(1) 1. በጡር (ጋራ)፤ እምላለሁ።
(2) 2. በተጻፈው መጽሓፍም፤
(3) 3. በተዘረጋው ብራና ላይ፤
(4) 4. በደመቀው ቤትም፤
(5) 5. ከፍ በተደረገው ጣራም፤
(6) 6. በእሳት በተሞላው ባህርም እምላለሁ::
(7) 7. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የጌታህ ቅጣት በእርግጥ ወዳቂ ነው (የማይቀር ነው)::
(8) 8. ለእርሱ ምንም ገፍታሪ የለዉም::
(9) 9. ሰማይ ብርቱ መዞርን በምትዞርበት ቀን (ይሆናል)::
(10) 10. ተራራዎችም መሄድን በሚሄዱበት ቀን::
(11) 11. ላስተባባዮችም ሁሉ ያን ጊዜ ወዮላቸው።
(12) 12. ለነዚያ ለእነርሱ በውሸት ውስጥ የሚጫወቱ ለሆኑት ሰዎች::
(13) 13. ወደ ገሀነም እሳት በሀይል መገፍተርን በሚገፈተሩበት ቀን
(14) 14. «ይህች ያቺ በእርሷ ታስተባብሉባት የነበራችሁት እሳት ናት ይባላሉ»።
(15) 15. «ይህ (ፊት ትሉን እንደነበራችሁት) ድግምት ነውን? ወይስ እናንተ አታዩምን?
(16) 16. «ግቧት ታገሱም ወይም አትታገሱ በእናንተ ላይ እኩል ነው:: የምትመነዱት ትሰሩት የነበራችሁትን ፍዳ ብቻ ነው» ይባላሉ::
(17) 17. አላህን ፈሪዎቹ በእርግጥ በገነቶችና በጸጋ ውስጥ ናቸው::
(18) 18. ጌታቸው በሰጣቸው ጸጋ ተደሳቾች ሆነው በገነት ውስጥ ናቸው:: የገሀነምንም ስቃይ ጌታቸው ጠበቃቸው::
(19) 19. «ትሰሩት በነበራችሁት ምክንያት ተደሳቾች ሆናችሁ ብሉ ጠጡም» (ይባላሉ።)
(20) 20. በተደረደሩ አልጋዎች ላይ ተደጋፊዎች ሆነው በገነት ይኖራሉ:: አይናማዎች በሆኑ ነጫጭ ሴቶችም እናጠናዳቸዋለን::
(21) 21. እነዚያም በአላህ ያመኑና ዝርያቸዉም በእውነት የተከተለቻቸው ዝርያቸውን ከእነርሱ ጋር እናስጠጋቸዋለን:: ከስራዎቻቸዉም ምንንም አናጎድልባቸዉም:: ሰው ሁሉ በሰራው ስራ ተጠያቂ ነው::
(22) 22. ከሚሹትም ሁሉ እሸትንና ስጋን እንጨምርላቸዋለን::
(23) 23. በውስጧ መጠጥን ይሰጣጣሉ:: በውስጧ ውድቅ ንግግርና መወንጀልም የለም::
(24) 24. ለእነርሱም የሆኑ ወጣቶች ልክ የተሸፈነ ሉል መስለው በእነርሱ ላይ ለማሰላፍ ይዘዋወራሉ::
(25) 25. የሚጠያየቁ ሆነዉም ከፊላቸው በከፊሉ ላይ ይዞራል::
(26) 26. ይላሉም: «እኛ ፊት በቤተሰቦቻችን ውስጥ ከቅጣት ፈሪዎች ነበርን።
(27) 27. «አላህ በእኛ ላይ ለገሰ:: የመርዛም እሳት ቅጣትንም ጠበቀን::
(28) 28. «እኛ ከዚህ በፊት እንለምነው ነበርን:: እነሆ እርሱ በጎ ዋይ አዛኝ ነውና» ይላሉ::
(29) 29. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) (ሰዎችን) አስታውስ አንተም በጌታህ ጸጋ ምክንያት ጠንቋይም እብድም አይደለህም::
(30) 30. «ይልቁንም የሞትን አደጋ በእርሱ የምንጠባበቅበት የሆነ ባለ ቅኔ ነው» ይላሉን?
(31) 31. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ተጠባበቁ እኔም ከናንተ ጋር ከሚጠባበቁት ነኝ» በላቸው::
(32) 32. አእምሮዎቻቸው በዚህ ተግባር ያዟቸዋልን? ወይስ በእውነቱ እነርሱ ወሰን አላፊ ህዝቦች ናቸው::
(33) 33. ወይም «ቀጠፈው» ይላሉን? አይደለም። ይልቁንም አያምኑም::
(34) 34. እውነተኞችም ከሆኑ መሰሉ የሆነን ንግግር ያምጡ::
(35) 35. ወይስ ያለ አንዳች ፈጣሪ ተፈጠሩን? ወይስ እነርሱ ፈጣሪዎች ናቸውን?
(36) 36. ወይስ ሰማያትንና ምድርን ፈጠሩን? አይደለም፤ አያረጋግጡም::
(37) 37. ወይስ የጌታህ ግምጃ ቤቶች እነርሱ ዘንድ ናቸውን? ወይስ እነርሱ አሸናፊዎች ናቸው?
(38) 38. ወይስ ለእነርሱ በእርሱ ላይ ከሰማይ የሚያዳምጡበት መሰላል አላቸውን? (እንግዲያውስ) አድማጫቸዉ ሰማሁ የሚለውን ግልጽ አስረጂ ያምጣ::
(39) 39. ወይስ ለእናንተ ወንዶች ልጆች እያሏችሁ ለእርሱ ሴቶች ልጆች አሉትን?
(40) 40. ወይስ ዋጋን ትጠይቃቸዋለህን? በዚህም እነርሱ በእዳው የተከበዱ ናቸውን?
(41) 41. ወይስ ሩቁ ሚስጢር እነርሱ ዘንድ በመሆኑ እነርሱ ይጽፋሉን?
(42) 42. ወይስ ተንኮልን (ባንተ) ይሻሉን? እነዚያም የካዱት የተተነኮለባቸው ናቸው::
(43) 43. ወይስ ለእነርሱ ከአላህ ሌላ አምላክ አላቸውን? አላህ ከሚያጋሩት ሁሉ ጠራ::
(44) 44. ከሰማይም ቁራጭን በእነርሱ ላይ ወዳቂ ሆኖ ቢያዩ ኖሮ «ይህ የተደራረበ ደመና ነው» ይሉ ነበር::
(45) 45. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!)ያንንም በእርሱ የሚገደሉበትን ቀናቸውን እስከሚገናኙ ድረስ ተዋቸው::
(46) 46. ተንኮላቸው ከእነርሱ ምንም የማይጠቅማቸውንና እነርሱም የማይረዱበትን ቀን እስከሚያገኙ ተዋቸው::
(47) 47. ለእነዚያም ለበደሉትም ከዚህ ሌላ ቅርብ ቅጣት አለባቸው:: ግን አብዛኞቻቸው አያውቁም::
(48) 48. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለጌታህ ፍርድም ታገስ:: አንተ በጥበቃችን ስር ነህና:: ጌታህንም በምትቆም ጊዜ ከማመስገን ጋር አጥራው::
(49) 49. ከሌሊቱና በከዋክብት መደበቂያም ጊዜ (ንጋት ላይም) አጥራው::