(1) 1. ያ ፉርቃንን (እውነትን ከውሸት የሚለየውን) ቁርኣን በባሪያው ላይ ለዓለማት አስፈራሪ ይሆን ዘንድ ያወረደው (አምላክ) ክብሩ ላቀ (ጥራት ተገባው)።
(2) 2. አላህ ያ የሰማያትና የምድር ንግስና የእርሱ ብቻ የሆነ፤ ልጅንም ያልያዘ (ልጅም የሌለው)፤ በንግስናዉም ተጋሪ የሌለው፤ ሁሉንም ነገር የፈጠረና በትክክልም (በስርአት) የመጠነው አምላክ ነው።
(3) 3. ከሓዲያን ከእርሱ ከአላህ ሌላ ምንንም የማይፈጥሩንና እነርሱ ራሳቸው የሚፈጠሩ፤ ለነፍሶቻቸዉም (ከራሳቸው ላይ) ጉዳትን መከላከልም ሆነ ለራሳቸው ጥቅምን ማምጣት (ማስከበር) የማይችሉ፤ ለሞት ማብቃትም ሆነ ህይወትን መለገስና ከሞት መቀስቀስንም የማይችሉን አማልክትን አምላክ አድርገው ያዙ።
(4) 4. እነዚያ በአላህ የካዱ ሰዎች «ይህ ቁርኣን እርሱ (ሙሐመድ) በራሱ የቀጠፈውና በእርሱም ላይ ሌሎች ህዝቦች ያገዙት ውሸት እንጂ ሌላ አይደለም።» አሉ። በእርግጥም በደልንና እብለትን ፈጸሙ።
(5) 5. «እነዚህ የመጀመሪያ ሰዎች ተረቶች (አፈታሪክ) ናቸው። አስጽፎታል፤ እናም በእርሱ ላይ ጧትና ማታ ትነበብለታለች።» አሉ።
(6) 6. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ያ በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለን ምስጢር የሚያውቀው አወረደው:: እርሱ መሓሪና አዛኝ ነውና።» በላቸው።
(7) 7. አሉም: «ይህ መልዕክተኛ ምን አይነት መልዕክተኛ ነው? ምግብ የሚመገብ ወደ ገበያ የሚመላለስ፤ ከእርሱ ጋር አስፈራሪ ይሆን ዘንድ ወደ እርሱ መልአክ (በገሃድ) አይወረድም ኖሯልን?
(8) 8. «ወይም ወደ እርሱ ድልብ አይሰጠዉምን? ወይም ከእርሷ የሚበላባት አትክልት ለእርሱ አትኖረዉምን?» አሉ። «በዳዮችም ላመኑት የተደገመበትን ሰው እንጂ ሌላን አትከተሉም።» አሉ።
(9) 9.(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ላንተ ምሳሌዎችን እንዴት እንዳደረጉልህና ከዚያም እንዴት እንደ ተሳሳቱ ተመልከት:: ወደ እውነት ለመድረስ መንገድንም አይችሉም::
(10) 10. ያ ቢሻ ከዚህ ካሉት የተሻለን ከስሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው አትክልት ስፍራዎችን ላንተ የሚያደርግልህ ህንጻ ቤቶችንም የሚያደርግልህ የሆነው ጌታ ችሮታው በዛ:: (ክብሩ ላቀ)
(11) 11. ይልቁንም እነርሱ በትንሳኤ አስተባበሉ:: በትንሳኤ ላስተባበለም ሁሉ አቃጣይ እሳት አዘጋጅተናል::
(12) 12. ከሩቅ ስፍራ ባየቻቸው ጊዜ የእርሷን የቁጭት መገንፈልንና ማናፋትን ይሰማሉ::
(13) 13. ከጓደኞቻቸው ጋር (ከሰይጣኖቻቸው ጋር) በአንድ የታሰሩ ሆነዉም ከእርሷ በጠባብ ስፍራ በተጣሉ ጊዜ በዚያ ስፍራ ጥፋትን ይጠራሉ:: (ዋ ጥፋታችን! ይላሉ)።
(14) 14. ዛሬማ አንድን ጥፋት ብቻ አትጥሩ:: ይልቁንም ብዙን ጥፋት ጥሩ ይባላሉ::
(15) 15. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) (እንዲህ) በላቸው: «ይህ የተሻለ ነውን? ወይስ ጥንቁቆቹ ተስፋ የተሰጡት የዘልዓለሟ ገነት?» ገነት ለእነርሱ ምንዳና መመለሻ ሆነች።
(16) 16. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለእነርሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ሆነው የሚፈልጉት ሁሉ አለላቸው:: ይህ ተስፋ ከጌታህ ሊለመን የሚገባው ተስፋ ነው::
(17) 17. እነርሱንና ከአላህ ሌላ የሚገዟቸውን የሚሰበስብበትንና «እናንተ እነዚህን ባሮቼን አሳሳታችሁን? ወይስ እነርሱው እራሳቸው መንገድን ሳቱ?» የሚልበትን ቀን አስታውስ።
(18) 18. (ተመላኪዎቹም): «አላህ ሆይ! ጥራት ይገባህ:: ከአንተ ሌላ ረዳቶችን ልንይዝ አይገባንም:: ግን እነርሱንም ሆነ አባቶቻቸውን መገንዘብን እስከ ተውና ጠፊ ህዝቦችም እስከሚሆኑ ድረስ አጣቀምካቸው።» ይላሉ።
(19) 19. በምትሉትም አማልክቶቻችሁ አስዋሹዋችሁ:: ቅጣቴን መገፍተርንም ሆነ እራሳችሁን መርዳት አትችሉም:: ከናንተም የሚበድልን ሰው ታላቅን ቅጣት እናቀምሰዋለን:: (ይባላሉ።)
(20) 20. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ካንተ በፊትም ከመልዕክተኞች እነርሱ በእርግጥ ምግብን የሚበሉ በገበያዎችም የሚሄዱ ሆነው እንጂ አላክንም:: ከፊላችሁንም ለከፊሉ ፈተና አድርገናል:: ትታገሳላችሁን? ጌታህም ተመልካች ነው::
(21) 21. እነዚያ መገናኘታችንን የማይጠብቁ ሰዎች «በእኛ ላይ ለምን መላእክት አልወረደም ወይም ጌታችንን ለምን አናይም?» አሉ። በነፍሶቻቸው ውስጥ በእርግጥ ኮሩ። ታላቅንም አመጽ አመጹ።
(22) 22. መላዕክትን በሚያዩበት ቀን በዚያ ጊዜ ለአመጸኞች የምስራች የላቸዉም። (መላዕክቱም) «የተከለከለ ክልክል» ይላሉ።
(23) 23. ወደ ሰሩት ስራም እናስባለን:: ከዚያም እንደ ተበተነ ትቢያ እናደርገዋለን::
(24) 24. የገነት ሰዎች በዚያ ቀን በመርጊያ የተሻሉ በማረፊያም በጣም ያማሩ ናቸው::
(25) 25. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሰማይ በደመና የምትቀደድበትንና መላእክትም መውረድን የሚወርዱበትን ቀን አስታውስ።
(26) 26. እውነተኛው ንግስና በዚያ ቀን ለአር-ረህማን ብቻ ነው:: በከሓዲያን ላይ አስቸጋሪ ቀን ነው::
(27) 27. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በዳይም «ዋ ምኞቴ! ከመልዕክተኛው ጋር ቀጥተኛን መንገድ ምነው ይዤ በሆነ፤ እያለ (በጸጸት) ሁለት እጆችን የሚነክስበትን ቀን (አስታውስ)::
(28) 28. «ዋ ጥፋቴ! እገሌን በወዳጅነት ባልያዝኩ ኖሮ እመኛለሁ።
(29) 29. (የእምነት ቃል የሆነው) «ቁርኣን ከመጣልኝ በኋላ ከማስታወስ በእርግጥ አሳሳተኝ።» ይላል:: ሰይጣንም ለሰው አጋላጭ ነውና።
(30) 30. መልዕክተኛዉም (ሙሐመድ) «ጌታዬ ሆይ! ህዝቦቼ ይህንን ቁርኣን የተተወ ነገር አደረጉት።» አለ።
(31) 31. ልክ እንደዚሁም ለነብያቱ ሁሉ ከአመጸኞች የሆነ ጠላትን አድርገናል:: መሪነትና ረዳትነት በጌታህ በቃ።
(32) 32. እነዚያ በአላህ የካዱ ሰዎችም «ቁርኣንን በእርሱ ላይ ለምን በጠቅላላ በአንድ ጊዜ አልተወረደለትም።» አሉ። ልክ እንደዚሁ በእርሱ ልብህን ልናረጋ (ከፋፍለን በተለያየ አወረድነው):: ቀስ በቀስ መለያየትንም ለየነው::
(33) 33. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በየትኛዉም ጥያቄ አይመጡብህም እውነተኛውን መልስና መልካም ፍቹንም የምናመጣልህ ብንሆን እንጅ::
(34) 34. እነዚያ በፊቶቻቻው ላይ እየተጎተቱ ወደ ገሀነም የሚሰበሰቡት እነዚያ ስፍራቸው የከፋ መንገዳቸዉም የጠመመ ናቸው።
(35) 35. በእርግጥም ለሙሳ መጽሐፍን ሰጠነው:: ከእርሱም ጋር ወንድሙን ሃሩንን ረዳት አደረግንለት::
(36) 36. «ወደ እነዚያም በተዓምራታችን ወደ አስተባበሉት ህዝቦች ሂዱ።» አልናቸው። (አስዋሿቸዉም) ማጥፋትንም አጠፋናቸው።
(37) 37. የኑህን ሰዎችም መልዕክተኞችን ባስተባበሉ ጊዜ አሰመጥናቸው:: ለሰዎችም መገሰጫ አደረግናቸው፤ ለበደለኞችም አሳማሚን ቅጣት አዘጋጅተናል::
(38) 38. ዓድንም፤ሰሙድንም፤ የረስ ሰዎችንና በዚህ መካከል የነበሩትንም ብዙ የክፍለ ዘመናት ህዝቦችንም አጠፋን።
(39) 39. ሁሉንም (ገሠጽን):: ለእነርሱ ምሳሌዎችን ገለጽን:: ሁሉንም ማጥፋትን አጠፋናቸዉም::
(40) 40. በዚያችም ክፉ ዝናብን በተዘነበችው ከተማ ላይ (የመካ ከሓዲያን) በእርግጥ መጥተዋል:: የሚያዩዋት አልነበሩምን? በእውነቱ መቀስቀስን የማይፈሩ ነበሩ::
(41) 41. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ባዩህም ጊዜ (እንዲህ) እያሉ መሳለቂያ እንጅ ሌላ አያደርጉህም: «ያ አላህ መልዕክተኛ እድርጎ የላከው ይህ ነውን?
(42) 42. «እነሆ በእርሷ ላይ መታገሳችን (ጽናታችን) ባልነበረ ኖሮ ከአማልክቶቻችን ሊያሳስተን ቀርቦ ነበር።» ሲሉም ይሳለቃሉ:: ወደ ፊትም ቅጣትን በሚያዩ ጊዜ መንገድን በጣም የተሳሳተው ማን እንደ ሆነ በእርግጥ ያኔ ያውቃሉ::
(43) 43. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ፍላጎቱን አምላኩ አድርጎ የያዘን ሰው አየህን? አንተም በእርሱ ላይ ጠባቂ ትሆናለህን?
(44) 44. ይልቁንም አብዛኛዎቻቸው የሚሰሙ ወይም የሚያውቁ መሆናቸውን ታስባለህን? እነርሱ እንደ እንስሳዎች እንጂ ሌላ አይደሉም:: ከቶውንም እነርሱ ከእንስሳዎች በባሰ መንገድን የተሳሳቱ ናቸው::
(45) 45. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ ጥላን እንዴት እንደ ዘረጋ አላየህምን? በሻም ኖሮ የረጋ ባደረገው ነበር:: ከዚያ ጸሐይን በእርሱ ላይ ምልክት አደረግን።
(46) 46. ከዚያም ቀስ በቀስ ወደ እኛ ሰበሰብነው::
(47) 47. እርሱም ያ ለእናንተ ሌሊትን ልብስ እንቅልፍንም ማረፊያ ያደረገ:: ቀንንም መተኛ ያደረገላችሁ አምላክ ነው።
(48) 48. እርሱ (አላህ) ያ ንፋሶችን አብሳሪዎች ሲሆኑ ከዝናቡ በስተፊት የላከ ነው:: ከሰማይም አጥሪ ውሃን አወረድን::
(49) 49. በእርሱ የሞተችን ሀገር ህያው ልናደርግበት፤ ከፈጠርነዉም ፍጡር እንስሳዎችንና ብዙ ሰዎችንም ልናጠጣበት አወረድነው።
(50) 50. ጸጋችንን ይገነዘቡም ዘንድ በመካከላቸው ከፋፈልነው አበላለጥነዉም:: ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች ክህደትን እንጂ እንቢ አሉ::
(51) 51. በሻንም ኖሮ በየከተማይቱ አስፈራሪን በላክን ነበር::
(52) 52. ከሓዲያንን አትታዘዛቸው:: በእርሱም (በቁርኣን) ታላቅን ትግል ታገላቸው::
(53) 53. እርሱ ያ ሁለትን ባህሮች አጎራብቶ የለቀቀ ነው:: አንዱ ጥም የሚቆርጥና ጣፋጭ ነው:: ሌላኛው ደግሞ የሚመረግግ ጨው ነው:: በመካከላቸዉም ከመቀላቀል መለያንና የተከለለን ክልል ያደረገ ነው::
(54) 54. እርሱም ያ ከውሃ ሰውን የፈጠረ የዝምድናና የአማችም ባለቤት ያደረገው ነው:: ጌታህም ሁሉን ነገር ቻይ ነው::
(55) 55. ከአላህ ሌላ የማይጠቅማቸውንና የማይጎዳቸውን አካል ይገዛሉ:: ከሓዲ በጌታው ላይ (በማመጽ ለሰይጣን) ረዳት ነው::
(56) 56. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን እንጂ አላክንህም::
(57) 57. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በእርሱ ላይ ዋጋን በፍጹም አልጠይቃችሁም። ወደ ጌታው መልካም መንገድን ለመያዝ የሻ ሰው ይስራ።» በላቸው።
(58) 58. በዚያም በማይሞተው ህያው አምላክ ላይ ተመካ፤ ከማመስገንም ጋር አጥራው:: የባሮቹን ኃጢአቶች ውስጥ በማወቅ በእርሱ በቃ::
(59) 59. ያ ሰማያትንና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ ብቻ የፈጠረ ነው። ከዚያም በዐርሹ ላይ ከፍ አለ:: አር-ረህማን ነው:: ከእርሱም አዋቂን ጠይቅ።
(60) 60. ለእነርሱም «ለአር-ረህማን ስገዱ።» በተባሉ ጊዜ «አር-ረህማን ማን ነው? ለምታዘንና ለማናውቀው እንሰግዳለን እንዴ?» ይላሉ። ይህም መራቅን ጨመራቸው። {1}
{1} እዚህ የንባብ ሱጁድ (ሱጁዱ ትላወህ) ይደረጋል።
(61) 61. ያ በሰማይ ቡሩጆችን ያደረገና በእርሷም አንጸባራቂን ጸሐይ አብሪ ጨረቃንም የፈጠረ ጌታ ክብሩ በጣም ላቀ።
(62) 62. እርሱም ያ ያመለጠውን ስራ ማስታወስን ለሚፈልግ ወይም ማመስገንን ለሚፈልግ ሌሊትንና ቀንን ተተካኪ ያደረገ ነው::
(63) 63. የአር-ረህማን ባሮች እነዚያ በምድር ላይ በዝግታ የሚሄዱት፤ ባለጌዎችም (በክፉ) ባነጋገሯቸው ጊዜ ሰላም የሚሉት ናቸው::
(64) 64. እነዚያም ለጌታቸው በግንባራቸው ተደፊዎችና ቋሚዎች (ሰጋጆች) ሆነው የሚያድሩት ናቸው።
(65) 65. እነዚያም (እንዲህ) የሚሉት ናቸው: «ጌታችን ሆይ! የገሀነምን ቅጣት ከእኛ ላይ መልስልን ቅጣቷ የማይለይለቅ ነውና።
(66) 66. «እርሷ መርጊያና መቀመጫ ለመሆን ከፋች!» የሚሉት ናቸው።
(67) 67. እነዚያም በለገሱ ጊዜ የማያባክኑት የማይቆጥቡትም ናቸው:: በዚህም መካከል ልግስናቸው ትክክለኛ የሆነ ነው::
(68) 68. እነዚያም ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ የማይገዙት፤ ያችንም አላህ እርም ያደርጋትን ነፍስ ያለ ህግ የማይገድሉ እና የማያመነዝሩት ናቸው:: ይህንን የሚፈጽም ሰው ወንጀለኛ ይሆናል::
(69) 69. በትንሳኤ ቀን ቅጣት ይደራረብበታል:: በእርሱም ውስጥ የተዋረደ ሆኖ ዘልአለሙን ይኖራል::
(70) 70. ተጸጽቶ የተመለሰና ያመነ መልካምንም የሰራ ሰው ብቻ ሲቀር እነዚያም አላህ መጥፎ ስራዎቻቸውን በመልካም ስራዎች ይለውጣል:: አላህም እጅግ መሓሪና አዛኝ ነው::
(71) 71. ተጸጽቶ የተመለሰና መልካምን ተግባር የሰራ እርሱ በአላህ ዘንድ የተወደደን መመለስ ወደ አላህ ይመለሳል::
(72) 72. እነዚያ በሐሰት የማይጣዱ፤ በውድቅ ቃል (ተናጋሪ) አጠገብም ባለፉ ጊዜ የተከበሩ ሆነው የሚያልፉ ናቸው::
(73) 73. እነዚያም በጌታቸው አናቅጽ በተገሠጹ ጊዜ (የተረዱ ተቀባዮች ሆነው እንጂ) ደንቆሮዎችና እውሮች ሆነው በእርሷ ላይ የማይደፉት ናቸው::
(74) 74. እነዚያ «ጌታችን ሆይ! ከሚስቶቻችንና ከዘሮቻችን ለዓይኖች መርጊያን ለእኛ ስጠን፤ አላህን ለሚፈሩትም መሪ አድርገን።» የሚሉ ናቸው::
(75) 75. እነዚያ በመታገሳቸው የገነትን ሰገነቶች ይመነዳሉ:: በእርሷም ውስጥ ውዳሴንና ሰላምታን ይሰጣሉ::
(76) 76. በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ሆነው (ይሰጣሉ):: መርጊያና መኖሪያይቱ ገነት አማረች::
(77) 77. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ) «ጸሎታችሁ ባልነበረ ኖሮ ጌታዬ እናንተን ከምንም አይቆጥራችሁም ነበር:: አስተባበላችሁ:: እናም ወደ ፊት ቅጣት ያዣችሁ ይሆናል።» በላቸው።