(1) 1. አሊፍ፤ ላም፤ ሚይም::
(2) 2. ሩም (በፋርሶች) ተሸነፈች፡፡
(3) 3. በጣም (ለዐረቡ ዓለም) ቅርብ በሆነችው ምድር ላይ እነርሱም (ከሶስት አመት ያላነሰ ከዘጠኝ ባልበለጠ በጥቂት አመታት ውስጥ) ከመሸነፋቸው በኋላ ያሸንፋሉ::
(4) 4. (ከሶስት አመት ያላነሰ ከዘጠኝ ባልበለጠ) በጥቂት አመታት ውስጥ (ያሸንፋሉ)። ጉዳዩ በፊትም ሆነ በኋላ የአላህ ነውና:: በዚያ ቀንም ምዕምናን ይደሰታሉ::
(5) 5. በአላህ እርዳታ (ይደሰታሉ)፡፡ አላህ የሚሻውን ሰው ይረዳል:: እርሱም ሁሉን አሸናፊና አዛኝ ነው::
(6) 6. አላህ እርዳታን በቁርጥ ቀጠረ:: አላህ ቀጠሮውን አያፈርስም:: ግን አብዛሀኞቹ ሰዎች አያውቁም::
(7) 7. ከቅርቢቱ ህይወት ግልጹን ብቻ ያውቃሉ:: እነርሱም ከኋለኛይቱ ዓለም ፍጹም ዘንጊዎች ናቸው::
(8) 8. በነፍሶቻቸው ሁኔታ አያስተውሉምን ? ሰማያትን፤ ምድርንና በመካከላቸው ያለውን ሁሉ በእውነትና በተወሰነ ጊዜ እንጂ አልፈጠራቸዉም:: ከሰዎች መካከል ብዙዎቹ ከጌታቸው ጋር በመገናኘት ከሓዲያን ናቸው::
(9) 9. በምድር ላይ አይሄዱምና የእነዚያን ከበፊታቸው የነበሩትን ሰዎች ፍፃሜ እንዴት እንደነበር አይመለከቱምን? በኃይል ከእነርሱ ይበልጡ ነበሩ:: ምድርንም አረሱ:: እነዚህ ከአለሟትም የበለጠ አለሟት:: መልዕክተኞቻቸዉም በተአምራቶች መጡባቸው:: ግና አስተባበሉና ጠፉ:: አላህም የሚበድላቸው አልነበረም:: ግና ነፍሶቻቸውን በራሳቸው ይበድሉ ነበር::
(10) 10. ከዚያም የእነዚያ ያጠፉት ሰዎች መጨረሻ በአላህ አናቅጽ ማስተባበላቸውና በእርሷ የሚሳሳቁ የሚያፌዙ መሆናቸው (ምክንያት መጥፎ ቅጣት) ሆነ።
(11) 11. አላህ መፍጠርን ይጀምራል:: ከዚያም ይመልሰዋል:: ከዚያም ወደ እርሱ ትመለሳለችሁ::
(12) 12. ሰዓቲቱም በምትከሰትበት ቀን አመጸኞች ጭጭ ይላሉ (ተስፋ ይቆርጣሉ)።
(13) 13. ለእነርሱም ከሚያጋሯቸው ጣዖታት መካከል አማላጆች አይኖሩዋቸዉም:: በሚያጋሯቸዉም ጣዖታት ከሓዲያን ይሆናሉ::
(14) 14. ሰዓቲቱም በምትከሰትበት ቀን በዚያ ቀን ይለያያሉ::
(15) 15. እነዚያ በአላህ ያመኑትና መልካሞችን ስራዎች የሰሩትማ እነርሱ በገነት ጨፌ ውስጥ ይደሰታሉ::
(16) 16. እነዚያም በአላህ የካዱትማ በአናቅጻችንና በኋለኛይቱም ዓለም መገናኘት ያስተባበሉት እነዚያ በቅጣት ውስጥ የሚጣዱ ናቸው::
(17) 17. አላህንም በምታመሹና በምታነጉም ጊዜ አጥሩት::
(18) 18. ምስጋናም በሰማያትና በምድር ውስጥ ለእርሱ ብቻ የተገባው ነው:: በሰርክም በቀትር ውስጥ በምትገቡም ጊዜ አጥሩት::
(19) 19. ህያውን ከሙት ያወጣል:: ሙትንም ከህያው ያወጣል:: ምድርንም ከሞተች በኋላ ህያው ያደርጋታል:: ልክ እንደዚሁም (ከመቃብር) ትወጣላችሁ::
(20) 20. እናንተንም ከአፈር መፍጠሩ ከዚያም እናንተ ወዲያውኑ የምትበታተኑ ሰዎች መሆናችሁ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው::
(21) 21. ለእናንተም ከነፍሶቻችሁ ሚስቶችን ወደ እነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው:: በዚህ ውስጥ ለሚያስተውሉ ህዝቦች ሁሉ አያሌ ተዐምራት አሉበት::
(22) 22. ሰማያትንና ምድርን መፍጠሩ የቋንቋዎቻችሁና የመልኮቻችሁም መለያየት ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው:: በዚህ ውስጥ ለአዋቂዎች አያሌ ታዐምራት አሉበት::
(23) 23. በሌሊትም ሆነ በቀን መተኛታችሁ ከችሮታዉም መፈለጋችሁም ከምልክቶቹ ነው:: በዚህ ውስጥ ለሚሰሙ ህዝቦች ሁሉ ብዙ ታዐምራት አሉበት::
(24) 24. ብልጭታንም ፈሪዎችና ከጃዮች ስትሆኑ ለእናንተ ማሳየቱ ከሰማይም ውሃን ማውረዱ በእርሱም ምድርን ከሞተች በኋላ ህያው ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው:: በዚህ ውስጥ ለሚያስቡ ህዝቦች ሁሉ አያሌ ታዐምራት አሉበት::
(25) 25. ሰማይና ምድርም ያለ ምሰሶ በትእዛዙ መቆማቸው ከዚያም መልአክ ለትንሳኤ ከምድር ጥሪን በጠራችሁ ጊዜ እናንተ ወዲያውኑ የምትወጡ መሆናችሁ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው::
(26) 26. በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለው ሁሉ የእርሱ ብቻ ነው:: ሁሉም ለእርሱ ታዛዦች ናቸው::
(27) 27. እርሱ ያ ፍጡራንን ከምንም የሚጀምር (የሚያስገኝ) ከዚያም የሚመልሳቸው ብቸኛ አምላክ ነው:: መመለሱም በእርሱ ላይ በጣም ቀላል ነው:: ለእርሱም በሰማያትና በምድር ከፍተኛው ምሳሌ (ባህሪ) አለው:: እርሱም ሁሉን አሸናፊና ጥበበኛ ነው።
(28) 28. (ጣዖት አምላኪዎች ሆይ!) ለእናንተ ከነፍሶቻችሁ የሆነን ምሳሌ አደረገላችሁ:: እርሱም እጆቻችሁ ከያዟቸው ባሮች ውስጥ በሰጠናችሁ ጸጋ ለእናንተ ተጋሪዎች አሏችሁን? ታዲያ እናንተና እነርሱ በእርሱ እኩል ለኩል (ትክክል) ናችሁን? ነፍሶቻችሁን (ብጤዎቻችሁን) እንደምትፈሩ ትፈሯቸዋላችሁን ? ልክ እንደዚሁ ለሚያስተውሉ ህዝቦች ሁሉ አናቅጽን እንገልጻለን::
(29) 29. ይልቁንም እነዚህ የበደሉ ሰዎች ያለ ዕውቀት ዝንባሌዎቻቸውን ተከተሉ:: አላህም ያጠመመውን ሰው የሚያቀናው ማነው? ለእነርሱም ከረዳቶች ምንም የላቸዉም::
(30) 30. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ወደ እውነት ተዘንባይ ሆነህም ፊትህን ለሃይማኖት ቀጥ አድርግ:: የአላህን ፍጥረት ያችን አላህ ሰዎችን በርሷ ላይ የፈጠረባትን ሃይማኖት (ያዟት):: የአላህን ፍጥረት መለወጥ የለም:: ይህ ቀጥተኛው ሃይማኖት ነው:: ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም::
(31) 31. ወደ እርሱ ተመላሾች ሆናችሁ የአላህን ሃይማኖት ያዙ:: ፍሩትም:: ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ:: ከአጋሪዎችም አትሁኑ::
(32) 32. ከእነዚያ ሃይማኖታቸውን ከለያዩትና ክፍልፍልም ከሆኑት አትሁኑ:: ህዝብ ሁሉ እነርሱ ዘንድ ባለው ነገር ብቻ ተደሳቾች ናቸው::
(33) 33. ሰዎችንም ችግር ባገኛቸው ጊዜ ጌታቸውን ወደ እርሱ ተመላሾች ሆነው ይጠሩታል:: ከዚያም ከእርሱ ችሮታንም ባቀመሳቸው ጊዜ ከእነርሱ ከፊሎቹ ወዲያውኑ በጌታቸው ጣዖትን ያጋራሉ::
(34) 34. በሰጠናቸው ጸጋ ሊክዱ (ያጋራሉ):: ተጣቀሙም:: በእርግጥም መጨረሻችሁን ወደፊት ታውቃላችሁ::
(35) 35. በእነርሱ ላይ አላህ አስረጅን አወረደን? ታድያ እርሱ በነዚያ በእርሱ ያጋሩ በነበሩት ነገር ይናገራልን? የለም::
(36) 36. ሰዎችንም ችሮታን ባቀመስናቸው ጊዜ በእርሷ ይደሰታሉ:: እጆቻቸዉም ባሳለፉት ምክንያት መከራ ብታገኛቸው ወዲያውኑ እነርሱ ተስፋ ይቆርጣሉ::
(37) 37. አላህ ለሚሻው ሰው ሲሳይን የሚያሰፋ የሚያጠብም መሆኑን አያዩምን? በዚህ ውስጥ ለሚያምኑ ህዝቦች አስደናቂ ምልክቶች አሉበት::
(38) 38.ስለዚህ (አማኝ ሆይ!) የዝምድናን ባለቤት ተገቢውን ስጠው:: ለድሃም ለመንገደኛም እርዳ:: ይህ ለእነዚያ የአላህን ፊት ለሚሹ ሁሉ መልካም ነው:: እነዚያ እነርሱም በሁለተኛው ዓለም የፈለጉትን የሚያገኙ ምርጥ ክፍሎች ናቸው::
(39) 39. (ሰዎች ሆይ!) በሰዎች ውስጥም ይጨመር ዘንድ በማቀድ የምትሰጡት ገንዘብ በአላህ ዘንድ ቅንጣት አይጨምርም:: የአላህን ፊት ብቻ የምትሹ ሆናችሁ የምትሰጡት ምጽዋት ግን እነዚያ እውነተኛ ሰጪዎች (አበርካቾች) እነርሱ ናቸው::
(40) 40. አላህ ያ የፈጠራችሁ ከዚያም ሲሳይን የሰጣችሁ ከዚያም የሚገድላችሁ ከዚያም ህያው የሚያደርጋችሁ ነው:: ከምታጋሯቸው ጣዖታት ውስጥ ከዚሃችሁ አንዳችን የሚሰራ አለን? ለአላህ ጥራት ይገባው በእርሱ ከሚያጋሩትም ሁሉ ላቀ::
(41) 41. የሰዎች እጆች በሰሩት ኃጢአት ምክንያት የዚያን የሰሩትን ከፊሉን ያቀምሳቸው ዘንድ መከራው በየብስና በባህር ተገለጠ (ተሰራጨ)። እነርሱ ሊመለሱ ይከጀላልና::
(42) 42. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በምድር ላይ ሂዱ የእነዚያንም በፊት የነበሩት ሰዎች መጨረሻ እንዴት እንደነበረ ተመልከቱ።» በላቸው:: አብዛኞቻቸው አጋሪዎች ነበሩ።
(43) 43. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለእርሱ መመለስ የሌለው ቀን የትንሳኤ ቀን ከአላህ ሳይመጣ በፊት ፊትህን ወደ ቀጥተኛው ሃይማኖት ቀጥ አድርግ :: በዚያ ቀን ወደ ገነትና ወደ እሳት ይለያያሉ::
(44) 44. በአላህ የካደ ሰው የክህደቱ ጠንቁ በእርሱው ላይ ብቻ ነው:: መልካምም የሰሩ ሁሉ ለነፍሶቻቸው ማረፊያዎችን ያዘጋጃሉ::
(45) 45. እነዚያን ያመኑትንና መልካሞችንም የሰሩትን ከችሮታው ይመነዳ ዘንድ (ይለያያሉ):: እርሱ ከሓዲያንን አይወድምና::
(46) 46. (ሰዎች ሆይ!) ንፋሶችንም (በዝናብ) ልታበስራችሁ ከችሮታዉም (በእርሷ) ሊያቀምሳችሁ መርከቦችም በትእዛዙ እንዲንሻለሉ ከችሮታዉም እንድትፈልጉ ታመሰግኑትም ዘንድ መላኩ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው::
(47) 47. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ካንተ በፊትም መልዕክተኞችን ወደ የህዝቦቻቸው በእርግጥ ላክን:: በግልጽ ማስረጃዎችም መጡባቸው:: ከእነዚያ ካመጹትም ተበቀልን:: ምዕመናኖችንም መርዳት በእኛ ላይ ተገቢ ሆነ::
(48) 48. አላህ ያ ! ንፋሶችን የሚልክ ነው:: ደመናንም ይቀሰቅሳል:: በሰማይ ላይም እንደሚሻ ይዘረጋዋል :: ቁርጥራጮችም ያደርገዋል:: ዝናቡንም ከደመናው መካከል ሲወጣ ታያለህ:: በእርሱም ከባሮቹ የሚሻውን በለየ ጊዜ ወዲያውኑ እነርሱ ይደሰታሉ::
(49) 49. በእነርሱም ላይ ከመውረዱ በፊት ከእርሱ በፊት በእርግጥ ተስፋ ቆራጮች ነበሩ::
(50) 50. ምድርንም ከሞተች በኋላ እንዴት ህያው እንደሚያደርጋት ወደ አላህ ችሮታ ፈለጎች ተመልከት:: ይህን አድራጊ ጌታ ሙታንንም በእርግጥ ህያው አድራጊ ነው :: እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና::
(51) 51. ንፋስንም በአዝመራዎች ላይ ብንልክና ገርጥቶ ቢያዩት ከእርሱ በኋላ በእርግጥ ችሮታውን የሚክዱ ይሆናሉ::
(52) 52. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አንተም ሙታንን አታሰማም:: ደንቆሮዎችንም ዟሪዎች ሆነው በሸሹ ጊዜ ጥሪን አታሰማም::
(53) 53. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አንተ እውሮችንም ከጥመታቸው የምታቀና አይደለህም:: በአናቅጻችን የሚያምኑትን ሰዎች እንጂ ሌላን አታሰማም:: እነርሱም ታዛዦች ናቸው::
(54) 54. (ሰዎች ሆይ!) አላህ ያ ከደካማ ፍትወት ጠብታ የፈጠራችሁ ነው:: ከዚያ ከደካማነት በኋላም ኃይልን አደረገ:: ከዚያም ከብርቱነት በኋላ ደካማነትና ሽበትንም አደረገ:: የሚሻውን ይፈጥራል:: እርሱም ሁሉን አዋቂውና ቻዩ ነው::
(55) 55. ሰዓቲቱ በምትከሰትበት ቀን ከሓዲያን «ከአንዲት ሰዓት በስተቀር በመቃብር (በዱንያ) አልቆየንም።» ብለው ይምላሉ:: ልክ እንደዚሁ በዚህኛው ዐለምም እያሉ ከእውነት ይመለሱ ነበር::
(56) 56. እነዚያም እውቀትንና እምነትን የተሰጡት «በአላህ መጽሐፍ ፍርድ እስከ ትንሳኤ ቀን በእርግጥ ቆያችሁ ይህም የካዳችሁት የትንሳኤ ቀን ነው:: ግን እናንተ የማታውቁ ነበራችሁ።» ይሏቸዋል::
(57) 57. በዚያም ቀን እነዚያን የበደሉትን ማመካኘታቸው አይጠቅማቸዉም:: እነርሱም በወቀሳ አይታለፉም::
(58) 58. በዚህም ቁርኣን ውስጥ ለሰዎች የምሳሌ አይነቶችን ሁሉ በእርግጥ ገለጽን:: በተዓምርን ብታመጣላቸው እንኳን እነዚያ በአላህ የካዱት ሰዎች «እናንተ አበላሺዎች የጥፋት ተጣሪ ዎች እንጂ ሌላ አይደላችሁም።» ይላሉ::
(59) 59 ልክ እንደዚሁ አላህ በነዚያ በማያውቁት ሰዎች ልቦች ላይ ያትማል::
(60) 60. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ስለዚህ ታገሥ:: የአላህ ቀጠሮ እውነት ነውና:: እነዚያም በትንሳኤ የማያረጋግጡት ሰዎች አያቅልሉህ::