህ መልካምን ሲሳይ በእርግጥ ይሰጣቸዋል:: አላህም እርሱ ከሰጪዎች ሁሉ በላጭ ነው::

(59) 59. የሚወዱትን መግቢያ ገነትን በእርግጥ ያስገባቸዋል:: አላህም በእርግጥ አዋቂና ታጋሽ ነውና::

(60) 60. (ነገሩ) ይህ ነው:: ያ በተበደለበት ብጤ (መጠን) የተበቀለና ከዚያ በእርሱ ላይ ግፍ የተዋለበት ሰው አላህ በእርግጥ ይረዳዋል:: አላህ ይቅር ባይና መሓሪ ነውና::

(61) 61. ይህ የሆነው አላህ ሌሊትን በቀን ውስጥ የሚያስገባ፤ ቀንንም በሌሊት ውስጥ የሚያስገባ (ቻይ) ፤ ሁሉንም ሰሚ፤ ሁሉንም ተመልካች በመሆኑ ነው።

(62) 62. ይህ የሆነው አላህም ፍፁም እውነት በመሆኑ፤ ከርሱም ሌላ የሚገዙት ነገር ፍጹም ውሸት በመሆኑና አላህም የሁሉ በላይ ታላቅ በመሆኑ ነው::

(63) 63. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ ከሰማይ ውሃን ማውረዱንና ከዚያ ምድር የምትለመልም መሆኗን አላየህምን? አላህ ፍጹም ሩህሩህና ውስጠ አዋቂ ነውና::

(64) 64. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በሰማያት ውስጥና በምድር ውስጥ ያለው ሁሉ የእርሱ ብቻ ነው:: አላህ እርሱ ተብቃቂዉና ምስጉኑ ነውና::

(65) 65. አላህ በምድር ውስጥ ያለን ሁሉ ለእናንተ የገራላችሁ መርከቦችንም በባህር ውስጥ በፈቃዱ የሚንሻለሉ ሲሆኑ የገራላችሁ መሆኑን፤ ሰማይንም በፈቃዱ ካልሆነ በምድር ላይ እንዳትወድቅ የሚይዛት መሆኑን አላየህምን? አላህ ለሰዎች በእርግጥ ሩህሩህና አዛኝ ነውና::

(66) 66. እርሱም ያ ህያው ያደረጋችሁ ነው:: ከዚያም ይገድላችኋል:: ከዚያም ህያው ያደርጋችኋል:: ሰው በእርግጥ በጣም ከሓዲ ነው::

(67) 67. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለየህዝቡ ሁሉ እነርሱ የሚሰሩበት የሆነን ስርዓተ ሃይማኖት አድርገናል:: ስለዚህ በነገሩ አይከራከሩህ:: ወደ ጌታህ መንገድም ጥራ:: አንተ በእርግጥ በቅኑ መመርያ ላይ ነህና።

(68) 68. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ቢከራከሩህም (እንዲህ) በላቸው: «አላህ የምትሰሩትን ሁሉ አዋቂ ነው።

(69) 69. «አላህ በትንሳኤ ቀን በዚያ በእርሱ ትለያዩበት (ትወዛገቡበት) በነበራችሁት ሁሉ በመካከላችሁ ይፈርዳል።» (በላቸው)

(70) 70. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ በሰማይና በምድር ውስጥ ያለን ሁሉ በእርግጥ የሚያውቅ መሆኑን አታውቅምን? ይህ በመጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ እውነት ነው:: ይህም በአላህ ላይ ገር ነው::

(71) 71. ከአላህ ሌላም ምንም ማስረጃን ያላወረደበትንና ለእነርሱም በእርሱ እውቀት የሌላቸውን ነገር ያመልካሉ፤ ለበዳዮች ምንም ረዳት የላቸዉም::

(72) 72. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አናቅጻችን የተብራሩ ሆነው በእነርሱ ላይ በሚነበቡ ጊዜ በእነዚያ በአላህ በካዱት ሰዎች ፊት ላይ ጥላቻን ታውቃለህ:: በእነዚያ አናቅጻችንን በሚያነቡት ላይም በኃይል ሊተናኮሏቸው ይቃረባሉ:: ይልቅ ከዚህ የከፋን ነገር ልንገራችሁን? እርሷም እሳት ናት:: አላህ ለእነዚያ በርሱ ለካዱት ሰዎች ሁሉ ቀጥሯታል:: መመለሻነቷ ምን ይከፋ በላቸው::

(73) 73. ሰዎች ሆይ! አስደናቂ ምሳሌ ተገለጸላችሁ:: ለእርሱም አድምጡት፤ እነዚያ ከአላህ ሌላ የምትገዟቸው ጣዖታት ሁሉ ዝንብን ለመፍጠር ቢሰበሰቡ ፈጽሞ መፍጠር እንኳ አይችሉም:: አንዳችንም ነገር ዝንብ ቢነጥቃቸው ከእርሱ አያስጥሉትም:: ፈላጊዉም (አምላኪው) ተፈላጊዉም (ተመላኪው) ደከሙ::

(74) 74. አላህን ተገቢ ክብሩን አላከበሩትም:: አላህ በጣም ሀያልና ሁሉን አሸናፊ ነውና::

(75) 75. አላህ ከመላእክት ውስጥ መልዕክተኞችን ይመርጣል:: ከሰዎችም መካከል እንደዚሁ መልዕክተኞችን ይመርጣል:: አላህ ሁሉን ሰሚ ሁሉን ተመልካች ነው::

(76) 76. በስተፊታቸዉም ሆነ በስተኋላቸው ያለን ሁሉ ያውቃል:: ወደ አላህም ነገሮች ሁሉ ይመለሳሉ::

(77) 77. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከአላህ ቁጣ ትድኑ ዘንድ በስግደታችሁ አጎንብሱ:: በግንባራችሁም ላይ ተደፉ:: (ሩኩዕና ሱጁድ አድርጉ) ጌታችሁንም በትክክል ተገዙት:: በጎንም ነገር ስሩ:: ልትድኑ ይከጀልላችኋልና:: {1}
{1} እዚህ የንባብ ሱጁድ (ሱጁድ ትላዋ) ይደረጋል።

(78) 78. በአላህም ሃይማኖት ተገቢውን ትግል ታገሉ:: እርሱ መርጧችኋል:: በናንተም ላይ በሃይማኖቱ ውስጥ ምንም ችግር አላደረገባችሁም:: የአባታችሁን የኢብራሂምን ሃይማኖት ተከተሉ:: እርሱ (አላህ) ከዚህ በፊት በነበሩት መጽሐፍትም ሆነ በዚህ ቁርኣን ሙስሊሞች ብሎ ሰይሟችኋል። (ይሄዉም) መልዕክተኛው በእናንተ ላይ መስካሪ እንዲሆን እና እናንተም በሰዎች ላይ መስካሪዎች እንድትሆኑ ነው:: ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ:: ዘካንም በአግባቡ ለተገቢው ስጡ:: በአላህም ተጠበቁ:: እርሱ ረዳታችሁ ነውና:: እርሱ ምን ያማረ ጠባቂ፤ ምን ያማረም ረዳት ነው።