38 - Saad ()

|

(1) 1. ሷድ፤ የግሳፄ ባለቤት በሆነው ቁርኣን እምላለሁ።

(2) 2. ይልቁንም እነዚያ በአላህ የካዱ ሰዎች በከባድ ትዕቢትና በአጓጉል ክርክር ውስጥ ናቸው።

(3) 3. ከእነርሱ በፊት ከክፍለ ዘመናት ህዝቦች ብዙን አጥፍተናል:: ጊዜው የመሸሻና የማምለጫ ጊዜ ሳይሆንም (ለእርዳታ) ተጣሩ::

(4) 4. ከእነርሱ መካከል የሆነ አስፈራሪ ስለመጣላቸውም ተደነቁ:: ከሓዲያንም አሉ: «ይህ ድግምተኛ ጠንቋይ ውሸታም ነው።

(5) 5. «አማልዕክቶችን አንድ አምላክ አደረጋቸውን? ይህ አስደናቂ ነገር ነው።» አሉ።

(6) 6. ከእነርሱም መካከል ባላባቶቹ (እንዲህ) እያሉ አዘገሙ: «ሂዱ በአማልክቶቻችሁም መገዛት ላይ ጽኑ:: ይህ ከእኛ የሚፈለግ ነገር ነውና

(7) 7. «ይህንንም አስተምህሮት ከኋለኛይቱ (ከመጨረሻይቱ) ሃይማኖት አልሰማንም:: ይህ ውሸትን መፍጠር እንጂ ሌላ አይደለም።

(8) 8. «ከመካከላችን በእርሱ ላይ ብቻ ቁርኣን ተወረደን?» (እያሉ አዘገሙ።) ይልቁን እነርሱ ከግሳጼየ በመጠራጠር ውስጥ ናቸው:: በእርግጥም ቅጣትን ገና አልቀመሱም::

(9) 9. ወይስ የአሸናፊውና የለጋሹ ጌታህ የአላህ የችሮታው መካዚኖች እነርሱ ዘንድ ናቸውን?

(10) 10. ወይስ የሰማይ የምድር እና የመካከላቸዉም ንግስና የእነርሱ ነውን? (ነው ካሉ) እስቲ በመሰላሎች ወደ ላይ ይውጡ::

(11) 11. እነርሱም እዚያ ዘንድ ከአህዛብ ሁሉ ተሸናፊ የሆነ ሰራዊት ናቸው::

(12) 12. ከእነርሱም በፊት የኑህ ህዝቦች፤ ዓድ እና የችካሎች ባለቤት የሆነው ፈርዖንም አስተባብለዋል።

(13) 13. ሰሙድም፤ የሉጥ ሰዎችም፤ የአይካ ሰዎችም፤ አስተባበሉ:: እነዚህ አህዛቦቹ ናቸው::

(14) 14. ሁሉም መልዕክተኞችን ያስዋሹ እንጂ ሌላ አይደሉም:: ከዚያ ቅጣቴ ተረጋገጠባቸው::

(15) 15. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚህ ያችን ለእርሷ መመለስ የሌላትን አንዲት ጩኸት ብቻ እንጂ ሌላን አይጠባበቁም::

(16) 16. (በመሳለቅም) «ጌታችን ሆይ! ከምርመራው ቀን በፊት ቅጣታችንን አጣድፍልን» አሉ።

(17) 17. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በሚሉት ነገር ላይ ታገስ:: የሃኃይል ባለቤት የሆነውን ባሪያችንንም ዳውድን አውሳው:: እርሱ በጣም መላሳ ነው::

(18) 18. እኛ ተራራዎችን ከቀትር በኋላና በረፋዱም ከእርሱ ጋር የሚያወድሱ ሲሆን እንዲታዘዙት አገራንለት::

(19) 19. በራሪዎችንም (አእዋፍን) የሚሰበሰቡ ሆነው አገራንለት:: ሁሉም ለእርሱ ማወደስ የሚመላለስ ነው::

(20) 20. ንግስናውንም አበረታንለት ጥበብንና ንግግርን መለየትንም ሰጠነው።

(21) 21. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የተከራካሪዎቹ ወሬ መጥቶልሃልን? እልፍኙን (ምኩራቡን) በተንጠላጠሉ ጊዜ።

(22) 22. በዳውድ ላይም በገቡ ጊዜ ከእነርሱም ሁኔታ በደነገጠ ጊዜ (እንዲህ) አሉት: «አትፍራ። እኛ ከፊላችን በከፊሉ ላይ ወሰን ያለፈ ሁለት ተከራካሪዎች ነን። በመካከላችንም በእውነት ፍረድ። አታዳላም። ወደ ትክክለኛው መንገድም ምራን።

(23) 23. «ይህ ወንድሜ ነው:: ለእርሱ ዘጠና ዘጠኝ ሴት በጎች አሉት ለእኔም አንዲት ሴት በግ አለችኝ ‹እርሷንም ለእኔ አድርጋት› አለኝ:: በንግግርም አሸነፈኝ።» አለው::

(24) 24. «ሴት በግህን ወደ በጎቹ ለመቀላቀል በመጠየቁ በእርግጥ በደለህ። ከተጋሪዎች ብዙዎቹ ከፊላቸው በከፊሉ ላይ ወሰን ያልፋሉ:: እነዚያ ያመኑትና መልካሞችን የሰሩት ብቻ ሲቀሩ፤ እነርሱም በጣም ጥቂቶች ናቸው።» አለ:: ዳውድም የፈተንነው መሆኑን ወዲያዉኑ አወቀ:: ከጌታዉም ምህረትን ለመነና ሰጋጅ ሆኖም ወደቀ። በመጸጸትም ተመለሰ:: {1}
{1} እዚህ አንድ ሱጁድ ይደረጋል

(25) 25. ያንንም ማርነው። ለእርሱም እኛ ዘንድ የመቅረብ ክብር መልካም መመለሻም አለው።

(26) 26. (እኛም አልነው) «ዳውድ ሆይ! እኛ በምድር ላይ ምትክ አድርገንሀልና በሰዎች መካከል በእውነት ፍረድ:: የግል ዝንባሌህንም አትከተል:: ከአላህ መንገድ ያሳስተሃልና።» እነዚያ ከአላህ መንገድ የሚሳሳቱ ሁሉ የምርመራውን ቀን በመርሳታቸው ለእነርሱ ብርቱ ቅጣት አለባቸው::

(27) 27. ሰማይን ምድርና በመካከላቸዉም ያለውን ሁሉ ለከንቱ አልፈጠርንም:: ይህ የእነዚያ የካዱት ሰዎች ጥርጣሬ ነው:: ለእነዚያም ለካዱት ሰዎች ሁሉ ከእሳት ወዮላቸው።

(28) 28. በእውነቱ እነዚያ ያመኑትና መልካም ተግባሮችን የሰሩትን ልክ በምድር ውስጥ እንደሚያጠፉት እናደርጋለንን? ወይስ አላህን ፈሪዎችን ልክ እንደ ከሓዲያን እናደርጋለን?

(29) 29. ይህ መጽሀፍ ወደ አንተ ያወረድነው ብሩክ መጽሀፍ ነው:: አናቅጽን እንዲያስተነትኑና የአእምሮ ባላቤቶችም እንዲገሰጹበት አወረድነው::

(30) 30. ለዳውድም ሱለይማንን ሰጠነው:: ሱለይማን ምን ያምር ባሪያ ነው:: እርሱ ወደ ጌታው መላሳ ነውና::

(31) 31. በእርሱ ላይ ከቀትር በኋላ በሶስት እግሮችና በአራተኛው እግር ኮቴ ጫፍ የሚቆሙ ጮሌ ፈረሶች በተቀረቡለት ጊዜ (የሆነዉን አስታውስ)::

(32) 32. (እንዲህም) አለ: «ጸሀይ በግርዶ እስከተደበቀች ድረስ ጌታየን ከማስታወስ ፈንታ ፈረስን መውደድን መረጥኩ!

(33) 33. «በሉ ፈረሶችን ወደ እኔ መልሷቸው።» (አለ)። ከዚያም እግሮቻቸዉንና አንገቶቻቸዉን መቁረጥ ያዘ::

(34) 34. ሱለይማንንም በእርግጥ ፈተንነው። በመንበሩም ላይ የሆነ አካልን ጣልን:: ከዚያም በመጸጸት ተመለሰ።

(35) 35. «ጌታዬ ሆይ! ማረኝ ከእኔ በኋላ ለአንድም የማይገባን ንግስናንም ስጠኝ:: ለጋሹ አንተ ብቻ ነህና» አለ።

(36) 36. ንፋስንም በትዕዛዙ ወደ ፈለገበት ስፍራ ልዝብ ሆና የምትነፍስ ስትሆን ገራንለት::

(37) 37. ሰይጣናትንም ገንቢዎችንና ሰማጮችን ሁሉ ገራንለት::

(38) 38. ሌሎችንም በሰንሰለቶች ተቆራኞችን ገራንለት::

(39) 39. ይህ ስጦታችን ነው ያለ ግምት ለግስ:: ወይም ጨብጥ (አልነው)

(40) 40. ለእርሱም እኛ ዘንድ መቅረብ መልካም መመለሻም በእርግጥ አለው::

(41) 41. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ባሪያችን አዩብንም: «እኔ ሰይጣን በጉዳትና በስቃይ ነካኝ» ሲል ጌታውን በተጣራ ጊዜ።የሆነውን አስታውስ

(42) 42. በእግርህ ምድርን ምታ:: ይህ ቀዝቃዛ መታጠቢያ መጠጥም ነው (ተባለ)::

(43) 43. ለእርሱ ከእኛ ዘንድ በሆነ ችሮታ ባለ አእምሮዎችንም ለመገሰጽ ቤተሰቦቹንም ከእነርሱ ጋር መሰላቸውን ሰጠነው።

(44) 44. «በእጅህ ጭብጥ አርጩሜን ያዝ በእርሱም (ሚስትህን) ምታ። ማላህንም አታፍርስ።» (አልነው) እነሆ ታጋሽ ሆኖ አገኘነው:: ምን ያምር ባሪያ ነው:: እርሱም በጣም መላሳ ነው።

(45) 45. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እንዚያን የኅይልና የማስተዋል ባለቤቶች የሆኑትን ባሮቻችንም ኢብራሂምን ኢስሐቅንና ያዕቆብንም ለህዝቦችህ አውሳላቸው።

(46) 46. እኛ ጥሩ በሆነች ጠባይ መረጥናቸው፤ እርሷም የመጨረሻይቱን አገር ማስታወስ ናት::

(47) 47. እነርሱም እኛ ዘንድ ከመልካሞቹ ምርጦች ናቸው::

(48) 48. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ኢስማኢልንም፤ ኢልያስንም፤ ዙልኪፍልንም አውሳ፤ ሁሉም ከበላጮቹ ናቸው::

(49) 49. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ይህ መልካም ዝና ነው:: አላህን ለሚፈሩም በእርግጥ ውብ የሆነ መመለሻ አላቸው።

(50) 50. በሮቻቸው ለእነርሱ የተከፈቱ ሲሆኑ የመኖሪያ ገነቶች አሏቸው::

(51) 51. በእርሷ ውስጥ የተደገፉ ሆነው በውስጧ በብዙ እሸቶችና በመጠጥም ያዝዛሉ::

(52) 52. እነርሱ ዘንድም ዓይኖቻቸውን በባሎቻቸው ላይ አሳጣሪዎች እኩያዎች ሴቶች አሉ::

(53) 53. ይህ ለምርመራው ቀን የምትቀጠሩት ተስፋ ነው::

(54) 54. ይህ ሲሳያችን ነው:: ለእርሱ ምንም ማለቅ የለዉም::

(55) 55. ይህ (ለትክክለኛ አማኞች ሲሆን።) ለጠማሞችም በጣም የከፋ መመለሻ አላቸው::

(56) 56. የሚገቧት ስትሆን ገሀነም አለቻቸው:: ምንጣፊቱም ምንኛ ከፋች::

(57) 57. ይህ ለከሓዲያን ነው:: ይቅመሱትም የፈላ ውሃና እዥ ነው::

(58) 58. ሌላም እነርሱን ከመሰሉ ብዙ አይነቶች አሉ::

(59) 59. ይህ ከናንተ ጋር በመጋፈጥ ገቢ ቡድን ነው (ይባላሉ):: ለእነርሱ አይስፋቸዉም:: እነርሱ እሳትን ገቢዎች ናቸውና (ይላሉ)::

(60) 60. ተከታዮቹም ይላሉ፡- «ይልቁን እናንተ አይስፋችሁ። እናንተ ክህደቱን ለእኛ አቀረባችሁት መርጊያይቱም ገሀነም ከፋች።»

(61) 61. «ጌታችን ሆይ! ይህንን ያቀረበልንን ሰው በእሳት ውስጥ ድርብ ቅጣትን ጨምርለት» ይላሉ።

(62) 62. ይላሉም «ለእኛ ምን አለን? ከመጥፎዎች እንቆጥራቸው የነበሩትን ሰዎች እዚህ አናይምሳ።

(63) 63. «(ሳይገባቸው) መቀለጃ አድርገን ይዘናቸው ነውን? ወይስ ዓይኖቻችን ከእነርሱ ዋለሉ?»

(64) 64. ይህ በእርግጥ እውነት ነው:: እርሱም የእሳት ሰዎች የእርስ በርስ የመካሰስ ወሬ ነው::

(65) 65. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በል: «እኔ አስፈራሪ ብቻ ነኝ። ኃያልና አንድ ከሆነ አላህ በስተቀር ምንም አምላክ የለም።

(66) 66. «የሰማያትና የምድር በመካከላቸዉም ያለው ሁሉ ጌታ አሸናፊና መሐሪ ነው።»

(67) 67. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በል: «እርሱ (ቁርኣን) ታላቅ ዜና ነው።

(68) 68. «እናንተ ከእርሱ ዘንጊዎች ናችሁ።

(69) 69. «በሚከራከሩ ጊዜ በላይኛዋ ሰራዊት ለእኔ ምንም እውቀት አልነበረኝም።

(70) 70. «ወደ እኔም አስፈራሪ ገላጭ በመሆኔ እንጂ በሌላ አይወርድልኝም።» በል::

(71) 71. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ጌታህ ለመላዕክት እኔ ሰውን ከጭቃ ፈጣሪ ነኝ ባለ ጊዜ (የነበረዉን አስታውስ)::

(72) 72. «ፍጥረቱንም ባስተካከልኩና ከመንፈሴ በነፋሁበትም ጊዜ ሁላችሁም ለእርሱ ሰጋጆች ሆናችሁ ውደቁ።» (አልኩ።)

(73) 73. መላው መላዕክትም በአንድነት ሰገዱ።

(74) 74. ዲያብሎስ ብቻ ሲቀር። ኮራም። ከከሓዲያንም ሆነ።

(75) 75. አላህ «ዲያብሎስ ሆይ! በሁለት እጆቼ ለፈጠርኩት ለአደም ከመስገድ ምን ከለከለህ? ኮርተህ ነው? ወይስ ፊቱኑ ከትዕቢተኞች ነበርክ?» አለው።

(76) 76. ዲያብሎስም «እኔ ከእርሱ የተሻልኩ ነኝ። እኔን ከእሳት የፈጠርከኝ ስትሆን እሱን ግን ከጭቃ ነው የፈጠርከው።» አለ።

(77) 77. (አላህም) አለ፡- «ከእርሷ ውጣ። አንተ የተባረርክ ነህና።

(78) 78. «እርግማኔም እስከ ፍርዱ ቀን ድረስ ባንተ ላይ ይሁን።» አለው።

(79) 79. (ዲያብሎስም) «ጌታየ ሆይ! እስከሚቀሰቀሱበት ቀን ድረስ እባክህ አቆየኝ።» አለ

(80) 80. (አላህም) አለ፡- «አንተ ከሚቆዩት ነህ።

(81) 81. «እስከ ታወቀው ወቅት ቀን ድረስ።»

(82) 82. (እርሱም) አለ: «በአሸናፊነትህ ይሁንብኝ ሁላቸዉንም አሳስታቸዋለሁ።

(83) 83. «ከእነርሱ መካከል ምርጥ ባሮችህ ብቻ ሲቀሩ።»

(84) 84. (አላህም) አለ: «እውነቱም ከእኔ ነው:: እውነትንም እላለሁ(እናገራለሁ)

(85) 85. «በአንተና ከእነርሱ መካከል በተከተሉህም ባንድ ላይ ገሀነምን በእርግጥ እሞላታለሁ» አለው።

(86) 86.(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በል: «በእርሱ ላይ ምንም ዋጋ አል ጠይቃችሁም:: እኔም ከተግደርዳሪዎቹ አይደለሁም።

(87) 87. «እርሱ (ቁርኣን) ለዓለማት መገሰጫ እንጂ ሌላ አይደለም።

(88) 88. «የትንቢቱን እውነትነት ከጊዜ በኋላም ቢሆን በእርግጥ ታውቁታላችሁ።» በላቸው።