9 - At-Tawba ()

|

(1) 1.(ሙስሊሞች ሆይ! ይህ) ከአላህና ከመልዕክተኛው ወደ እነዚያ ቃል ኪዳን ወደ ተጋባችኋቸው አጋሪዎች የሚደርስ የውል መሻሪያ መልዕክት ነው::

(2) 2. (ከሓዲያን ሆይ!) በምድር ላይ አራት ወሮችን ጸጥተኛ ስትሆኑ ተንቀሳቀሱ:: እናንተ ከአላህ ቅጣት የማታመልጡ መሆናችሁንና አላህ ከሓዲያንን አዋራጅ መሆኑንም እወቁ፡፡

(3) 3. (ይህ) ከአላህና ከመልዕክተኛው በታላቁ ሐጅ ቀን የወጣ አላህ እና መልዕክተኛው ከአጋሪዎቹ ንጹህ መሆናቸውን የሚገልፅ አዋጅ ነው:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከክህደት ብትጸጸቱ እርሱ ለእናንተ በላጭ ነው:: ከእምነት ብትሸሹ ግን እናንተ አላህን የማታቅቱት መሆናችሁን እወቁ በማለት ወደ ሰዎች የሚደርስ ማስታወቂያ ነው:: እነዚያን በአላህ የካዱትን ሰዎች በአሳማሚ ቅጣት አብስራቸው::

(4) 4. እነዚያ ከአጋሪዎቹ መካከል እነዚያ ቃል ኪዳን የተጋባችሁላቸውና ከዚያ ምንም ያላጎደሉባችሁ፤ በእናንተ ላይ ለማጥቃት አንድንም ያልተባበሩባችሁ ቃል ኪዳናቸውን እስከ ጊዜያቸው መጨረሻ ድረስ ሙሉላቸው:: አላህ ጥንቁቆችን ይወዳልና::

(5) 5. የተከበሩት ወሮች ባለቁ ጊዜ አጋሪዎቹን ባገኛችሁባቸው ስፍራ ሁሉ ግደሏቸው:: ያዟቸዉም:: ክበቧቸዉም:: እነርሱንም ለመጠባበቅ ስትሉ በየኬላው ላይ ተቀመጡ:: ሆኖም ቢጸጸቱ፤ ሶላትን በደንቡ ቢሰግዱና ግዴታ የሆነባቸውን የዘካ ምጽዋትን በትክክል ከሰጡ መንገዳቸውን ልቀቁላቸው:: አላህ መሀሪና አዛኝ ነውና::

(6) 6. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከአጋሪዎች መካከል አንዱ ጥገኝነትን ቢጠይቅህ የአላህን ቃል ይሰማ ዘንድ አስጠጋው:: ከዚያ ወደ ሰላም ማግኛው ስፍራ አድርሰው:: ይህም የሆነው እነርሱ የማያውቁ ህዝቦች በመሆናቸው ነው ::

(7) 7. ለአጋሪዎች ከአላህና ከመልዕክተኛው ዘንድ የሰላም ቃል ኪዳን እንዴት ይኖራቸዋል? እነዚያ በተከበረው መስጊድ ዘንድ ቃል ኪዳን የገባችሁላቸው ሰዎች ብቻ ሲቀሩ:: እነዚያማ በቃል ኪዳናቸው ለእናንተ ቀጥ እስካሉላችሁ ድረስ ለእርሱም በቃላችሁ ቀጥ በሉላቸው:: አላህ ጥንቁቆችን ሁሉ ይወዳልና::

(8) 8. በእናንተ ላይ ቢያይሉ ዝምድናንና ቃልኪዳንን የማይጠብቁ ሰዎች ሲሆኑ እንዴት ከአላህና ከመልዕክተኛው ዘንድ ቃልኪዳን ይኖራቸዋል? በአፎቻቸው ይሸነግሏችኋል:: ልቦቻቸው ግን እምቢ ይላሉ:: አብዛኞቻቸዉም አመጸኞች ናቸው::

(9) 9. በአላህ አናቅጽ ጥቂትን ዋጋ ገዙ:: እናም ከመንገዱም ሰዎችን አገዱ:: እነርሱ ይሰሩት የነበሩት ሥራም እጅግ በጣም ከፋ::

(10) 10. በትክክለኛ አማኞች ላይ ዝምድናንም ሆነ ቃል ኪዳንን አይጠብቁም:: ወሰን አላፊዎች ማለት እነርሱው ናቸው::

(11) 11. (ሙስሊሞች ሆይ!) ቢጸጸቱ፤ ሶላትንም ደንቡን አሟልተው ቢሰገዱና ግድ የሆነባቸውንም ዘካን በትክክል ቢሰጡ የእምነት ወንድሞቻችሁ ናቸው:: ለሚያውቁ ህዝቦች ሁሉ አናቅጽን እናብራራለን::

(12) 12. ከቃልኪዳናቸው በኋላ መሀላዎቻቸውን ካፈረሱና ሃይማኖታችሁን ካንቋሸሹ የክህደት መሪዎች ከክህደት ተግባራቸው ይከለከሉ ዘንድ ተዋጓቸው:: እነርሱ ምንም ቃልኪዳን የላቸዉምና::

(13) 13. እነዚያ መሀላዎቻቸውን ያፈረሱትን፤ መልዕክተኛውንም ከሀገር ለማውጣት ያሰቡትን ህዝቦች እነርሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ጦርነት የጀመሯችሁን ህዝቦች ሲሆኑ ለምን አትወጓቸዉም? ትፈሯቸዋላችሁን? ትክክለኛ አማኞች ከሆናችሁ አላህን ይበልጥ ልትፈሩት የተገባው ነው::

(14) 14. (ሙስሊሞች ሆይ!) ተጋደሏቸው:: አላህ በእጆቻችሁ ያሰቃያቸዋል:: ያዋርዳቸዋልም:: በእነርሱም ላይ ይረዳችኋል:: የአማኝ ህዝቦችን ልቦችንም ያሽራል::

(15) 15. የልቦቻቸውንም ቁጭት ያስወግዳል:: አላህ ከሚፈልገው ሰው ላይ ጸጸትን ይቀበላል:: አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነውና::

(16) 16. አላህ ከመካከላችሁ በትክክል ለአላህ መስዋዕት የሚከፍሉትንና (የታገሉትንና) ከአላህ፣ ከመልዕክተኛውና ከትክክለኛ አማኞች በስተቀር አማካሪ ያልያዙትን ክፍሎች ለይቶ ሳያውቅ (ሳይገልጽ) የምትተዉ መሰላችሁን? አላህ የምትሰሩትን ሁሉ ዉስጠ አዋቂ ነው::

(17) 17. አጋሪዎች በራሳቸው ላይ በክህደት የሚመሰክሩ ሲሆኑ የአላህን መስጊዶች ሊንከባከቡ አይገባቸዉም:: እነዚያ ሥራዎቻቸው የተበላሹና በአኼራም በእሳት ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው::

(18) 18. የአላህን መስጊዶች የሚንከባከቡ ሰዎች በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመኑ፤ ሶላትንም ደንቡን ጠብቀው የሚሰግዱ፤ ግዴታ ምጽዋትን በትክክል የሚሰጡ፤ ከአላህ ሌላ ምንንም ያልፈሩ ሰዎች ብቻ ናቸው:: እንዲህ ያሉት ሰዎች ቀናዉን መስመር ከያዙት መሆናቸው ይከጀላልና::

(19) 19. ሰዎችን ማጠጣትንና የተከበረውን መስጊድ መንከባከብን፤ በአላህና በመጨረሻው ቀን እንዳመነና በአላህ መንገድም እንደታገለ ሰው እምነትና ትግል አደረጋችሁትን? በአላህ ዘንድ ፈጽሞ ሁለቱ ተግባሮች አይስተካከሉም:: አላህ በዳይ ህዝቦችን ሁሉ ወደ ቀጥተኛው መንገድ አይመራምና::

(20) 20. እነዚያ በአላህ ያመኑት ከየአገሮቻቸዉም የተሰደዱት በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸዉም በአላህ መንገድ ላይ የታገሉት አላህ ዘንድ በደረጃ በጣም የላቁ ናቸው:: ፍላጎታቸውን ያገኙ ማለትም እነርሱው ናቸው::

(21) 21. ጌታቸው ከእርሱ በሆነው እዝነትና ውዴታ፤ በውስጧ የማያቋርጥ መጠቀሚያ ባለባት ገነትም ያበስራቸዋል::

(22) 22. በውስጧ ዘላለም ዘውታሪዎች ሲሆኑ ያበስራቸዋል:: አላህ እርሱ ዘንድ ታላቅ ምንዳ አለና::

(23) 23. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አባቶቻችሁንና ወንድሞቻችሁን ክህደትን ከእምነት አብልጠው ከወደዱ ወዳጆች አድርጋችሁ አትያዟቸው:: ከናንተ መካከል እነርሱን ወዳጅ የሚያደርጓቸው ሁሉ በዳዮች ማለት እነርሱው ናቸው::

(24) 24. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አባቶቻችሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁ፤ ወንድሞቻችሁ፤ ሚስቶቻችሁ ዘመዶቻችሁ፤ የሰበሰባችኋቸው ሀብቶች፤ መክሰሯን የምትፈሯት ንግድና የምትወዷቸው መኖሪያዎች በእናንተ ዘንድ ከአላህ፤ ከመልዕክተኛውና በእርሱ መንገድ ከመታገል ይበልጥ የተወደዱ ከሆኑ አላህ ጉዳዩን እስከሚያመጣ ድረስ ተጠባበቁ በላቸው:: አላህ አመጸኞች ህዝቦችን ሁሉ አይመራም::

(25) 25. (ሙስሊሞች ሆይ!) አላህ በብዙ የጦር ሜዳዎች ላይ እገዛውን ለግሶላችኋል:: የሁነይንም ቀን ብዛታችሁ ባስደነቀቻችሁና ለእናንተም ብዛት ምንም ባልጠቀመቻችሁ ጊዜ ምድርም ከስፋቷ ጋር በጠበበቻችሁና ከዚያ ተሸናፊዎች ሆናችሁም በዞራችሁ ጊዜ ረዳችሁ::

(26) 26. ከዚያም አላህ እርጋታውን በመልዕክተኛውና በምዕመናኖች ላይ አወረደ:: ያላያችኋቸውንም ሰራዊት አወረደ:: እነዚያን የካዱትንም ሰዎች በመግደልና በመማረክ አሰቃየ:: ይህም የከሓዲያን ፍዳ ነው::

(27) 27. ከዚያም ከዚህ በኋላ አላህ ከሚፈልገው ሰው ላይ ጸጸትን ይቀበላል:: አላህ እጅግ መሀሪና አዛኝ ነውና::

(28) 28. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህ አጋሪዎች እርኩሶች ብቻ ናቸው:: እናም ከዚህ ዓመታቸው በኋላ ወደ ተከበረው መስጊድ እንዳይቀርቡ። ድህነትንም ብትፈሩ አላህ ቢፈልግ ከችሮታው በእርግጥ ያከብራችኋል:: አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነውና።

(29) 29. (ሙስሊሞች ሆይ!) ከእነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡ ሰዎች መካከል እነዚያን በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑትን ክፍሎች አላህና መልዕክተኛው እርም ያደረጉትንም እርም የማያደርጉትን፤ እውነተኛውንም ሃይማኖት የማይቀበሉትን የተዋረዱ ሆነው ግብርን በእጆቻቸው እስከሚሰጡ ድረስ ተዋጓቸው::

(30) 30. አይሁድ «ኡዘይር የአላህ ልጅ ነው።» አሉ:: ክርስቲያኖችም «አል-መሲህ የአላህ ልጅ ነው።» አሉ:: ይህ በአፎቻቸው የሚናገሩት ጸያፍ ቃላቸው ነው:: የእነዚያን ከእነርሱ በፊት የካዱትን (ሰዎች) ቃል ያመሳስላሉ:: አላህ ያጥፋቸው:: ከእውነት እንዴት ያፈነግጣሉ?

(31) 31. አይሁድና ክርስቲያኖች ከእርሱ በስተቀር ሌላ አምላክ የሌለውን አንዱን አምላክ አላህን ብቻ ሊገዙ እንጂ ያልታዘዙ ሲሆኑ ሊቃውንቶቻቸውን፤ መነኮሳቶቻቸውንና የመርየምን ልጅ አልመሲሕንም ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው ያዙ:: ከእርሱ በስተቀር ትክክለኛ አምላክ የለም:: አላህ ግን ከሚያጋሩት ሁሉ የጠራ ነው::

(32) 32. ከሓዲያን የአላህን ብርሃን በአፎቻቸው ለማጥፋት ይፈልጋሉ:: እርሱ (አላህ) ከሓዲያን ቢጠሉም እንኳ ብርሃኑን መሙላትን እንጂ ሌላን አይሻም::

(33) 33. አላህ ያ አጋሪዎቹ ቢጠሉም ከሃይማኖት ሁሉ በላይ ይፋ ያደርገው ዘንድ መልዕክተኛው ሙሓመድን በቅን መንገድና በእውነተኛ ሃይማኖት ላይ አድርጎ የላከው ብቸኛ አምላክ ነው።

(34) 34. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከሊቃውንትና ከመነኮሳት ብዙዎቹ የሰዎችን ገንዘቦች በውሸትም ይበላሉ:: ከአላህም መንገድም ሰዎችን ያግዳሉ:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያንም ወርቅንና ብርን የሚያደልቡትን በአላህም መንገድ ላይ የማያወጧቸውን ሰዎች በአሳማሚ ቅጣት አብስራቸው::

(35) 35. (በብሩና በወርቁ) ላይ በገሀነም እሳት ውስጥ በሚግሉበትና ግንባሮቻቸውም፣ ጎኖቻቸውም፣ ጀርቦቻቸውም በእርሱ በሚተኮሱበት ቀን አሳማሚ በሆነ ቅጣት አብስራቸው:: «ይህ ለነፍሶቻችሁ ያደለባችሁት ነው:: ታደልቡት የነበራችሁትንም ቅመሱ።» ይባላሉ::

(36) 36. የወራት ቁጥር አላህ ዘንድ በአላህ መጽሐፍ ውስጥ ሰማያትንና ምድርን በፈጠረበት ቀን አስራ ሁለት ወር ብቻ ነው:: ከእነርሱም መካከል አራቱ የተከበሩ ወሮች ናቸው:: ይህ ቀጥተኛው ሃይማኖት ነው:: በእነርሱ ውስጥም (ክብሮቻቸውን በመጣስ) ነፍሶቻችሁን አትበድሉ:: አጋሪዎችንም በአንድ ላይ ሆነው እንደሚጋደሏችሁ በአንድ ላይ ሆናችሁ ተጋደሏቸው:: አላህ በእርዳታው እርሱኑ ከሚፈሩት ጋር መሆኑን እወቁ::

(37) 37. የአንዱን ወር ክብር ወደ ሌላው ማዘግየት በክህደት ላይ ክህደትን መጨመር ነው:: በዚህ ተግባር ላይ እነዚያ በአላህ የካዱት (ሰዎች) ይሳሳቱበታል:: በአንደኛው ዓመት የተፈቀደ ያደርጉታል:: በሌላው ዓመት ደግሞ ያወግዙታል:: ይህም አላህ ያከበራቸውን ወሮች ቁጥር ሊሞሉበትና አላህ እርም ያደረገውን ደግሞ የተፈቀደ ሊያደርጉበት ነው:: መጥፎ ሥራዎቻቸው ለእነርሱ ተዋበላቸው:: አላህ ከሓዲያን ህዝቦችን ወደ ቀናው መንገድ አይመራም::

(38) 38. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! «በአላህ መንገድ ለመታገል ዝመቱ።» በተባላችሁ ጊዜ ወደ ምድር የምትወዘፉት ለምንድን ነው? የቅርቢቱን ህይወት ከመጨረሻይቱ ህይወት ይበልጥ ወደዳችሁን? የቅርቢቱ ህይወት ጥቅም ከመጨረሻይቱ ህይወት አንፃር ጥቂት እንጂ ምንም አይደለም::

(39) 39. ( አማኞች ሆይ!) ለዘመቻ ባትወጡ አላህ አሳማሚ ቅጣት ይቀጣችኋል:: ከናንተ ሌላ የሆኑን ህዝቦችም ይለውጣል:: አላህን በምንም አትጎዱትምም:: አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና::

(40) 40. (ሙስሊሞች ሆይ!) ነብዩ ሙሐመድን ባትረዱት እነዚያ በአላህ የካዱት ህዝቦች የሁለት ሰዎች ሁለተኛ ሆኖ ከመካ ባስወጡት ጊዜ አላህ ረድቶታል:: ሁለቱም በዋሻው ሳሉ ለጓደኛው «አትዘን አላህ ከእኛ ጋር ነውና» ባለ ጊዜ አላህ እርጋታውን በእርሱ ላይ አወረደ:: ባላያችኋቸዉም ሰራዊት አበረታው:: የእነዚያን በአላህ የካዱትን ሰዎች ቃል የበታች አደረገ:: የአላህ ቃል ግን የበላይ ነው:: አላህ ሁሉን አሸናፊና ጥበበኛ ነውና::

(41) 41.(አማኞች ሆይ!) ቀላሎችም ከባዶችም ኾናችሁ ዝመቱ:: በአላህ መንገድ በገንዘቦቻችሁና በነፍሶቻችሁ ታገሉ :: ይህ ተግባር የምታውቁ ከሆናችሁ ለእናንተ በጣም የተሻለ ነው::

(42) 42. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የጠራህባቸው ነገር ቅርብ ጥቅምና መካከለኛ ጉዞ በሆነ ኖሮ በተከተሉህ ነበር:: ግን በእነርሱ ላይ መንገዲቱ ራቀችባቸው:: «በቻልንም ኖሮ ከናንተ ጋር በወጣን ነበር» ሲሉ በአላህ ይምላሉ:: እራሳቸውን ለጥፋት (በውሸት) ይዳርጋሉ :: አላህ እነርሱ ውሸታሞች መሆናቸውን ያውቃል::

(43) 43. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ! ) አላህ ይቅር ብሎሀል:: እነዚያ እውነተኞቹ እስከሚገለጹልህና ውሸታሞቹን ለይተህ እስከምታውቅ ድረስ ለእነርሱ ከዘመቻ እንዲቀሩ ለምን ፈቀድክላቸው?

(44) 44. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑት በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው ከመታገላቸው ለመቅረት ፈቃድን አይጠይቁህም:: አላህም በትክክል የሚፈሩትን ሰዎች ሁሉ አዋቂ ነው::

(45) 45. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ፈቃድ የሚጠይቁህ እነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑት፤ ልቦቻቸው የተጠራጠሩት ሰዎች ብቻ ናቸው:: እነርሱም በጥርጣሬያቸው ውስጥ ይዋልላሉ::

(46) 46. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ወደ ዘመቻ መውጣት ባሰቡ ኖሮ ለእርሱ ዝግጅትን ባሰናዱ ነበር:: ግን አላህ ለመውጣት እንቅስቃሴያቸውን ጠላውና አሰነፋቸው:: «ከተቀማጮቹ ጋር ተቀመጡ።» ተባሉም::

(47) 47. (አማኞች ሆይ!) ከናንተ ጋር በወጡ ኖሮ ጥፋትን እንጂ አይጨምሩላችሁም ነበር:: ሁከትንም የሚፈልጉላችሁ ሲሆኑ በመካከላችሁ ነገርን በማሳበቅ ይቻኮሉ ነበር:: በእናንተ ውስጥ ለእነርሱ አዳማጮች አሏቸው:: አላህም በዳዮችን አዋቂ ነው::

(48) 48. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነርሱ ጠይዎች ሲኾኑ እውነቱ እስከመጣና የአላህም ትዕዛዝ እስከተገለጸ ድረስ ከዚህ በፊት ሁከትን በእርግጥ ፈለጉ፡፡ ነገሮችንም ሁሉ አገላበጡልህ፡፡

(49) 49. ከእነርሱም ውስጥ «ፍቀድልኝ አትሞክረኝ» የሚል ሰው አለ። (ሙስሊሞች) አስተውሉ! እነኝህ ሰዎች በመከራ ውስጥ ወደቁ:: ገሀነም ከሓዲያንን ከባቢ ናት::

(50) 50. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) መልካም ነገር ቢያገኝህ ያስከፋቸዋል:: መከራ ቢያገኝህ ግን «ፊቱንም ይህን ፈርተን የግል ጥንቃቄያችንን ይዘናል።» ይላሉ። ተደሳቾች ሆነዉም ይሸሻሉ::

(51) 51. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «አላህ ለእኛ የጻፈልን እንጂ ሌላ አይነካንም:: እርሱ ረዳታችን ነው:: ምዕምናን በአላህ ላይ ብቻ ይመኩ።» በላቸው::

(52) 52. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በእኛ ላይ ከሁለቱ መልካሞች አንደኛዋን እንጂ ሌላን ትጠባበቃላችሁን? እኛም አላህ ከእርሱ በሆነው ቅጣት ወይም በእጆቻችን የሚያጠፋችሁ መሆኑን በእናንተ ላይ እንጠባበቃለን:: ተጠባበቁ:: እኛም ከናንተው ጋር ተጠባባቂዎች ነንና።» በላቸው::

(53) 53. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ወዳችሁም ሆነ ጠልታችሁ ለግሱ ከናንተ ተቀባይ የላችሁም:: እናንተ አመጸኞች ህዝቦች ናችሁና።» በላቸው::

(54) 54. ልግስናዎቻቸውን ከእነርሱ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ያደረገው በአላህና በመልዕክተኛው የካዱ፤ ሶላትንም ስልቹዎች ሆነው እንጂ የማይሰግዱ፤ እነርሱም ጠይዎች ሆነው እንጂ የማይሰጡ ከመሆናቸው በስተቀር ሌላ ነገር አልከለከላቸዉም::

(55) 55. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ገንዘቦቻቸውና ልጆቻቸው አይድነቁህ:: አላህ የሚሻው በቅርቢቱ ህይወት በእነርሱ (በገንዘቦቻቸውና በልጆቻቸው) ሊቀጣቸው ነፍሶቻቸዉም ከሓዲያን ሆነው ሊሞቱ ብቻ ነውና::

(56) 56. እነርሱም ከናንተ ጋር ለመሆናቸው በአላህ ይምላሉ:: እነርሱ ግን ከናንተ ጋር አይደሉም:: ይልቁንም እነርሱ አጋሪዎችን ያገኘው ነገር እንዳያገኛቸው የሚፈሩ ህዝቦች ናቸው::

(57) 57. (ሙስሊሞች ሆይ!) መጠጊያ ወይም መሸሸጊያ ዋሻዎችን ወይም መግቢያ ቀዳዳዎችን ባገኙ ኖሮ በፍጥነት ወደ እርሱ በሸሹ ነበር::

(58) 58. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከእነርሱ መካከል በምጽዋቶች ክፍፍል ዙሪያ የሚዘልፉህ ሰዎች አሉ:: ከእርሷም የሚሹትን ያህል ቢሰጡ ይደሰታሉ:: ከእርሷ ምንም ካልተሰጣቸው ግን ይጠላሉ::

(59) 59. እነርሱም አላህና መልእክተኛው የሰጣቸውን በወደዱ፤ «አላህ በቂያችን ነው አላህ ከችሮታው በእርግጥ ይሰጠናል፣ መልክተኛውም (ይሰጠናል) እኛ ወደ አላህ ከጃዮች ነን።» ባሉ ኖሮ ለነርሱ በተሸላቸው ነበር::

(60) 60. ግዴታ ዘካን የሚከፈሉት ለድሆች፤ ለችግረኞች፤ በእርሷም ላይ ለሚሰሩ ሠራተኞች፤ ልቦቻቸው በኢስላም ለሚለማመዱት ወገኖች፤ ጫንቃዎችን (ባሪያዎች) ነጻ ለማውጣት፤ ባለ እዳ ለሆኑት፤ በአላህ መንገድም ለሚሰሩና (ስንቅ ላለቀበት) መንገደኛ ብቻ ነው:: ይህ ስርአት ከአላህ የተደነገገ ግዴታ ነው:: አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነውና።

(61) 61. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ! ) ከአስመሳዮች መካከል ነብዩ ሙሐመድን የሚያስቸግሩና «እርሱ እኮ ወሬ ሰሚ ነው።» የሚሉ አሉ። «ለእናንተ የበጎ ወሬ ሰሚ ነው:: በአላህ ያምናል:: አማኞችንም ያምናቸዋል:: ከናንተ መካከል ለእነዚያ በአላህ ላመኑት ሰዎችም እዝነት ነው።» በላቸው:: እነዚያ የአላህን መልዕክተኛ የሚያስቸግሩ ሰዎች ሁሉ አሳማሚ ቅጣት አለባቸው።

(62) 62. አላህንና መልዕክተኛውን ሊያስወድዱ ሲገባቸው እናንተን ሊያስወድዷችሁ ዘንድ በአላህ ይምሉላችኋል። ትክክለኛ አማኞች ከሆኑ (ግን አላህንና መልዕክተኛው ሊያስወድዱ ይገባቸዋል)::

(63) 63. አላህንና መልዕክተኛውን የሚከራከር ሰው ሁሉ በውስጡ ዘውታሪ ሲሆን የተዘጋጀችለት የገሀነም እሳት መሆኑን አያውቁምን? ይህ ደግሞ ታላቅ ውርደት ነው::

(64) 64. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አስመሳዮች በልቦቻቸው ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ የሚነግራቸው ምዕራፍ በእነርሱ ላይ መወረዱን ዘወትር ይፈራሉ:: «ተሳለቁ:: አላህ የምትፈሩትን ነገር ሁሉ ገላጭ ነው።» በላቸው::

(65) 65. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ብትጠይቃቸው «እኛ የምንዘባርቅና የምንጫወት ሰዎች ብቻ ነበርን።» ይላሉ:: «በአላህ፤ በአናቅጹና በመልዕክተኛው ላይ ትቀልዱ ነበራችሁን?» በላቸው::

(66) 66. (አስመሳዮች ሆይ!) አታመካኙ ከእምነታችሁ በኋላ በእርግጥ ክዳችኋልና:: ከናንተ አንዷን ቡድን ብንምር የሌላዋን ቡድን አባላት ግን ኃጢአተኞች በመሆናቸው እንቀጣለን::

(67) 67. የወንድ አስመሳዮችና የሴት አስመሳዮች ከፊሎቻቸው ከከፊሉ ናቸው:: በመጥፎ ነገር ያዛሉ:: ከደግ ነገርም ይከለክላሉ:: እጆቻቸውን ከልግስና ይሰበስባሉ:: ለአላህ መታዘዝን ረሱ (ተዉ):: ስለዚህ እርሱም ተዋቸው:: አስመሳዮቹ አመጸኞች ማለት እነርሱው ናቸው::

(68) 68. የወንድ አስመሳዮችንና የሴት አስመሳዮችን እንዲሁም ከሓዲያንን የገሀነምን እሳት በውስጧ ዘውታሪዎች ሲሆኑ አላህ ቃል ገብቶላቸዋል:: እርሷ በቂያቸው ናት:: አላህ ረግሟቸዋል:: ለእነርሱም ዘውታሪ ቅጣት አለባቸው::

(69) 69. (አስመሳዮች ሆይ!) ተግባራችሁ ልክ እንደእነዚያ ከናንተ በፊት እንደነበሩት ህዝቦች ነው:: ከናንተ ይበልጥ በሃይል የበረቱ በገንዘብና በልጆችም ከናንተ ይበልጥ የበዙ ነበሩ:: በእድላቸው ተጠቀሙ:: እነዚያም ከእናንተ በፊት የነበሩት በዕድላቸው እንደተጠቀሙ በዕድላችሁ ተጠቀማችሁ፡፡ እንደዘባረቁትም ዘባረቃችሁ:: እነዚያ ስራዎቻቸው በቅርቢቱም ሆነ በመጨረሻይቱ ዓለም ተበላሸ:: ከሳሪዎቹም ማለት እነርሱው ናቸው::

(70) 70. የእነዚያ ከእነርሱ በፊት የነበሩት የኑህ፤ የዓድ፤ የሰሙድ፤ የኢብራሂም ህዝቦች፤ የመድየን ባለቤቶችና የተገልባጮቹም ከተሞች ታሪክ አልመጣላቸዉምን? መልዕክተኞቻቸው ግልጽ ተዓምራትን አመጡላቸው:: አላህ የሚበድላቸው አልነበረም:: ግን በራሳቸው ነፍሶቻቸውን የሚበድሉ ነበሩ::

(71) 71. ወንድ አማኞችና ሴት አማኞች ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው:: በደግ ነገር ያዝዛሉ:: ከክፉም ነገር ይከለክላሉ:: ሶላትን ይሰግዳሉ:: ዘካን ይሰጣሉ:: አላህንና መልዕክተኛውን ይታዘዛሉ:: እነዚያን አላህ በእርግጥ ያዝንላቸዋል:: አላህ ሁሉን አሸናፊና ጥበበኛ ነውና::

(72) 72. አላህ የወንድ ትክክለኛ አማኞችንና የሴት ትክክለኛ አማኞችን ከስሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲሆኑ በመኖሪያ ገነቶችም ውስጥ መልካም መኖሪያ ቤቶችን ቃል ገብቶላቸዋል:: ከአላህ የሆነው ውዴታ ደግሞ ከሁሉ የበለጠ ነው:: ይህ እርሱ ታላቅ ዕድል ነው::

(73) 73. አንተ ነብዩ ሆይ! ከሓዲያንንና አስመሳዮችን ታገል:: በእነርሱ ላይም ጨክን:: መኖሪያቸዉም ገሀነም ናት:: መመለሻይቱም በጣም ከፋች::

(74) 74. ምንም ያላሉ ለመሆናቸው በአላህ ይምላሉ:: ግን የክህደትን ቃል በእርግጥ አሉ:: ከእስልምናቸዉም በኋላ ካዱ:: ያላገኙትንም ነገር አሰቡ:: አላህና መልዕክተኛው ከችሮታው ያከበራቸው መሆኑን እንጂ ሌላን አልጠሉም:: ቢጸጸቱም ለእነርሱ የተሻለ ይሆናል:: ቢሸሹም አላህ በቅርቢቱና በመጨረሻይቱ ዓለም አሳማሚን ቅጣት ይቀጣቸዋል:: ለእነርሱም በምድር ውስጥ ምንም ወዳጅና ረዳት የላቸዉም::

(75) 75. ከእነርሱም መካከል አላህን «ከችሮታው ቢሰጠን በእርግጥ እንመጸውታለን::በእርግጥ ከመልካሞችም እንሆናለን።» ሲል ቃል የገባ አለ::

(76) 76. ከዚያም ከችሮታዉም በሰጣቸው ጊዜ ሰሰቱ:: እነርሱ ቃል ኪዳናቸውን የተው ሆነዉም ዞሩ::

(77) 77. ለአላህ ቃል የገቡትን በማፍረሳቸውና ይዋሹትም በነበሩት ውሸት ምክንያት እስከሚገናኙት ቀን ድረስ ንፍቅናን በልቦቻቻው አስከተላቸው::

(78) 78. (አስመሳዮችን) አላህ ምስጢራቸውንና ውይይታቸውን የሚያውቅ መሆኑንና አላህም ሩቅ ነገሮችን ሁሉ በጣም አዋቂ መሆኑን አያውቁምን?

(79) 79. እነዚያ ከምዕምናን በምጽዋቶች ፈቃደኛ የሆኑትን የችሎታቸውን ያክል እንጂ የማያገኙትን ሰዎች የሚያነውሩና በእነርሱ የሚሳለቁ ሰዎች ሁሉ አላህ ከእነርሱ ይሳለቅባቸዋል:: ለእነርሱም አሳማሚ ቅጣት አለባቸው::

(80) 80. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለእነርሱ ምሕረትን ብትለምንላቸዉም ወይም ባትለምንላቸው ሁሉም እኩል ነው:: ለእነርሱ ሰባ ጊዜ ምህረትን ብትለምንላቸው እንኳን አላህ በፍጹም አይምራቸዉምና:: ምክንያቱም እነርሱ በአላህና በመልዕክተኛው ክደዋልና:: አላህ አመጸኞች ህዝቦችን አያቀናም::

(81) 81. እነዚያ ከዘመቻ የቀሩት ሰዎች ከአላህ መልዕክተኛ በኋላ ተገንጥለው በመቀመጣቸው ተደሰቱ:: በአላህ መንገድ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው መታገልን ጠሉ:: ለሌሎችም «በሐሩር አትሂዱ» አሉ:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «የገሀነም እሳት ትኩሳት በጣም ከዚህ የበረታ ነው።» በላቸው:: እናም የሚያውቁ ቢሆኑ ኖሮ ከዘመቻው አይቀሩም ነበር::

(82) 82. አስመሳዮች ጥቂት ጊዜን ብቻ ይሳቁ:: ይሠሩት በነበሩት እኩይ ተግባር ምክንያት ዋጋ ብዙ ጊዜ ያለቅሳሉና::

(83) 83. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከእነርሱ መካከል ወደ ሆነችው ቡድን አላህ በሰላም ቢመልስህና ካንተ ጋር ዘመቻ ለመውጣት ቢያስፈቅዱህ «ከእኔ ጋር በፍጹም አትወጡም:: ከእኔም ጋር ጠላትን አትዋጉም:: እናንተ በመጀመሪያ ጊዜ መቀመጥን ወዳችኋልና:: ይልቁንም ከተቀማጮች ጋር ተቀመጡ።» በላቸው::

(84) 84. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከእነርሱ መካከል በሞተ በአንዱም ሰው ላይ ቢሆን ፈጽሞ አትስገድ:: በመቃብሩም ላይ አትቁም:: እነርሱ በአላህና በመልዕክተኛው ክደዋል:: እነርሱ አመጸኞችም ሆነው ሞተዋልና::

(85) 85. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ገንዘቦቻቸውና ልጆቻቸው አይድነቁህ:: አላህ የሚፈልገው በቅርቢቱ ዓለም በገንዘቦቻቸውና በልጆቻቸው ሊቀጣቸውና ከሓዲያንም ሆነው ነፍሶቻቸው እንዲወጡ ሊያደርግ ብቻ ነውና::

(86) 86. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በአላህ እመኑ:: ከመልዕክተኛው ጋር ሆናችሁ ታገሉ በማለት የቁርኣን ምዕራፍ በተወረደ ጊዜ ከእነርሱ የሰፊ ሀብት ባለቤቶች የሆኑት ሰዎች ለመቅረት ፈቃድ ይጠይቁሃል:: «ከተቀማጮቹ ጋር እንሁን ተወን» ይሉሃል::

(87) 87. በቤት ከሚቀሩት ወገኖች ጋር መሆናቸውን ወደዱ:: በልቦቻቸዉም ላይ (ዝገት) ታተመባቸው:: ስለዚህ እነርሱ አያውቁም::

(88) 88. ግን መልዕክተኛውና ከእርሱ ጋር ያመኑት ሰዎች በገንዘቦቻቸዉም በነፍሶቻቸዉም ታገሉ:: እነዚያም መልካሞች ሁሉ ለእነርሱ ብቻ የተዘጋጁ ናቸው:: እነዚያም እነርሱ ምኞታቸውን ያገኙ ናቸው::

(89) 89. አላህ ለእነርሱ በሥራቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶችን በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲሆኑ አዘጋጅቶላቸዋል:: ይህ ታላቅ ማግኜት (እድል) ነው::

(90) 90. ከአረብ ዘላኖች መካከል ይቅርታ ፈላጊዎቹ እንዲፈቀድላቸው መጡ:: እነዚያ አላህንና መልዕክተኛውን ያስተባበሉት ግን ተቀመጡ:: እነዚያን በአላህ የካዱት ሰዎች አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ይነካቸዋል (ያገኛቸዋል)::

(91) 91. በደካሞች ላይ፤ በበሽተኞች ላይ፤ በእነዚያም ለስንቅና ለትጥቅ የሚያወጡት ገንዘብ በማያገኙት ላይ ለአላህና ለመልዕክተኛው ፍጹም ታዛዦች ከሆኑ ወደ ዘመቻ ባይወጡም ኃጢአት የለባቸዉም:: በበጎ አድራጊዎች ላይ ምንም የመወቀሻ መንገድ የለባቸዉም:: አላህ መሓሪና አዛኝ ነውና::

(92) 92. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በነዚያም መጓጓዣያ እንድትሰጣቸው ፈልገው ወደ አንተ በመጡ ጊዜ «እናንተን የምጭንበት (አጋሰስ) አላገኝም።» ያልካቸው ስትሆን የሚያወጡት ገንዘብ ባለማግኘታቸው ለማዘናቸው ዓይኖቻቸው እንባን እያፈሰሱ በዞሩት ላይ ምንም ወቀሳ የለባቸዉም::

(93) 93. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የሚወቀሱት እነዚያ ባለጸጋዎች ሆነው ሳሉ ለመቅረት ፈቃድ በሚጠይቁህ ሰዎች ላይ ብቻ ናቸው:: ከቀሪዎቹ ጋር መሆናቸውን ወደዱ:: አላህ በልቦቻቸው ላይ አተመባቸው:: ስለዚህ እነርሱ አያውቁም::

(94) 94. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ወደ እነርሱ በተመለሳችሁ ጊዜ ምክንያቶቻቸውን ያቀርቡላችኋል:: «አታመካኙ እናንተን ፈጽሞ አናምንም:: አላህ ከወሬዎቻችሁ አስቀድሞ ነግሮናልና:: አላህና መልዕክተኛው ሥራችሁን ያያሉ:: ከዚያ ሩቅንና ቅርብን ሁሉ አዋቂ ወደ ሆነው አላህ ትመለሳላችሁ:: ወዲያዉም ትሠሩት የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል።» በላቸው::

(95) 95. (አማኞች ሆይ!) ከዘመቻ ወደ እነርሱ በተመለሳችሁ ጊዜ ጥፋታቸውን ይቅር እንድትሉሏቸው ለእናንተ በአላህ ይምላሉ:: እነርሱን ተዏቸው:: እነርሱ እርኩሶች ናቸውና:: ይሠሩትም በነበረው ኃጢአት መኖሪያቸው ገሀነም ነው::

(96) 96. እነርሱ ትወዱላቸው ዘንድ ለእናንተ ይምሉላችኋል:: እናንተ ብትወዱላቸውም አላህ ከአመጸኛ ህዝቦች አይወድም::

(97) 97. ዘላን አረቦች በክሕደትና በንፍቅና በጣም የበረቱ፤ አላህ በመልዕክተኛው ላይ ያወረደውን ህግጋት ባለማወቅም የተገቡ ናቸው:: አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነው::

(98) 98. ከዘለኖች መካከል በአላህ መንገድ የሚያወጣውን ገንዘብ እዳ አድርጎ የሚይዝና በእናንተ ላይ የጊዜን መገለባበጥ የሚጠባበቅ ሰው አለ:: በእነርሱ ላይ ጥፋቱ ይዙርባቸው:: አላህ ሁሉን ሰሚና ሁሉንም አዋቂ ነው::

(99) 99. ከአረብ ዘላኖች መካከል በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን የሚሰጣቸውንም ምጽዋቶች አላህ ዘንድ መቃረቢያዎችና ወደ መልዕክተኛው ጸሎቶች መዳረሻ አድርጎ የሚይዝ ክፍል አለ:: አስተዉሉ! እርሷ ለእነርሱ በእርግጥ አቃራቢ ናት:: አላህ በችሮታው ውስጥ በገነቱ በእርግጥ ያስገባቸዋል:: አላህ መሓሪና አዛኝ ነውና ::

(100) 100. ከስደተኞቹም ሆነ ከረዳቶቹ የመጀመሪያዎቹ ቀዳሚዎችና እነዚያም በበጎ ሥራ የተከተሏቸው ሰዎች አላህ የእነርሱን ተግባር ወዶላቸዋል:: እነርሱም ወደውለታል:: በሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸዉም ዘለዓለም ነዋሪዎች ሲሆኑ ለእነርሱ አዘጋጅቶላቸዋል:: ይህ ታላቅ እድለኛነት ነው::

(101) 101. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በዙሪያችሁም ካሉት የዐረብ ዘላኖች አስመሳዮች አሉ:: ከመዲና ሰዎችም በንፍቅና ላይ በማመጽ የዘወተሩ አሉ:: አታውቃቸዉም:: እኛ እናውቃቸዋለን:: ሁለት ጊዜ እንቀጣቸዋለን:: ከዚያ ወደ ታላቅ ቅጣት ይመለሳሉ::

(102) 102. ሌሎችም ኃጢአቶቻቸውን የተናዘዙ መልካም ሥራንና ሌላን መጥፎ ሥራ የቀላቀሉ አሉ:: አላህ ጸጸታቸውን ሊቀበል ይከጀላል:: አላህ መሓሪና አዛኝ ነውና::

(103) 103. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ከገንዘቦቻቸው የምታጠራቸውና የምታፋፋቸውን ምጽዋት ያዝ:: ለነሱም ዱኣ አድርግላቸው፡፡ ዱኣእህ ለእነሱ እርጋታ ነውና አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡

(104) 104. አላህም እርሱ ከባሮቹ ንሰሃን የሚቀበልና ምጽዋቶችንም የሚወስድ፤ አላህ ብቸኛ ጸጸትን ተቀባይና አዛኝ መሆኑን አያውቁምን?

(105) 105. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ሥሩ:: አላህ መልዕክተኛውና አማኞችም ሥራችሁን በእርግጥ ያያሉና:: ሩቁንና ቅርቡን ሁሉ አዋቂ ወደ ሆነው አላህ በእርግጥ ትመለሳላችሁ:: ትሰሩት የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል።» በላቸው::

(106) 106. ሌሎችም የአላህን ውሳኔ ትዕዛዝ እንዲጠብቁ የተቆዩ ህዝቦች አሉ:: ይቀጣቸዋል ወይም ጸጸታቸውን ይቀበላቸዋል:: አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነዉና፡፡

(107) 107. እነዚያም አማኞችን ለመጉዳት ክህደትንም ለማበረታታት በአማኞችም መካከል ለመለያየት ከአሁን በፊት አላህንና መልዕክተኛውን የተዋጋውን ሰው ለመጠባበቅ መስጊዱን የሠሩት ሰዎች ከእነርሱ ናቸው:: «መልካምን እንጂ ሌላ አልሻንም።» ሲሉ በእርግጥ ይምላሉ:: አላህ ደግሞ ውሸታሞች መሆናቸውን በእርግጥ ይመሰክራል::

(108) 108. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በእርሱ ውስጥ በፍጹም አትስገድ:: ይልቁንም ከመጀመሪያ ቀን ይዞ በአላህ ፍራቻ ላይ የተመሠረተው (የቁባ ) መስጊድ በውስጡ ልትሰግዱበት የተገባው ነው:: በውስጡ መጥራራትን የሚወዱ ወንዶች አሉ:: አላህ ተጥራሪዎችን ይወዳል::

(109) 109. አላህን በመፍራትና ውዴታውን በመፈለግ ላይ ግንቡን የመሠረተ ሰው ወይስ ጎርፍ በሸረሸረው ለመናድ በተቃረበ ገደል አፋፍ ላይ ግንቡን የመሠረተውና እርሱንም ይዞት ወደ ገሀነም እሳት ውስጥ የወደቀው ይበልጣልን? አላህ በደለኛ ሕዝቦችን አይመራም::

(110) 110. ያ የካቡት ግንባቸው ልቦቻቸው በሞት ካልተቆራረጡ በስተቀር በልቦቻቸው ውስጥ የመጠራጠር ምክንያት ከመሆን አይወገድም:: አላህ ሁሉን አዋቂና ጥበበኛ ነው::

(111) 111. አላህ ከትክክለኛ አማኞች ነፍሶቻቸውንና ገንዘቦቻቸውን ገነትን ለእነርሱ በማድረግ ገዛቸው:: በአላህ መንገድ ላይ ይጋደላሉ:: ይገድላሉም:: ይገደላሉም:: በተውራት፤ በኢንጂልና በቁርኣንም የተነገረውን ተስፋ በእርሱ ላይ አረጋገጠ:: ከአላህ የበለጠ በቃል ኪዳኑ የሚሞላ ማን ነው? (ትክክለኛ አማኞች ሆይ!) በዚያም በእርሱ በተሻሻጣችሁበት ሽያጫችሁ ተደሰቱ:: ይህ ታላቅ ዕድል ነውና::

(112) 112. እነርሱ ተጸፃቾች፤ ተገዢዎች፤ አመስጋኞች፤ ፆመኞች፤ (በሶላት) አጎንባሾች፤ በግንባር ተደፊዎች፤ በበጎ ሥራ አዛዦች፤ ከክፉ ከልካዮች እና የአላህንም ሕግጋት ጠባቂዎች ናቸው:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ትክክለኛ አማኞችንም አብስር::

(113) 113. መልዕክተኛዉም ሆነ እነዚያ በእሱ ያመኑት ሰዎች ለአጋሪዎቹ የዝምድና ባለቤቶች ቢሆኑም እንኳ ከሓዲያን እነርሱ የእሳት ጓዶች መሆናቸው ከተገለጸላቸው በኋላ የአላህን ምሕረት ሊለምኑላቸው የሚገባ አልነበረም::

(114) 114. ኢብራሂምም ለአባቱ ምህረትን መለመኑ ቀድሞ ገብቶለት የነበረውን ቃል ለመሙላት እንጂ ለሌላ አልነበረም:: እናም የአላህ ጠላት መሆኑ በተገለጸለት ጊዜ ከእርሱ ራቀ:: (ተወው):: ኢብራሂም በእርግጥ አልቃሻ እና ታጋሽ ነበርና።

(115) 115. አላህ ህዝቦችን ካቀናቸው በኋላ የሚጠነቀቁትን ነገር እሥከሚገልጽላቸው ድረስ ሳያውቁ በሰሩት ጥፋት ጥፋተኛ የሚያደርግ ጌታ አይደለም:: አላህ በነገሩ ሁሉ አዋቂ ነውና::

(116) 116. አላህ የሰማያትና የምድር ንግስና የእርሱ ብቻ ነው:: ህያው ያደርጋል:: ይገድላልም:: ለእናንተም ከእርሱ በስተቀር ጠባቂም ሆነ ወዳጅ የላችሁም::

(117) 117. በመልዕክተኛው በስደተኞችና በረዳቶች በእነዚህም በችግሩ ጊዜ (በተቡክ ዘመቻ) ከእነርሱ የከፊሎቹ ልቦች ለመቅረት ሊዘነበሉ ከተቃረቡ በኋላ በተከተሉት ላይ አላህ በእርግጥ ጸጸታቸውን ተቀበለ:: ከዚያ ከእነርሱ ንሰሃ መግባታቸውን ተቀበለ:: እርሱ(አላህ ) ለእነርሱ ሩህሩህና አዛኝ ነውና::

(118) 118. በእነዚያም ወደ ኋላ በቀሩት በሶስቱ ሰዎች ላይ ምድር ከስፋቷ ጋር በእነርሱ ላይ እስከምትጠብባቸው፤ ነፍሶቻቸዉም በእነርሱ ላይ እስከምትጠብባቸው፤ ከአላህም ወደ እርሱ ብቻ እንጂ ሌላ መጠጊያ አለመኖሩን እስከሚያረጋግጡ ድረስ በተቆዩት ላይ አላህ ጸጸትን ተቀበለ:: ከዚያም ይጸጸቱ ዘንድ ወደ ጸጸት መራቸው:: አላህ ጸጸትን ተቀባይና አዛኝ ነውና::

(119) 119. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን በትክክል ፍሩ:: ከእውነተኞቹም ጋር ሁኑ::

(120) 120. የመዲና ሰዎችና በዙሪያቸው ያሉት የዘላን ዓረብ ህዝቦች ከአላህ መልዕክተኛ ጥሪ ወደ ኋላ ሊቀሩና ነፍሶቻቸውንም ከነፍሱ አብልጠው ሊወዱ አይገባቸዉም ነበር:: ይህም የሆነው ለእነርሱ መልካም ሥራ የሚጻፍላቸው ቢሆን እንጂ በአላህ መንገድ ላይ ጥምም ድካምም ርሀብም የማይነካቸው ከሓዲያንንም የሚያስቆጭን ስፍራ የማይረግጡ ከጠላትም የሚጎዳን ነገር (መግደል) የማያገኙ በመሆናቸው ነው:: አላህ የመልካም ሠሪዎችን ምንዳ አያጠፋምና::

(121) 121. ትንሽንም ትልቅንም ልግስና አይለግሱም ወንዝንም አያቋርጡም አላህ ይሠሩት ከነበረው የበለጠን ምንዳ ይመነዳቸው ዘንድ ለእነርሱ የሚጽፍላቸው ቢሆን እንጂ::

(122) 122. ምእምናንም (ከነቢዩ ጋር ካልኾነ) በሙሉ ሊወጡ አይገባም፡፡ ከእነሱ ውስጥ ከየክፍሉ አንዲት ጭፍራ ለምን አትወጣም፡፡ (ሌሎቹ) ሃይማኖትን እንዲማሩና ወገኖቻቸው ወደነርሱ በተመለሱ ጊዜ እንዲጠነቀቁ ይገስጹዋቸው ዘንድ (ለምን አይቀሩም)፡፡

(123) 123. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እነዚያን በአቅራቢያችሁ ያሉትን ከሓዲያን ተዋጉ:: በናንተ ውስጥ ብርታትን ያግኙ:: አላህም ከሚጠነቀቁት ጋር መሆኑን እወቁ::

(124) 124. ምዕራፍ በተወረደ ጊዜ ከአስመሳዮች ውስጥ «ማንኛችሁ ነው ይህ ምዕራፍ እምነትን የጨመረለት?» የሚል ሰው አለ:: እነዚያ ያመኑት ሰዎች የሚደሰቱ ሲሆኑ እምነትን ጨመረላቸው::

(125) 125. እነዚያ በልቦቻቸው ውስጥ በሽታ ያለባቸው ክፍሎች ግን በርክሰታቸው ላይ እርክሰትን ጨመረላቸው:: እነርሱም ከሓዲያን ሆነው ሞቱ::

(126) 126. በየዓመቱ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ እነርሱ የሚሞከሩ መሆናቸውን አያዩምን? ከዚያ አይጸጸቱምን?እነርሱም አይገሰጹምን?

(127) 127. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነርሱን የሚያወሳ ምዕራፍም በተወረደ ጊዜ «የሚያያችሁ (ሰው) አለን?» እያሉ ከፊሎቻቸው ወደ ከፊሉ ይመለከታሉ:: ከዚያ ተደብቀው ይሄዳሉ:: እነርሱ የማያውቁ ህዝቦች በመሆናቸው አላህ ልቦቻቸውን አዞረ::

(128) 128. (ሰዎች ሆይ!) ከጎሳችሁ ውስጥ የሆነ መቸገራችሁ በእርሱ ላይ ከባድ ጉዳይ የሆነበት፤ እናንተ እምነት እንዲኖራችሁ በጣም የሚጓጓና ለትክክለኛ አማኞችም ሩህሩህና አዛኝ የሆነ መልዕክተኛ (ሙሐመድ) መጣላችሁ::

(129) 129. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ቢያፈገፍጉ አላህ በቂዬ ነው:: ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም:: በእርሱ ላይ ብቻ ተመካሁ:: እርሱም የታላቁ ዐርሽ ጌታ ነው።» በላቸው::