58 - Al-Mujaadila ()

|

(1) 1. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ የዚያችን በባሏ ጉዳይ ላይ የምትከራከርህንና ወደ አላህ ስሞታን የምታሰማውን ሴትዮ ቃል ሰማ:: አላህ በንግግር መመላለሳችሁን (መወያየታችሁን) ይሰማል:: አላህ (ለሚባለው) ሁሉ ሰሚ (ለሚፈጸመው ሁሉ ነገር) አዋቂ ነውና።

(2) 2. እነዚያ ከናንተ መካከል ሚስቶቻቸውን እንደእናቶቻቸው ጀርባዎች ይሁኑብን በማለት የሚምሉ ሰዎች እነርሱ እናቶቻቸው አይደሉም:: ትክክለኛ እናቶቻቸው እነዚያ የወለዷቸው ሴቶች ብቻ ናቸው:: እነርሱ በዚህ ቃል የተጠላ ንግግርንና ውሸትን በእርግጥ ይናገራሉ:: አላህ ለሚጸጸት ሰው ሁሉ ይቅር ባይና መሀሪ ነው::

(3) 3. እነዚያ ሚስቶቻቸውን እንደእናቶቻቸው ጀርባዎች ይሁኑብን በማለት የሚምሉና ከዚያ ወደ ተናገሩት የሚመለሱ ሳይነካኩ በፊት በባርነት የተያዘችዋን ጫንቃ ነፃ ማውጣት ግዴታ አለባቸው:: ይህ ህግ (የተጠቀሰው ህግ) በእርሱ ትገሰጹበታላችሁ:: አላህ በምትሰሩት ነገር ሁሉ ውስጠ አዋቂ ነው።

(4) 4. ይህን ላላገኘም ሰው ከመነካካታቸው በፊት ሁለት ተከታታይ ወሮችን መፆም አለበት:: ይህን ላልቻለም ሰው ስልሳ ድሆችን ማብላት አለበት:: ይህ በአላህና በመልዕክተኛው እንድታምኑ ነው:: እነኚህ ህግጋት የአላህ ህግጋት ናቸው:: (እናም አትተላለፏቸው::) ለከሓዲያንም ሁሉ አሳማሚ ቅጣት አለባቸው::

(5) 5. ግልጽ ማስረጃዎችን ያወረድን ስንሆን እነዚያ አላህንና መልዕክተኛውን የሚከራከሩ ሰዎች እነዚያ ከእነርሱ በፊት የነበሩ ሰዎች እንደተዋረዱት ሁሉ ተዋርደዋል:: ለከሓዲያን አዋራጅ ቅጣት አለባቸው::

(6) 6. አላህ ሁላቸውንም በአንድ አድርጎ (አንድም ሳይቀር በአንድ ዓይነት) በሚቀሰቅሳቸው ቀን (ይቀጣቸዋል):: ከዚያም በዚህ ዓለም የሰሩትን ነገር ሁሉ ይነግራቸዋል:: እነርሱ የረሱት ሲሆን (መዝገባቸው ተመዝግቦ ያገኙታል) አላህ ግን አንድም ሳይቀር አውቆታል:: አላህ ሁሉንም ነገር ተመልካች ነውና::

(7) 7. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለውን ሁሉ የሚያውቅ መሆኑን አታውቅምን? (በእውነቱ ሁሉንም አካቧል::) የሶስት ሰዎች መንሾካሾክ አይከሰትም፤ አላህ አራተኛው ቢሆን እንጂ፤ የአምስትም ሰዎች መንሾካሾክ አይከሰትም እርሱ ስድስተኛ ቢሆን እንጂ፤ ከዚያ ያነሰም ይሁን የበዛ ሰው መሾካሾክ አይከሰትም እርሱ ባሉበት ቦታ አብሯቸው ቢሆን እንጂ:: ከዚያ በትንሳኤ ቀን የሰሩትን ሁሉ ይነግራቸዋል:: አላህ ሁሉን ነገር አዋቂ ነው።

(8) 8. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ወደ እነዚያ በመጥፎ ነገር ከመመሳጠር ወደ ተከለከሉት፤ ከዚያ ከእርሱ ወደ ተከለከሉት ነገር የሚመለሱትንና በኃጢአት፣ በጠላትነትና መልዕክተኛውን በመቃወም ወደ ሚመሳጠሩ አላየህምን? (ሰላም ሊሉ) ወደ አንተ በመጡ ጊዜ አላህ ባላናገረህ ቃል ያናግሩሃል:: ውስጣቸው ይህ ሰው ነብይ ከሆነ በምንለው ነገር አላህ አይቀጣንም ኖሯልን? (ነብይ ከሆነስ) የለመነውን ነገር አላህ ተቀብሎት በሞትን ነበር ይላሉ:: ገሀነም የሚገቡባት ሲሆኑ ከአሁኑ ሞት ይልቅ በቂያቸው ናት:: ገሀነምም መመለሻነቷ ከፋች!

(9) 9. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በተመሳጠራችሁ ጊዜ በኃጢአት ወሰንን በማለፍና መልዕክተኛውንም በመቃወም አትሾካሾኩ ግን በበጎ ስራና አላህን በመፍራት ተወያዩ:: ያንንም ወደ እርሱ የምትሰበሰቡበትን አላህን ፍሩ::

(10) 10. በመጥፎ መመሳጠር ከሰይጣን ማስዋብና ማሳመር የሚመጣ ብቻ ነው:: እነዚያ ያመኑ ሙስሊሞች ያዝኑ ዘንድ ይቀሰቅሰዋል:: ከአላህ ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር የሰይጣንም መመሳጠር በምንም ነገር አይጎዳቸዉም:: እናም ትክክለኛ አማኞች በአላህ ብቻ ይመኩ::

(11) 11. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለእናንተ በመቀመጫዎች ስፍራ ተስፋፉ በተባላችሁ ጊዜ ስፍራን አስፉ:: አላህ በገነት ያሰፋላችኃልና:: ተነሱ በተባለም ጊዜ ተነሱ:: አላህ ከናንተ መካከል እነዚያን በትክክል ያመኑትንና እነዚያንም እውቀትን የተሰጡትን በደረጃዎች (በዚች ዓለምም ሆነ በአኼራ) ከፍ ያደርጋል:: አላህ በምትሰሩት ነገር ሁሉ ውስጠ አወቂ ነውና::

(12) 12. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከመልዕክተኛው ጋር በተወያያችሁ ጊዜ ከመወያየታችሁ በፊት ምጽዋትን አስቀድሙ:: (ሰደቃ ስጡ):: ይህ (ምጸዋትን አስቀድሞ መስጠት) ለእናንተ መልካምና አጥሪ ነው:: ባታገኙም ምንንም (ሳትከፈሉ) ሳትሰጡ ብትወያዩ ችግር የለባችሁም:: አላህ መሀሪና አዛኝ ነውና::

(13) 13. ከውይይታችሁ በፊት ምጽዋቶችን በማስቀደም ድህነትን ፈራችሁን? የታዘዛችሁትን ባልሰራችሁ ጊዜ አላህ ከናንተ ጸጸትን የተቀበለ ሲሆን ሶላትን ስገዱ፤ ዘካንም ስጡ፤ አላህንና መልዕክተኛውንም ታዘዙ:: አላህ በምትሰሩት ነገር ውስጠ አዋቂ ነውና::

(14) 14. ወደ እነዚያ አላህ በእነርሱ ላይ የተቆጣባቸውን ህዝቦች (አይሁዶች) ወደ ተወዳጁት አስመሳዮች አላየህምን? እነርሱ ከናንተ አይደሉም:: ከእነርሱም አይደሉም። እያወቁ በውሸት ይምላሉ።

(15) 15. አላህ ለእነርሱ (በዚህ መወዳጃና የሀሰት መሀላ) ብርቱ ቅጣትን አዘጋጀ:: እነርሱ ይሰሩት የነበሩት መጥፎ ስራ ምንኛ ከፋ!

(16) 16. መሓሎቻቸውን ጋሻ አድርገው ያዙ:: ሰዎችንም ከአላህ መንገድ አገዱ:: ስለዚህ ለእነርሱ አዋራጅ ቅጣት አለባቸው::

(17) 17. ገንዘቦቻቸውና ልጆቻቸውም ከአላህ (ቅጣት) ምንም አያድኗቸዉም:: እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው:: እነርሱ በእርሷ ውስጥ ዘወታሪዎች ናቸው::

(18) 18. አላህ የተሰበሰቡ ሆነው በሚያስነሳቸውም ቂያማ ቀን ለእናንተ እንደ ሚምሉላችሁ በሚጠቅም ነገር ላይ መሆናቸውን የሚያስቡ ሆነው ለእርሱም (ለአላህም) ይምላሉ:: ሙስሊሞች አስተዉሉ:: ውሸታሞች እነርሱ ብቻ ናቸው::

(19) 19. በእነርሱም ላይ ሰይጣን ተሾመባቸው (ተመቻቸባቸው) እናም አላህን ማስታወስን አስረሳቸው( ትዕዛዛቱን ተው):: እነዚያ የሰይጣን ቡድኖች ( ሰራዊቶች) ናቸው:: ሙስሊሞች አስተዉሉ:: የሰይጣን ቡድኖች ከሳሪዎች እነርሱ ብቻ ናቸው::

(20) 20. እነዚያ አላህንና መልዕክተኛውን የሚከራከሩ ሁሉ እነዚያ በዱንያም ሆነ በአኺራ በጣም ከተዋረዱ ወገኖች ውስጥ ናቸው::

(21) 21. አላህ እኔ አሸንፋለሁ መልዕክተኞቼም እንዲሁ ያሸንፋሉ ሲል ድሮውኑ ጽፏል:: አላህ ብርቱና አሸናፊ ነውና::

(22) 22. በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑትን ህዝቦች አላህንና መልዕክተኛውን የሚከራከሩት ሰዎች አባቶቻቸው ወይም ልጆቻቸው ወይም ወንድሞቻቸው ወይም ዘመዶቻቸው ቢሆኑም እንኳ የሚወዳጁ ሆነው አታገኛቸዉም:: እነዚያ አላህ በልቦቻቸው ውስጥ እምነትን ጽፏል:: ከእርሱም በሆነ መንፈስ ደግፏቸዋል:: ከስሮቻቸዉም ወንዞች የሚፈሱባቸው ገነቶች በውስጣቸው ዘወታሪዎች ሲሆኑ ያስገባቸዋል:: አላህ ተግባራቸውን ወዷል:: እነርሱም የእርሱን ችሮታ ወደዋል:: እነዚያ የአላህ ህዝቦች ናቸው:: ንቁ! የአላህ ህዝቦች ምኞታቸውን የሚያገኙ እነርሱ ናቸው::